>

ውስጠ ወይራዋ "ዴሞክራሲ"

ውስጠ ወይራዋ ዴሞክራሲ

 

ፋንታዬ ሠርጸ

አንድ አገር መንግሥት ያስፈልገዋል። መንግሥት በሌለበት አገር ህግ የለም። መንግሥት በሌለበት አገር – የአገር ሃብት በዘራፊዎች ይመዘበራል። መንግሥት ከሌለ እናት ሃገር በውጭ ጠላት ትወረራለች። መንግሥት አስፈላጊ ነው። በእርግጥም ጥሩ መንግሥት እጅግ አስፈላጊ ነው። ዴሞክራሲ አንድ ሕዝብ ሊያገኘው የሚችለው የተሻለው የመንግሥት ቅርጽ ነው። በእርግጥ የእግዚአብሄር መንግሥት ከሌለ ወይንም እንከን የለሿ መንግሥት (ideal state) ምኞት ሆና ከቀረች የተሻለው አማራጭ በዴሞክራሲ የተመረጠ መንግሥት ነው።

ዴሞክራሲ ለሕዝቡ እኩል እድል (equal opportunity) እና እኩል መብት (equal rights) ታጎናጽፋለች። ይህም ማለት ሕዝቡ ራሱ በመረጣቸው ተወካዮቹ አማካኝነት እነዚህን መብቶች ይቀዳጃል ማለት ነው። ይህ በመርህ ደረጃ ነው። መሬት ላይ አውርደን ስናየው ግን ብዙ ውጥንቅጦች አሉ። ለነገሩ ዴሞክራሲ ይዘመርላታል እንጂ በአሜሪካና በስካንዴኒቭያን አገሮች መካከል እንኳን በሰው ልጆች መብት ላይ ጉልህ ልዩነቶች ይንጸባረቃሉ። ዞሮ ዞሮ ሁሉም ዴሞክራሲዎች – ፍትህ (justice)፣ ነጻነት (freedom) እና እኩልነት (equality) የሚሉትን የፖለቲካ ጽንሠ ሃሳቦች ያራግቧቸዋል። እነዚህ ሶስቱ ጽንሰ ሃሳቦች ግን እንደየአገሩ የፖለቲካ ባህልና እንደ መንግሥታቱ አወቃቀር ይለያያሉ።

ሙያ የሚተገበረው የሙያው ችሎታ ባላቸው ሰዎች ነው። የሕክምና ሙያ የሚተገበረው ሕክምና ባጠኑ ዶክተሮች ነው። ሕንጻ፣ ድልድይና አውራ ጎዳናዎች የሚሠሩት የግንባታ ሙያ ባላቸው መሃንዲሶች ነው። ድል የሚያጎናጽፍ ውጊያ የሚነደፈው የጦር ስልት ሙያ ባላቸው መኮንኖች ነው። ሙያ የሚተገበረው ሙያውን በተካኑ ሰዎች እንደመሆኑ መንግሥትም ሥራውን የሚተገብረው የአመራር ክህሎት ባላቸው የፖለቲካ ሙያተኞች ነው። ችግሩ እዚህ ላይ ነው። ዴሞክራሲ ሁልጊዜ የፖለቲካ ሙያተኞችን ይዛ ልትመጣ አትችልም። እንደ ሐኪሙ፣ እንደ መሃንዲሱ እና እንደ ጦር መኮንኑ የፖለቲካን ሰው ሙያ መለክያ (yardstick) የለም። ዶክተሩ፣ መሃንዲሱና የጦር መኮንኑን ወደ ሙያ ያመጣቸው ትምህርት (education) ሲሆን የፖለቲካውን ሰው ወደ ቢሮ ያመጣው የሕዝብ ምርጫ (election) ነው።

