ጌታቸው ምስጋናው፥ ቃል በተግባር
( ጋዜጠኛና ፋኖ ጌጥዬ ያለው )
እርሱ ወግ አጥባቂ ነው፡፡ አለባበሱ፣ አነጋገሩ፣ አመጋገቡ፣ አኗኗሩ ብሎም ጠቅላላ ስብዕናው ሀገሩን ካልመሰለ ደስ አይለውም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሱሪያቸውን ዝቅ አድርገው የሚሄዱ ጓደኞቻችንን አጥብቆ ይነቅፋቸው ነበር፡፡ በትምህርት ህይወታችን ከመፀሐፍትና እስክብሪቶ ጀምሮ እስከ አነስተኛ ገንዘብ መዋዋስ የተለመደ ነው፡፡ ታዲያ ብዙዎቻችን ከገንዘቡ አነስተኛነት የተነሳ ትኩረት ስለማንሰጠው የተዋስነውን በሌላኛው ጊዜ አንመልስም፡፡ እርሱ ግን ሦስት ጊዜ የታጠብኩበትን እላቂ ሳሙና እንኳን ካዋስኩት ታጥቦ ሲጨርስ የቀረችውን ምላጭ የመሰለች ሳሙና በክብር ይመልሳል፡፡ የመርህ ሰው ነው፡፡ ከመመለሱም ላይ ትህትናውና ምስጋናው ይታወሰኛል፡፡ ከሁሉም ጎልቶ ትዝ የሚለኝ ግን ከሰባት ያላነስን ተማሪዎች ተደራራቢ አልዎችን ተጋርተን በምንተኛባት መኖሪያ ክፍላችን ውስጥ እየደጋገመ ጠዋት ጠዋት በድምጹ የሚያንጎራጉረው የወረታው ውበት ሙዚቃ ነው፡፡ በእርግጥ እንዳው ሙዚቃ አልሁት እንጂ ከጉሮሮው ሲያወጣው ዜማው ጠፍቶ ግጥም ብቻ ነበር ማለት ይቻላል፡-
አሳድገሽኛል በማር በወተት፣ ኢትዮጵያዬ እማማ ምድራዊ ገነት። ጋራው ሸንተረሩ ጫካው ሸለቆሽ፣ ልብን ይማርካል አትኩሮ ላየሽ፣ ትላለች እህ እህ፣ ሲከፋት እናት፣ ጠባቂ ስታጣ አይዞሽ የሚላት። የሰውነት ክብር ግርማ ሞገሳችን፣ እስከዘላለሙ ትኑር ሀገራችን። በተዋበ ሰበዝ የተሰራሽው፣ በማራኪ አለላ የተሸለምሽው፣ በእምነት በሀይማኖት አምረሽ ያጌጥሽልን፣ ኢትየጵያ እመቤት ነሽ ጥበብ ልበሽልን፡፡
የሚያሰበውን የኖረ፤ የተናገረውን በተግባር ያደረገ፤ አንድ እንቁ ጀግና እናስተዋውቃችሁ፡፡ ነሐሴ 26/2013 ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ዳባት ወረዳ ጭና የጦር ግንባር ከወያኔ ጋር ሲፋለም በክብር እስከተሰዋበት ጊዜ ድረስ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ነበር፡፡ ሀገር ወዳዱ፣ የመርህ ሰው፣ ታታሪው፣ ቃሉን በተግባር የፈፀመው፣ ለሀገሩ እና ለአማራዊ ማንነቱ ያለውን እውነተኛ ፍቅር አንድ ነፍሱን አሳልፎ በመስጠት የገለፀው፣ ምሁሩ ፋ፦ እርሱ ፋኖ መምህር ጌታቸው ምስጋናው ይባላል፡፡
አርበኛ መምህር ጌታቸው ምስጋናው ጳጉሜ 3 ቀን 1979 ዓ.ም. ጥይት እንደ ጅራፍ በሚጮህበት፤ እረኞች በአብራራው ከብት በሚጠብቁበት ዳባት ወቅን ቀበሌ እንደ ብዙሃኑ የአማራ ህፃናት የጥይት ባሩድ እያሸተተ ተወለደ፡፡ አባቱ ምስጋናው አለሙ ፈንቅለው ይባላሉ፡፡ እናቱ ወ/ሮ ጦቢያ ገላ ጥሩነህ ናቸው፡፡
