>
5:28 pm - Wednesday October 10, 7601

የፕሮቴስታንት የሥራ ህግና የካፒታሊዝም "መንፈስ" 

የፕሮቴስታንት የሥራ ህግና የካፒታሊዝም መንፈስ” ማክስ ዌበር ()
(
አዲሱ ዓመት 2017 – የማስተዋል፣ የአንድነትና ሰላም ዘመን ይሁንልን)
ከፋንታዬ ሠርፀ

ሥራን ማክበር፣ ለሥራ ተነሳሽነት፣ የሥራ ሥነምግባር፣ የመሳሰሉት መልካም ነገሮች እንደምን የካፒታሊዝም መንፈስ” ሆኑካፒታሊዝም ዓላማው ምንድነውጦርነቶች የሃይማኖት ጦርነቶች ቅጥያ ናቸውንይህ ጽሁፍ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሙከራ ያደርጋል። ማክስ ዌበር (Max Weberየፕሮቴስታንት ሥነምግባር/ግብረገብ ህጎች እና የካፒታሊዝም መንፈስ (The Protestant Ethic and the Spirit of Capitalismበሚለው እውቅ መጽሃፉ ዘርዘር አድርጎ ጥልቀት ባለው መንገድ ስለ ፕሮቴስታንት ሥነምግባር/ግብረገብ ህጎች እና የካፒታሊዝም መንፈስ ጥምረት አስረድቷል። የራሴን ሃሳብ በመጠኑ ጨምሬ የማክስ ዌበር አንኳር ሃሳቦችን ቀልል አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

መግቢያ

ንግድ አዲስ ነገር አይደለም፣ የሰው ልጅ ታሪክን ያህል ረዥም እድሜ አለው። ሆኖም ግን ካፒታሊዝም ህግን ተገን አድርጎ በደምወዝተኛነት በተቀጠሩ ሠራተኞች (wage-earners) ጫንቃ ላይ የቆመ ገንዘብ መቆለያ ምጣኔኃብታዊ ድርጅታዊ ሥርዓት ነው። ይህ አዲሱ የባለሃብቶቹ አልያም የተወካዮቻቸው ተቋም አሻራውን በመላው ማህበረሰብ ላይ ማሳረፍ የቻለ ተፅዕኖ ፈጣሪ ክስተት ነው” ይላል ማክስ ዌበር። ካፒታሊዝም ሠፊ ሃብት የሚያስገኙ፣ ትላልቅ የፋይናንስ ተቋማትን የመትከልና በርካሽ ጉልበት ትርፍ የማካበት የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ነው።

ካፒታሊዝምን የፈጠሩት በወቅቱ አንዣበው የነበሩት ሥነልቦናዊ ሁኔታዎች (psychological conditions) ናቸው። ነገ ምን ይከሰታል – በማለት ትንበያን ወይንም ግምትን (speculation) በማስላት፣ ገንዘብ በማበደር (money-lending)፣ የንግድ ድርጅቶችን (comermercial interprise) በማስፋፋት፣ ምግባረ ሠናይ ያልሆኑ ተግባራትን በመፈጸምና በማስፈጸም (buccaneering) እንዲሁም በጦርነቶች (war) አማካኝነት ነው ካፒታሊዝም የፈረጠመው።

ሁሉም አብዮቶች አይቀሬ እና ተፈጥሯዊ ናቸው። የምዕራቡ ዓለም እና የአሜሪካ ካፒታሊዝምም እንዲሁ በአሸናፊነት የወጣ የአብዮት ክስተት ነው። አጀማመሩ ላይ ሽባ የሚመስለው ካፒታሊዝም ከመቶ ዓመታት በኋላ ነው ጭራቅነቱ ገጦ የወጣው። አሁን ላይ ካፒታሊዝም ምጣኔ ኃብታዊ የንግድ ምልክትን መታወቅያው በማድረግ ከህግም፣ ከቤተክርስትያንም ሆነ ከአብዛኛው የአውሮፓ መንግሥታት ጋር የሚያስማማው ማህበራዊ ሥነምግባር አበጅቷል። የሥርዓቱ ቀዳሚ መስራቾች (pioneers) ሥርዓቱን በእግሩ ለማቆም እንዲሁም አስተማማኝ እና ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ብዙ ዳክረዋል። ለዚህ ነው” አለ ማክስ ዌበር ሥርዓቱ የተሠፋበትን ድር መፍታት አዳጋች የሆነው

