>

ዶ/ር አክሎግ ቢራራ በእንግሊዘኛም ሆነ በአማርኛ ጽፎ እንዲነበብ ላደረገው የተሰጠ ትችታዊ መልስ!!

እኔ የምላችሁንና የማዛችሁን የማትቀበሉ ከሆነ ጦርነት አካሂድባችኋላሁ ካለና ተግባራዊም ካደረገ ኃያል አገዛዝ ነኝ ከሚል ለፍትህ ቁም ብሎ ጥያቄ ማቅረብ የኢምፔሪያሊዝምን ምንነትና የካፒታሊዝምን አፀናነስ አለመረዳት ነው!! አክሎግ ቢራራ በእንግሊዘኛም ሆነ በአማርኛ ጽፎ በዘሃበሻ ላይ እንዲነበብ ላደረገው የተሰጠ ትችታዊ መልስ!!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                          

ዶ/ር አክሎግ ቢራራ በዚህና ባለፉት አስር ዓመታት በሚጽፋቸው ጽሁፎች፣ በተለይም የአሜሪካንን የውጭ ፖሊሲ አስመልክቶ ያልገባው ነገር እንዳለ በግልጽ መረዳት ይቻላል። በመጀመሪያ ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ከመግባቴ በፊት እንደዚህ ዐይነቱ ምሁር ነኝ ባይ በተደጋጋሚ ይህንን መሰል ጽሁፍ ሲጽፍ እንደኔ ከመሰለው ክሪቲካል ወይም ሂሳዊ አመለካከት ካለው ሰው ትችት ሲቀርብበት ይህንን በመሰለ ምሁር ነኝ ባይ ላይ እንደዚህ ዐይነት ትችት ሊቀርብ ይቻላል ብሎ ሊጠይቅና ግራ ሊጋባ የሚችል ሰው ይኖራል፤ በእርግጥም ግራ መጋባቱ አይቀርም። ግልጽ መሆን ያለበትና በአገራችንም ያልተለመደ የአመለካከት ግድፈት አለ። የአንድን ህብረተሰብ አወቃቀር፣ የኃይል አሰላለፍ፣ የሀብት ቁጥጥርና ከዚህ በመነሳት የሚነደፈውን አጠቃላይ ፖለቲካና ፖሊሲ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖለቲካ ስም ይህንን ያህልም በኢኮኖሚ ባላደጉና ከፍተኛ የምሁራዊ ድክመት በሚታይባቸው አግሮች ላይ የሚደረግባቸውን ጫናና ግፊት አስመልክቶ በሚገባ እያብላሉ ሂሳዊ በሆነ መልክ የሚጽፍ ግለሰብም ሆነ በድርጅት ተደራጅቶ ህዝባችንን የሚያሰተምርና የሚያነቃ ስለሌለ ክፍተኛ ግራ መጋባትና የአስተሳሰብ ወይም የአመለካከት ግድፈት ይታያል። ማንኛውም ከውጭ የሚመጣውንና የሚተገበር ፖሊሲና በዘመናዊነት ስም የሚካሄድ ፖለቲካ በሂሳዊ መልክ ስለማይገመገም ይኸው እንደምናየው አገራችንን ከፍተኛ ትርምስ  ውስጥ በመክተት የህዝባችንን ሞራልና ስነ-ልቦና በከፍተኛ ደረጃ አናግቷል። በነፃ ገበያ ስም ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ህዝባችንን ከድህነት በማውጣት ምርታማ የሆነ ኃይል ብቅ እንዲል በማድረግ ኢኮኖሚው በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመደገፍ እንዲንቀሳቀስ አላደረገም። ስለሆነም በገበያ ኢኮኖሚ ስም የሚካሄደውን ዐይን ያወጣና አገርን ማመሰቃቀልና ሰፊውንም ህዝብ የባሰውን ወደ ድህነት እንዲገፈተር በማድረግ አቅመ-ቢስ እንዲሆን ማድረግ እንደ ተራ ነገር ወይም እንደ ተፈጥሮአዊ ህግ ተደርጎ ይወሰዳል።

አክሎግ ቢራራ በተደጋጋሚ ሰለ አገራችን ኢኮኖሚም ሆነ ስለ አሜሪካን የውጭ ፖሊሲ በሚጽፍበት ጊዜ አጻጻፉ ክርቲካል እንዳልሆነ በእርግጥም መረዳት ይቻላል። በሌላው ወገን ደግሞ በአጠቃላይና ግራ በሚያጋባ መልክ ስለሚጽፍ ምን ዐይነት የአሰራር ስልትና የትምህርት ዘዴን(School of Thought) እንደሚከተል ሊነግረን አይችልም። ዝም ብሎ በጥሩ የእንግሊዘኛና የአማርኛ ቋንቋ ብቻ ስለሚጽፍ የሚጽፈውና በጥያቄም መልክ ለሚቀርብለት የሚሰጠው መልሶች እንደትክክል ተብለው ሊወሰዱ ይችላሉ። አንድን አቋም ወይም የአሰራር ስልት ደግሞ መከተል አንድ ጸሀፊ እንዴት አድርጎ የአንድን አገር ተጨባጭ ሁኔታዎች፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታዎችና በስልጣን ላይ ያለውም አገዛዝ ከውጭው ኃል ጋር ያለውን ግኑኘነት በትክልል ያንብ አያንብ እንደሆን መረዳት የሚያስችል ሳይንሳዊ የአሰራር ዘዴ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በሳይንስ የአሰራር ዘዴ ዝም ብሎ በደፈናው የሚጻፍና የሚተነተን ነገር የለም። ይህ ሳይንሳዊ የአሰራር ዘዴና አንድን አቋም መከተል ደግሞ የዕምነትም ጉዳይ ስለሆነ የአንድን ህብረተሰብ የተወሳሰቡ ችግሮች ከመረዳት ባሻገር ተቀራራቢ መፍትሄም መስጠት ይቻላል። ስለሆነም የምከተለው የአሰራር ስልት ይህንን ነው ብሎ መናገር እጅግ አስፈላጊና ለአንድ አገር ሁለንታዊ ዕድገትም በጣም ወሳኝ ነው። ከዚህ በመነሳት አክሎግ ቢራራ በመሰረቱ የሚከተለው የአሰራር ዘዴ በእኔ ዕምነት ኢምፔሪሲስታዊ በሚባል የሚታወቅ የአሰረራና የአጻጻፍ ዘዴ ሲሆን፣ ይህም በመሰረቱ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚሆነው ፖለቲካና ፖሊሲ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦችን የሚጎዳ ወይም የሚገድልና ህይወታቸውንም የሚያሰናክል ቢሆንም ነገሩ እንደተራ ነገር ይታያል። አብዛኛው ሰው ንቃተ-ህሊና ስለሌውና ጥያቄም ስለማይጠይቅ ዝም ብሎ ያልፋል። ጥያቄ ለመጠየቅና ለማገናዘብ በማይቻልበት አገር ውስጥ ደግሞ ጭቆናዊ አገዛዞች ፈርጥመው በመቅረት ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ያስፋፋሉ። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱን ቅጥ ያጣ ፖሊሲና ፖለቲካ ትችታዊ ወይም ሂሳዊ በሆነ መልክ መጋፈጥ ትክክል አይደለም፤ ከዚህም የተሻለ አማራጭ ስለሌለ እሱን በመለማመጥና በመለመን ብቻ ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው የሚል የተስፋፋና ተቀባይነትም ያገኘ ለመሆን በቅቷል። በሌላ ወገን ደግሞ ክሪቲካል አመለካከት ከፈለቀበት ከዛሬ ሶስት ሺህ ዓመት ጀምሮ ስልጣን ላይ የተቀመጡ ኃይሎች በአመጽ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ፣ በመሰረቱ ከስግብግብነትና ኃይልን(Power & Greed) በማስቀድም የመነጨ የአገዛዝ  በመቃወም የሰውን ልጅ ከጨለማ ኑሮና ከጭፍን አገዛዝ ለማላቀቅ የሚደረገብት የትግል መሳሪያና ሳይንሳዊ ዘዴ ነው። ማንኛውም ሰው በአምላክ ምስል የተፈጠረ ስለሆነ የማስብና የራሱን ኑሮ የመለወጥና የማሻሻል ውስጣዊ ኃይል አለው፤ ስለሆነም ማንኛውም ሰው እንደከብት መነዳት የለበትም፤ እኔም ሰው ነኝ፣ የማሰብ ኃይልም አለኝ ብሎ መነሳት አለበት ከሚለው የፀናና ሳይንስዊ ከሆነ አስተሳሰብ የመነጨ ትክክለኛ የትግል ዘዴ ነው። ስለዚህ ነው ከእነ ሶክራተስና ከፕላቶ ጀምሮ እስከ አስራሰባተኛውና አስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የዘለቀው በሂሳዊ ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊ የሆነውና በዚህም አማካይነት ብቻ ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል የተረጋገጠው። ሰልሆነም ነው ልዩ ልዩ የሆኑ ሳይንሳዊ ዕውቀቶች በመዳበር በስልጣን በመሳከር እስከመቶ ዓመታት የፈጁ ጦርነቶችን ያካሂዱ የነበሩ በርዕዮተ-ዓለም የታወሩ ባለስልጣናትን ቀስ በቀስ በማስወገድ ቢያንስ የሊበራል አስተሳሰብ በአሽናፊነት ሊወጣ የቻለውና ካፒታሊዝምም ሊዳብር የቻለው። ይሁንና ግን የካፒታሊዝምን ዕድገት ስንመለከትና ስንመረምር ደግሞ በለሰለስ መልክና በስምምነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በአመጽ ላይና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን በማፈናቀልና(Primitive Accumulation) ሌሎችን አገሮች ደግሞ ባሪያ በማድረገና የህብረተሰባቸውን አወቃቀር በማዘበራረቅና ሀብታቸውንም በመዝረፍ ነው። ይህ ዐይነቱ ዘረፋና የደካማ አገሮችን ሀብት በነጻ ገበያና በነጻ ንግድ ስም አሳቦ ህብረተሰቦቻቸውንም ማዘበራረቅ በረቀቀ መልክ የሚካሄድ ነው። ይህ ዐይነቱ ድብቅና የረቀቀ ዘረፋና ህብረተሰብን ማዘበራረቅ ደግሞ በየአገሮች ውስጥ በስልጣን ላይ የተቀመጡትንና ይህንንም ያህል የተወሳሰበ ዕውቀት የሌላቸውን በመጠቀም ነው። በዚህ መልክ ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያልትሰተካከለ ዕድገት የሚታየውና እንደኛ ያሉ አገሮችም ተፈጥሮአዊ ሀብት ቢኖራቸውም እሱን ለመጠቀም ባለመቻል በዘለዓለማዊ ድህነት ውስጥ እንዲኖሩ የተገደዱትና የሚገደዱት።

ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ጋ ልምጣ። አክሎግ ቢራራ በአጠቃላይ ሊነግረንና ሊያሳምነን የሚፈልገው በአሜሪካን ምድር የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ በሚገባ የሚሰሩና የሚንቀሳቀሱ ተቋማት እንዳሉ፣ የህዝቡም መብት የተረጋገጠና ይህም መብቱም በየአራት ዓመቱ በሚካሂድ ሚርጫ የሚገለጽና፣ ምርጫውና የምርጫው ውጤት በምርጫው የተካፈለውን ህዝብ ስሜትና ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ነው የሚለን። በእሱ አባባል ይህ ፍትሃዊነት የሚታይበትና የሚተገበርበት የአሜሪካን ዲሞክራሲ የተለያዩ የአሜሪካ አገዛዞች በውጭው ፖለቲካቸው ሲመሩበትና ተግባራዊ ለማድረግም ሲጥሩ አይታይም። ስለሆነም ፍትሃዊነት የተሞላበት የአሜሪካን ዲሞክራሲ ከሚያካሂደው በመሰረቱ በጉልበት ላይ ወይም በጦርነት ላይ ከተመረኮዘው የውጭው ፖለቲካው ጋር ሲነፃጸር በአገር ውስጥ ከሚተገበረው ፍትሃዊነትና የዲሞክራሲ ስርዓት ጋር የሚጋጭ ነው ይለናል። በሌላ ወገን ደግሞ በየአራት ዓመቱ  በሚካሄድ ምርጫ የሚሳተፈውና የመምረጥ መብት ያለው አሜሪካን ህዝብ የቱን ያህል የአሜሪካንን ህገ-መንግስትና የየፓርቲዎችን ፕሮግራምና የሚከተሉትንም ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ በትክክል በመረዳት ይመርጣቸው እንደሆን የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁንና የማንኛውም አገር ህዝብ ለአንድ አገዛዝ ሌሎች አገሮችን መውረር ትችላለህ፤ ህብረተስቦቻቸውንም የማዘበራረቅ መብት አለህ ብሎ ፈቃድ የሰጠበት ጊዜ የለም፤ በየአገሮች ህገ-መንግስት ውስጥም ይህንን አስመልክቶ የሰፈረ ልዩ አንቀጽ የለም። ቢጻፍ እንኳ ማንኛውም አገር በሌላው አገር ውስጥ ጣልቃ የመግባትና ጦረነትም የማወጅ መብት የለውም፤ ሊኖረውም አይገባም።  