ብላቴናው ጌታቸው ምስጋናው ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በተወለደበት ቀበሌ በወቅን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡ የደረጃ ተማሪም ነበር፡፡ ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን ደግሞ ወደ ደባርቅ ከተማ በመዛወር በሚሊኒየም ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት አጠናቋል፡፡ ጌታቸው እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በዘለቀው የትምህርት ቤት ቆይታው ከፍተኛ የጋዜጠኝነት ዝንባሌ ነበረው፡፡ በትምህርት ቤት የሚኒ ሚዲያ ክበብ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደነበርም አጫውቶኛል፡፡ ከእኔም ጋር እንድንገናኝ ምክንያት የሆነን ሳንተዋወቅ በያለንበት የልጅነት ህልማችን ተመሳሳይ ስለነበረ ነው፡፡ ያገናኘን የጋዜጠኝነት ዝንባሌ ነው፡፡
በ2005 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን መግቢያ ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጣን ተማሪዎች በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፔዳ ወይም ዋናው ግቢ ‘የጋራ መኖሪያችሁ ነች’ ተብለን አንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ተገናኝተናል፡፡ ሁላችንም እርስ በእርስ አንተዋወቅም፡፡ አንዳንዶች ከሰፈራችን ወጥተን ለማናውቀው የአማራ ተማሪዎች እንግዳ የሆነብንን ሌላ ሌላ ቋንቋዎች ይናገራሉ፡፡ በበኩሌ የገባኝ ነገር ቢኖር ወደ ዩኒቨርሲቲው ገብተን ባደርንበት የመጀመሪያው ምሽት ሁላችንም ከቤተሰቦቻችን ጋር ስለመንገዱ፣ በሰላም ስለመግባታችን፣ የግቢው ውበት ስለማማሩ ወዘተ በስልክ እያወራን መሆኑን ነው፡፡ ወዲያውኑ ሁሉም በተሰጠው ተደራራቢ አልጋና ፍራሽ ላይ ከየሻንጣው አንሶላ እያወጣ አነጠፈ እና ጋደም አለ፡፡ ብዙዎቹ ሀገር አቆራርጠው የመጡ በመሆናቸው በጉዞው ሰውነታቸው ደክሟል፡፡ ከሁሉም አጭር ርቀት የተጓዝኹት እዚያው ባሕር ዳር አቅራቢያ ከአቸፈር ወንድዬ የተነሳሁት እኔ ስሆን የደባርቁ ጌታቸው ምስጋናውም እንደ ሌሎቹ ከአንዱ ሀገር አቋራጭ አውቶብስ ወደ ሌላኛው እየተገለባበጠ ለሁለት ቀናት ወይም ለአንድ ሙሉ ቀን ተጉዞ የመጣ ሳይሆን ከደባርቅ ጎንደር፣ ከጎንደር ባሕር ዳር፣ ሁለት መለስተኛ አውቶብሶችን አቀያይሮ ከተፍ ያለ በመሆኑ እምብዛም የድካም ስሜት አይታይበትም፡፡
በማለዳው እርስ በእርሳችን ከየት እንደመጣን መነጋገር ጀመርን፡፡ በዚህ መልኩ ከአርበኛ መምህር ጌታቸው ምስጋናው ጋር የጀመርነው ጓደኝነት በክብር እስከተሰዋበት ዕለት ድረስ ቀጥሏል፡፡
የወያኔ ጦር ዘሪማን አቋርጦ ወደ ዳባት እየገሰገሰ በነበረበት ጊዜ ጌች ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ከሚያስተምርበት ዲላ ዩኒቨርሲቲ ወደ ትውልድ ቀየው ሄዷል፡፡ የወያኔ ሰራዊት ወረራ እየፈፀመ ወደ መንደር ከመግባቱ በፊትም የአካባቢውን ወጣቶች እያስተባበረ ወደ ጦር ግንባር ገሰገሰ፡፡ የአካባቢውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለዜና ግብዓት በሚሆን