>

‹‹የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ፤ የተጠቀሰችባቸው ዐውዶች› ሃይማኖታዊ/ ትውፊታዊ እውነቶች እና ሐሳቦች

‹‹የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ፤ የተጠቀሰችባቸው ዐውዶች››

ሃይማኖታዊ/ ትውፊታዊ እውነቶች እና ሐሳቦች

 

 

ከይኄይስ እውነቱ

በርእሱ የተጠቀሰው ጉዳይ ‹‹አስተምህሮ ዘተዋሕዶ›› በተሰኘ ድረ ገጽ/የጡመራ መድረክ እ.አ.አ. ጃንዌሪ 23/2021 የቀረበ ጽሑፍ ነው፡፡ ጽሑፉ እገሌ በሚባል ሰው ስም ተለይቶ አልቀረበም፡፡ አንብቤ እንደተረዳሁት የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማና ይዘት በጥቅሉ ሲታይ ኢትዮጵያ በቅዱሳት መጻሕፍት በበርካታ ቦታዎች በመጠቀሷ ብቻ አገሪቱን የተቀደሰ አያደርጋትም፡፡ በዚህ ረገድ ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር ቀላቅለው የሚመለከቱ በርካታ ምእመናን የተሳሳተ ግንዛቤ ስላላቸው፣ በተለይም ሀገርና ሰንደቅ ዓላማን መውደድና ማክበር ተገቢ ቢሆንም ቅዱሳት መጻሕፍት ከተጻፉበት ዓላማ አኳያ ሲታዩ ምድራዊ ጉዳዮች መሆናቸውን፣ በመሆኑም ‹ኢትዮጵያ› የሚለው ስም የተነሣባቸውን የቅዱሳት መጻሕፍቱን ክፍሎች በተለይም ዐውዶች በመልክዐ ምድርም ሆነ ይዘት ረገድ በመመርመርና በመዘርዘር ስሕተቶችን ለማረም ያለመ እንደሆነ ነው፡፡

የአሁኑ ጸሐፊ ዐቢይ ትኩረት ‹ሀገርና ሰንደቅ ዓላማ› ቅዱሳት መጻሕፍት ከተጻፉባቸው አምጻኤ ዓለማት/ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔርን አምኖ ሕጉን ጠብቆ፣ ትእዛዙን አክብሮ፣ መልካም ምግባራትን ሠርቶ የሰማያዊ መንግሥቱ ወራሽ ከመሆን ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡ ወይም ባጭሩ ከሃይማኖት ጋር ያልተያያዙ ዓለማዊ ጉዳዮች ናቸው የሚለውን በጽሑፉ የተገለጸውን አስተሳሰብ ይመለከታል፡፡

በቅድሚያ ‹‹አስተምህሮ ዘተዋሕዶ›› የተሰኘው ድረ ገጽ ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእምናን እምነታቸውን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አድርገው ለመንግሥተ እግዚአብሔር የሚበቁበትን ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ የበኩሉን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ መመስከር ይገባል፡፡ 

በጽሑፍ እንደተገለጸው የአንድ አገር ስም በቅዱሳት መጻሕፍት ደጋግሞ መጠቀስ በራሱ ብቻውን የአገሩን ቅድስና አያሳይም የሚለው አባባል የሚያስማማ ነው፡፡ አገሪቱ በመጻሕፍቱ የተጠቀሰችባቸውን ዐውዶች መመርመሩ ተገቢነትም አያከራክርም፡፡ በበጎም በመጥፎም ልትነሣ ትችላለችና፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢትዮጵያን ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቡን ሕዝበ እግዚአብሔር ያሰኘው በቅዱሳት መጻሕፍት ስለተነገሩ የቃል ኪዳን ቃሎችና መልካም ምስክርነቶች ብቻ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሦስቱም ሕግጋት (በሕገ ልቡና/ኅሊና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል) በአምልኮተ እግዚአብሔር ውስጥ ባላት ቀዳሚና ጉልህ ሥፍራና ይህንንም በሚያረጋግጡ ግዙፍና ረቂቅ አሻራዎች፤ እንዲሁም እግዚአብሔር በመረጣቸው ቅዱሳን ኪደተ እግር ስለተባረከችና ስለተቀደሰችም እንጂ፡፡ ቤተ ክህነቱን ጨምሮ አሁን ላይ ያለው ትውልድ ባመዛኙ ከሕገ እግዚአብሔርና ሥርዓተ እግዚአብሔር ፈቀቅ ማለቱ የተነገረውን እውነታ አይቀይረውም፡፡ ስለ ጥቂቶች ምርጦቹ ብሎ እግዚአብሔር አሁንም ሥራውን ይሠራልና፡፡ እግዚአብሔር በሁሉም ዘመን ሰው አያጣምና አሁንም ምርጦች እንዳሉት እናምናለን፡፡ ‹ኢይኀድጋ እግዚአብሔር ለብሔር ዘእንበለ አሐዱ ኄር/ኖላዊ ኄር› (እግዚአብሔር አገርን ያለ አንድ ቸር/ቸር ጠባቂ አይተዋትም) የሚለውን መንፈሳዊ ብሂል መዘንጋት አይገባምና፡፡  