አሜሪካን ከሰባ ዓመታት በላይ የኃያልነትን ሚና የታጫውተና፣ በተለይም ደግሞ የኮሙኒስቱ ስርዓት 1989 .ም ከፈራረስ በኋላ እስከዛሬ ድረስ በብቸኝነት የኃያልነትን ሚና ሲጫውትና የራሱንም ጥቅም ለማስተግበር በተለይም በደካማ አገሮች ላይ ጫና ሲያደርግ የቆየ ነው። ከዚህ አልፈን ስንሄድ ደግሞ አሜሪካ ኃያል መንግስት ሆኖ ከወጣበት ጀምሮ እንደ ቬትናም በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ ካለምንም ምክንያት በቀጥታ ጦርነት በመክፈት ለብዙ መቶ ሺሆች ሰዎች ዕልቂት ምክንያት እንደሆነና፣ ከዚያም በኋላ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ አገዛዞችን በማስወገድ የእሱን ጥቅም ሊያስጠብቁ በሚችሉ አምባገነናዊ አገዛዞች ጋር በጥቅም በመተሳሰር ይሰራ እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው። አክሎግ ቢራራ ይህንንም አምኖ ይቀበላል። እነዚህ ጣልቃ ገብነቶችና በዲሞክራሲ መንገድ የተመረጡ አገዛዞችን አስወግዶ ለእሱ በሚስማሙ አምባገነናዊ አገዛዞች መተካት በመሰረቱ በአሜሪካን ምድር የሚተገበረውንና አክሎግ ቢራራ የሚኖርበትንና የሚለማመደውን ፍትሃዊነት የተሞላበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሚቀናቀንና ይህም ተገቢ እንዳልሆነና አሜሪካንም ያለው አማራጭ  በአገሩ ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርገውን ፍትሃዊ ስርዓት በተለይም በአፍሪካ ምድር እንዲተገበር አጥብቆ መስራት አለበት ይለናል። በአንድ በኩል አሜሪካ በህዝብ ድምጽ የተመረጡና ለህዝብም ጥብቅና የቆሙ አገዛዞችን ከስልጣን አስወርዶ የእሱን ጥቅም ሊያስጠብቁ በሚችሉ መተካት የሚለው በግልጽ የተቀመጠ አይደለም። የተለያዩ የአሜሪካ አገዛዞችና ተቋሞቻቸው በውስጥ ፍትሃዊነትን ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነና ዲሞክራሲያዊ ተቋማትስ ካሏቸው ለምን ወደ ውጭ ይህንን በመፃረር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳያብብና ፍትሃዊነትም እንዳይነግስ መሰናክል ይሆናሉ? ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ቢኖር፣ ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም የተስተካከለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቢኖር፣ ሰፊውም ህዝብ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ካለውና የየአገሮች የውስጥ ገበያ ካደገ ይህ ዐይነቱ ጤናማ ስርዓት ለአሜሪካንም ሆነ ለተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊዝም የተሻለ አይሆንም ወይ? ለምንስ ነው አሜሪካንም ሆነ የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች ከዲሞክራሲያዊ ስርዓትና በየአገሮች ውስጥ ያሉ ህዝቦችን ጥቅም የሚያስጠብቁ አገዛዞች ስልጣን ላይ ከሚቀመጡ ይልቅ ፍትሃዊነትን የሚቀናቀኑና ያልተስተካከለ ዕድገትን ተግባራዊ የሚያደርጉ አገዛዝች ስልጣን ላይ እንዲወጡ የሚመኙትና ለዚህም የአጥብቀው የሚሰሩት? ለምድን ነው የውስጥ ፖሊሲያቸውና የውጭው ፖሊሲያቸው የሚጋጨው? ይህንን አስቸጋሪ ጥያቄ ለመመለስ የካፒታሊዝምን አፀናነስ፣ ማደግና ወደ ኢምፔሪያሊዝምነት መለወጥ ጠጋ ብለን እንመልከት።

ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመለከት በአንድ በኩል የተገለፀላቸው ምሁራን ከአስራስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ለህግ የበላይነት መከበር ሲታገሉ በመሰረቱ በጊዜው በተለይም በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ስልጣን ላይ የነበሩና ዋና ተግባራቸውም ጦርነትን ማካሄድና ህዝብን መበዝበዝ የሆነውን ዲስፖታዊ አገዛዞችን በመቃወም ነበር። በእነሱም ዕምነት ይህ ዐይነቱ በአንድ ሰው ላይ የተመሰረተ አምባገነናዊ አገዛዝና የጥቂት ሰዎችን፣ በጊዜው የፊዩዳሎችንና የአሪስቶክራሲውንና፣ እንዲሁም የካቶሊክ ሃይማኖትን መሪዎች ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቀው ለሰላም እጦት ዋናው ምክንያት በመሆኑና፣ በዚህም ምክንያት የተነሳ ሰፊው የአውሮፓ ህዝብ ራሱን ለመግለጽና ማንነቱን ለማወቅ ባለመቻሉ ለተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት ሆኖበት እንደነበር የሚታወቅ። ዕጣውም ሰላምን ማጣትና ማለቂያ በሌለው ጦርነት መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ በዚህም ምክንያት የተነሳ ሰፊው ህዝብ በረሃብና እንደተስቦ በመሳሰሉ በሽታዎች የሚሰቃይና የሚሞትም ነበር።  