ኅዳር ሲታጠን፤ ‹‹የዘመኑ የኅዳር በሽታ››
ከይኄይስ እውነቱ
አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ‹‹ዐዲስ፤ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› በተባለ መጽሐፋቸው ‹‹ኅዳር ታጠነ›› የሚለውን ሐረግ ከመንፈሳዊ ትርጓሜው በተጨማሪ ‹‹ስለ ወባና ስለ ወረርሽኝ ቈለኛ ኹሉ በየመሬቱ እሳት አንድዶ ጪስ አጨሰ፡፡ ከዚህ በኋላ የደጋው ቈላ ወረደ፤ የደጋው ቈላ ወጣ፡፡›› በማለት ይገልጹታል፡፡ መልእክቱ ወረርሽኝ÷ በሽታን ለማራቅ የሚደረግ ማዕጠንት እንደማለት ይመስላል፡፡ በዘመነ ብሉይ በእሥራኤላውያን ዘንድ ቸነፈር ገብቶ ብዙዎችን በፈጀ ጊዜ ሊቀ ካህኑ አሮን እና ሌዋውያኑ ካህናት ማዕጠንታቸውን ይዘው ሕሙማኑን ባንድ ወገን ጤነኞችን ባንድ ወገን አድርገው ቢያጥኑላቸው ደዌው ከሕሙማኑ ወደ ጤነኞች የማይተላለፍ መሆኑ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመዘገበ ማለት ነው፡፡
የዛሬ106 ዓመት በዐዲስ አበባ በተለይ፣ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች ባጠቃላይ ወረርሽኝ ወይም በወቅቱ አጠራር ቸነፈር ገብቶ ከ40 ሺሕ በላይ የዐዲስ አበባን ነዋሪ እንደፈጀ የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን ‹‹የሐያኛው ክፍለዘመን መባቻ (የዘመኑ ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት ፲፰፻፺፮ – ፲፱፻፳፪ ዓ.ም)›› የሚለው መጽሐፋቸውን እየጠቀሱ ብዙዎች በታሪክ ዘግበውታል፡፡ በሽታው የተከሰተው በኅዳር ወር በመሆኑ በተለምዶ የኅዳር በሽታ እየተባለ ይጠራል፡፡ ያም ደዌ (‹‹የስፔን ኢንፍሉዌንዛ›› ይባል እንደነበር ያስተውሏል) እንደ ቅርቡ ኮሮና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገባ ነበር፡፡ አሁንም ድረስ ከምዕራቡ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ‹ደዌ› እንጂ ‹ፈውሰ/መድኃኒት› አይደለም፡፡
መቼም ታሪክ በጎውንም ሆነ ክፉውን ጊዜ ያስታውሳልና ወቅቱ ላዲሳባ ሕዝብ የመከራ ጊዜ ነበር፡፡ ቸነፈሩ የሚፈጀውን ፈጅቶ ካለፈ በኋላ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በዐዲስ አበባ በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን ይታሰብ ነበር፡፡ የመታሰቢያውም ሥርዓት አካባቢን በማጽዳትና በማለዳ ቆሻሻ ሰብስቦ በማቃጠል ይከናወን ነበር፡፡ ክንውኑንም ‹‹ኅዳር ሲታጠን›› ብለውታል፡፡ ይኽም መታሰቢያ በትውፊት ሲተላለፍ ቆይቶ እኛ ዘመን ደርሷል፡፡
አጽራረ ኢትዮጵያና ሕዝቧ የሆኑት ወያኔና ኦነግ እንዲሁም ለኹለቱም ገረድ ደንገጥር ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው ባሪያቸው ብአዴን በጥላቻና በክፋት ዐቅላቸውን ስለሳቱ በመንፈሳዊው ሳይገደቡ ባህላዊ ትውፊትን ጭምር በጎጂ ባህልና ‹‹በአካባቢ ጥበቃ›› ስም ማጥፋት ቋሚ ተግባራቸው አድርገውታል፡፡ ነገ ተነገወዲያ ‹ደመራ› ወይም በየበዓላቱ ችቦ አታብሩ በማለት በፈረንጆቹ ‹ርችት› ይለውጡታል፡፡ አፍቃሬ-ፈረንጅ የሆነው የደነዘዘው ትውልድ ‹ርችቱን› ማቀጣጠል ከጀመረም ከራርሟል፡፡ ወገኔ ሕዝብ የሚጨፈጭፍና አገር የሚያጠፋ ፋሺስታዊ አገዛዝ ለአካባቢ ይቆረቆራል ብለህ አትሞኝ፡፡ የአካባቢ ጥበቃ የሚባለው ጉዳይ ልክ እንደ ‹ሰብአዊ መብት ጉዳይ› የፖለቲካ አጀንዳና የጮሌ ፖለቲከኞች አፍ ማሟሿ ከሆነ ከርሟል፡፡ ቆሻሻ ሰብስበህ ኅዳርን አጥን፡፡ ሐሳቤ ያልገባህ አንዳንድ አንባቢ ካለህ የአካባቢ ጥበቃ አያስፈልግም ብሏል ብለህ አዛብተህ እንዳትተረጕምብኝ፡፡ ምዕራቦቹ አዳጊውን ዓለም የኢንዱስትሪ ዝቃጮቻቸው ማራገፊያ፣ በማዕድን ቊፋሮ ፕሮጀክታቸው አማካይነት ደግሞ ተፈጥሮን ከማዛባት በተጨማሪ አእላፋትን ለዘላቂ በሽታና እልቂት እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡ እነሱ የኛን የተፈጥሮ ሀብትና አየር አዛብተው፣ በክለውና አእላፋትን ለእልቂት በመዳረግ ካደጉ ከለሙ በኋላ ‹‹በአካባቢ ጥበቃ›› ስም እኛን አትልሙ፤ ለዚህም ትንሽ ርጥባን እንጥልላችኋለን ማለት ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ካልሆነ በቀር ሌላ ትርጕም የለውም፡፡