የካፒታሊዝም መንፈስ

ብልሆች – ሥነምግባር፣ ግብረገብ፣ ቅንነትን የመተሳሰብ ባህል የመሳሰሉትን እሴቶች ካፒታሊዝምን መጠንሰሻ ጌሾ አደረጉት። ለመሆኑ ሃሳቡ ከየት መነጨመለሱ ቀላል አይደለም። የአካባቢ ሁኔታዎች መለዋወጥ ምናልባት አዳዲስ ምጣኔ ኃብታዊ ገጽታዎች የመከሰታቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል። በ16 ኛው ክፍለ ዘመን ውድ የሆኑ የብረታ ብረት ጥሬ ኃብቶች በገፍ ከአሜሪካ አውሮፓ ወዳሉት የንግድ ተቋማት እየጎረፉ ነበር። የንግድ ቤቶችም በሕዝብ ቁጥር ልክ ፍላጎቶችን ማሰራጨት ነበረባቸው። የሳይንስና እድገት የቴክኖሎጂ መሻሻሎችን እያመጣ ነው (steam power)። ይህም ሆኖ ውስብስብ የሆነውን የካፒታሊዝም አመሠራረት ሁሉን ምክንያቶችን ለመረዳት አዳጋች እንደሆኑ ዌበር – General Economic History  በሚለው መጽሃፉ አትቷል። ካፒታሊዝም አዝጋሚ በሆነ ሁኔታ ያደገ ሥርዓት ነው። አንድ ወቅት ላይ ከፍ ያለ የቁሳቁስና የገንዘብ ቁልል በቅንጦትና ጦርነት ምክንያት ሲባክን ታይቷል (dissipated in luxury and war)። ዛሬ ላይ ደግሞ ቅንጦትና ጦርነት ካፒታሊዝምን ያወፍሩታል።

ዌበር የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ባህርይ ለመረዳት ሲነሳ – ካፒታሊዝም መንፈስ” (Spiritየመሆኑ ምሥጢር ለማሳየትና የእግዚአብሄር ጥሪ” (a calling) የሚለውን ሃይማኖታዊ ቃል እንደምን መሥራቾቹ እንደተጠቀሙበት ለማስረዳት ነበር። ለሉተርም (Luther) ሆነ ከሱ ቀደም ለነበሩት የመካከለኛው ዘመን የሥነመለኮት ሊቃውንት (mediaeval theologians) የሰው ልጅ ወደ መንግሥተ ሠማያት የሚገባው እግዚአብሄር የሠጠውን ትዕዛዛት በመፈጸም ወይንም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ቃል በመተግበር ነው። ትዕዛዛቱን መፈጸም ጥሪውን መቀበል ነው። እምነት የለሽነት አመጻ ነው።

የካፒታሊዝምን መንፈስ” ለማስረዳት ጽንሠ ሃሳባዊ ትርጉም ማግኘት ይከብዳል። ገንዘብ የደስታ ምንጭ ባይሆንም አጓጊ ነው። በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት ሰባኪዎች ሥነልቦና ስለሚረዱ የእግዚአብሄር ቃል ሲፈልጉ ማስፈራርያ፣ ሲፈልጉ ማማለያ፣ ሲፈልጉ ማደናገርያ በማድረግ ዓዕምሮን ይቆጣጠሩበታል። ሥራ የቅድስና ጥሪ (Holy Call) ነው” የሚለው ስብከት ፕሮቴስታንታዊ የሥራ ህግ (Protestant work ethic) በመሆን በሰዎች ዓዕምሮ ውስጥ ሠረጾ የካፒታሊዝም መንፈስ” ሆነ።

የካቶሊክን ሥርዓተ ኃይማኖት ያስቀረው ሉተር ለየት ያለ ሥርዓተ እምነት (doctrine) ቀረጸ። ሉተር ዓዕምሮ ሥራ ላይ ሲውል ጸጸት ይረሳል” አለ። ሁሉም ይህችን ዓለም ለመለወጥ የሞራል ግዴታ አለበት” የሚልው የሉተር አስተሳሰብ በአውሮፓ አዲስ የሥራ ሥነምግባር (work ethics) ፈጠረ።

የሉተር ተሃድሶ ዓላማ ቤተ ክርስትያን ቀድሞ የነበራትን ሥልጣን መሻር ሳይሆን ተሃድሶ (reformation) ቢሆንም ይህ በጀርመን የተወለደው አዲሱ ሃይማኖት በአውሮፓ ለዘመናት ጸንቶ የነበረውን የቤተ ክርስትያን ክብር ዝቅ አደረገ። ከሉተር በኋላ ክፍፍሉ ብዙ የኃይማኖት አስተሳሰቦችን ወለደ። ከፕሮቴስታን ኃይማኖት ውስጥ የወጣው ኬልቪኒዝም በመጨረሻ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ በመውጣት ለካፒታሊዝም መንፈስ” (spirit of capitalism) መንሠራፋት ጥርጊያ መንገድ አበጀ።

የእግዚአብሄር ጥሪ በኬልቪን አስተሳሰብ ደግሞ ይለያል። ኬልቪን ወደ መንግሥተ ሠማያት የሚገባው ራሱ እግዚአብሄር የመረጠው ብቻ ነው” ሲል አዲስ ዶክትሪን አመጣ። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ መዳንና አለመዳን በአርባ ቀን እድሉ ላይ የተመሠረተ ነው ማለቱ ነበር። የኬልቪን ቴኦሎጂ በሥነልቦና ላይ ትልቅ ተጽዕኖ በማሳረፍ ካፒታሊዝምን መንፈስ” አደረገው። ኬሊቪኒዝም በቆዩት ዘመናት ለነፍስ አደገኛ ነው ተብሎ ሲቆጠር የነበረው የንግድ ሥራን ማንጻት አስፈለገው።

