>

በአገራችን ምድር ለተፈጠረው ውዝግብና እስከዛሬም ድረስ ዘልቆ ለሚታየው የፖለቲካ ቀውስ....ለልጅ ተድላ መላኩ የተሰጠ ትችታዊ መልስ!!

በአገራችን ምድር ለተፈጠረው ውዝግብና እስከዛሬም ድረስ ዘልቆ ለሚታየው የፖለቲካ ቀውስ ተጠያቄው የግራ አስተሳስብ በመግባቱ ምክንያት አይደለም፤ ዋናው ምክንያት ሌላ ቦታ ላይ ነው!!

 

ለልጅ ተድላ መላኩ የተሰጠ ትችታዊ መልስ!!

 

 ፈቃዱ በቀለ  (ዶ/ር)

   

የአገራችን የፖለቲካ ችግር የመነጨው በመሰረቱ የግራን ወይም የቀኝ ፖለቲካን በሚያራምዱ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች አማካይነት አይደለም። በአጠቃላይ  ስለኢትዮጵያ፣ በተለይም ደግሞ የአማራውን ብሔረሰብ እንወክላለን፣ ወይም ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅት አለን የሚሉ ሰዎች ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአገራችን ምድር ለተፈጠረው የፖለቲካ ምስቅልቅልና መገዳደል ዋናው ተጠያቂ የሚያደርጉት የግራን ፖለቲካ ያራምዳሉ የሚሏቸውን ድርጅቶች ነው። በሌላ ወገን ግን የግራ ፖለቲካ ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ይሁንና  ግን ግራነክ ወይም በማርክስና የእሱን ቲዎሪ እናራምዳለን በሚሉ ግለ ሰቦች ወይም ድርጅቶች የተጻፉ መጽሀፎችን በደንብ ላነበበ ወይም ላጠና በአንዳቸውም ጽሁፍ ውስጥ ሰውን ግደል ወይም አንድን አገር አመሰቃቅል የሚል ነገር አልተጻፈም። ለምሳሌ በማርክስ የተጻፉትን የመጀመሪያዎቹ ጽሁፎቹን፣ Ground Work ዳስ ካፒታልንና ሌሎችንም ላነበበ የሚገነዘበው ጽሁፎቹ በሙሉ በጊዜው የነበሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የህብረተሰብና የሀብት ቁጥጥርን ሁኔታዎችን የሚመለከቱ የቲዎሪ ጽሁፎችና ሳይንሳዊ ሀተታዎች ናቸው።  እነዚህ ጽሁፎችና መጽሀፎች በሙሉ የተጻፉት ከጊዜው ሁኔታ በመነሳትና በጊዜው የነበረውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ በመመርኮዝ የተጻፉና ሁኔታውንም የሚያንፀባርቁ ናቸው። ዝምብለው በአቦሰጡኝ የተጻፉ ሳይሆኑ ሳይንሳዊ የአጻጻፍ ስልትና አቀራረብ ነው።  በእነዚህ ጽሁፎች ውስጥ አልፎ አልፎ በተለይም የፖለቲካ ጽሁፎች ውስጥ ማርክስ ለማሳየት የሞከረው በፕረሽያ አገዛዞች የሰፈነውን ጭካኔ የበዛበትን ፖለቲካ ነው። ስለሆነም የግዴታ የፖለቲካ ነፃነት መኖር አለበት ብለው ነው እነማርክስ ብቻ ሳይሆኑ የሊበራል አመለካከት አለን የሚሉ ግለሰቦችም ሁሉ ይጽፉና ይታገሉ ይታገሉ የነበረው። ማርክስም ራሱ ሊበራልና ለፓለቲካ ነፃነት እንታገላለን ከሚሉት ጋር ሁሉ የሚወያይና የሚከራከር ነበር። እነማርክስ በነበሩበት ዘመን እንደዛሬው ብዙ ፓርቲዎች አልነበሩም ስልጣንም በአንድ ዲስፖታዊ አገዛዝ ቁጥጥር ስር የነበረና ይህ ዐይነቱ አገዛዝ ለፖለቲካ ነፃነት ጠንቅ የነበረና አስተያየትን የመግለጽ መብት አልነበረም። ስለሆነም ህብረተሰቡ እየተሰበጣጠረ ሲመጣና በጊዜው በነበረው የፈጣን የኢንዱስትሪ ፖለቲካ የተነሳ ብዙ ህዝብ ከገጠር እየተፈናቀለ የሚመጣ ስለነበርና በኢንዱስትሪዎቹም ውስጥ ተቀጥሮ ይሰራ ስለነበር የሚሰራበት ሁኔታ እጅግ አሰቃቂ ነበር። በተጨማሪም አንድ ሰራተኛ በቀን ከ12 ሰዓት በላይ ስለሚሰራና በእየኢንዱስትሪዎችም ውስጥ ሰራተኛው የእሱን ጥቅም የሚወክልና የሚከራከርለት ስላልነበር በከፍተኛ ደረጃ ይበዘበዝ ነበር። ሰራተኛውም በእየኢንዱስትሪዎች ውስጥም ሆነ በአጠቃላይ ሲታይ የሰራተኛ ማህበር በመመስረት የመደራጀት መብት አልነበረውም። ስለሆነም ይህንና የብዝበዛን ሁኔታ አስመልክቶ ማርክስ ብቻ ሳይሆን ነቁ የሚባሉና የተማሩ ኃይሎች ይህ ዐይነቱ ጭቆና መቆም አለበት፤ የሰራተኛውም መብት መጠበቅና በማህበርም መደራጀት አለበት ብለው ይጽፉ ነበር። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በእንግሊዝ አገርም በግልጽ የሚታይና በትላልቅ ከተማዎች ከገጠር እየተፈናቀለ የሚመጣው ህዝብ በከፍተኛ ድህነትና ስቃይ የሚኖርበት ዘመን ነበር። ይህም ማለት ለሊበራል ዲሞክራሲ መታገል የተጀመረው 16ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ቢሆንም አገዛዞችና የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ከሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ በጣም የራቁና ኋላ የቀሩም ነበሩ ማለት ይቻላል። ስለሆነም እነ ማርክስና ኤንግልስ ያነሱት ጥያቄና ኋላ ላይም የተቀጣጠለው ትግል በጣም አስፈላጊና የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነበር። መብትህ ሲገፈፍና ስትበዘበዝ ዝምብለህ ተመልከት፣ አትከራከርም የሚል የተፈጥሮ ህግ ስለሌለ እነማርክስም ሆነ ሌሎች የነነፃነትን ትርጉምና አስፈላጊነት የተረዱ ምሁራን ያነሱ የነበረው የፖለቲካ ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ነበር። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተለመደው ነገር የመንፈስ ተሃድሶ ከጀመረበት 15ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ለፖለቲካ ነፃነት መታገል ነበር። ለዚህም ነው  የኋላ ኋላ ላይ ቀስ በቀስ የአስተሳሰብ አድማስ ሊሰፋ የቻለውና የተለያዩ ዕውቀቶችም ሊያብቡ የቻሉት። በዚህም ምክንያት ነው የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ በማበብ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ፈር የተቀደደው። በዚህም ምክንያት ነው ካፒታሊዝም ሊዳብርና ዓለም አቀፋዊ ሊሆን የቻለው። በዚህም ምክንያት ነው ሁላችንም ልንቀሳቀስ የቻልነው። ስለሆነም በአጠቃላይ ሲታይ ለሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለም መታገል ኋላ ላይ ብቅ ያለና በጊዜው የነበረውን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያንፀባርቅና የአጠቃላዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አንድ አካል ነበር። በመሆኑም የሶሻሊዝም አስተሳሰብና የግራ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመፈጠሩና በመስፋፋቱ የአውሮፓ ህዝብ ወደ ኋላ አልቀረም። የወዝ አደሩም በሙያ ማህበሩ በመደራጀቱ የተነሳ በእየኢንዱስትሪዎች ውስጥ የምርት እንቅስቃሴ በፍጹም አልቀነሰም። የኋላ ኋላ ላይ  የወዝ አደሩ የመግዛት ኃይል እያደገ ሲመጣ በአጠቃላ ሲታይ ኢኮኖሚውም ማደግና የውስጥ ገበያም እየሰፋ ሊመጣ  ችሏል። ይህ ሁሉ የትግል ውጤት እንጂ በካፒታሊስቶችና በገዢው መደብ እንደ ቡራኬ የተሰጠ አይደለም። ነገሩን በዚህ መልክ ነው ማየት ያለብን።

