የመቄዶንያው ብንያም በለጠ ከጎዳና ላይ የታደጋቸው ሌተናል ኮ/ል ካሣሁን ትርፌ ትዝታዎችን በጨርፍታ!!
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
ክፍል- 2
በክፍል- 1 ጽሑፌ ‹የመቄዶንው ብንያም በለጠ ከጎዳና ሕይወት የታደጋቸውን የወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ከፍተኛ መኮንን የነበሩትን፤ ነፍሰ ኄር ሌተናል ኮ/ል ካሣሁን ትርፌን› በተመለከተ አጫጭር መረጃዎችን ለማካፈል ሞክሬያለሁ፡፡
በዚህ በዛሬው ጽሑፌ ስለ ኮሎኔል በማስታወሻዬ ካሰፈርኳቸው ትዝታዎቻቸው ጥቂት ሰበዞችን ለመምዘዝ ወደድኹ፡፡
1. ትውልድ፤ ዕድገት እና ትምህርት፤
ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌ ተወለዱት በሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ከተማ በ1939 ዓ.ም. ሲሆን፤ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዐፄ ዘርዓያዕቆብና በልጅ ኃይለ ማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት፡፡
በሁለተኛ ደረጃ መለቀቂያ ፈተና ከፍተኛ የሆነ ውጤት ያስመዘገቡት የ17 ዓመቱ ወጣት ካሣሁን በጊዜው የላቀ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ወደሚላኩበት ወደ ሐረር የጦር አካዳሚ ለሦስት ዓመት ወታደራዊ ሥልጠና ገቡ፡፡
ኮሎኔል ካሣሁን ስለ ሐረር የጦር አካዳሚ ትምህርት ቤት የትምህርት አሰጣጥ ጥራት፣ ብቃትና በአካዳሚው ስለነበራቸው ቆይታ ሲያጫውቱን፤ በአካዳሚው ከሚሊታሪ ሳይንስ በተጨማሪም እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋ፤ ከሳይንስ ትምህርቶችም ሂሳብና ፊዚክስ፣ ከሶሻል ሳይንስ ደግሞ ኢኮኖሚክስ፣ ኅብረተሰብና የታሪክ ትምህርት ጭምርም ይሰጥ ነበር፡፡
ኮሎኔል ከእርሳቸው ጋር የነበሩትን ሰልጣኝ ጓደኞቻቸውንና መምህራኖቻቸውን ሲያስታውሱም፤ ‹‹ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊ ስሜትና ወኔ ያላቸው፣ በሚሊታሪ ሳይንስና በወታደራዊ ዲሲፕሊን የታነጹ፣ ለአገርና ለወገን ክብር ተቆርቋሪ የሆኑ፣ ሰልጣኞችና መምህራን ነበሩ፤›› በሐረር የጦር አካዳሚ፡፡
ኮሎኔል ከሐረር አካዳሚ ተመርቀው ከወጡ በኋላ በምክትል መቶ አለቃነት በጊዜው በተሰጣቸው ወታደራዊ ግዳጅ መሠረት ለሁለት ዓመት አገልግሎት ወደ ኦጋዴን ተላኩ፡፡ በዛም ‹የአንበሳው ክፍለ ጦር 22ኛ ሻለቃ› ጦርን ተቀላቀሉ፡፡ በኦጋዴን የሁለት ዓመት ወታደራዊ ግዳጃቸውን ከጨረሱ በኋላም በወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ትምህርት ስፔሻላይዝድ ለማድረግ ወደ ሆለታ ገነት ጦር አካዳሚ አቀኑ፡፡
በሆለታ አካዳሚ ለአንድ ዓመት ሥልጠና የወሰዱት ኮሎኔል ካሳሁን ከዚህ በኋላ ዋና ሥራቸው የነበረው የወታደራዊ መረጃና ደኅንነት ሥራ ነበር፡፡
ኮሎኔል ከሆለታ ገነት ሥልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዳግመኛ ወደ ኦጋዴን/ገላዲ በመመለስ በ3ኛ ሻለቃ ውስጥ በመረጃ መኮንንነት ማገልገል ጀመሩ፡፡ በ1966 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢም ወደ ሐረር ክፍለ ጦር መምሪያ በመምጣት የክፍለ ጦሩ የደኅንነት/ሴኩሪቲ ኦፊሰር በመሆን ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡
2. ኮ/ል ካሣሁን ትርፌ እና የሶማሊያ ወረራን በጨረፍታ፤
በአገሪቱ የለውጥ ንፋስ እየነፈሰበት በነበረበት በ1960ዎቹ በአገራችን ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘው ሶማሊያ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት የደፈጣ ጥቃት በማድረግ ትንኮሳ ታደርግ ነበር፡፡