ሃይማኖታዊና ርዕዮተዓለማዊ ሽፋን የተሠጠው ንግድ – የምጣኔ ኃብት ምንጭ ብቻ ሳይሆን ጽድቅንም ያለብሳል ተባለ። ጉጉትና ምኞት (covetousness) የነፍስ በሽታ ሆነው ሳለ የስንፍናን (sloth) ያህል ጠንቅ አይደሉም – ሥራ ፈትነት (idleness) የሥጋ ፈተና ነው፣ ሥራና ታታሪነት ደግሞ የእግዚአብሄርን ፀጋ ያበዛሉ እንዲሁም ድህነትን ለማሸነፍ በይበልጥ የንግድ ሥራ (business) አዋጪ ነው ተብሎ በይፋ ተሰበከ። መምህራን በሚያስተምሩበት ወቅት (ministerial practice) ገንዘብን ማካበትና ቅድስና አብረው የማይጓዙ ሆነው ሳሉ የተፈጥሮ ዝምድና አላቸው ብለው ማደናገርን እንደ ሙያ ተያያዙት።

ቁጠባ (thrift)፣ አሳቢነት (sobriety)፣ አስተዋይነት (prudence) የመሳሰሉ ወደ ብልጽግና (prosperity) የሚወስዱ እሴቶች (virtues) ሲሆኑ – ጊዜን በዋዛ ፈዛዛ ማባከን (loss of time)፣ መዝናናት leisure)፣ ብዙ መኝታ (more sleep) ግብረገባዊ ናቸው ተብለው ተወገዙ። ቀድሞ ህብረተሰቡ ይፈራው የነበረው ሃብትን ማሳደድ (pursuit of riches) አሁን ላይ እንደ መልካም ወዳጅ (ally) “እንኳን ደህና መጣችሁ” ተባሉ። ሲጀመር ሃሳባዊተግባራዊ ማጠንጠኛ ሆኖ ቡርዣነትን የወለደው ካፒታሊዝም” ይላል ማክስ ዌበር መጨረሻው ቅጥ ያጣ (orgy) ሁሉን ለኔ የሚል ስግብግብ የቁስአካል ቀዳሚነት (materialism) ሥርዓት ይሆናል” በማለት ስጋቱን አስቀመጠ።

ዘመናዊው ካፒታሊዝም ገንዘብ ማግኘት ብቻ ሳይሆን በተጠና መንገድ የሚካሄድ ትርፍ እሴትን (surplus valueየመሰብሰብሰብ ስሑት አሠራር ነው። ካፒታሊዝም የትም ፍጭው ዲቄቱን አምጭው” የሚል ግብረገብን ያጣጣለ ገንዘብን በመሰብሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ ዓይን አውጣነት ነው። ገበያ ይሳብ እንጂ ንግድ ኢግብረገብ ቢሆንም ይሞካሻል። የንግድ አገናኙ ወይንም የንግድ ድርጅቱ ኃላፊ (entrepreneur) መንዝሮ – አመናዝሮ፤ አበድሮ – ተበድሮ፣ እንዴትም ይሁን እንዴትም፣ ትርፍን ማጋበስ የሚቻልበትን ዘዴ የሚያውቅ ብልህ ነው። አወሳሳቢ ቢሮው (bureaucracyከባለ ሃብቱ ጎን የቆመ ንግድ ማሳለጫ ተቋም ነው። እነሆ ከህግ በላይ የሆነው ቅንጡ ወይንም በፍንደቃ (ecstatic) የሚንፈላሰሰው ባለሃብት ቢጠሩት የማይሰማ ባለሞገስና ግርማ” ሆነ። የትርፉና የቅንጡ ኑሮው ውህደት አጓጊ ምስጢር ነው ካፒታሊዝምን መንፈስ” ያደረገው።

ኬልቪንዝም ይቀጥላል። እግዚአብሄር የተሻለች ዓለምን ማየት ይወዳልና ጊዜን በስንፍናና በመሞላቀቅ ማባከን ጥሩ አይደለም፣ ጊዜን ማባከን ከኃጢዓቶች ሁሉ ኃጢዓት ነው” ይላል። ሃሳቡ አይደለም ስህተት አንቀሳቃሽነቱና ድብቅ ዓላማው (motive and hidden intention) እንጂ። ስብከቱ ሁሉንም ለሥራ ተነሳሽ አደረገ። ሠራተኛው የጉልበቱ ዋጋ መመዝበሩ (exploit) ሳይገባው፣ ትክክለኛው የጉልበቴ ዋጋ ይከፈለኝ” ብሎ እንዳይታገል እንኳን ዓዕምሮው ተሸብቦ ሌት ተቀን በማገልገል ለበርቴው የገንዘብ ምንጭ ለሃገሪቱ ደግሞ ሥልጣኔ ከመሆኑም ባሻገር የተመረጡት” (elected) ናቸው ወደ መንግሥተ ሠማያት የሚገቡት (predestination) በመባሉም ሃብታምነት የመንግሥተ ሠማያት መግቢያ የፅድቅ ምልክት ሆነ። ሃይማኖት አጓጊና ማማለያያ መንፈስ” መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሠራተኞች ላይ በፈጠረው ተስፋና ፍርሃት (hopes and fear) ሳብያ መበዝበዥያ መሳርያ ሆነ። ሃብታም ሲንጎማለል፣ ከጉልበት በሚያገኘው ትርፍ እሴት እስከነቤተሰቡ ሲቀናጣ ባለ ፀጋ” ነው ተባለ።