ይህንን በመረዳትና የዲስፖታዊ አገዛዞች የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ መሆናቸውን በመገንዘብ ነው የተገለፀላቸው ምሁራን በህግ የበላይነት በሚገለጸው ለሊበራል ዲሞክራሲያዊ  ስርዓት የታገሉት። በዚህም መሰረት በሶስቱ ተቋማት መሀከል፣ ማለትም በስራ አስፈጻሚው፣ በህግ አውጭውና በፍርድቤቶች መሀከል ግልጽ የስራ ክፍፍል ሲኖር፣ በዚህ ዐይነቱ የስራ-ክፍፍል ውስጥ ፖለቲካዊ ጣልቃ-ገብነት መኖር የለበትም። በአጠቃላይ ሲታይ የተገለፀላቸው ምሁራን ለህግ የበላይነት መከበር ቢታገሉም ወደ ፊት ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ስርዓት ሊመጣ እንደሚችል በግልጽ የተናገሩት ነገር የለም። በሌላው ወገን ግን የኋላ ላይ በተነሱት እነ ሁምና አዳም ስሚዝ መሀከል በተለይም ከመንግስት ቁጥጥር ስር ውጭ የሆነ ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ አስፈላጊ እንደሆነና፣ ይህም በራሱ ሰፊውን ህዝብ ሊጠቅም እንደሚችል አብራርተዋል። እንደ ግል ሀብት የመሳሰሉትም ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ቅድመ-ሁኔታዎችና አስፈላጊ መሆናቸውን ቢናገሩም ይህ ዐይነቱ የግል ሀብት ቀስ በቀስ ሌላውን ህዝብ የማግለል ኃይል ሊኖረው እንደሚችል የተናገሩት ነገር የለም። ይሁንና ከአጻጻፋቸውና ከትንተናቸው ስንነሳ የገበያ ኢኮኖሚ ውስጠ-ኃይል እንደሌለውና ወደፊት በሳይንስና በቴክኖሎጂ በመመስረት ወደተወሳሰበ የአመራረት ስልትና ኢኮኖሚያዊ  እንቅስቃሴ ሊሸጋገር እንደሚችል ቀድመው ማየት አልቻሉም፤ ሊያዩም አይችሉም። ይህንን ዐይነቱን የካፒታሊዝምን ውስጠ-ኃይልና ወደ ተወሳሰበ ስርዓት ባህርይ በመሸጋገር ኢምፔሪያሊስታዊ ሊሆን እንደሚችል ካርል ማርክስ ነው በግልጽ ለመተንተንና ለማየት የቻለው። የእሱንም ፈለግ የተከተሉ ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው ምሁራን ካፒታሊዝም ከአገሩ ድንበር በመሻገር ዓለም አቀፋዊ በመሆን ሌሎች አገሮችን ተበዝባዥ በማድረግ ዕድገታቸውን እንደሚያቀጭጭ በበቂው ለማብራትና ለማስተማር ችለዋል። ስለሆነም ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በዓለም አቀፈ ደረጃ ሲስፋፉ ነፃነትን በማራማድ በየአገሮች ውስጥ ለተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመች ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብ ወይም እንዲዳብር አመቺ ሁኔታዎችን የመፍጠር የተቀደሰ ተልዕኮ የላቸውም።  በአንፃሩ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳያብብና ፍትሃዊነት እንዳይነግስ አጥብቀው የሚሰሩ ናቸው። ዛሬም የሚታየው ሀቅ ይህ ነው።

ይሁንና የተገለፀላቸው ምሁራን ኃይሎች በተለይም ዲስፖታዊ አገዛዞች እንዲወገዱ፣ በዚህም አማካይነት ሊበራል ዲሞክራሲ እንዲያብብና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መሰረት የሆኑ ግኝቶች እንዲፈጠሩና ካፒታሊዝም እንዲዳብር ፈሩን ቢቀዱም ሃሳባቸው ተምኔታዊ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ዲስፖታዊ አገዛዝች ከተወገዱና የከበርቴው አገዛዝ የበላይነትን ከተቀዳጀ በኋላ በተለይም የከበርቴው መደብ በአንድ በኩል በገጠር ውስጥ ገበሬውን ከመሬቱ የሚያፈናቅል ነበር፤ አካባቢያቸውንም ጥለው በመሄድና በከተማዎች ውስጥ በመኖር ለከፍተኛ አደጋ ለመጋለጥና በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል።  ኢንዱስትሪዎች ወደተቋቋሙባቸው ከተማዎች ስንመጣ የሰራተኛው የኑሮ ሁኔታ እጅግ አሰቃቂና በአንድ ክፍል ውስጥ አስርና ሃያ ሰው እየተጨናነቀ የሚኖርበት ሁኔታ ነበር። ይህም ማለት ካፒታሊዝም በአፃናነሱም ሆነ እያደገ ከመጣ በኋላ እስከ 20ኛው ክፍለዘመነ መግቢያ ድረስ ሰራተኛውን ህዝብ በመዝበዝና ነፃነቱን በመግፈፍ ነው ቀስ በቀስ ከጨቋኝነት ስርዓቱ እየተላቀቀ የመጣው ማለት ይችላል። ይህም ቢሆን በከበርቴው መደብና የመንግስቱን መኪና በሚቆጣጠረው ፍላጎት ተግባራዊ የሆነ  ሳይሆን ራሱ የሰራተኛው መደብ ለነፃነቱና የስራ ቦታውም እንዲሻሻልለት፣ የስራ ሰዓትም እንዲቀንስለት አጥብቆ በመታገሉ ብቻ ነው። በተለይም ለሰራተኛው መደብ ጠበቃ የሚሆኑ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚና የሶስይሎጂ መጽሀፎች መጻፍና መራባት ስለጀመሩ የሰራተኛው መደብ መመሪያ በማግኘት የከበርቴውን መደብ ለመጋፈጥ ቻለ። በአጠቃላይ ሲታይ የሰራተኛውም ሆነ የሰፊው ህዝብ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሳተፍና የመግዛት ኃይሉ ማደግ ከ1945 . በኋላ፣ በተለይም 1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ነው ወደ ተግባር እየተመነዘረ ሊመጣ የቻለው። ካፒታሊዝምም ማደግና መስፋፋት የሚችለው የሰራተኛው መደብ የመግዛት ኃይል ማደግ ሲችል የተረዱ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ሳይወዱ በግድ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ ተገደዱ። ይሁንና ይህ ዐይነቱ የኑሮ መሻሻልና የስራ ስዓት መቀነስ፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ መካፈልና ድምጽን በሚዲያ መልክ መግለጽ የካፒታሊዝምን ምንነት በተሟላ መልክ የሚገልጽ አይደለም። በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ተጨባጭ ሀብትና በገንዘብ የሚተመን ሀብት ከአምስት እስከ አስር በመቶ በሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥጥር ስር ያለ ሲሆን፤ በአሜሪካን ምድር ደግሞ 1% የሚሆነው የህብረተሰብ  ክፍል 90% የሚሆነውን ተጨባጭና በገንዘብ የሚተመን  ሀብት ይቆጣጠራል። የቤት ኪራይ ለመክፈል የማይችለው በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠር የአሜሪካ ዜጋ ደግሞ በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ ድንኳን በመጣል በየሜዳው ላይ ሲተኛና መኖሪያውንም እዚያው አድርጎ ይታያል። ቋሚ ስራም ያለው በተለይም ሃይቴክ ባሉባቸው ከተማዎች ውስጥ የቤት ኪራይ ለመክፈል ስለማይችል መኖሪያውን በትላልቅ መኪናዎች ውስጥ ያደረጉ ይታያል። ስለሆነም በአሜሪካን ምድር የተሟላ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፍርድቤትና የፖለቲካ ፍትሃዊነት የለም። በተለይም ከፍተኛውን ሀብት የሚቆጣጠሩ ጥቂት ሀብታሞች በፖለቲካው መስክ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማድረግ ህግ ለእነሱ በሚስማማ መልክ እንዲረቅ የማድረግ ኃይል አላቸው። ስለሆነም በአሜሪካን ምድር የሰፈነው ፍትሃዊነት የተሟላ አይደለም ማለት ይቻላል።

በተለይም የአሜሪካንን ካፒታሊዝም አነሳስ ስንመለከት ነጮች ከተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ወደ አሜሪካ ሲሄዱና እዚያም መቀመጫቸውን ሲያደርጉ ወደ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ እንዲያኖችን ገድለዋል ወይም አርደዋል። በዚያውም አኗኗራቸውንና ስልጣኔያቸውን እንዳለ አውድመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ተሽጠው የመጡ ጥቁር አፍሪካውያንን እንደ እንስሳ በማየት የሚሸጡና እጅግ በጨከነ መንገድ በፕላንቴንሽን ኢኮኖሚ ላይ እንዲሰሩ በማስገደድና በመበዝበዝ ነው የአሜሪካን ካፒታሊዝም ሊያድግ የቻለው። ሰለሆነም ተገለጸላቸው የሚባሉ የኋላ ኋላ ላይ ፕሬዚደንት ለመሆን የበቁት ግለሰቦች ሳይቀሩ ራሳቸው በባሪያ ንግድ ላይ የተሰማሩና የሚበዘብዙ ነበሩ። የሚያድጉ ጥቁር ልጆችም እንደ ነጩ የመማር ዕድል የሌላቸውና አንዳንዶችም ደግሞ ዕድል ቢያገኙም ይህ ዐይነት ትምህርት ለአንተ አይገባም እየተባሉ ተስፋ ቆርጠው ትምህርታቸውን ጥለው እንዲወጡ የተገደዱና በአሰቃቂ ሁኔታ ላይ እንዲኖሩ የተገደዱ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ጥቁር አሜሪካውያን እንደነበሩ ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ ጥቁሩን አሜሪካዊ በእኩልነት አለማየትና ማግለል በሃያኛው ክፍለዘመን እስከ 1960ዎቹ ዓመታት ድረስ በግልጽ የሚታይ ነበር። ጥቁር አሜሪካውያን ይህንን ጭቆናና ዘረኘንት በመቋቋም ነው የኋላ ኋላ ላይ በሙዚቃና በፊልም ኢንዱስትሪ ማንነታቸውን ሊገልጹና ችሎታም እንዳለቸው ለማረጋገጥ የቻሉት። የጥቁር አሜሪካውያን የተለያዩ ዘፈኖች ማበብ ለአሜሪካ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋት ልዩ ዐይነት አዎንታዊ ተፅዕኖ በመንፈስ ላይ ያሳደረና በዐይነትም ሆነ በጥራትም ተወዳዳሪነት የማይገኝለት የሙዚቃ ስልት ነው ማለት ይቻላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጥቁር አሜሪካኖች በልዩ ልዩ ሙያዎችና በሳይንስ ዘርፍ በመሰማራት ብቃትነታቸውን ያረጋገጡ ናቸው። ይሁንና አሁንም ቢሆን በተለይም ከፖሊስ የሚደርስባቸው ግፍና ግድያ መጠነ-ሰፊ ነው። ይህም የሚያረጋግጠው የአሜሪካ ዲሞክራሲ ፍትሃዊነት የጎደለውና የሰውን ልጅ እኩልነት በማያውቁና ጭንቅላታቸው ባልበሰለ ፖሊሶችና ወታደሮች የተያዘና ይህም አድልዎና ግፍ በግልጽ የሚታይ ነው። በተለይም አንዳንዶች በሰበብ አስባብ ወንጀል ስርተሃል፣ ሰው ገድለሃል በመባል ካለምንም ማረጋገጫ ሰላሳ ዓመትና ከዚያም በላይ እስር ቤት ውስጥ ከማቀቁ በኋላ ምንም ማስረጃ ስላልተገኘብህ በነፃ ተለቀሃል የሚባሉ ቁጥራቸው ብዙ ነው። አክሎግ ቢራራ አሜሪካን አገር ለብዙ ዓመታት እየኖረ ይህንን የነጭ ኦሊጋርኪውንና የተቋማቱን ግፍ ሊረዳና በፍጹም ሊመለከት አልቻለም። በእሱ ዕምነት በአሜሪካን ምድር የተሟላ ፍትህ እንዳለና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ የፍትሃዊው ስርዓት ተጠቃሚዎች እንደሆኑ አድርጎ ነው በመጻፍ ሊያሳምነን የሚቃጣው።