የማርክስን የኢኮኖሚ ጽሁፎችንም ስንመለከት ዳስ ካፒታልንና ሰርፕለስ ቫልዩ የሚባሉትን የኢኮኖሚ ጽሁፎችን የጻፈው ለንደን ላይብረሪ ውስጥ ሰላሳ ዐመት ያህል እዚያው በማጥናት ነው። በገንዘብም ይደግፈው የነበረው የፋብሪካ ባለሀብት ልጅ የነበረው ፍሪድርሽ ኤንግልስ ነው። በተጨማሪም ለጋዜጦች የፖለቲካ ትንተናዎችን በመጻፍና ገንዘብ በማግኘት ቤተሰቦቹን ያስተዳድር ነበር። ሌሎችም የማርክስን ሳይንሳዊ የአጻጻፍ ስልት መሠረት አድርገው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታዎችን ይጽፉ የነበሩት ምሁራን በሙሉ ስለአመጽና ስለግድያ አስፈላጊነት አንዳችም ቦታ ላይ ጽፈው አያውቁም። አመጽን፣ ግድያንና ጭቆናን ተግባራዊ ያደርጉ የነበሩት ስልጣን ላይ የነበሩትና ከስልጣን ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ባለሀብታሞች፣ በተለይም አሪስቶክራቶችና ፊዩዳሎች ነበሩ። እነዚህ ኃይሎች የጥገና ለውጥንና የፖለቲካ ነፃነትን አጥብቀው ይጠሉ ስለነበር ሆን ብለው የያዙት የሶሻሊስት አስተሳሰብ አሏቸው የሚሏቸውን ምሁሮች በሙሉ እያሳደዱ መግደል ነበር። በተለይም በጀርመን ምድር 19ኛው ክፍለዘመን መጨረሻና 20ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ ላይ ግራ አስተሳሰብ አላቸው የሚሏቸውን ግለሰቦች በሙሉ እያሳደዱ መግደል የተለመደ ነበር። በተለይም ሮዛ ሉክሰምበርግና ካርል ሊበክኔችት የሚባሉት የወዝአደሩ መሪዎች በፋሺሽት ኃይሎች ነው ተገድለው  ገደል ውስጥ የተጣሉት። እነሂትለር ከዚህ በመነሳት ነው ፋሺሽታዊ እንቅስቃሴያቸውን ለማስፋፋት የቻሉትና 50 ሚሊዮን ህዝብ መገደልና ለስልጣኔ ውድመት ምክንያት  የሆኑት። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ኃያል ሆኖ ሲወጣ ለፋሺዝም ምክንያትና መነሻ የሆኑቱን ነገሮች ከማጥናትና ፋሺዝም እንደገና እንዳይንሰራራ  ሳይንሳዊ ጥናት ከማካሄድ ይልቅ ሆን ብሎ የያዘው ሶሻሊዝንም እንደዋና ጠላትና የአመጽ ምንጭ በማድረግ ነው የውሸት ትረካ ያስፋፋውና እንደኛ ባሉ የፖለቲካ ብስለት በሌሉን ሰዎች ጭንቅላት ውስጥ መትከል የቻለው። ካፒታሊዝም በእኩለነት ላይ ተመስርቶ የተገነባ ባለመሆኑና በእኩልነትም የማያምን ስለሆነ የግዴታ ለእኩልነትና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል በሙሉ የሶሻሊስት አስተሳሰብ ነው እያለ በማጥላላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያልተሰተካከለና ብዝበዛ የሰፈነበት ስርዓት እንዲመሰረት ለማድረግ በቃ።  ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካን የመንግስቱን መኪና፣ ማለትም የሚሊተሪውን፣ የፖሊሱንና የፀጥታ መዋቅሩን የገነባው ወይም ያዋቀረው የጀርመንን የፋሺስቶችን የመንግስታዊ አወቃቀር እንደምሳሌና እንደመመሪያ በማድረግ ነው። ይህንንም የአወቃቀር ስልት ሌሎችም አገሮች እንዲኮርጁ በማድረግ በተለይም የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ መኮንኖች ፓናማ እየሰለጠኑ የኋላ ኋላ ላይ በመንግስት ግልበጣ አማካይነት ስልጣን ላይ ለመውጣት ችለዋል። በዚህም ምክንያት ፋሽስታዊ አገዛዞችን ሊመሰርቱ ችለዋል። የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ ጄኔራሎችም ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ዋናው ጠላታችን ኮሙኒዝም ነው በማለት ለዲሞክራሲያዊ መበት፣ ለሰብአዊ መብት መከበርና ለኑሮ መሻሻል የሚታገሉትን ኃይሎች በሙሉ እንዳላ ሲያጭዷቸው፣ ከዚህ የተረፉት ደግሞ ወደ አውሮፓ ለማምለጥ ችለዋል። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምም  ኮሙኒዝምን ለመዋጋት በሚል ሰበብ እነዚህን አገሮች ምሁራዊ አልባ ለማድረግ በቅቷል። አንድ አገር ደግሞ በምሁር አልባ ከሆነች ዲሞክራሲያዊ ባህልን ማዳበር አትችልም። የዲሞክራሲ ባህል በሌለበት አገር ደግሞ የሃሳብ ልወውጥና ክርክር አይኖርም። ክርክር ከሌለና ጥያቄ የማይጠየቅ ከሆነ ደግሞ ጥቂት አምባገነኖች እንደፈለጋቸው ይፈነጫሉ። ሳይንስና ቴክኖሎጂም እንዳያብቡ እንቅፋት ይሆናሉ። ሳይንስና ቴክኖሎጂ  ማደግ በማይችሉበት አገሮች ደግሞ  ሁለገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት አይፈጠርም ወይም አይኖርም። ሁለገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት በሌለበት አገር ሰፋ ያለ የስራ-መስክ አይፈጠርም። ሰፋ ያለ የስራ መስክ በሌለበት አገር ደግሞ ማህበራዊና ባህላዊ ችግሮች ይፈጠራሉ። በዚያውም የስነ-ልቦና ወይም የህሊና ቀውስ ይፈጠራል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ስልጣን ላይ ለመውጣት ለሚቋምጡና አምባገነናዊ አገዛዝን ለመመስረት ለሚፈልጉ የሚያመች ነው። ይህ በራሱ ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ለግብረአበሮቹ በጣም ያመቻል። ስለሆነም ሳይንሳዊ በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ሀብትን ለመዝረፍ ያመቸዋል። ስልጣን ላይ ካሉት ፋሽስታዊ አገዛዞች ጋር በመተባበርና ማንኛውንም ድጋፍ በመስጠት ነፃነት እንዳይኖር ያደርጋል። ሰፊው ህዝብ ለዝንት-ዓለም ነፃነቱ ተገፎና እየተበዘበዘ እንዲኖር ያደርጋል። ስለሆነም በዚህ መልክ ኋላ-ቀርነትና ድህነት ፈርጥመው መቅረት ይችላሉ። በሌላ አነጋገር፣ ካፒታሊዝም ስላደገና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተበላሸ መልክ ስለተስፋፋ  የነፃነት ተልዕኮ አለው ማለት አይደለም። ካፒታሊዝም የነፃነትና የኢኮኖሚ ዕድገት ተልዕኮ ቢኖረው ኑሮ የኮሙኒስት ብሎክ ከፈራረስ ከ1989 ዓ.ም በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውነተኛ የሊበራል ዲሞክራሲን በማስፋፋት በሁሉም አገሮች ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ብቅ እንዲል አመቺ ሁኔታዎችን በፈጠረ ነበር። ይህንን ከማድረግ ይልቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን ነው ዓለም አቀፋዊ በማድረግ የአንድን አገር ህዝብ በሃይማኖትና በጎሳ በመከፋፈል ርስ በርሳቸው የሚያጫርሳቻው። ይህ ዐይነቱ የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ የካፒታሊዝምና የኢምፔሪያሊዝም ውስጣዊ ባህርዮች ናቸው። በዚህም አማካይነት ብቻ ነው የበላይነቱን ይዞ መቆየት የሚችለው።