መልኩ መረጃዎችን ሲሰጠኝ ሰንብቷል፡፡ በዚህ ዕለትም እርሱ ወደ ጦር ግንባር እየሄደ እኔ ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ አሰልችውን የአዲስ አበባ ታክሲ ሰልፍ ተሰልፌ ደወለልኝ፡፡ እየሆነ የነበረውን ሲግረኝ ከጀርባው የጥይት ድምጽ ይሰማኝ ነበር፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የእነ እስክንድር ነጋን የችሎት ወሎ በተመለከተ ባወጣሁት ዘገባ ላይ ክስ ቀርቦብኝ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ፀረ ሽብርና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት እንደቀረብኹ በዚያው ወደ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ተወረወርኩ፡፡ ከሳምንታት በኋላ ጌች በክብር መሰዋቱን ሰማሁ፡፡
አርበኛ መምህር ጌታቸው ምስጋናው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኝነት ትምህርትን ለማጥናት በኖርዌይ ኤን ኤል ኤ ዩኒቨርሲቲ ከ2009 እስከ 2010 ዓ.ም. በቆየበት አንድ ዓመት ውስጥ በዚያው እንዲቀር ሁኔታዎች ተመቻችተውለት ነበር፡፡ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ እንዲሄድም ተጠይቆ ነበር፡፡ ሆኖም ከሀገር ውጭ መኖር የሚጎረብጠው የጦቢያ ልጅ ሁሉንም ትቶ ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመልሷል፡፡ በኖርዌይ ቆይታው “በዚያ የሚያየውን የሥልጣኔ ውጤት እና በጎ ሥርዓት ሁሉ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እንዳለበት ያስብ ነበር” ይላል አብሮት የተማረው የቅርብ ጓደኛው፡፡ በዚያ በነበሩበት ጊዜ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነቱ ሥርዓትና ትውፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርግ እንደነበርም ይናገራል፡፡ እንደ ጓደኛው አባባል ጌታቸው ራሱ በቤት ውስጥ አብስሎ ካልሆነ በስተቀር ከካፍቴሪያ ውስጥ ስጋ እና የወተት ተዋፅኦዎችን ፈፅሞ አይመገብም ነበር፡፡ ይህ የሆነው ከኦርቶዶክስ እምነት ሥርዓትና ቱፊት ውጭ የሆኑ ነገሮች በምግብነት ይቀርባሉ የሚል ጥርጣሬ ስለነበረው ነው፡፡
በአንድ ወቀት አትክልትና የአትክልት ተዋጽኦዎች ወደ ቀረቡበት ገበታ ተጠግቶ አነሳ፡፡ ጠረንጴዛው ላይ ተቀምጦ መጉረስ ሲጀምር ግን በአትክልት የተጠቀለለ አይብ አገኘ። ከዚህ ቀን በኋላ ጥርጣሬው የበለጠ ጨምሮ በካፍቴሪያ ውስጥ መመገብን እንዳቆመ ጓደኛው ያስታውሳል፡፡
አርበኛ ጌታቸው ምስጋናው ከኖርዌይ መልስ በሀገሩ ትዳር መስርቷል፡፡ ሳምራዊት አምባቸውን አግብቶ ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. መድኃኒት ጌታቸው የተባለች ህፃን ልጅ አባት ለመሆን በቅቷል፡፡