ሶማሊያውያን አሉን ኮሎኔል ካሣሁን፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዲፕሎማሲው መስክ የግዛት ይገባኛል ጥያቄቸውን ለአፍሪካ አንድነትና ለዓለም አቀፉ መንግሥታት ድርጅት ድረስ በማሳወቅ በኢትዮጵያ ላይ ጫን በመፍጠር- ‹‹ታላቋን ሶማሊያን›› የመፍጠር ቅዠታቸውን ዕውን ለማድረግ ሩጫውን ተያያዙት፡፡
‹‹የዛን ጊዜያዋ ሶማሊያ ከአሜሪካና ከራሺያ ባገኘችው ከፍተኛ የሆነ የጦር መሳሪያ ዕርዳታ ከ1966 አብዮትና ለውጥ በኋላ ሶማሊያ በምሥራቅ አገራችን ክፍል እስከ ኦጋዴንና ሐረር ድረስ ዘልቃ በመግባት የደፈጣ ጥቃት ሰነዘረች፡፡ ይህ የሶማሊያ ጥቃት በለውጥ ግርግርና ገና አለመረጋጋት ላይ ለነበረችው አገራችን ኢትዮጵያና የወታደራዊው የደርግ መንግሥት እንደ ዱብዳ ነበር፤›› ይላሉ ኮሎኔል፤ የሶማሊያን ወረራን ወደኋላ ተጉዘው ሲያስታውሱት፡፡
በወቅቱ ኮሎኔል ካሣሁን በምሥራቅ ግንባር ዋና ሥራቸው የነበረው የጦር መረጃ መሰብሰብና የአየር ላይ ቅኝት በማድረግ የጠላትን እንቅስቃሴና የማጥቃት ርምጃ ቀድሞ ለወገን ሠራዊት መረጃ በማቀበል፣ ለሠራዊቱ የማጥቃትና የመከላከል ዕቅድ መንደፍ ነበር፡፡
ሶማሊያ በኦጋዴንና በካራማራ ግንባር ስትልካቸው የነበሩትን የጦር ጄቶች፣ ሚጎችንና ሚሳዬሎችን በአየር ላይ እያሉ በማጋየትና በማምክን ረገድም ተሳትፎአቸው የላቀ ነበር፡፡
እንዲሁም በረቀቀ ምሥጢራዊ ተልእኮዎች/ኦፕሬሽኖች ወደ ጠላት ገዢ መሬቶች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከፍተኛ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎችን በመሰብሰብና፣ መተንተን፤ የአየር ላይ ቅኝት በማድረግ አኩሪ የሆነ ሀገራዊ ግዴታቸውን በድል ተወጥተዋል፡፡
‹‹የሰማዩ ነብር›› በመባል የሚታወቁትን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረባ የነበሩት የጦር ጄት አብራሪው ኢትዮጵያዊው ጀግና ጄ/ል ለገሠ ተፈራ፤ የሶማሊያን አየር ኃይል ከጥቅም ውጪ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ለሠሩት ጀግንነትና ለከፈሉት መሥዋዕትነት የእነ ኮ/ል ካሣሁንና የሥራ ባልደረቦቻቸው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ ጦር በሐረርና በኦጋዴን ግንባር የነበረው ጦር ያለውን ኃይል ሁሉ አስተባብሮ የሶማሊያን ወራሪ ኃይል ተቋቁሞ ለመመከት ችሎ ነበር፡፡ በኋላም ደርግ በክተት ዘመቻ በታጠቅ የጦር ማስልጠኛ ለሦስት ወራት ያሰለጠናቸው የሚሊሻ ሠራዊት ዓለምን ባስደነቀ ኢትዮጵያዊ ወኔና በዐድዋው የጀግንነት መንፈስ የእናት ሀገር ኢትዮጵያን ነጻነትና ሉዓላዊነት በደማቸው ለማስከበር ወደ ምሥራቅ ግንባር ተመሙ።
እንዲሁም ከሶሻሊስት ወዳጅ አገሮች ከኩባ፣ ከየመን፣ ከኮሪያ፣ ከዩጎዝላቪያ፣ ከሶቪዬት ኅብረት በተገኘ የጦር መሳሪያ ዕርዳታና ወታደራዊ ኃይል ድጋፍ የሶማሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ጀግኖች አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ዳግም ላያንሰራረራ፣ አክርካሪውን ተመትቶ በመጣበት እግሩ ሽንፈትን ተከናንቦ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡
ዳግማዊ ዐድዋ በሆነው ‹የካራማራ የጦር ግንባር› የሲያ አድባሬ ታላቋን ሶማሊያን የመፍጠር ከንቱ ምኞትም- በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተጋድሎ የቁም ቅዠት ሆኖ ቀረ፡፡ የደርግ ወታደራዊ መንግሥትም፤ ‹‹የምሥራቁ ድል በሰሜንም ይደገማል!›› በሚል መፈክር ፊቱን ወደ ሰሜን ጦረር ግንባር አዞረ፡፡
የምሥራቁ ግንባር ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት በድል ከተደመደመ በኋላ ኮሎኔል ካሣሁን በሐረር ከቤተሰባቸው ጋር ለጥቂት ሳምንታት ቆይታ ካደረጉ በኋላ በቀጥታ የተላኩት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የኤርትራ የጦር ግንባር ነበር፡፡
ኮሎኔል ካሣሁን በኤርትራ- በአቁርደት፣ በከረን በመጨረሻም በናቅፋ ግንባር…!!
ይቀጥላል …