ባንፃሩም ምድራዊቷ ቤተ ክርስቲያን የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳል ከሆነች፤ አንድም የጽድቅ ሥራ ሠርተን፣ ብንወድቅ ደግሞ ንስሓ ገብተን ተነሥተን ለሰማያዊ መንግሥት ዝግጅት የምናደርግባት ምድራዊቷ አገር ለሰማያዊው አገር አምሳል የማትሆንበት ምን ምክንያት አለ? ጽድቅም ሆነ ኩነኔ ያለው እኮ እዚሁ ምድር/እግዚአብሔር በሰጠን ግዛት በምንኖረው ሕይወት ነው፡፡ ተከትሎን የሚሔደው ምድራዊ ሥራችን ነውና፡፡ ከሞት በኋላ ንስሓ የለምና፡፡ 

በሌላ በኩል አገር የጋራ ‹ቤተ መቅደስ› ነች፡፡ የአገርና የሕዝብ ሃይማኖታዊ ማንነት ወይም ቅድስና የሚታየው አሁን ባለው (በሥጋዊ ዓይን በምናስተውለው) እውነታ ብቻ ሳይሆን ኃላፊውም ሆነ መጻኢው አብሮ ግምት ውስጥ ገብቶ ነው፡፡ ‹ሰብእ ይቄድሶ ለመካን፤ መካን ይቄድሶ ለሰብእ› የሚለው መንፈሳዊ ብሂል የሚያስረዳን አካሔዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው አገርን ቦታን ይቀድሳሉ፡፡ የተቀደሱ መካናት/ቦታዎችም እግዚአብሔር በሚገባው የማይታበል ቃል ኪዳን ሰዎች ይከብሩባቸዋል፤ይቀደሱባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ አሁን ኢትዮጵያ ተብላ የምትታወቀው አገር ከጥንት ጀምሮ ባገር ውስጥ የተነሡም ይሁኑ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተመርተው የመጡ የውጭ ቅዱሳኖች በኪደተ እግራቸው የባረኳት አገር ለመሆኑ ሕያው አሻራዎች (በርካታ ገቢረ ተአምራት ወመንክራት የሚፈጸምባቸው ገዳማትና አድባራት) ምስክሮች ናቸው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ በረከት የታደሉ ጥቂት አገሮች ናቸው፡፡ ሕክምና የለም ለማለት በሚያስደፍርበት አገር አሁንም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳት መካናቷ አማካይነት ፈዋሴ ድውያን በመሆን ‹የጤና ጥበቃ› ተግባሯን ቀጥላለች፡፡