ትምህርትና ምርጫ ይለያያሉ። የተማረ ሕዝብ በበዛበት አገር ላይ የፖለቲካ ባህል ያደገ ነው። የተማረ ሕዝብ ባልበዛበት አገር ላይ የፖለቲካ ባህል ዝቅተኛ ነው። ያደገ ባህል ለፖለቲካ ቢሮው ብቁ የሆነ ሰው ሊያመጣ ሲችል ዝቅተኛ የፖለቲካ ባህል ለፖለቲካው ብቁ ያልሆነ ሰው ይዞ ይመጣል። ለፖለቲካው ሙያ ብቁ ያልሆነ ሰው ወደ ቢሮ ሲመጣ – ዴሞክራሲ የአፈ ጮሌ (demagogy) ምሽግ በመሆን ድካም ይጫናታል። የተማረ ሰው በንግግር አይመጣም፣ በሙያ እንጂ። የፖለቲካ ሰው ግን ሥነልቦናን ስለሚያውቅ በጥራዝ ነጠቅ ንግግሮችና (superficial statements) በአሸብራቂ ገጽታዎች ብቅ ሊል ይችላል። የፖለቲካ ባህሉ ዝቅ ያለ ህዝብ በጮሌ ንግግርና በማራኪ ገጽታ በመማረክ መጭውን ዘመን በፍዳ ያሳልፋል።

ሕዝብ ጎበዝ ሐኪም፣ ጠንካራ መሃንዲስ እና ጀግና የጦር መኮንን እንደሚመኘው ሁሉ በሳል የፖለቲካ ሰውም ማግኘት አለበት። የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ የውጭ ግኑንነቶችና የሃገር ደህንነትና ድንበር መከበር በሕዝብ ሰላምና ኅልውና ላይ ልዩ ተጽዕኖዎችን ያሳድራሉ። ብቃት የሌለው የፖለቲካ ሰው ወደ ቢሮ ከመጣ ወጥቶ መግባትም ሆነ በልቶ ማደር ሊከብድ ይችላል። በመሆኑም ሕዝብ – ሃገር እንደ ሃገር እንድትቀጥል ከፈለገና ዴሞክራሲን ከወደደ ማንን መምረጥ እንዳለበት ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። ማንን መምረጥ እንዳለብን የማናውቅ ከሆነ – ሰላምን የሚያስጠብቅ፣ ወተን ስንገባ የሚያየን፣ ከጉልበተኞችና ዘራፊዎች የሚታደገን፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችን የሚያሟላልን ጠንካራ አገር ወዳድ ሰው እንዲያመጣልን ወደ እግዚአብሄር አጥብቆ መጸለዩ ይሻላል። እዬዬም ሲደላ ነው” እንዲሉ ልማትና እድገት በህልውና ከመኖር በኋላ የሚመጡ ናቸው።

ሰው በተፈጥሮው ይለያያል። በድህነት ያደገም ተቀማጥሎ ያደገም አል። ወደ ፖለቲካው ቢሮው ሲመጡ ሁለቱም የተለያየ ጠባይ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። ተቀማጥሎ አድጎ ለደሃው ተቆርቋሪ እንዳለ ሁሉ በድህነት አድጎ ክፉ ሊሆን የሚችል ግለሰብም አይጠፋም። በሌላ በኩል ደግሞ በሃብት ዙርያ ያደጉ ናቸው፣ ይራራሉ፣ ለገንዘብ አይጓጉም ተብለው ወደ ቢሮ የመጡ ሆዳቸው በልጦባቸው ደሃውን ሲያንገላቱና ወጣቱን በቁም ሲገድሉ ይታያሉ። ወገኖቼደሃውንም ሃብታሙንም እኩል የሚያደርጋቸው ትምህርትና ግብረገብ ነው። ለዚህም ነበር ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርት በነጻ እንዲሰጥና ተማሪዎች በግብረገብ እንዲታነጹ ያደረጉት። ከደሃ ወገን ተወልደው በትምህርት ተኮትኩተው ኢትዮጵያን እጅግ ያኮርዋት እንደ ጸሃፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወልድና ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ የመሳሰሉት ምሳሌዎች ነበሩ። እነሱን ሁሉ ቀብረን ነው ዛሬ እንዲህ ፍዳችንን የምናየው።