ብዙ ገንዘብ – ብዙ ክብር ነው የሚሉት ኬሊቪኒስቶች – ሃብታም እንጉሡ ፊት ለመቅረቡ ከመጽሃፍ ቅድሱ ማስረጃ ያቀርባሉ። በሥራው የቀለጠፈ ሰው አይተሃልንበነገሥታት ፊት ይቆማል፣ በተዋረዱም ሰዎች ፊት አይቆምም” (ምሳሌ ምዕራፍ 22 ቁጥር 29) የሚለውን ጥቅስ መዘው በማስተማር ምዕመኑን ያሳምናሉ። እነሆ ድህነት ማፈርያ ሃብታምነት ጽድቅ ሆኑ። ሰዎች ድህነትን በመፍራት ስንፍናን ኮንነው ለጉልበታቸው ሳይሳሱ ይሠሩ ጀመር።

ብልጣብልጦች የእግዚአብሄርን ቃል እየጠቀሱ ካፒታሊዝምን ቅዱስ አድርገውት ሲያበቁ ከአምላክ ጥሪ ጋር አቆራኙት። ማህበራዊ ህጉም ቢሆን እያደር ለካፒታሊዝም ባህል መንሰራፋትና ልቅ መሆን ተባባሪ ሆነ። ቀድሞ ካቶሊኮች ሥርየትን በገንዘብ በመሸጥ (selling indulgnce) ብዙ የሠጠ ኃጢዓቱ በብዛት ይሰረይለታል ብለው ምዕመኑን የሚበዘብዙበት ዘዴ በሉተር ነበር የተወገዘው። ከፕሮቴስታንታዊነት የተወለደው ኬሊቪንዝም መልኩን ለውጦ ሃብታምነት እንደ ጽድቅ ምልክት ከፍ ብሎ እንዲታይ አደረገ። ምጣኔ ኃብቱን ለመቆጣጠር ሁኔታ የተመቻቸለት (favourable condition) ካፒታሊዝም ያላቸው የሌላቸውን መጫን የሚችሉበት የጉልበተኞች ሥርዓት ፈጠረ (economic survival of the fittest)። የካፒታሊዝም ክፋት እዚህ ላይ ይጀምራል።

የካፒታሊዝም ተጽዕኖ እና የእምነት መንሸርሸር

ምዕራብያውያን በፕሮፖጋንዳኒስትነታቸው አቻም አይገኝላቸውም። እንኳንስ ካፒታሊዝምን የመሰለ አማላይ፣ ደማቅ፣ አጓጊና ሁሉም የሚሰደድለት ሥርዓት እያላቸው ይቅርና ዛፉን ሳር ነው ብለው ማሳመን የሚችሉ ባለ ምጡቅ ዓዕምሮ ናቸው። ባደጉት አውሮፓውያን ፕሮቴስታኖች ዘንድ እግዚአብሄር አልቦ (atheist) ናቸው ተብለው የሚፈረጁት የአዲሱ ጋርዮሽ ሥርዓተ ማህበር አቀንቃኝ ኮሙኒስቶች በእርግጥ ቁሳካላዊ (materialist) ናቸው። ይሁንና ግን በዝባዡን ካፒታሊዝም የጠሉት ነገ ተነገወድያ በዓለም ላይ ውስብስብ ችግር እንደሚያስከትል አስቀድሞ ስለተረዱ ነበር እንጂ እማህላቸው አማኞች ስለሌሉ አይደለም። ከኮሙኒስቶች መካከል አማኞች እንዳሉ ሁሉ በክርስትያኖችም መሃከል አስመሳዮችና ሸንጋዮችም አይጠፉም። የሥርዓቱ ደጋፊውች ይህን ይደብቃሉ።

ለነገሩ – ኢአማኝነት (atheism) ከተነሳማ – ዛሬ በምዕራብ አውሮፓ ምን ያህል አማኝ ይገኛልብሎ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል። ብዙዎችን የምዕራብ አውሮፓ ሰዎች ቁሳዊ አድርጎ እግዚአብሄርን እንዲተዉ ያደረጋቸው ራሱ ካፒታሊዝም ነው። ሸቀጥ ሲያማርጥና ሲገዛ የሚውል ቅንጡ እንደምን ለእግዚአብሄር ጊዜ ሊሰጥ ይችላልማንስ ቢሆን ትላንት የነበረበትን ጉስቁልና እያስታወሰ ዛሬ ላይ በቅንጦት ፈረስ የሚያስጋልበውን ካፒታሊዝም ሊነቅፍ ይችላልን?