በሰምና ወርቅ ትርጓሜ ተሸፍነው እንጂ በቅዱሳት መጻሕፍት በርካታ የአገር (የኢትዮጵያን) እና ሃይማኖትን ቊርኝት የሚያሳዩ ክፍሎች መኖራቸው አይካድም፡፡ ዝርዝሩን ለሊቃውንቱ በመተው፣ እዚህ ላይ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር 73/74 ቊ. 14 ከተናገረው አንዱን ለአብነት ማንሳት እወዳለሁ፡፡ ‹‹ወወሀብኮሙ ሲሳዮሙ ለሕዝብ ኢትዮጵያ›› (ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምግባቸውን ሰጠሀቸው)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለኢትዮጵያ መንፈሳዊ ሀብት፣ ጸጋና በረከት አድርጎ ከሰጣት በርካታ ሀብታት መካከል ምድራዊ መልአክ የተሰኘው፣ ሰማያዊውን ዜማ/ምስጋና ወደ ምድር ያመጣልን፣ የብሉያትና የሐዲሳት ትርጓሜ ሊቅ እንዲሁም የቅኔ ፈር ቀዳጅ የሆነው፣ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን የሚባለው ኢትዮጵያዊው የዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ በሦስት ስልት (ግእዝ፣ ዕዝል፣ አራራይ) ያዘጋጀው ያሬዳዊው ዜማ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙት ሊቃውንት አባቶቻችን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ምግብ›› ያለውን ‹አንድም› እያሉ ከሚያስቀምጡት ትርጓሜ መካከል ዋነኛው 24 ሰዓታት ስብሐተ እግዚአብሔር የሚቀርብባት አገር ያደረጋት ይኸው ያሬዳዊው ዜማ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ‹ስንዱ እመቤት› ካሰኙአትና ከልደተ እስከ ሞት ያለውን መንፈሳዊ አገልግሎቷን የተሟላ ያደረገው ይኸው የመላእክት ዝማሬ ያሬዳዊው ዜማ ነው፡፡ የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሯ የሚከፈተው በቅዱስ ያሬድ ዜማ ነው፡፡ ይህ ነፍስና አጥንትን የሚያለመልም፣ ከመላእክት ጋር አንድ ማኅበር የሚያደርገን ጸዋትወ ዜማ (ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ዝማሬ፣ ምዕራፍ እና መዋሥዕት) በጥንታዊቷም ሆነ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚገኝ ጸጋ እግዚአብሔር ነው፡፡ ‹ሰብእ ይቄድሶ ለሀገር› ማለት ከዚህ የተለየ ምን ትርጕም አለው? ሰው በምድር ሆኖ መልአክ መሆን እንደሚቻል ማኅሌታዊ ያሬድን ጨምሮ በርካታ ቅዱሳን ምስክሮች አሉን፡፡ እንደ ነቢያቱ ሔኖክ እና ኤልያስ፣ እንደ ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ በስዋሬ የሚገኘው ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያን ምስጋና የማይቋረጥባት ሰማያዊ የመላእክት ከተማ (ኢዮር፣ ራማና ኤረር) መንፈሳዊት ሀገር አድርጓታል፡፡ በምድር እያለች ‹ሰማያዊት› አድርጓታል፡፡ ላለፉት ግማሽ ምእት ዓመታት አገር በዓላውያን አገዛዞች፣ ባድር ባዮችና በሆዳም ተባባሪዎቻቸው እንዲሁም ቊጥሩ ቀላል በማይባል የሕዝባችን ክፍል የቁም ‹ሬሳነት› ጭምር እየተናጠች መሆኗ ልንወጣው የሚገባ ፈተና እንጂ እውነታውን አይቀይረውም፡፡ በመሆኑም የጻድቁ ቅድስና ለሀገር ተርፎ ኢትዮጵያን ሀገረ እግዚአብሔር ማድረጉን አያስቀርም፡፡ ግለሰብ ቢወድቅ በንስሓ ይነሣል፡፡ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ቢበድል አሁንም ከእግዚአብሔር መታረቂያው ንስሓ ነው፡፡ እግዚአብሔር የመረጠውን ማን ያቃልለዋል? እግዚአብሔር የቀደሰውን ማን ያረክሰዋል? እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደረገውን ማን ያዋርደዋል? ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም እንል የለም እንዴ? ሰቃልያነ እግዚእ፣ አሁንም ከክርስትናው በአፍኣ ያሉ አይሁዳውያን መኖሪያ ነች፡፡ የምርጦቹም የነቢያትና የሐዋርያቱ መኖሪያ ነበረች፡፡ ባለቤቱ መድኃኔ ዓለም ከፅንሰቱ እስከ ዕርገቱ ስለ ባረካት ቅድስትነቷ አያቋርጥም፡፡ ኢትዮጵያችንም እንደዚሁ ነች፡፡ ‹‹የእስራኤል ልጆች ሆይ÷ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር፡፡›› ትንቢተ አሞጽ 9÷7፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የቅዱስ ትውፊት አካል መሆናቸውን ካመን፣ በመንፈሳዊው ትውፊት – በጽሑፍ፣ በቃልና በቁስ – የተላለፈልን በቅዱሳት መጻሕፍቱ ከተካተተው እጅጉን የላቀ እንዳሆነ ካመን፣ ምድራዊቷ ኢትዮጵያ ‹ሰማያዊ› የሆነችባቸው በዙሪያዋ ያሉ እንደ ደመና የከበቧት በርካታ ምስክሮች አሏት፡፡ የቃል ኪዳኑ ታቦት (ታቦተ ጽዮን)፣ ግማደ መስቀሉ፣ የእመቤታችን ዐሥራት ሀገርነት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብዝና ወዘተ. ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ልቦለድ ወይም አፈ ታሪክ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን የሚያራክሱ፣ ሥር በሰደደ ጥላቻ ስሟ አይነሣብን የሚሉ ሁሉ ውገናቸው ከጠላት ዲያቢሎስና ሠራዊቱ ጋር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ‹አረሞች› ለጊዜው ሠልጥነዋል፡፡ ስም አጠራራቸው ያለ ጥርጥር ይጠፋል፡፡ ‹ርኢክዎ ለኃጥእ ዐብየ ወተለዐለ ከመ አርዘ ሊባኖስ፤ ወሶበ እገብዕ ኃጣእክዎ› (ኀጥእን ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት፡፡ ብመለስ ግን አጣሁት፤መዝ. 36÷35) እንዳለ ቅዱስ ዳዊት የኢትዮጵያ ጠላቶች ዕጣ ፈንታቸው ይኸው ነው፡፡ ያውም የከፋ፡፡ ‹ሞቱ ለኀጥእ ጸዋግ› (የኀጥእ ሰው ሞት ክፉ ነው፡፡ መዝ. 33÷21) እንዳለ ክቡር ዳዊት፡፡