የውጭው የአሜሪካ ፖሊሲ የዚህ የውስጡ የተዛባ ፍትሃዊነትና በጥቂት ኩባንያዎችና ግለስቦች ቁጥጥር ስር የወደቀ በገንዘብና በተጨባጭ ሀብት የሚተመን ነፀብራቅ ነው። አሜሪካን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ኃያል መንግስት ሆኖ ሲነሳ ሆን ብሎ የሰራው በዓለም አቀፍ ደረጃ የበላይነቱን ማረጋገጥና በተለይም በአፍሪካ ምድር፣ በማዕከለኛው አሜሪካና በደቡብ አሜሪካ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቶች እንዳያብቡ ነው። ስለሆነም አብዛኛዎቹ የማዕከለኛው የአሜሪካ አገሮች ወደ ፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በመለወጥ ለአሜሪካን ገበያ ሙዝ፣ ስትሮውቤሪ፣ ካካኦና ቡና እንዲያመርቱ ተገደዋል። በተለይም ዩናይትድ ፍሩት ካምፓኒ በመባል የሚታወቀው የአሜሪካን ኩባንያ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በማዕከለኛው የአሜሪካ አገሮች እንዲተከሉ በማድረግ ፍሬዎቹ በአሜሪካን ገበያ ላይ እንዲሸጡ የሚያደርግና በብዙ የመንግስት ግልበጣዎች የተካፈለና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይተገበርና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳያብብ ያደረገ ነው። እንደነቺሌ፣ ብራዚልና አርጀንቲና የመሳሰሉት ደግሞ ፓናማ ውስጥ በሰለጠኑ የየአገሩ ጄኔራሎች ወይም መኮንኖች ስልጣን ላይ እንዲወጡ በማድረግ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይገነባና እነዚህ አገሮች ወደ ውስጥ ያተኮረ እኮኖሚያዊ ዕድገት ተግባራዊ እንዳያደርጉ መሰናክል የፈጠረ ነው። እንደ ቺሌ በመሳሰሉት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በተደረገባቸውና በህዝብ ድምጽ ብልጫ የተመረጡትን መሪዎች በመገልበጥ ፋሺሽታዊ ስርዓት እንዲመሰረት በቅጥታ ያገዘ ነው። ከዚያም በመቀጠል በእነዚህ አገሮች ውስጥ በነፃ ገበያ ስም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማስገደድ በዕዳ የተበተበና ኢንዱስትሪዎቻቸውንም ያፈራረሰ ነው። አርጀንቲና በሃምሳኛውና በስድሳኛው ዓ.ም  ከደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ በኢኮኖሚ ዕድገት ገፍታ የሄደችና በአንደኛ ደረጃም የምትቆጠር አገር ነበረች። ይሁንና በአሜሪካን የስለላ ድርጅትና በቺካጎ ልጆች ተብለው በሚጠሩ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች በመመከር በነፃ ገበያ ስም ተግባራዊ የነሆው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀድሞ የነበሯት ቀልጣፋ ኢንዱስትሪዎች ሊፈራርሱና በዕዳ ልትተበተብ በአታለች። በዛሬው ወቅት 40% የሚሆነው አርጄንቲናዊ በድህነት ዓለም ውስጥ የሚኖርና ማህበራዊ ትስስሩ የወደመበትና አቅጣጫው የጠፈባት ነው። አንዳንድ የተገለጸላቸውና ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው አሜሪካኖች እንደሚጽፉት በአጠቃላይ ሲታይ ማዕከለኛው አሜሪካና ደቡብ አሜሪካ እዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥ ሊወድቁና ህዝቦቻቸውም በድህነት ሊማቅቁ የቻሉት በአሜሪካን የቀጥታ ጣልቃ-ገብነት የተነሳ እንደሆነ ነው። አብዛኛውም የጥሬ-ሀብት በትላልቅ የአሜሪካን ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር ያለና፣ እነዚህ ትላልቅ የጥሬ-ሀብት ዘራፊ ኩባንያዎች´ የየአካባቢውን የማህበራዊና የአካባቢ ሁኔታ በማዘበራረቅና በማበላሸት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አገሩን እየጣለ የተሻለ ዕድል አገኛለሁ በማለት ወደ አሜሪካ በመሰደድ እዚያ ጉልበቱ እየተበዘበዘ እንደሚኖር የታወቀ ጉዳይ ነው። ከማዕከለኛውና ከደቡቡ አሜሪካ ሜክሲኮን በማቋረጥ ወደ አሜሪካ የሚፈልሱት በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ስደተኞች የአሜሪካን አገዛዞች ጣልቃ-ገብነት ውጤቶች መሆናቸውን ለምርጫ የሚወዳደሩ ፕሬዚደንቶችና ሌሎች ፖለቲክኞች ይህንን ሀቅ ባለመረዳት ህጋዊ አይደሉም በሚሏቸው ስደተኞች ላይ አግባብ የሌለው ዘመቻ ያካሂዳሉ። የተለያዩ የአሜሪካ አገዛዞች እንደዚህ ዐይነቱን ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ዕድገት አካሄዳቸውን እስካላቆሙና በየአገሮች ውስጥ ገብተው መፈትፈታቸውን እስካልተው ድረስ የተሻለ ዕድል የሚፈልገው የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ ህዝብ ወደ አሜሪካን መጓዙን በፍጹም ሊያቆም አይችልም። በሌላ ወገን ደግሞ በአጠቃላይ ሲታይ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በተፈጥሮው የሌሎችን አገሮች የተሟላ  ዕድገት ስለማይፈልግ ከእርኩስ ተግባሩ በፍጹም ሊቆጠብ አይችልም። ህዝብን ማፈናቀል፣ በሃይማኖትና በጎሳ ስም አሳቦ አንድን ህዝብ መከፋፈልና አለመረጋጋጥ በመፍጠር ጥሬ-ሀብትን በመዝረፍ የተሟላ ዕድገት እንዳይመጣ የሚያድረገውን ተግባሩን ይቀጥላል ማለት ነው። ከዚህ ዐይነቱ ኃይልም ፍትሃዊነትን መጠየቅ አላዋቂነት ነው። 