ጌታቸው በአስተማሪነትም ሆነ በተማሪነት ባሳለፋቸው ጊዜያት ሁሉ ለሀገሩ እና ለህዝብ የነበረው ፍቅር ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነበር፡፡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የጋዜጠኛነት ተማሪዎች በነበርንበት ጊዜ ሀገር አቀፍ ምርጫ ይደረግ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በዩኒቨርስቲው ውስጥ ከነበሩ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ጌታቸው የፔዳ ምርጫ ጣቢያ ታዛቢ ነበር፡፡ ምግቡን ለመብላት እንኳን አይኑን ከኮሮጆው ሳይነቅል በዚያው ውሎ አደረ፡፡ ምርጫው እንዳይጭበረበር ከሰዎች ጋር ተጣልቷል፡፡ ሆኖም የአንድ እርሱ ብቻ ለፍትሃዊ ምርጫ መሥራት ለውጥ ሊያመጣ ስላልቻለ የተሳካለት አልመሰለኝም፡፡
በአንድ ወቅት የገጠመን ደግሞ ትዝ ይለኛል፡፡ የቴሌቪዢን ዜና አዘገጃጀት (Television News Production) የሚባል ትምህርት ስንማር ለአምስት አንድ የእቅድ ዜና እንድንሠራ ታዘዝን፡፡ ዜናው ለእኛ ውጤት ከማስገኘትና ለትምህርታችን ከመጥቀሙ በተጨማሪ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም ጠቃሚ አንዲሆን አስበናል፡፡ በመሆኑም ከምልከታችን ተነስተን የግቢውን ካፍቴሪያዎች የምግብ ጥራትና ንፅህና ብሎም መስተንግዶ ለመተቸት አቅደናል፡፡ ለዚህ ግብዓት የሚሆኑ ቃለ መጠይቆችን እየሠራን ነው፡፡ ሁለት ተማሪዎችን ማኪያቶ ከሚጠጡበት ጠረንጴዘ ተጠግተን ለቃለ መጠየቅ እንዲተባበሩን አግባባናቸው፡፡ ሁለቱም ሴቶች ናቸው፡፡ እርስ በእርስ እየተያዩ፣ እየተሸኮረመሙ ፈቃደኛ ሆኑልን፡፡ እኔ ማይኩን ይዤ ቃለ መጠይቅ ሳደርግ ጌች ደግሞ የዩኒቨርሲቲውን የማስተማሪያ ኤች ዲ ቪዲዮ ካሜራ ተሸክሞ መቅረፅ ጀመረ፡፡ ሴቶቹን በቁም ነገር እየጠየቅናቸው ንግግራቸውን አቋርጠው በፍልቅልቅ ገፅታቸው እየተሸኮረመሙ ሳቃቸውን ይለቁታል፡፡ “አዎ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ካፍቴሪያው በትክክል አይሠራም” እያሉ ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ጥቅል መልስ ከመስጠት በዘለለ ተመልካችን የሚያሳምን መረጃ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ እኛም ለዜናችን የምንፈልገውን መረጃ እንዲናገሩልን መሪ ጥያቄዎች እየጠየቅን የካፍቴሪያውን ገመና አፍርጠው እንዲናገሩ ገፋፋናቸው፡፡
“ችግሮቹ ምን ምንድናቸው?” አልኋቸው። “ምግቡ ላይ መጥፎ ነገር አግኝተን እናውቃለን” አለችኝ አንደኛዋ፡፡
“መጥፎ ነገር ማለት ምንድነው?” ስል ተከታይ ጥያቄ አነሳሁ፡፡
“ጥሩ ያልሆነ ነገር” አለችኝ፡፡
“ምንድን ነው እሱ? ፀጉር አግኝታችሁ ነው ወይ?” አልኋት፡፡