ለጽሑፌ መነሻ የማደርገው መሠረታዊ መነሻ አገርን ከሃይማኖት ነጥሎ ምድራዊ/ዓለማዊ ጉዳይ ብቻ አድርጎ ማሰብ የሃይማኖትና ፖለቲካ ግንኙነትንና ልዩነትን ካለመገንዘብ የመነጨ አስተሳሰብ ይመስላል፡፡ ይህም የተሳሳተ የክርክር መነሻ (wrong premise) ነው ‹አስተምህሮ ዘተዋሕዶ› ባቀረበው ጽሑፍ ውስጥ ባለማወቅም ይሁን በማወቅ ስለ አገርና ሰንደቅ ዓላማ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያበቃው፡፡

ጠቅለል ባለ አገላለጽ ፖለቲካ ሰፋ ባለ ብያኔው የአገርና የሕዝብ አስተዳደር ጥበብ/ፍልስምና እና ሳይንስ ነው፤ ጠበብ ባለ ብያኔው ደግሞ በማኅበር/ፓርቲ ተደራጅቶ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገውን ሒደትና ውጤቱን ሁሉ ያካትታል፡፡ በዚህ በኋለኛው ብያኔ ፖለቲካ የሥልጣን ወይም የፓርቲ ፖለቲካ (power/party politics) ይባላል፡፡ በቀዳሚ ብያኔው ፖለቲካ የዕለት ተዕለት ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ሕይወትን ሁሉ ይጨምራል፡፡ በዚህ ብያኔ የአንድ አገር ዜጋ (የሚከተለው እምነት ግምት ውስጥ ሳይገባ) በሙሉ ‹ፖለቲከኛ› ነው፡፡ ባንፃሩም ሃይማኖት ስለ እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳት መጻሕፍት የተገለጠውን በፍጹም ልብ አምኖ፣ በተግባርም መስክሮ (ታምኖ) የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም የሰማያዊ መንግሥቱ ወራሽ የሚሆንበት መንገድ ነው፡፡ በማለት በጥቅሉ ልናስቀምጠው እንችላለን፡፡ ባጭሩ ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጠ ጸጋ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰጠ እኛ (አማንያን) ተቀበልን፡፡ ምድራዊ ሕይወታችንን ባግባቡና በሥርዓት መርተን ወደ ሰማያዊው ሕይወት የምንሸጋገርበት ፍኖት (መንገድ) ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሃይማኖት ሰማያዊውን ብቻ ሳይሆን ተከትሎን የሚሔደውን ምድራዊ አነዋወራችንን ሁሉ ይመለከታል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት (በብሉያቱም ሆነ በሐዲሳቱ) የተመዘገቡት እውነታዎች ከጊዜ፣ ከታሪክ፣ ከባህል ወዘተ. አኳያ የራሳቸው ዐውድ ቢኖራቸውም የሰውን ልጅ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት በመሉ አካትተዋል፡፡ የሕዝብና የአገር አስተዳደር ጉዳይ በነ ሙሴ፣ ኢያሱ፣ በነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት፣ በልጁ በጠቢቡ ሰሎሞን በሌሎችም መሳፍንትና ነቢያት ታይቷል፡፡ በዘመነ ሐዲስም አምላክ ራሱ ሰው ሆኖ፣ ከኀጢአት በቀር ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን በቃልም÷ በተግባርም (በተአምራት) አብነት ሆኖ አስተምሮናል፤ ቅዱሳን ሐዋርያቱና ተከታዮቻቸውም የሰው ልጆችን ማኅበራዊ ሕይወት መልክ በማስያዝ በቃልም በተግባርም አስተምረዋል፡፡ ርስት (አገር) ሃይማኖት የምንለው የፍኖተ እግዚአብሔር አንድ አካል ነው፡፡ ምድረ ርስት ከነዓን ለሰማያዊቷ ርስት መንግሥት ሰማያት ምሳሌ እንደሆነች ሁሉ፡፡ በመሆኑም አገርን ከሃይማኖት ጋር ያልተያያዘ ምድራዊ ገንዘብ ብቻ አድርጎ መመልከት በቅዱሳት መጻሕፍት ከተገለጸው እውነት ያወጣናል፡፡ ሃይማኖትና ፖለቲካን አንዱ የሌላው ተፃራሪ፣ ሙሉ በሙሉ የተለያዩ ወይም አንዱ ከሌላው ጋር አብሮ የማይሔድ፣ የሚገናኙበት/የሚደራረቡበትሁናቴ እንደሌለ (mutually exclusive) አድርጎ ከማሰብ የመነጨ ስሕተት ነው፡፡ ‹ኮረንቲና ፖለቲካ› በሚል የተሳሳተ ዐላዋቂ አነጋገር ፋሺስታዊ አገዛዞች  እንደ ሰም አቅልጠው እንደ ገል ቀጥቅጠው÷ በእጃቸው ጭብጥ በግራቸው ርግጥ አድርገው በባርነት እንዲገዙን የሚያመቻቹን ከርሣሞች ብዙዎች ናቸው፡፡ ገሚሶቹ ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው፣ ሌሎቹም ላገር ተቆርቋሪ መስለው ነው፡፡ በዚህ ጥፋት ‹ጨዋው› ብቻ ሳይሆን አብዛኛው የቤተ ክህነቱ ሰዎች ተርመጥምተውበታል፡፡ በነገራችን ላይ ባሁኑ ጊዜ አብዛኛው የቤተ ክህነቱም አውደልዳይ ‹ጨዋ› መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከአምላክ ለተሰጠው የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት ሕይወት በቊርጠኝነት እስከ መሥዋዕትነት በጥብዐት እንዳይታገል ወኔውን የሚሰልቡት አገርና መለያ ማተቧን ሰንደቅ ዓላማን በማስጠላት፣ በመናቅና በማዋረድ ነው፡፡ 