የምዕራባውያኑ ቅጥረኛ የሆኑ በኢትዮጵያችን የሠለጠኑ አገዛዞችም ደን እየጨፈጨፉ፣ ብዝኃ ሕይወትን እያጠፉ፣ የተፈጥሮ ፓርኮችን ምድረ በዳ÷ ከተማውን በረሃ እያደረጉ፣ ሀገር-በቀል ዛፎችንና ዕፅዋትን እያጠፉ፣ የተፈጥሮ ባልሆነ ማዳበሪያ መሬት እያመከኑ፣ ጢስ እሳት ፏፏቴን የመሰለ ታላቅ የተፈጥሮ ጸጋና የቱሪስት መስሕብ ሆን ተብሎ እንዲጠፋ አድርገው፣ የውኃ አካላትን ወደ የብስነት እየቀየሩ (የአለማያ ሐይቅን ያስታውሷል፤ ዝዋይ፣ አዋሳና ጣና ሐይቆችምም አደጋ ላይ እንዳሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ) ስለ አካባቢ ጥበቃ የአዞ እምባ ሲያነቡ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከፈረንጆቹ ለሚገኝ ርጥባን ሲባል በአካባቢ ጥበቃ ስም ማለቂያ የሌላቸው ፍሬያማ ያልሆኑ ስብሰባዎች ማድረግ አጉል ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ አጀንዳውንም የሚሰጡን ፈረንጆቹ ናቸው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ኅዳር በመጣ ቊጥር የብአዴን ካድሬዎች ‹ኅዳር እንዳይታጠን› በየቀበሌው ባዶ መፈክሮችን ሲሰቅሉና ሲደሰኩሩ ይሰማል፡፡ የአገዛዙ የሆኑት ሚዲያዎችም ይህንኑ ያራግቡላቸዋል፡፡ ታዲያ ሥራ ፈት ሁላ ኅዳርን እንዳናጥን ደርሶ ከልካይ መሆኑ ይገርማል፡፡ ኅዳር ይታጠን!
ዛሬም ርእሰ ከተማችን ዐዲስ አበባና መላዋ ኢትዮጵያ በቸነፈር ከተመቱ ድፍን 50 ዓመታት አለፉ፡፡ የቀደመው ወረርሽኝ ብዙ ሰዎች ቢያሳጣንም በሕክምና የሚወገድ ደዌ ነበር፡፡ ቆይታውም አጭር (ከኅዳር 7 እስከ 20/1911 ዓ.ም.) ነበር፡፡ ደዌውም ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት አይለይም ነበር፡፡ የአሁኑ ግን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለማጥፋት ያለመ ነው፡፡ መሠረቱ ዘርና ሃይማኖት ነው፡፡ ከነባር እሤቶችና ቅርሶች ጋር ሁሉ የተጣላ ነው፡፡ ቸነፈሩ ስር የሰደደ ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ ድንቊርናና ዕብደት የተባሉ ገዳይ ተህዋስያን አስተባብሮ ይዞ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ያለ ነው፡፡ የተህዋስያኑ ዋና ተሸካሚዎች ወያኔ ትግሬ፣ በድኑ ብአዴን እና ዓይነቱን በየጊዜው የሚቀያይረው ‹ብልግና› (ኦሕዴድ/ኦነግ) እና ለፖለቲካ ዓላማ በጐሣ የተደራጁ ቡድኖች በሙሉ ናቸው፡፡ የተህዋስያኑ መራቢያ ወይም መፈልፈያ ደግሞ የአውሮጳና የአሜሪቃ ቤተ-ሙከራዎች ናቸው፡፡ ተልእኮውም ከዚያው የሚመጣ ሲሆን፣ አስፈጻሚዎቹም ቅጥረኞች አገዛዞች ናቸው፡፡ እነዚህን ነው የዘመናችን ‹የኅዳር በሽታ/ወረርሽኝ› ያልኋቸው፡፡
ስለሆነም ከመቼውም ጊዜ በተለየ መዲናችንን እና አገራችንን ማጠን፣ አካባቢያችንን ከ‹‹ተህዋስያን›› ማጽዳት፣ ‹‹ቆሻሻም›› ሰብስቦ ማቃጠል፣ በዚህም ከዘመናችን ‹የኅዳር ቸነፈር› መገላገል ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለመፈጸም የግድ ድርጅት አያስፈልግም፡፡ እኛ ተዘልለን ተቀምጠን ሌሎች እንዲያደርጉልንም መጠበቅ የለብንም፡፡ ሁላችን በተናጠል ድርሻ እንዳለን አንዘንጋ፡፡
ወገኔ ኅዳር ይታጠን!!!፡፡ በሰሙም በወርቁም፡፡