በአጠቃላይ ሲታይ ግድያና አመጽ ይፈጸሙ የነበረው በካፒታሊዝም አፍላ ወቅትና ካፒታሊዝምም እያደገ ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ነው። በአውሮፓ ምድር 20ኛው ክፍለዘመን የተከሰቱት ጦርነቶች በሙሉ ከካፒታሊዝም ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። የባርያ ንግድና የቅኝ አገዛዝም ከካፒታሊዝም ጋር በቀጥታ የተያያዙና ለአፍሪካ ኋለመቅረት ዋናው ምክንያት የሆኑ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ ልጅ ተድላ መላክ እንደሚለው የግራ አስተሳሰብ በመስፋፋቱ አይደለም በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ አመጸኛነት ሊስፋፋ የቻለው። የአገራችንም አገዛዝ በተለይም አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ አመጽን ሊጋብዝ የሚችልና ለኢኮኖሚ ዕድገት ዕንቅፋት የሆነ መንግስታዊ አወቃቀር ሊመሰረትና ሊገነባ የቻለው በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች ዕርዳታና ድጋፍ ነው። የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን የመንግስት አወቃቀር ለተመለከተ ሆን ተብለው በቅኝ-ገዢዎች ለብዝበዛ እንዲያመቹ የተዋቀሩና ይህ ሁኔታ እስካሁንም ድረስ የቀጠለ ነው። በመንግስታዊ መኪና አወቃቀርና በፖሊሲውና በፖለቲካው አማካይነት ነው አንድ አገር በኢኮኖሚም ሆነ በማህበራዊ መስክ ልታድግ የምትችለው። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር የመንግስት መኪና አወቃቀር ከመጀመሪያውኑ ጨቋኝ ሆኖ እንዲዋቀር ከተደረገ ዲሞክራሲያዊ ነፃነትን በማፈን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይኖር ያደርጋል። ስለሆነም ነው በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን የተመሰረተው የመንግስት መኪናና፣ የአገዛዙ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከስልጣን እንዲወገዱ ያበቃቸው። በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥርና ፍላጎቱን ማሟላት የሚችሉ ቀልጣፋና የሰለጠኑ ተቋማት መገንባት ባለመቻላቸው እየተባባሰ በመጣው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ እየተንገዳገዱ ከስልጣን ላይ ሊወገዱ ችለዋል።  ይህንን የሚስት ሰው ካለ አንድ አገር በምን መሰረት ላይ ተመርኮዙ ወደፊት መጓዝ እንዳለበት አልተረዳም ማለት ነው። እንደሚታወቀው በአንድ አገር የሚኖር ህዝብ ሰው እንደመሆኑ መጠን ፍላጎትና ህልም አለው። ፍላጎቶቹም ልዩ ልዩ ነገሮች ሲሆኑ፣ በተለይም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስፈልገዋል። በዚያውም ነፃነትን ሲጎናፀፍ የመፍጠር ኃይሉም እየዳበረ ይመጣል። ልዩ ልዩ አስተሳሰቦችም በመፍለቅና በመዳበር ለህብረተሰብ ዕድገት አስተዋፅዖ ማድረግ ይችላሉ። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የነበረውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ላጠናና ለተመራመረ የሚገነዘበው ነገር ኢትዮጵያችን በሁሉም አቅጣጫ ወደ ኋላ የቀረች አገር እንደነበረች ነው። ይህንን የሚክድ ሰው ካለ አንድ ህብረተሰብ እዚያው ቆሞ መቅረት አለበት የሚል ሰው ብቻ ነው። ይሁንና ግን ከሰው ልጅ የአስተሳሰብና የፍላጎት አንፃር ስንነሳ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም። ይኸኛው ሆነ ወይም ያኛው ዐይነት አመለካከት ያላቸው የህብረተሰብ ወይም የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪዎች የሚስማሙብት አስተሳሰብ የሰው ልጅ አንድ ቦታ ላይ ረግቶ የሚቆም ሳይሆን፣  የሚያድግና ከአንድ ዝቅተኛ ሁኔታ ወደ ተሻለ የህብረተሰብ እንደሚሸጋገር ነው፤ ችሎታም እንዳለው ነው። ለዚህም ነው ከአዳኝነት በመላቀቅ ተቀማጭ በመሆን ማረስ የቻለው። በዚህም አማካይነት ነው መንደሮችንና ከተማዎችን እየመሰረተና እያዳበረ ሲመጣ በዚያው መጠንም የዕደ-ጥበብ ስራና የንግድ እንቅስቃሴ ማበብ የቻሉት።  ይህ ዐይነቱ ዕድገትና መሻሻል ሁልግዜ ሊሰናከል ወይም ሊዘገይ የሚችለው ስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ የዕድገትን ትርጉም ያልተረዳ ከሆነና አፋኝና ጨቋኝም ከሆነ ነው።