ሰው ቢማርም በግብረገብ ካልታነጸ ስግብግብነት (greed) ያድርበታል፣ በሙስና ቆሻሻም (corruption) በቀላሉ ይዘፈቃል። ሰው ግብረገብ ከሌለው ያንንም ያንንም ይሻል (acquisitive)፣ ጉጉት (ambitious) ያጉላላዋል፣ የሌላው ያምረዋል (competitive) ቀናተኛም (jealous) ይሆናል። እንዲህ አይነት ሰው ወደ ቢሮው ሲመጣ በብድር የተገኘ ገንዘብ እየተመዘበረ ወደ ውጭ ይላካል፣ ሕዝብ በበሽታ ያልቃል፣ መሃይምነት ይነግሳል፣ ምጣኔ ኃብት ይደቃል። ለዚህ ዓይነቱ ሰው ሥልጣን ገንዘብ ነው። ዴሞክራሲ” እንዲህ ዓይነቱን ሰው ወደ ሥልጣን ልታመጣ ትችላለች። ለዚህም ነው አሪስቶትልና ፕላቶ በዴሞክራሲ ላይ ጥርጣሬ ያደረባቸው። ዴሞክራሲ፣ ምርጫ፣ እድገት” የሚሉት ቃላት ግብረገብ በሌላቸው ሙሰኞች ዘንድ ሊዘወተሩ ይችላሉና፣ ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም። ዛሬ ጊዜ ፖለቲካ አስተዳደር መሆኗ ቀርቶ ገንዘብ ሆናለች።

መፍትሄው ትምህርት ነው። መፍትሄው ከዕድሜና ከታሪክ መማር ነው። በሁሉም ዘርፍ ትምህርት እጅግ አስፈላጊ ነው። በሰው ልጆች መሃከል ልዩነት የለም፣ ሁሉም የእግዚአብሄር ፍጡር ነው። በሰው መሃከል ልዩነት ቢኖር እንኳን የችሎታና የሙያ ልዩነት ብቻ ነው። ይህም ቢሆን በሳይንሳዊ የሥራ ክፍፍል (division of labour) ይስተካከላል። ጥሩ መንግሥት ሊኖረን የሚችለው አብዛኛው ሰው ሲያስተውል፣ ትላንትን ሲመረምርና ካለፈው ሲማር ነው። ትምህርት የፖለቲካ ባህልን ከፍ ያደርጋል። ሃገርጠል መሪዎች ትምህርትን የሚጫንዋት ትውልድን በማኮላሸት በሥልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጠው ለመቶ ዓመት ለመብላት ነው። መልካም እሴትን የሚያጠለሹት ሃገርጠል መሪዎች ለሆዳቸው እንጂ ለኅሊናቸው ግድ የላቸውም።

የጥንቶቹ ፈላስፎች ያቀነቀኑላት እንከን የለሿ መንግሥት ተምናታዊ ሆና ከቀረች አማራጩ ዴሞክራሲ ነው። ቢሆንም ግን ሺህ ጊዜ እንጠንቀቅ። በዴሞክራሲ ስም፣ በኢትዮጵያ ስም፣ በሕዝብ ስም፣ ወዘተ፣ የሚግተለተሉትን አፈ ጮሌውችን እንመርምራቸው። ማንን ወደ ሥልጣን እንደምናመጣ እንወቅ። ደግሞ ደጋግሞ መሳሳት በመሃይሞች መዳፍ ተይዞ መፍጨርጨር ነውና ከዚህ እንዲሰውረን አጥብቀን እንጸልይ። ዴሞክራሲ” ውስጠ ወይራ ነችና እግዚአብሄር አምላካችን ገልጠን ገላልጠን የምናይበትን የውስጥ ዓይናችንን ያብራልን፣ አሜን።

Filed in: Amharic