በነገራችን ላይ ሃይማኖትና ፖለቲካን ለማለያየት የሚፈልጉ አብዛኛዎቹ ሰዎች አንድም ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ፖለቲካ ግንኙነት ያልገባቸው፣ በሌላም ወገን የዐላውያን ገዢዎችን ጥቅምና ፍላጎት በማስከበር ዓላማ ሕዝብን አፍዞና አደንግዞ ለባርነት እንዲመቻች የሚያደርጉ፣ እግዚአብሔር በነፃነትና በእኩልነት እንዲኖር የፈጠረውን የሰው መብት የሚያስገፍፉ ጮሌዎች ሲሆኑ፤ አንድም ስለ ምድራዊ ሕይወት አትጨነቁ በሚል ዐውዱን በሳተ ከንቱ ‹ስብከት› ሞኝ ምእመናን እያታለሉ፣ የምእመኑን ገንዘብ አጥንቱ እስኪታይ ድረስ በቅጥር ‹ካድሬዎች› የሚዘርፉና የሚያዘርፉ፣ በሃይማኖት ሽፋን ሞኞችን የሚያጃጅሉ፣ ሰውን ተንቀሳቃሽ ‹ሬሳ› የሚያደርጉ መሠሪዎች ናቸው፡፡ የመጨረሻ ግባቸውም ክርስቲያኑን በአገሩ ጉዳይ የማያገባው በማድረግ ላገርና ለቤተ ክርስቲያን አፍራሾች ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ እኩያን ናቸው፡፡ አገሩን፣ ቤተ ክርስቲያኑን እና መልካም ዕሤቶቹን የተነጠቀ ሕዝብ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ ነው የሚሆነው፡፡ የምናመልከው እግዚአብሔር አምላክ በነፃነት ፈጥሮን በነፃነት እንድንኖር የፈቀደ አምላክ ነው፡፡ በሕዝብና አገር ላይ ባርነት፣ ግፍና በደል የሚያሰፍኑ፣ አገርን የሚያፈርሱና የሚነጣጥሉ አገዛዞች ከእግዚአብሔር መንገድ የወጡ የሰይጣን መልእክተኞች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ፍትሕ ርትዕ ገንዘቡ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ለባርነት አልፈጠረንም፡፡

የሕዝብን መንፈሳዊውም ሆነ ሥጋዊ ሕይወት ምስቅልቅሉን የሚያወጡትን፣ እግዚአብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው ከትንኝ ሳይቆጥሩ በጭካኔ የሚጨፈጭፉትን፣ የባዕዳን ቅጥረኞች ሆነው አገር እስከነ መልካም ዕሤቶቿ የሚያፈርሱትን ታግሎ ፍትሕ ርትዕ ማስፈን ሰብአዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ አገሩን፣ ሰንደቁንና ቤተ ክርስቲያኑን የሚወድ ሕዝብ መገለጫው ይህ ነው፡፡ አገር ከሌለ ቤተ ክርስቲያን የለምና፤ አገር ከሌለ በሥርዓት አምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸም አይቻልምና፡፡ ዓላውያኑ ይህንኑ በተግባር እያሳዩን ነው፡፡

ሌላው ሃይማኖትና አገር የተለያዩ ተደርገው – አንዱ ሰማያዊ ሌላው ምድራዊ – እንዲሣሉ ምክንያት የሆነው ዐላውያን ገዢዎች ሥልጣንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚቀርፁትን፣ ሳይመቻቸው የሚጥሱትን፣ ላገርና ለሕዝብ አይበጅም ሲባሉ በመቃብራችን ላይ ከልሆነ ማን ነክቶት በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ ብለው የሚጮኹለትን በተለምዶ አጠራሩ ‹ሕገ መንግሥት›÷ ለነዚህ ዓይነት ፋሺስታዊ አገዛዞች በሚገባ ስሙ ‹ሕገ አራዊት› ላይ ‹መንግሥትና ሃይማኖት ለየቅል ነው፤ አንዱ በሌላው ጣልቃ አይገባም› በማለት ያስቀመጡትን ድንጋጌ መሠረት አድርገው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ወያኔ በቀረፀውና ውሉዱ ሙጥኝ ብሎ የያዘው ‹ሕገ አራዊት› ለአሳዳሪዎቻቸው ለመሸጥ ለይስሙላ ከሰነቀሩአቸው ‹የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች› ውጭ በዓለም ላይ የሌለ ‹ካልዕ ፍጥረት› ነው፡፡ ጎበዝ! ‹መንግሥት›/አገዛዝና አገር እኮ አንድ ዓይነት ‹ፍጡራን› አይደሉም፡፡ ምድር የትኛውንም የአገር ስም እንስጠው ባንፃራዊነት ቋሚ፣ እንደ ክርስትናው በዕለተ ምጽአት የሚያልፍ ነው፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ እንደሚለው ባዲስ ሰማይና ባዲስ ምድር እስኪተካ ድረስ፡፡ አገዛዞች/‹መንግሥታት› ግን (ኃያላንም ይሁኑ ደካሞች) ተለዋዋጭ ናቸው፡፡ ጉልበታቸውን ተመክተው ‹የዕድሜ ልክ ገዥ› ብለው ራሳቸውን ቢሰይሙም እንኳን ጉልበቱም ይነጥፋል፤ ዐረፍተ ዘመንም ይገታቸዋል፡፡