በነገራችን ላይ ለሶቭየት ሕብረት ኮሙኒስት ሥርዓት መገርሰስ የፖለቲካ አስተያየቶችን ማቅረብ ቢቻልም ዋናው ምክንያት ግን ሌላ ነው። ከመጀመርያው የኒቂያ ጉባዔ መጠራት 325 ዓም በኋላ በነመቅዶንዮስ፣ ንስጥሮስ፣ አውጣኪስ፣ አርዮስ በመሳሰሉት የስህተት ትምህርት (heresy) ምክንያት ክርስትና በሁለት ቦታ ተከፍላ ምዕራብ (ካቶሊክእና ምሥራቅ (ኦርቶዶክስተባለች። በዚህ የተነሳ – ምሥራቆቹ የፓትርያርኩ መቀመጫ የነበረችዋ የመጀመርያዋ ሮማ ትተው መንበሩን ቆንስጣንጢኖስ አደረጉ። ኦቶማን ቱርኮች ቡልጌርያንና ሰርብያን ሲወሩ የኦርቶዶክስ አገሮች በእስልምና ሥር ወድቀው በ1453 እስላሞች ቆንስጣንጢኖስን ሲይዙ ሁለተኛዋ ሮማ ወደቀች። ይህ በዚህ እንዳለ በ15ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሁኔታዎች ሞስኮ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን መቀመጫ እንድትሆን አደረጋት።

እነሆ ሞስኮ ሶስተኛዋ ሮማ ሆነች። ፊሎቴኦስ (Philotheus) የተባለው መነኩሴ – ሞስኮ፣ ሶስተኛዋ ሮማ (The Third Rome)፣ በምድር ዙርያ ከጸሃይም በላይ አበራች፣ ሁለቱ ሮማዎች ወደቁ፣ ሶስተኛው ግን ጸንታ ትቆማለች፣ አራተኛም አይኖርም” ሲል ተናገረ። ከ1917 ዓም ጀምሮ ኮሙኒስቶች የምሥራቋን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን መቀመጫ የሆነችውን ሩስያን በማናወጥ በቤተ ክርስትያኒቱ እምነት ላይ ተጽዕኖ በማድረግ አማኞችን ማሳደድ ጀመሩ። እግዚአብሄር በቃ ሲል ሥርዓቱን እ..አ ታህሳስ 1991 ዓም ተገርስሶ ዛሬ የሩስያ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በነጻነት ትንቀሳቀሳለች። ይህ ጉዳይ ሠፊ ስለሆነ ወደፊት እመለስበታለሁ። አሁን ወደ ተነሳሁበት ነጥቤ ልመለስ።

ፕሮቴስታንታዊውን አውሮፓዊ ቀስ በቀስ እግዚአብሄርአልቦ ያደረገው የምጣኔ ኃብቱ፣ የሳይንስ የምክንትና ኢምክንያት ፍልስፍና (reason and unreason) መወለድና የእምነት መዛባት እንዲሁም የአብርሆነት ዘመኑ (age of enlightnment) የፈጠረው ቀውስ ቢሆንም – ቃሉን በመንፈስ ተረድቶ ካለፈው ሁኔታ ጋር አዛምዶ፣ ሰምና ወርቁን ለይቶ፣ ሰዋሰዋዊ አገባቡን አበጥሮ፣ ግሱን ገስሶ እንዲሁም ባህላዊ አባባሎችን ተርጉሞና ምሥጢሩን ፈቶ (contexualization/exegesis) ማስተማር የማይችሉ ሰባኪዎች (preachers) የሚፈጥሩት ማደነጋገር (confusion) ሌላኛው ምክንያት ነበር።

አንዱ ሰባኪ ሃብታም አይጸድቅም” ምክንያቱም ዳግመኛ እላችኋለሁ፣ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሄር መንግሥት ከሚገባ ግመል መመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል” (ማቴዎስ19:24) ተብሎ ተጽፏል – ብሎ ሲያስተምር ታድያ እንዴት እንሁንብለው ምዕመናን በፍርሃት ሆነው ሲጠይቁት “የተዋረደው ወንድም ግን በከፍታው፣ ባለጠጋም በውርደቱ ይመካ” (ያዕቆብ 1:10) ተብሏልና በምድር ሥርዓት ላይ አታተኩሩ – ሲል ይመልስላቸዋል። ይህ ትምህርት ደግሞ ባለጸጋ በነገሥታት ፊት ይቆማል፣ በተዋረዱም ሰዎች ፊት አይቆምም” የሚለውን ጥቅስ ያፈርስባቸዋል። በሌላ ሳምንት አንዱ ሰባኪ “ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፣ ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፣ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ” (ምሳሌ 30:8) ተብሎ ተጽፏልና ብዙ አትድከሙ፣ ለዕለት ምግባችሁ ከሠራችሁ ጉልበታችሁን ለሥርዓቱ አታባክኑ” ብሎ ያስተምራቸዋል። በዚህ አባባሉ ስንፍናን ልትመልስ ነው” ተብሎ ከቤተ ክርስትያን ሊባረር ይችላል።