ይህን ሁሉ ትተን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንሄድ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከስድስተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ እስከ አስራስምንተኛው ክፍለዘመን ድረስ የነበሩ ጭቆናዎችና ጦርነቶቾ በሙሉ በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎችና በባላባቶች የሚካሄዱ ነበሩ። ጋሊሊዮ እስር ቤት ውስጥ የተወረወረው በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች ነው። እስርቤትም እንዲገባ የተደረገው የእነሱን ቀኖናዊ አስተሳሰብ በመቃወሙ ነው። ብሩኖ ጋርዲያኖ የሚባለው ቄስና ምሁር 16ኛው ክፍለዘመን ከእነ ነፍሱ የተቃጠለው የእነሱን አንድ ወጥና ቀኖናዊ አስተሳሰብ በመቃወሙ ነው። ከዚያ በኋላ እነ ሬኔ ዲካ የመሳሰሉት ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች እንገደላለን ብለው ሰለፈሩ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል። እስከ 20ኛው ክፍለዘመን ድረስ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሊበራል አስተሳሰብ የሰፈነው ሆላንድና እሰከተወሰነ ደረጃ ድረስ ደግሞ እንግሊዝ አገር ብቻ ነበር። ሆላንድ ውስጥ የሊበራል አስተሳሰብ ሊሰፍን የቻለው ደግሞ ፊዩዳላዊ ስርዓት በፍጹም ስላልነበረ ነው። በማዕከለኛው ክፍለዘመንና እሰከ 19ኛው ክፍለዘመን ድረስ ሆላንድ የትናንሽ ገበሬዎች አገር ነበረች።