በዚህ መሀል ሁለቱም እየተቀባበሉ ዝንብ እንዳገኙ አብራሩልን፡፡ በምርመራ ጋዜጠኝነት ትምህርታችን ስለ አሜሪካው የእነ ፕሬዚዳንት ሚክሰን የዋተርጌት ቅሌት ዘገባ የተማርሁት ትዝ እያለኝ ጥሩ መረጃ እንዳገኘን ተሰማኝ፡፡ ጓደኛዬ እና እኔ እራሳችንን የዋተርጌቱን ቅሌት ባጋለጡት የዋሽንግተን ፖስት ዘጋቢዎች ውድ ዋርድ እና ካርል ብሬስተን ቦታ ባናስቀምጥም ምርጥ ሥራ እንደሠራን ተሰምቶናል፡፡ ሆኖም በብዙ ማግባባት እና ጉትጎታ ያነገገርናቸው ተማሪዎች ቃለ መጠይቅ ለካንስ አልተቀረፀም ኖሯል፡፡ ጌች ካሜራውን አስተካክሎ ወደ እኛ ቢያዞረውም ምስልና ድምጽ እንዲቀርጽ አላዘዘውም ኗሯል፡፡ በካሜራው እስክሪን ሲመለከተን ብቻ ነው የቆየው፡፡ ይህን ሳውቅ ተናደድሁ፡፡ በግድየለሽነት እንዳላደረገው ባውቅም ጌች አበሳጨኝ፡፡ ሌላ ሰው በዚህ ልክ ደፍሮ የሚናገርልን እንደማናገኝ ገብቶናል፡፡
ጌታቸው ምስጋናው እነኚህን ሴቶች ፍለጋ በውቡ የፔዳ ግቢ ተንቀዋለለ፡፡ ከኦዲቶሪየም እስከ ጆኮ ግቢ፣ ከቤተ መፅሐፍት እስከ ሌላ ቤተ መፅሐፍት፣ ከካፌ እስከ ሌላ ካፌ፣ ከለቭ ስትሪት እስከ መማሪያ ክፍሎች ፈለጋቸው፡፡ ተሳክቶለትም አገኛቸው፡፡ ነገር ግን መጀመሪያውኑም በብዙ ማግባባት ፈቃደኛ የሆኑት ተማሪዎቹ “ድጋሜ አንቀረፅም” አሉ፡፡ በትጋት አስረድቶ አሳመናቸው፡፡ ተሳክቶልን ቀረፃውን እንደገና ለማድረግም በቃን፡፡ ስህተቱን ለማረም እና ሥራችንን የተቃና ለማድረግ ያሳየው ትጋት ሁልጊዜም ትዝ ይለኛል፡፡
አርበኛ መምህር ጌታቸው ምስጋነው የተሳሳተ ከመሰለው ስህተቱን ለማረም የማያቅማማ፣ ጥፋቱን ለማስተካከልም የሚኳትን የመርህ ሰው ነበር፡፡ ሰዎች ከተሳሳቱ እንደ ተራራ የገዘፉ አይነኬ እንኳን ቢሆኑ “ተሳስታችኋል” ሲል የሚነካ፣ በጎ የሠሩ ከመሰለው የእርሱ ወገን ያልሆኑትን ጭምር “እዚህ ላይ ትክክል ናቸው” በማለት በአደባባይ የሚያመሰግን፤ አለፍ ሲልም አኮቴት የሚያቀርብ ለኅሊናው ተጠሪ ሰው ነበር፡፡ ከማናቸውም ምድራዊ ህግ በላይ ህገ ልቦናን የሚያከብር ሰው ነበር፡፡
ጌታቸው ከሰዎች ሲዋደድ የሚቀድስ፣ ሲጣላ የሚያረክስ አልነበረም፡፡ እውነት የተዛባ ከመሰለው “እርሱ በዚህ የሚታማ አይደለም” በማለት ለተጣላው ሰው ጭምር ይከራከራል፡፡ ያ ሰው ፍርደ ገምድል አልነበረም፡፡ ይህ ስብዕናው በሄደበት ሁሉ ሲያስመሰግነው ኗሯል፡፡ የሚታመን ምስክር ነበር፡፡ ስለ አማራዊ ማንነቱ የነበረውን ክብር፣ ለአማራ ህዝብ የነበረውን ተቆርቋሪነት በቅርበት አውቃለሁ፡፡
እያንዳንዱ አማራ ብሔራዊ የውትድርና ስልጠና ያስፈልገዋል ብሎ ያምን ነበር፡፡ ይህንንም ከእራሱ ለመጀመርባሕር ዳር ወደ ጀኔራል አሳምነው ፅጌ ቢሮ ለመሆድ በእቅድ ላይ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጀኔራሉ በቀጠሮ ወደማይገኝበት ቀድሞ ስለሄደ ሳይሳካ ቆየ፡፡ አርበኛ መምህር ጌታቸው ምስጋናው አልፎ አልፎ የአማራን ብሔርተኝነት የሚያቀነቅኑ አስተያየቶችንና መረጃዎችን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በፌስቡክ ይጽፍ ነበር፡፡ አድር ባይ ምሁር አልነበረም፡፡ አማራ በቀላሉ የሚዘነጋው ሰው አይደለም፡፡ ታሪክ በአምዱ ሲዘክረው ይኖራል፡፡ በቅርቡ ቋሚ መታሰቢያ እንደሚደረግለትም ተስፋ አደርጋለሁ፡