ወደ አፍሪካ ስንመጣ የዛሬዬቱ አፍሪካ የባርያ ንግድ፣ የቅኝ-ግዛትና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ውጤት ነች። አባዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች በባሪያ ንግድና በቅኝ-ግዛት የተነሳ እስከዚያ ጊዜ ድረስ የነበራቸውን ስልጣኔና የአገዛዝ መዋቅሮች እንዳሉ ይወድሙባቸዋል። በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተው የውስጥ ኢኮኖሚያቸው እንዳይዳብር ይገታል። የቅኝ ገዢዎች ወደ አፍሪካ ሲመጡ ስልጣኔን ይዘው የመጡ ሳይሆን የነበረውን በማፈራረስ ገበሬውን ለአውሮፓ ገበያ ብቻ የሚሆን የእርሻ ምርት ላይ እንዲሰማራ ነው ያስገደዱት። ቡና፣ ካካኦ. ኦቾሎኒና ሌሎች ምርቶችን እየተመረቱ ወደ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች የሚላኩ ነበሩ። የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ለብዙዎች አስርት ዓመታት በአፍሪካ ምድር ውስጥ በቆዩባቸው ዘመናት ከተማዎችንና መንደሮችን ስርዓት ባለው መንገድ አልገነቡም። የስራ-ክፍፍል እንዲዳብር አላደረጉም። የትምህርትና ልዩ ልዩ ተቋማትን አልገነቡም። ባጭሩ አፍሪካን አራቁተውና አደንቁረው ነው የሄዱት። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ነፃ ወጡ ከተባለበት ከስድሳዎች ዓመታት ጊዜ ጀምሮ በምንም ዐይነት ዕውነተኛ ነፃነታቸውን አልተቀዳጁም። የመንግስታት መኪናዎች በተዘዋዋሪ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች የተገዙና ቁጥጥርም የሚደረግባቸው ነበሩ። አንዳንድ የተገለጸላቸው አመራሮች እንደ ክዋሜ ንክሩማ የመሳሰሉትን በመገልበጥ የጋና ሁኔታ እንዳይረጋጋ ለማድረግ በቅተዋል። የአሜሪካኑ፣ የእንግሊዙና የፈረንሳይ የስለላ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ሞሳድ የሚባለው የስለላ ድርጅት በአፍርካ አገሮች የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ በመግባት አገሮች ነፃነትን ተቀዳጁ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ከስድሳ በላይ የሚቆጠር የመንግስት ግልበጣዎች አካሂደውባቸዋል። እንደ ሳንካራ የመሳሰሉ ወጣት መሪዎች በጠራራ ፀሀይ ላይ ተገድለዋል። ከዚህ ስንነሳ አሜሪካንም ሆነ የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም በአፍሪካ ምድር ውስጥ የተሟላና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ዕድገት እንዲመጣ አይፈልግም። ስለሆነም ዲሞክራሲያዊ ስርዓትም እንዲመጣ ምኞቱ አይደለም። በአንድ አገር ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ሁለ-ገብ የሆነ ዕድገት ሊመጣና ህዝቡንም ከድህነት ሊያላቅቀው የሚችለው በተገለጸላቸው ምሁራንና በሰፊው ህዝብ ትግል ተሳትፎ ብቻ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በጃፓን፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በታይዋንና በሲንጋፖር የተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ የቻለው እነዚህ ህዝቦች ቀላ ያለ የቆዳ ቀለም ስላላቸውና የኮሙኒስት ርዕዮተ-ዓለምም እንዳይስፋፋ በማሰብ ብቻ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የነጭ ኦሊጋርኪው መደብ በምንም ዐይነት በአፍርካ ምድር ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያብብና በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በአጭሩ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይመጣ አጥብቆ ይሰራል። ዋናው ፍልጎቱም አፍሪካ ሁልጊዜ የጥሬ-ሀብት አምራች አህጉር ሆና እንድትቀር ማድረግ ነው። ለዚህም ነው አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች ነፃ ወጡ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ በነጻ ገበያ ስም ኢ-ሳይንሳዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚገደዱት። በየአገሩ ያሉትም የመንግስት መኪናዎች፣ ማለትም የወታደሩ፣ የፖሊሱ፣ የፀጥታ ኃይሉ፣ የስቪል ቢሮክራሲውና ቴክኖክራቶች በሙሉ ለአሜሪካን በሚስማማ መንገድ የሰለጠኑና ከውስጥ ሀብት እንዲበዘበዝ በማድረግ ሰፊው ህዝብ ደግሞ በድህነት ማቆ እንዲቀር የሚያደርጉ ናቸው። አብዛኛዎቹ የተገለጸላቸው ስላልሆኑና የተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበረሰብ ከታቸ ወደ ላይ እንዴት እንደሚገነባ ስለማያውቁ የአሜሪካንና የግብረ-አበሮቻቸው አሽከር ሆነው ሊቀሩ ችለዋል። በተለይም ግሎባል ካፒታሊዝም እየተወሳሰበ ስለመጣና አንድ ወጥ አስተሳሰብ ብቻ ስለተስፋፋ ሁሉም ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ የሌለው ይመስል ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግና ራሱ የተደላደለ ኑሮ እየኖረ በአንፃሩ ደግሞ ህዝቡን እያደኸየና አገሩን እያፈራረሰ ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ የአክሎግ ቢራራ አጻጻፍ ወይም ትንተና እ-ሳይንሳዊ የሆነና ተጨባጭ ሁኔታዎችን እንድንገነዘብና በትክክል እንድናነብ የሚያደርግ አይደለም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አክሎግ ቢራራ የካፒታሊዝምን አፀናነስና ዕድገት፣ እንዲሁም ውስጣዊ የአሰራር ህግ በሚገባ የተረዳ አይመስለኝም። በተለይም ኢምፔሪያሊዝም ምን እንደሆነና እምፔሪያሊዝም ካለጦርነትና ካለብዝበዛ የበላይነቱን ይዞ ሊቆይ እንደማይችል የተገነዘበና በትክክል የተከታተለ አይመስልም። ስለሆነም ሊሆን የማይችለውንና የአሜሪካንን ውስጥ ባህርይና ወደ ውጭ በመውጣት አገሮችን የሚያከረባብተውን አካሄዱን ባለመረዳት የተነሳ የሚያስተጋባው የፍትህ መልዕክት በጣም አሳሳችና ትጥቅ አስፈቺ ነው። በዓለም አቀፍ የሚካሄዱ ጦርነቶች በሙሉ ካለ አሜሪካን ተሳትፎ በፍጹም አይካሄዱም። ብላክ ወተር የሚባለው መርሲነሪዎችን የሚያሰለጥነውና የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲን የሚያካሄደው የግል ኩባንያ ከአሜሪካ የስለላ ድርጅት ጋር በጥብቅ የሚሰራና በብዙ ሚሊዮን ዶላር እየተከፈለው የርስ በርስ ጦርነት እንዲካሄድ የሚሰራ ሰይጣናዊ ኃይል ነው። ኢራክ ውስጥም በጦርነት በመካፈል ስንት ግፍ እንደፈጸመ የሚታወቅ ነው።  ወደ አገራችንም ስንመጣ ወያኔና ኦነግ ሸኔ የሚባሉት ከሲአይኤና ከብላክ ወተር ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ያላቸውና የጦር መሳሪያም የሚያገኙም ናቸው። አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹም የሲአይኤና የሌሎች የስለላ ድርጅቶች ቅጥረኞች ናቸው፡ ለዚህም ነው በተለይም የአማራው ህዝብ ሲጨፈጨፍ ዝም ብለው የሚመለከቱት። ይህም የአሜሪካና የግብረ-አበሮቹ ሌላው ስትራቴጂ ነው። አንድ አገር በማያቋርጥ ጦርነት መያዝና መወጠር አለባት። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህዝቡ የመኖርን ትርጉም እንዳይገነዘብ በማድረግ አቅጣጫውን ይስታል። አንደኛው ሌላውን ስለሚጠራጠርና ስለሚፈራው አለመተማመን ይፈጠራል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በጋራ መስራት አይቻልም። ሁኔታው በዚህ መቀጠል አለበት። በዚህ መልክ ነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮች የአፍሪካን አገሮች ወጥረው የያዙትና በድብቅና ድብቅ ያልሆነ ጦርነት በማካሄድ ኋላ-ቀርነትና ድህነት ፈርጥመው እንዲቀሩ የሚያድርጉት። ስለሆነም ከአሜሪካንና ከግብረ-አበሮች ፍትሃዊነትን መጠበቅና ለዚህም ቁሙ ማለት በጣም የዋህነት ብቻ ሳይሆን አሳሳችም ነው። ከዚህ ዐይነቱ አዘናጊ አስተሳሰብና አጻጻፍ የግዴታ መቆጠብ ያስፈልጋል። መላክም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

 https://www.youtube.com/watch?v=G3xUUVTJSz4

 

ማሳሳቢያ እንደምመለከተው ሳይንሳዊ የሆነ ትንተና ለመስጠት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የአንድ አገር ተጨባጭ ሁኔታና  የዓለም ፖለቲካ ሂሳዊና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ካልታዩና ሀተታም ለመስጠት ካልተቻለ አንድ ህዝብ የተሟላ ነፃነት በፍጹም ለማግኘት አይችልም። ስለሆነም ሳይንሳዊና ሂሳዊ የሆኑ ጽሁፎችን መጻፍና በተለይም ታዳጊውን ወጣት ማስተማር ታሪካዊ ግዴታ ነው። ይህ ዐይነቱ ኃላፊነትንና ግዴታ በአንድ ወይም በሁለት ሰዎች ትከሻ ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም። ስንዴውን ከእንክርዳዱ ለመለየትና ሳይንሳዊ አመለካከት እንዲዳብር ከተፈለገ የብዙ ሰዎችን ተሳትፎ ይፈልጋል። ካለበለዚያ የጨለማው ዘመን እየተራዘመ ይሄዳል ማለት ነው። ከዚህም ባሻገር ሳይንሳዊና ክሪቲካል የሆኑ ትንተናዎች ተከታታይነት እንዲኖራቸው ከተፈለገ በሃሳብም ሆነ በማቴሪያል መደገፍ አስፈላጊ ነው። አንድን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የብዙ ሳምንታት ጊዜን ስለሚጠይቅ የግዴታ ማበረታታትና መደገፍ ያፈልጋል። ስለሆነም በድረ-ገጼ ውስጥ የሰፈሩትን ጽሁፎች ማንበብ ያስፈልጋል። ማንኛውም መረጃ እዚያው ውስጥ ተቀምጧል።

Filed in: Amharic