ለማንኛውም የሊበራል አስተሳሰብን አነሳስና የሳይንስን አፀናነስ ሰንመለከት ከዚህ አሰገዳጅ ሁኔታ በመነሳት ነው። ዋና ዓላማውም ስልጣንን ለመገደብና የህግ የበላይነትን ለማስፈን ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የማይካድ ነገር 16ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ የፍጹም ሞናርኪዎች የሚባሉትና የተገለፀላቸው መሪዎች ዩኒቨርሲቲዎችንና መጻህፍት ቤቶችን በመክፈትና በማስፋፋት ለምሁራዊ እንቅስቃሴና መዳበር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ይህም የዘመኑ ሞድ ወይም ስልት የነበረና አንደኛው የአውሮፓው አገር ከሌላው በመኮረጅ ዕውቀትን ሊያስፋፉ ችለዋል። በዕውቀትም አማካይነት ጥበብና ሳይንስ ማበብ ችለዋል። አያሌ ፈላስፋዎች፣ የሳይንስ ሰዎች፣ የከተማ ዕቅድ አውጭዎች፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ ኢኮኖሚስቶችና ሶስዮሎጂስቶች ብቅ በማለት ከአረጀው አስተሳሰብ ጋር መጋፈጥ ችለዋል። ስለሆነም ዘመኑ ከጨለማ አስተሳሰብ ወደብርሃን የሚጓዙበት ስለነበር The Age of Enlightenment በመባል ይታወቃል። ለዚህ አስተሳሰብ መፍለቅ ዋናው ምክንያት የሆነው ደግሞ በጊዜው የነበሩት ፈላስፋዎች የደረሱበት ድምደማ ለመጥፎ ወይም ለሰይጣናዊ ስራዎች በሙሉ ተጠያቂው ጭንቅላት ወይም አዕምሮ መሆኑን በመረዳታቸው ነው። ይህንንም ጉዳይ የግሪክ ፈላስፋዎችም ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። በእነሱ፣ በተለይም በፕሌቶ ዕምነት የሰው ልጅ ዋናው ችግር ትክክለኛ ዕውቀት ያለማግኘትና መንፈሱም በሚገባ ያለመታነፅ ችግር ነው። ጭንቅላቱ በትክክለኛ ዕውቀት ያልተገነባና ሀቀኛውን መንገድ ለመፈለግ የማይጥር ሰው ደግሞ አርቆ ማሰብ አይችልም። በደመነፍስ የሚመራና ገዳይም የሚሆን ነው። ባጭሩ የሚሰራውን የማያውቅ ስለሚሆን አገርንና ታሪክን እንዳለ ያወድማል። ስራው ሁሉ ለስልጣን መስገብገብና ልታይ ልታይ ማለት ይሆናል። በዚህም ምክንያት ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የርስ በርስ ጦርነት ይታይ የነበረው። ሰፋ ያለና ጭንቅላትን ክፍት የሚያደርግ እንቅስቃሴ በአውሮፓ ምድር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋ ቢሆንም፣ አውሮፓና አሜሪካ ከሌሎች አህጉሮች ጋር ሲወዳደሩ በጦርነት የተዋከቡ ነበሩ። ሌሎች አህጉሮች ውስጥ እንደ አውሮፓ ውስጥ የተከሰተውንና የተስፋፋውን የሚመስሉ ጦርነቶች በፍጹም አልተካሄዱም። 20ኛውና 21ኛው ክፍለዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱትን ጦርነቶች በሙሉ ስንመረምር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጦርነቶቹ በሙሉ የአሜሪካንና የአውሮፓውያን ጦርነቶች ናቸው። የአሜሪካና የአውሮፓ የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የስለላ ኤሊት የሰለጠነ ቢሆንና ሙሉ በሙሉ በሊበራሊዝም አስተሳሰብ ቢያምን ኖሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱትንና የሚከሰቱትን ጦርነቶች በሙሉ በውይይት በፈታ ነበር። እንደሚታወቀው የአንድ ሰው ወይም የፖለቲካ ኤሊት መስልጠን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ምጥቀት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን ማንኛውንም አገራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ግጭቶችን በውይይት መፍታት የቻለ እንደሆነ ብቻ ነው። የተወሳሰቡና የሰውን ልጅ እንዳለ የሚያጠፉና ተፈጠሮንም  እንዳለ የሚበክሉ የአቶም ቦምብ፣ የባይሎጂና የኬሚካል መሳሪያዎችን የሚሰራና የዓለምን ህዝብ የሚያስፈራራ በመሰረቱ እንደዚህ ያለ ኤሊት መንፈሱ በጥሩ ዕውቀት ያልተገራና አርቆም ማሰብ የማይችል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በአሜሪካንም ሆነ በምዕራብ አውሮፓ በሳይንስ ኮሙኒቲውና በፖለቲካ ኤሊቱ መሀከል  የሰማይንና የምድርን ያህል ርቀት ያለ ይመሳላል። አንዳንዶች ካልሆኑ በስተቀር፣ ለምሳሌ የታሪክ ተመራማሪዎች ነን የሚሉና፣ የታሪክን ሂደት በተጣመመ መልክ የሚያቀርቡና በኒዎ-ሊበራል አስተሳሰብ ጭንቅላታቸው የተበከለ ካልሆነ በስተቀር በአጠቃላይ ሲታይ የሳይንስ ኮሙኒቲው አስተያይቱ መልካም ነው።  ያም ተባለ ይህ በሶሻሊዝምና በግራ ስም ከተካሄዱት ጦርነቶች ይልቅ በካፒታሊዝም ስምና በስልጣኔ ስም የተካሄዱት ጦርነቶች የሰውን ልጅ በመግደልና አገሮችን በማውደም  በብዙ ሺህ እጥፍ የሚበልጥ ነው። ዋናው የብዝበዛና የጭቆና ምንጭም ራሱ ካፒታሊዝም ነው። በሶሻሊዝም ስም ለምሳሌ የቀድሞዋ ስቭየት ህብረትና የተቀሩ የሶሻሊስት አገሮች ተብለው የሚጠሩትና በቻይና ውስጥ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ  ፖሊሲ በመሰረቱ ከኋላ መያዝና በተሟላ መልክ ህብረተሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማምጣት ነው። የእነዚህ አገሮችም ታሪካዊ ሂደትና ባህላዊ ክንዋኔ ለየት ያለ ስለነበር የሊበራል ዲሞክራሲ ሊያብብ አልቻለም። በሌላ ወገን ደግሞ እያንዳንዱ አገር የየራሱ የሆነ ለየት ያለ ታሪክና የህብረተሰብ አወቃቀር  ስላለው ሁሉም አገሮች በተመሳሳይ አንድ ወጥ አስተሳሰብና የዕድገት ፈለግ ይዘው ሊጓዙ በፍጹም አይችሉም። በአጠቃላይ ሲታይ የሊበራል አስተሳሰብንና የነፃ ገበያን  ብንከተል ኖሮ እዚህ ዐይነቱ የፖለቲካ ኪሳራና ዝቅጠት ውስጥ ባልወደቅን ነበር የሚለው አነጋገር አላዋቂነትን ነው የሚያሳየው። በተደጋጋሚ ጽሁፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩትና እዚህም ላይ እንዳሳየሁት የተሻለና የተገለጸለት አስተሳሰብ ይዘው የሚነሱ ኃይሎች በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው። በጣም ጥቂት የተገለጸላቸውና ሁለ-ገብና የጠለቀ ዕውቀት የነበራቸው ምሁራን ናቸው በአውሮፓ ምድር ለፖለቲካ ነፃነት፣ ለህግ የበላይነት፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መሰረቶች የጣሉት። በአገራችንም የነበረውና አሁንም ያለው ትልቁ ችግር የተገለጸለት፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ፣ እንዲያም ሲል ለሁለ-ገብ የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚታገል ምሁራዊ ኃይል አለመኖሩ ነው። 