የስብከቱ ሐሳበጽኑነት ማጣት ወይንም ወጥነት (consistency) አለመኖር እንዲሁም በብዝበዛ በተገኘ ልማት ምክንያት ድህነት መገርሰሱ – ከሥልጣኔ ጋር ተዳምሮ – ምዕራብ አውሮፓውያን ከክርስትና እየሸሹ የእርስ በእርስ ግኑኝነታቸው (relationship) ላይ ገደብ በማበጀት የካፒታሊዝም እንዱስትሪዎች በሚያመርቱት ሸቀጥ ላይ አይናቸውን ተከሉ። ካርል ማርክስ ሃይማኖት የድሆች ዕጽ ነው” (religion is opium of the poor…) ማለቱ ሃብታምነት ሃይማኖትን ያስተዋል ማለቱ ነበር። አምልኮተ ሸቀጥ” (fetishism of commodity) ይላሉ ካርል ማርክስ ሆነ ማክስ ዌበርም ሃይማኖትን የማስረሳት ኃይል አለው። ሥልጣኔ፣ ሃብትና ምቾት (civilization, wealth and luxury) እግዚአብሄርን ለማስተዉ ምዕራቡ አውሮፓ ምሳሌ ነች። ፕሮቴስታንት በነበሩት ምጣኔ ኃብቱ ባደገበት በምዕራብ አውሮፓ እምነት እየቀረ የቀድሞ ቤተ ክርስትያናት ሙዚየም ሆነዋል። በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙ ካቶሊኮች ደግሞ አብዛኛዎቹ አሁንም የሃይማኖቱ ተከታይ ናቸው።

ጦርነት፣ ሙስናና ስደት

በጦርነት፣ ሙስናና ስደት መካከል ትስስሮች አሉ። በካቶሊክና ፕሮቴስታን መካከል የነበረው ጦርነት የሃይማኖት ጦርነት ነበር። በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል የነበረው ልዩነት ከሮ ከስምንት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለኅልፈት የዳረገውን ከሰላሳ ዓመቱ በላይ (1618-1635) የዘለቀውን ጦርነት አስከተለ። በምዕራብ አውሮፓ ካቶሊካዊነት ሲዳከም እያደር በመንግሥት መዋቅርም ሆነ በትምህርት፣ በንግድና በሁሉም የሥራ ዘርፎች የላዩንም የታቹንም ሥልጣን የተቆጣጠሩት አቅም ያላቸው የፕሮቴስታንት ተከታዮች ሆኑ። ይህ ደም አፍሳሽ ጦርነት በዌስትፋልያ የሰላም ስምምነት (Peace of Westphalia) ነበር የተቋጨው። ደች ነጻ ወጣች፣ በጀርመን ሥር የነበሩት ዴንማርክና ስዊድን ከጦርነት ተገላገሉ፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ኔዘርላንድ መርከቦቻቸውን አስነስተው በዓለም ዙርያ በንግድ ሥራ ተሰማሩ፣ እንግሊዝ ዋነኛዋ ተጸዕኖ ፈጣሪ አገር ሆነች። ሩስያ ግዛትዋን ወደ ምሥራቁ በማስፋፋት በ1648 ዓም የፓሲፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ መመድረስ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን አስፋፋች።

በምዕራብ አየርላንድ (Nortern Ireland) በካቶሊኮችና ፕሮቴስታኖች መሃከል የነበረው ከሰላሳ ዓመት በላይ (1960-1998) የዘለቀው ጦርነት የሃይማኖት ጦርነት ነበር፡፡ በምዕራብያውያኑ አገሮችና በሩስያ መካከል የሚደረገው ጦርነት ቤተ ክርስትያን ለሁለት ከተከፈለችበት ጊዜ ጀምሮ በልዩነት ምክንያት የተከሰተ የሃይማኖት ጦርነት መዘዝ ነው። ኦርቶዶክሳዊቷ ሩስያ የምዕራቡ ዓለም ለዘረጋው ባህልና ሥርዓት ተገዢ ላለመሆን ብዙ ታግላለች። ዛሬ ሩስያን ከዩክሬን ጋር እያዋጋ መጠነ ሰፊ ገንዘብ የሚሰበስበው የአሜሪካ ካፒታሊዝም ለአውሮፓም ቢሆን ጥሩ አይደለም። ካፒታሊዝም ገንዘብ አለው፣ ቅጥረኛ ወታደሮችን እየገዛ የእሳት እራት ያደርጋል። የኔቶ መሪ የንስ ስቱልተንበርግ ቢሆንም እንደ ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የሚያዘው ቮሎዲሚር ዜሌኒስኪ ነው። ኔቶዎች ዜሌኒስኪ ሲመጣ ምን ያህል እንደሚሾሩ መታዘብ ይቻላል። ዜሌኒስኪ ለካፒታሊዝም የገንዘብ ምንጭ ሲሆን ለዩክሬናውያን ስደትና አበሳ ነው። ጦርነት ካለ የጦር መሳርያ ይሸጣል። በአካባቢው ያሉት የኒውክለር ማብላያ ጣብያዎች ላይ አደጋ ቢደርስ ጠንቁ ለአውሮፓ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጭምር ነው። በለምለሟ ኦርቶዶክሲያዊቷ ዩክሬን ስቃይ ምክንያት ዜሌኒስኪ በጸጸት ይበግናል።