ሃይማኖት/የእግዚአብሔር መንግሥት ዳር ድንበር አይበጅለትም፡፡ በ‹መንግሥት› ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚል የአገዛዞች ልብ ወለድ ድርሰት ነው፡፡ ሰማያዊው ብቻ ሳይሆን ምድራዊውም ነገር ያገባዋል፡፡ ፍርድ ሲጓደል ደሀ ሲበደል ሰማያዊው መንግሥት ያገባዋል፡፡ አገር ከነ ሙሉ ክብሯ፣ ነፃነቷ፣ ኩራቷ የምትኖረው በሃይማኖት (በፈሪሃ እግዚአብሔር) ስትጠበቅ ነው፡፡ የሕዝብና የአገር አስተዳደር ያልነው ፖለቲካ ባገርና በሕዝብ ጉዳይ ያገባኛል ማለት ነው፡፡ ጠባቦች ፖለቲካን የሚያስቡት በሸፍጥ በተንኰል በተተበተበው በሥልጣን/ፓርቲ ፖለቲካ ወስነው ነው፡፡ የዕለት ተዕለት ማኅበረ-አኮኖሚያዊ ሕይወታችን በሙሉ የፖለቲካ አካል ናቸው፡፡ በመሆኑም ክርስቲያኖች ከዚህ ውጭ አይደለንም፡፡ የሰማያዊው መንግሥት አምሳል የሆነች ቤተ ክርስቲያን በአየር ላይ የተንሳፈፈች አይደለችም፡፡ በምድር ላይ ሆና በአገር የምትገለጽ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሁሉም ትርጓሜዋ ያለ አገር አትጸናም፡፡ ባገር ብትገለጽም ከሰማያዊው መንግሥት ጋር የተሰናሰለች በመሆኗ ለቆመችለት ዓላማ አጥር ቅጥር አይወስናትም፡፡