ወደ መሠረቱ ሃሳቡ ስንመጣ አንዳንድ ጭንቅላታቸው ያልበሰለና በጥሩ ዕውቀት ያልተገነባ ኢትዮጵያውያን በአገራችን ምድር ለተፈጠረው የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የስነልቦና ቀውስ ዋናው ምክንያት የግራ አስተሳሰብ በመስፋፋቱ ነው ብለው ሲወነጅሉ የጭንቅላትን ወይም የአዕምሮን በጥሩ ዕውቀት  መኮትኮት ግንዛቤ ውስጥ ባለማሰገባት ነው። ሁላችንም ብንሆን ከደሀም ሆነ ከሀብታም ቤተሰበ፣ ወይም የመሳፍንት ቤተሰብ እንወለድ፣  ከተወለድን በኋላ ዝም ብለን ነው የምንወረወረው። አንዳችንም ብንሆን መንፈሳችን በጥሩ ዕውቀትና አዕምሮን ከሚያፍታታ ልዩ ልዩ ነገሮች ጋር በፍጹም አላደግንም። እንደ ሙዚቃ፣ ጂምናስቲክና ሌሎች ለጭንቅላት መደባር ከሚያስፈልጉ ነገሮች ጋር እየተለማመድን በፍጹም አላደግንም። በተጨማሪም ጂኦሜትሪ፣ ስነጽሁፍና ቋንቋ ከመሳሰሉት ጋር አየተለማመድንና ጭንቅላታችንም እየተኮተኮተ አላደግንም። ሰለሆነም ሎጂካልና በረቀቀ መልክ ማሰብ አንችልም፤ አርቆ ማሰብም አንችልም። ባጭሩ ድርጊታችን ሁሉ በደመነፍስ መመራትና አገርን ማጥፋት ነው። በተለይም የሰውን ልጅ ጭንቅላት አስመልክቶ በፔዳጎጂና በህሊና-ሳይንስ ምሁሮች የተደረሰበት ድምዳሜ የአንድ ሰው አርቆና ሎጂካዊ በሆነ መልክ ማሰብና ያለማሰብ የሚወሰነው በጣም ልጅ በነበረበት ጊዜ የሚደረግለት፣ በተለይም ጭንቅላትን በጥሩ መንፈስ የሚቀርጽ እንክብካቤና የትምህርት አሰጣጥ የኖረ ወይም ያልኖረ ከሆነ ነው። ይህ ዐይነት እንክብካቤ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የሰዎች አስተሳሰብ በጣም ደካማ ነው። ግጭትንና አለመግባባትን በሰላምና በውይይት ከመፍታት ይልቅ በጉልበት ለመፍታት ይቃጣል። ሰው ችክ የማለት ባህርይ ይኖረዋል። በተለይም ደግሞ አንድ ሰው ወይም ማህበረሰብ ከልዩ ልዩ መጽሀፎች ጋር ካልተዋወቀና ካላነበበ፣ እንዲሁም ይዘታቸውን በሚገባ ካልተረዳ በጥራዝ ነጠቅ የሰለጠነ ሰው ስራው ሁሉ ተንኮል ይሆናል። ለዚህ ነው በአገራችን ምድር ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት ያለው ፖለቲካ ወደ ተንኮልነትና ወደ ጦርነት መቀስቀሻነት የተለወጠው። 