በፍልስጤሞችና እስራኤል መካከል ያለው ደም አፍሳሽ ጦርነት መነሻው ሃይማኖት ሲሆን አባባሹ ካፒታሊዝም ነው። የኢትዮጵያም መከራ ከመካከለኛው ምሥራቅ እየነፈሰ ወደ አፍሪቃ ቀንድ ከሚመጣው ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው። እግዚአብሄር በቅኝ ገዥዎች ላይ ያጎናጸፋት የአድዋ ድልና የሃይማኖት ጽናትዋ እንዲሁም የአባይ ወንዝ ምንጭነትዋ ከካፒታሊዝም መንፈስ” ጋር ይጋጫል። ይህ መንፈስ” በግብጽ አማካኝነት ኢትዮጵያን ያምሳል። ግብጽ እንደ ጭቃ ጠፍጥፋ የምትሰራቸው አማሾች ኢትዮጵያን ያስጨንቃሉ። ለግብጽ ባደሩ ራስ ወዳድ ፖለቲከኞች አላዋቂነት – የትላንትናው እየተሻለ መጪው እያስፈራ ኢትዮጵያ አኬል ዳማ ሆነች። ኢትዮጵያ ልጆችዋን ለመንፈሱ” እስከመቼ ትገብር?

የዓለም ባንክ ለድሆች አገሮች የሚሠጠው ብድር በሙሰኛው ፖለቲከኛ ተዘርፎ መልሶ ወደ አበዳሪው ካፒታሊስት አገር ይሄዳል። ሙሰኛው ፖለቲከኛ በተሰደደበት አገር ላይ ሆኖ የጦር ነጋሪት ይመታል። የዋህ ሕዝብ ይፋጃል፣ ጉልበተኛው ያግታል፣ ህጻናት ይደፍራሉ፣ ባለሥልጣኑ ይዘርፋል። ይህ ሁሉ ዓለም ባንክ የሠጠውን ብድር ለመቀራመት ነው። ብድር ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው። በርካታ የደሆች አገሮች ፖለቲከኞች የተሰባሰቡት እምዕራቡ አገር ነው። እነዚህ የካፒታሊዝም መንፈስ” ቡራኬን ያገኙት ፖለቲከኞች ሁኔታ ሲመቻችላቸው ተመልሰው በደሃ አገራቸውን ላይ ጢባ ጢቤ ይጫወታሉ፣ ይሞስናሉ፣ ይበደራሉ፣ ተመልሰው ደግሞ ወደ ምዕራቡ ይሰደዳሉ።

በምድር ዙርያ ያሉ ጎስቋሎች – የተማሩ ያልተማሩ፣ ልህቃን ደቂቃን፣ ቀሳውስት ምዕመን፣ ፊታቸውን ወደ ፓሪስና ዋሺንግተን አዙረው ባገኙት መጓጓዣ ይሰደዳሉ። ብዙዎች መንፈስ” ለሆነው ለከበርቴው ሥርዓት ጉልበት ወይንም እውቀት ለመገበር ይጣደፋሉ። ያደለው ከሚያገኘው ምንድዓ ቀንሶ አገር ቤት ላሉ ዘመዶቹ ይልካል (remittance)፣ ያልታደለው ባክኖ ይቀራል።

መደምደምያ

ካፒታሊዝም መንፈስ” የሆነው የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እየተጠቀመ፣ የእግዚአብሄርን ጥሪ እያወላገደ ሃይማኖትን ስለበከለ ነው። ካፒታሊዝም ቅኝ ለመግዛት ወደ አፍሪካም ሲመጣ መጽሃፍ ቅዱስ ይዞ ነበር። ሠይጣን ጤፍ የምታህል ማደናገርያ ይዞ በሃሰት ያጅባታል። ካፒታሊዝም የዓለም ባንክ ቤት፣ የዓለም ፖሊስ፣ የጦር ኃይል፣ ሆሊዉድ፣ ዶላር፣ ወዘተ፣ ነው። ውልፍት ያሉትን በማዕቀብ (sanction) ጀምሮ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት (military intervention) ያንበረክካቸዋል። ሥርዓቱ በዲሞክራሲ ስም የተባበሩት የዓለም መንግሥታትን፣ የአለም ባንክንና ዓለም አቀፉን ፍርድ ቤት ማዘዝ የሚችል ከሰማይ በታች ብቸኛ ኃያል ነው። ዴሞክራሲ” ሥርዓቱ አፍ የፈታበት አፍማስያዥያ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ሥርዓቱ በታላላቆቹ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች (trans-national corporations) አማካኝነት ገበያውን ይቆጣጠራል። ሥርዓቱን ታግሎ ማሸነፍ ባይቻልም ተላላኪዎቹንና አሸርጋዶቹን ተዉ” ማለት ይቻላል። ይህን ማድረግ የሚቻለው የፖለቲካ ባህልን በማሳደግና አንድነትን በመልበስ ነው።

ካፒታሊዝም – የጠላውን ሌላውም እንዲጠላው – አቋምን ማስለወጥ፣ አስተሳሰብን ማዛባት የሚችሉ ታላላቅ የሜድያ ተቋማት አሉት። የእግዚአብሄር ጸጋ ካልታከለበት በቀር አጓጊ ለሆነው ለካፒታሊዝም አልገዛም” ማለት ቀላል አይደለም። ምስኪኖች ከአሜሪካና ከሞት ማንም አይቀርም” ይላሉ። ካፒታሊዝም ምድራዊ ኃይልና ምድራዊ ምቾት በመሆኑ የድሆች ተስፋና መዳረሻ ሆነ። በሰላም መኖር ያልቻለ ምን ሌላ አማራጭ ይኑረውበእርግጥ ዋጋ ቢያስከፍልም፣ እግዚአብሄርን የሙጥኝ ማለት ግን ማትረፍ ነው። ለሁለት ጌቶች፣ ለእግዚአብሄርም ለምድራዊ ሥርዓትም መገዛት አይቻልም። እየሱስ ክርስቶስ ነው የዘላለም ህይወት።