ለአገር የሚሰጠው ዓለማዊው ትርጓሜ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሃይማኖት ዓይን ስንመለከት እግዚአብሔር ፈቅዶ ለሰው ልጆች በሰጠው ምድር ያሉ ነዋሪዎች የጋራ ‹ቤተ መቅደስ› ነው፡፡ በታሪክ ሒደት መጥበብና መስፋት የሰዎች ጣልቃ ገብነት ሆኖ፣ ስም ተሰጥቶትና ድንበር ተወስኖለት ባለው ግዛት ውስጥ የሚኖር ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ቊርኝት አገሩን ሀገረ እግዚአብሔር፣ ሕዝቡን ሕዝበ እግዚአብሔር ሊያሰኘው እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ በዚህ ረገድ አሁን የዚህ ጽሑፍ ዋና ጉዳይ ባለመሆኑ ወደዚህ ሐተታ መግባት አስፈላጊ ባይሆንም ኢትዮጵያ ብለን በምንጠራት የዓለም ክፍል ውስጥ የምትገኝ አገር ሲሰፋ ሲጠብ የኖረው የመጽሐፍ ቅዱሷ ኢትዮጵያ ዋና ክፍል እንደሆነች የጥንታዊ ታሪክ በተለይም የክርስትና ሃይማኖት ታሪክ በቂ ማስረጃዎች አሉ፡፡ በዘመናት ሒደት ያልጠፉ እስካሁን ያሉ በርካታ በግዘፍም በርቀትም የሚገኙ አሻራዎችም አሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት ሉዐላዊ በሆነው የቅዳሴ ጸሎቷ ‹‹መቅድመ ኅሡ ሰላማ ለብሔር›› (ከሁሉ አስቀድማችሁ ስለ አገር ሰላም/ደኅንነት ጸልዩ) የምትለው ያገርና የሃይማኖት ጥብቅ ግንኙነትን የሚያመለክት ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹እግዚኦ ሰላመከ ሀባ ለሀገር ወጽድቀከኒ ለቤተ ክርስቲያን፡፡ አግርር ፀራ ታሕተ እገሪሃ ዕቀብ ሕዝባ ወሃይማኖቷ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ›› (አቤቱ ሰላምህን ላገራችን ኢትዮጵያ ስጣት፤ እውነትህንም ለቤተ ክርስቲያን፡፡ ጠላቶቿን ከእግሯ በታች አስገዛላት፤ ሕዝቧንና ሃይማኖቷንም ጠብቅ ) እያለች አምላኳን የምትለምነው ምድራዊቱ አገር የሰማያዊው አገር ሰዋስው በመሆኗ ጭምር ነው፡፡ ምን ነካን ጎበዝ! ዓላውያን ገዢዎችና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው አገርን ለማፍረስ በቅድሚያ የክርስቶስ አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ማፍረስ አለብን ብለው ሲዘምቱባት የዚህ ቅድስና መገለጫ የሆነችውን አገር እያፈረሱ እንደሆነ አይገባንም እንዴ? ሆዱን ሳይሆን እግዚአብሔርን አምላኩ ያደረገ ክርስቲያን አገሩ ‹ሃይማኖቱ› ጭምር ናት፡፡

አገርንና መለየዋ ማተብ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ መውደድና ማክበር ከሃይማኖት ዕሤቶቻችን መካከል አንዱ ነው፡፡ አያት ቅደመ አያቶቻችን ለኢትዮጵያ በግብዝና የተሰጣትን ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርስ (ቅዱስ ትውፊትን ያስተውሏል) ለስሙ መታሰቢያ ቤተ ክርስቲያን አንጸው፣ ታቦት ቀርፀው፣ ወርኀዊና ዓመታዊ ክብረ በዓላቱን በማክበር ብቻ አላበቁም፡፡ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይዘው ዓድዋ የዘመቱት ነፃነታችን፣ ክብራችን፣ ኩራታችን፣ ከሁሉም በላይ የሃይማኖታችን መገለጫ የሆነችውን አገራችንን ለማስጠበቅ ነው፡፡ ቀደምት አበው ወእመው ላገር መዋደቅ ሃይማኖትን፣ ቤተ ክርስቲያንን ማስጠበቅ እንደሆነ ገብቷቸዋልና፡፡ አገር ከጠባቡ የሥልጣን ወይም ፓርቲ ፖለቲካ በላይ ናት፡፡  

አገር የሃይማኖት ርእሰ ጉዳይ መሆኗ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሃይማኖትን÷ ቤተ ክርስቲያንን÷ ቃለ እግዚአብሔርን የግልና ምድራዊ ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅ የሚጠቀሙ የሉም ማለት አይደለም፡፡ የአምልኮ መልክ እንጂ እውነተኛ መንፈሳዊነት በጠፋበት፣ የበዓል ክርስትና በነገሠበት ባለንበት ዘመን እንዲህ ያሉቱ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ይህ ግን አገርን እንደ ተራ ምድራዊ ጉዳይ ብቻ እንድናያት አያደርገንም፡፡ እናስተውል! ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ‹መንግሥት›/አገዛዝ እና አገር ተለዋዋጭ ሐሳቦች አይደሉም፡፡

 

ማሳሰቢያ፤ ይህ ጽሑፍ ቀጥታ ‹‹አስተምህሮ ዘተዋሕዶ›› ለተባለው ድረ ገጽ ያልተላከው የአገር ጉዳይ በመሆኑ ተደራሽነቱን ለማስፋት በማሰብ ነው፡፡

Filed in: Amharic