በአገራችን ምድር ስለተፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታና ግድያ እየደጋገመ የሚያነሳውና የሚወነጅለው የግራ አስተሳሰብ ወይም ፖለቲካ በአገራችን ምድር ስለገባ ነው የሚለውና ከባላባት ወይም ከመሳፍንት ቤተሰብ እወለዳለሁ የሚለው ራሱን ልጅ ተድላ መላኩ ብሎ የሚጠራውና አጫፋሪዎቹ ናቸው። ይህ ሰው የአውሮፓውና የአሜሪካ ካፒታሊዝም እንዴት እንደተፈጠሩና እዚህ ደረጃ ላይ እንዴትስ እንደደረሱ ምንም ዕውቀት ስለሌለው ወይም ስላልተመራመረ ልክ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የራሱን ወንጀል ለመሸፈን ሲል የሚያስፋፋውን የውሸት ክስ ቀበል በማድረግ በአገራችንና በተቀረው የሶስተኛው ዓለም አገሮች ለደረሰው ሰቆቃና ግድያ በሙሉ ተጠያቂ የሚያደርገው የግራ አስተሳሰብንና ሶሻሊዝምን ነው። የሶሻሊስት አገሮች ተብለው በሚጠሩበት አገሮች ውስጥ ደግሞ እንደዚያ ዐይነት ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው በሶሻሊዝም ምክንያት ሳይሆን አብዛኛዎቹ መሪዎች የተሻለ ምሁራዊ አስተሳሰብ  ቢኖራቸውም ለምሳሌ እንደስታሊን የመሰለው መሪ መንፈሱ በሃማኖት የተቀረጸ በመሆኑና በጊዜው ራሽያ ውስጥ የሰፈነው ኋላ-ቀር ስርዓት ጭንቅላቱ ውስጥ በመቅረቱና ይህም አስተሳሰብ በማየሉ የተነሳ አመጽን ማስቀደም ቻለ። በዚህም ምክንያት የተነሳ በጣም በሳል የነበሩ እንደነ ቡሃሪን የመሳሰሉ ምሁራንን ገደላቸው።  በሌላ ወገን ልጅ ተድላ መላኩ በሶሻሊዝምና በግራ አስተሳሰብ ላይ እንደዚያ የጥላቻ ዘመቻ እያደረገና ለአማራውም ህዝብ ጠበቃ ሆኖ የሚከራከር ቢመስልም ስለአሜሪካ ፖለቲካና በእሱ ላይ ያለው ዕምነት ማንነቱን ያጋልጣል። ራሱን እንደ ነፃ ዜጋ የሚቆጥርና ንቃተ-ህሊና እንዳለው ሰው ሆኖ የሚከራከር ሳይሆን ሙሉ ዕምነቱ በአሜሪካን ላይ ነው። በተለይም ዶናልድ ትረምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ በመመረጡ የተደሰተና ተስፋውም በእሱና ለዕጩነት በቀረቡት የትረምፕ ሚኒስተሮች ላይ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። አብዛኛዎቹ በትረምፕ ለሚኒስተርነት የታጩት ግለሰቦች ደግሞ በጣም አክራሪዎች እንደሆኑና በውጭ ፖለቲካቸውም ከእነ ባይደን እንደማይሻሉ ከአነጋገራቸው ማረጋገጥ ይቻላል። በተለይም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስተርነት የታጨው ማርኮ ሩቢዮ የሚባለው ሴናተር በጣም አደገኛ የሆነ የውጭ ፖለቲካ እንደሚከተል በግልጽ ተናግሯል። ልጅ ተድላ መላኩም በማርኮ ሩቢዮ ላይ ሙሉ ዕምነት እንዳለውና፣ በተለይም አማራውን አስመልክቶ የተለየ ፖለቲካ እንደሚከተል ነግሮናል። ይሁንና ልጅ ተድላ መላኩ የማይገነዘበው ነገር ለየትኛውም ፓርቲ በፕሬዚደትነት ተወዳድሮ የሚያሸንፍ ግለሰብ የአሜሪካንን ጥቅም የሚጎዳ ፖለቲካ በፍጹም ሊከተል አይችልም። የአሜሪካ የውጭ ፖለቲካ ደግሞ አገሮችን ማከረባበትና የሶስተኛው ዓለም ገዢዎችን ቡችላው ማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም የሶስተኛው ዓለም አገር፣ በተለይም የአፍሪካ አገር የራሱ የሆነና ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳያደርግ መዋጋት ነው። ባጭሩ የአሜሪካን የውጭ ፖለቲካ ጦርነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስፋፋትና በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ ወደ ውስጥ ያተኮረና ሰፊውን ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ሊያወጣው የሚችል ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን መሰናክል መፍጠር ነው።  ልጅ ተድላ መላኩ ይህንን ዐይነቱ የአሜሪካን የውጭ ፖለቲካ የሚመኝ ወይም የሚፈልግ ከሆነ ለአማራው ህዝብ ጠበቃ ሆኖ ሊከራከር በፍጹም አይችልም። የአማራው ህዝብም እስካሁን ድረስ የሚገደለውና የሚሳደደው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ባስታጠቃቸው በህወሃትና በአቢያ አህመድ አገዛዝ ምክንያት ነው። ታዲያ ይህንን የመሰለ እርኩስ የውጭ ፖለቲካ የሚባለውን ከሚያራምድ ኃያል መንግስት ነኝ ከሚል የተቀደሰ ነገር መጠበቅ ይቻላል ወይ? 

ወደ አገራችንም ስንመጣ የሶሻሊዝምን አርማ ይዘው ለውጥ እናመጣለን ብለው የታገሉት በሙሉ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውስጥ የተፈጠሩ፣ ያደጉና ለአቅመ-አዳም እስኪደርሱ ድረስና ከዚያም በላይ እዚያው አገራችን ውስጥ ሶሻላይዝድ የነበሩ ናቸው።  በጊዜው በአገራችን ምድር የነበረው ፊዩዳላዊ ስርዓትና ቁንጽል በሆነ መልክ የገባው ቢሮክራቲክ ካፒታሊዝም፣ በፈጠራ ስራና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ግኝት ሳይሆን ይበልጥ በፍጆታ አጠቃቀም ይገለጽ የነበረው ስርዓት የብዙዎቻችንን መንፈስ ሊቀርጹት ችለዋል። በአንዳንድ ቦታዎችም ዘመናዊ ትምህርት ቢስፋፋም የአስተማሪዎች የጥራት ጉድለትና በቂ ቤተ-መጻህፍቶች ስላልነበሩና ስለሌሉ ከልዩ ልዩና ጭንቅላትን ከሚከፍቱ ዕውቀቶች ጋር በፍጹም መተዋወቅ አልተቻለም። ስለሆነም አንዳንዱ ከሶሻሊዝም አስተሳሰብ ጋር ሲተዋወቅ ያነብ የነበረው በተበላሸ መልክ የተጻፈውን ፈንዳሜንታል ኦፍ ማርክሲዝምና ሌሊኒዝም የሚለውን መጽሀፍ ነው። የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ አንዳንድ ወደ አውሮፓ የመጡ ኢትዮጵያውያንና በኋላ ላይ የሶሻሊዝምን አስተሳሰብ ለብዙዎች ያስተዋወቁት በብዛት ያነበቡት በሌኒንና በስታሊን የተጻፉ መጽሀፎችን ነው። እነዚህ መጽሀፎች  ደግሞ ቶሎ ብሎ ወደድርጊት እንዲያመሩ የሚያደርጉ እንጂ አንድ ህብረተሰብ ከታች ወደ ላይ እንዴት እንደሚገነባ የሚያመለክቱ አልነበሩም። በሌላ ወገን ግን እነሌኒን ከእኛዎቹ አገሮች ምሁራን ጋር ሲወዳደሩ በጣም የተሻለ ዕውቀት ሲኖራቸው በአነሳሳቸውም የራሽያን ገበሬና ወዝ አደር ከነበረው ኋላቀር ስርዓት ለማላቀቅ ነበር። በተለይም The Development of Capitalism in Russaia  የሚለውን የሌኒን መጽሀፍ ላነበበ የሚረዳው የቱን ያህል የራሽያ ህብረተሰብ በቅራኔዎች እንደተያዘ ነው። ሌኒን ስዊዘርላንድ 17 ዓመት ያህል በስደት በሚኖርበት ዘመን የተገነዘበው ነገር ካፒታሊዝም በጊዜው የኋላ ኋላ ላይ የተስተካከለ ዕድገትን እንዳመጣ ነው። ስዊዘርላንድንና አንዳንድ የጀርመንን እንደሙንሺን የመሳሰሉ ከተማዎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ የደረስበት ድምዳሜ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ለሶሻሊዝም እታገላለሁ ብሎ መነሳት እንደ እብድ የሚያስቆጥር ነው በማለት ነው።  በሌላ ወገን ደግሞ ማርክስ እንደሚለን የምርት ኃይሎች፣ ማለትም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባላደገበትና የሰው የማሰብ ኃይል ጥልቀትን ባላገኘበት አገር ውስጥ ለሶሻሊዝም መታገልና ተግባራዊም ማድረግ እንደማይቻል ነው። በሌላ አነጋገር፣ የማቴሪያል ሁኔታዎችና የንቃተ-ህሊና ዕድገት ለሶሻሊዝም ህብረተሰብ ለመታገል በጣም ወሳኞች ናቸው።     