የካፒታሊዝም መንፈስ” ለሰው ልጆች ነፍስ፣ ለዓለም ሰላም ደንታም የለው። መንፈሱ” ለአሜሪካና አውሮፓ ቅንጡዎች ቤተአምልኮ ሲሆን ለምርኮዎች ደግሞ የህልም ሩጫ ሠፊ ሜዳ ነው። መንፈሱ” የሚፈራው ማስመሰል በሌለበት ልብ መስቀሉን የያዙትን ብቻ ነው።

ወገኖቼእግዚአብሄር ይርዳን። ፈጣሪ አምላካችን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን፣ አሜን።

ማሳሰብያ –

ምን ጊዜም ጥናት፣ ምርምርና ውይይት አስፈላጊ ነው። ስለ ካፒታሊዝም መንፈስነት በቅጡ ለመረዳት፣ ተረድቶም ሃገርን ለመታደግ መጻህፍትን ማገላበጥና መወያየት ያስፈልጋል። ይህ ጽሁፍ ለውይይት ይጋብዛል እንጂ ምሉዕ አይደለም። የካፒታሊዝምን ብልጣብልጥ አነሳስ ለመረዳት ፕሮቴስታንቲዝምን ብቻ ሳይሆን ኬልቪኒዝምን (Calvinism)፣ ፒቲይዝምን (Pietism)፣ ሜቶዲዝምን (Methodism)፣ ባብቲዝምን (Baptism) እንዲሁም የእንግሊዙን ፑሪታኒዝም (puritanism) እና አንገሊካኒዝም (Angelicanism) የመሳሰሉ ኃይማኖቶችን አጀማመራቸውን እያጠኑ ውስጣዊ ባህርያቸውን በቅጡ ማየት ያስፈልጋል። ከካቶሊክ ሃይማኖት ከወጣው ፕሮቴስታንቲዝም በኋላ ለምን በርካታ ዶክትሪኖች እንደ አሸን ፈሉብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።

ካርል ማርክስ የምጣኔ ኃብቱ ዘርፍ (economic sector) ነው ሃይማኖትን የበከለው” ሲል ማክስ ዌበር ደግሞ ሃይማኖት ነው ካፒታሊዝምን እንደ መንፈስ” በሰዎች ዓዕምሮ ውስጥ እንዲርጽ ያደረገው” ይላል። የሁለቱ ሃሳብ አንዳንዴ ይስማማል አንዳንዴ ደግሞ አይስማማም። ዞሮ ዞሮ የካፒታሊዝም ኃያል መሆንን – ምክንቱንና ውጤቱን (cause and effect) ጠንቅቆ ለመለየት የሁለቱንም ሥራዎች መረዳትና ሃሳብን አንግቦ መወያየት ጠቀሜታ አለው። ካልተወያዩበት ግንዛቤ አይገኝም። ካርል ማርክስና ማክስ ዌበር የጻፉት በወቅቱ የሠፈነውን የምዕራቡን ክርስትና ሃይማኖት አስመልክቶ እንጂ ስለ አፍሪካ፣ እስያና ላቲን አሜሪካ ሃይማኖት አይደለም።

በአንድ በኩል የዓለም ችግሮችን መንስዔ እየመረመሩ በሌላ በኩል ደግሞ የካፒታሊዝምን አካሄድና የማጥቃት ዘዴውን ማጥናት ይበጃል። ካፒታሊዝምን ማሸነፍ ባይቻል እንኳን መከላከል ይቻላል። የመከላከል መፍትሄ የሚገኘው ሲወያዩ ነው። ካፒታሊዝም አንድ የዓለም ሥርዓት (one world order) ለመዘርጋት ምን ያህል የሰው ልጆችን እማይወጡበት መከራ ውስጥ እንደዘቀጠ ይታወቃል። ከኋላ የሚገፋውን ስውሩን ሥርዓት ያጎለበተው ካፒታሊዝም አይደለምንየሰው ልጆችን ሥነልቦና በማማለል ህብረተሰቡ አምላኩን ረስቶ ቀልቡን በሸቀጦች ላይ እንዲጥል ያደረገው የካፒታሊዝ መንፈስ” አይደለምንየካፒታሊዝም መንፈስ” አይበገሬ ቢሆንም በማስተዋልና በአንድነት ይገደባል። ኢግብረገባዊነት፣ ብልሹ ባህል፣ ድህነት፣ ጦርነት፣ ስደት፣ ብድር፣ እገታ፣ ደፈራ፣ ወዘተ፣ እነዚህን ሁሉ መቅሰፍቶች መከላከል የሚቻለው በአንድነት በመቆም ነው። አንድነት ኃይል ነው።

Filed in: Amharic