ነገሩን ለማጠቃለል፣ በአገራችን ምድር ለተከሰተውና ለብዙ ሺሆች  ለሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን መሞት ዋናውም ምክንያት የግራ አስተሳሰብ ወይም ሶሻሊዝም በአገራችን ምድር ሰተት ብለው በመግባታቸው ሳይሆን ያደግንበትና መንፈሳችን በተበላሸ መልክ ስለተቀረጹ ብቻ ነው። ይሁንና ግን ሁሉኑም በሶሻሊዝም ስም ይታገሉ የነበሩትን ኃይሎች በሙሉ አርቆ-አሳቢ አልነበሩም ብሎ መወንጀል በጣም ስህተት ነው። በጣም ጥቂት አርቆ ማሰብ የጎደላቸው ኃይሎች ናቸው እልክ ውስጥ በመግባት ሁኔታውን ውስብስብ ያደረጉት። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ በስለጠነና ሎጂካል በሆነ መልክ መወያየት አይቻልም ነበር። የፖለቲካ ዲያሎግና ሎጂካዊ ክርክር በማይታወቅበት አገር ውስጥ ደግሞ አጥፍቶ መጥፋት የሚለው የትግል ስትራቴጂ ነው የሚቀድመው። የሚገርመው ነገር ይህ ሁኔታ ትላንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ከደማችን ጋር የተዋሃደ አስተሳሰብ ነው። በሶሻሊዝም የሚታማውና ለብዙ ወንጀላዊ ድርጊቶች ተጠያቂ ነበር የተባለው የደርግ አገዛዝ ስልጣኑን እንዲለቅ ከተገደደና በህወሃት ከተተካ በኋላ ግድያውና አገርን ማተረማመስ በሌላ መልክ እንዲቀጥል ተደርጓል። ይሁንና ደርግ ከህወሃትና ከዛሬው የአቢይ አህመድ አገዛዝ ጋር ሲወዳደር ቢያንስ የአገሩን ብሄራዊ ነፃነት ጉዳይ ለድርድር ያስገባ አልነበረም። ህወሃትና የአቢይ አህመድ አገዛዞች በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ስልጣን ላይ የወጡና የእሱን አገሮችን የማተረማመስና ኋላ-የማስቀረት ስትራቴጂ ተግባራዊ የሚያደርጉ ናቸው። ሁለቱም ኃይሎች ከሶሻሊዝም ጋር ምንም ነገር የሚያገናቸው ነገር የለም። ስራቸው በሙሉ ተንኮልና ፖለቲካን ወደ ተንኮል መስሪያነት በመለወጥ የሚጠረጥሩትን በሆነ ባልሆነ መንገድ ማስወገድ ነው።  ለማንኛውም መጨረሻ ላይ ሁሉንም ለማሳሰብ የምወደው ጠለቅ ያለ ዕውቀት ሳይኖረንና፣ በተለይም ካፒታሊዝም በምን መልክና እንዴትስ በአውሮፓ ምድር ብቻ እንዳደገ ሳይገባን የምናካሂደው የፖለቲካ ትግልና በጭፍን በሶሻሊዝም ላይ የምናደረገው የጥላቻ ዘመቻ በጣም አደገኛ ነው። ስለሆነም የፖለቲካ ትግል ከመጀመሪያችን በፊት ቢያንስ አስር ዓመት ያህል ረጋ ብለን እናጥና፤ መንፈሳችንንም ከኋላ-ቀር አስተሳሰብ ለማጽዳት እንሞክር። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

 www.fekadubekele.com

ማሳሰቢያ፦ ለፖለቲካ ለውጥ የሚደረገው ትግል ፕሮፌሽናሊዝምን ይጠይቃል። ስራዎች በጥንቃቄና በጥናት መሰራት ያለባቸው ሲሆን፣ የብዙ ሰዎችንም ተሳትፎ ይጠይቃል። በትርፍ ሰዓትም የሚሰራ ጉዳይ አይደለም። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱን አቀራረብ መደገፍ በጣም አስፈላጊ ነው። ድረ-ገጹን በመጎብኘት በቂ ማስረጃ ማግኘት ይቻላል። በጣም አመሰግናለሁ!!

Filed in: Amharic