>

ሀገር ሻጩ የመሬት አዋጅ

ሀገር ሻጩ የመሬት አዋጅ

ፋኖ አርበኛ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው 

 

የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ከ1950ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በኢትዮጵያ  ፖለቲካ ውስጥ ሲያከራክር ቆይቶቷል። የመሬት ለአራሹ ጥያቄ የአደባባይ ተቃውሞዎች፣ የአዳራሽ ውስጥ ውይይቶች ብሎም የጋዜጣ ገፆች ማዳመቂያ ሆኖ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ማጠናቀቂያ ቀጥሏል። በደርግ አገዛዝ ጥያቄው ተቀልብሶ መሬት ለገበሬው መሆኑ ቀርቶ ለጥቂት ወታደራዊ መኮንኖች ሆኖ ኖረ። በወያኔ ዘመንም የመሬት ጉዳይ አከራካሪነቱ የቀጠለ ቢሆንም የማይሸጥ የማይለወጥ ንብረት መሆኑ ግን በሕገ መንግሥታቸው አንቀጽ 40 በግልፅ ተደንግጓል። መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር ሳይለወጥ በወጥነት የዘለቀው ይኸው የመሬት አይሸጤ እና አይለወጤነት ነው። ይህ ከሩቁ ቢሞቁትም እንደ እሳት አይነኬ ሆኖ የቆየው ኢትዮጵያ የሩሲያ ሩብል ስለማያስፈልጋት፣ የአሜሪካ ዶላር ስለማያሻት፣ ፓውንድ ችግሯን ስለማይወቅም ወይም ድርሀም ከብር ምንዛሬ ያነሰ ሆኖ አልነበረም። የመሬት ጉዳይ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ስለሆነ እንጂ። ለጠኔ ሀገርን መሸጥ ቀርቶ ከሀገር መሰደድ እንኳን ብሔራዊ ነውር ስለሆነ ነው። ይህ በአውደ ምህረትም በመማሪያ ክፍልም፣ በንጉሱም በዻዻሱም አንደበቶች ሲነገረን ባጅቷል። በዝርው፣ በግጥም፣ በመዝሙር፣ በልብ ወለድ ወዘተ አጥንትና ደማችን ውስጥ ተዋህዷል። ከቁንጮ እስከ ሽበት፣ ከሳዱላ እስከ ቁንዳላ የተማርነው የሕይዎት ዘመን ትምህርታችን ነው። አኮቴት ለአባቶቻችን! 

ሆኖም ዘንድሮ ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ሆነ። ትውልዱ እንደዚያ ዘመን በሀገር ፍቅር ስሜት መቀረጹ ቀርቶ ከቤተ መንግሥቱም ሆነ ከቤተ ክህነቱ እረኛ ያጣ መንጋ ሆኗል። አገዛዙ ደግሞ ኢትዮዽያን የሚፀየፍ ኢትዮዽያዊ ሆነ። ሐቀኛው ደራሲና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ በ1950ዎቹ “ጥቁር ጣልያናውያን” ይላቸው የነበሩት ጸረ ኢትዮዽያ ኢትዮዽያውያን ዛሬ የሀገር መሪ ሆነዋል። የምድሩም የሰማዩም አዛዥ ናዛዥነታቸው ቀጥሏል። እነሆ አለቃቸው አብይ አሕመድ እናት ሀገራችን ኢትዮዽያ “ይህ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው። ለልጅ አይሰጥም” ብላ ዜጎቿን ስንኳን ከልክላን የቆየቺውን የመሬት ባለቤነት መብት ለውጭ ሀገር ዜጎች ሰጣቸው። ነገሩ ጠይሙ ጣልያን ለነጩ ጣልያን እንደመደርጎት  ነው። የኦነጋውያንን የወረራ ሥልጣን ለመጠበቅ የተቀመጠው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሰሞኑን በአብላጫ ድምፅ እና በሁለት ተቃውሞ ሀገር መሸጫ አዋጁን አጽድቋል። የሚንስትሮች ምክር ቤት አርቅቆ ያመጣውን አዋጅ አለማጽደቅን እንደ ነውር፣ ብሎም ጠቅላይ ሚንስትር ተብየውን እንደ መዳፈር የሚቆጥረው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ይህንንም  ሲያጸድቅ ሙዝ የመላጥ ያህል ቀሎታል። አላከራከረውም። አላጨቃጨቀውም። አላወዛገበውም። 

አዋጁ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንደሚቀርፍም ተነግሮለታል። መላሽ ባይኖርም እዚህ ላይ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ እናንሳ፡- ሀገር ተሽጦ የሚመጣው የውስጥስ ሆነ የውጭ ምንዛሬ ለማን ይጠቅማል? ያለ ሀገር የት ይኖራል? የት ይበላል? ሀገርን ሽጦ ገንዘብ መሰብሰብ በሬውን አርዶ ስጋውን ለበሬው መኖ እንደማዘጋጀት አይሆንም ወይ? 

ዜጎቿ በድህነቷ ድለዋት ይሰደዳሉ። መሪዎቿ ይባስ ብሎ በድህነቷ ይሸጧታል። በይህቺ  ሀገር ሰርቶ ለመብላት የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ሰጥታ እያለ በራስ ስንፍና በመጣ ድህነት ስንቱን መከራ ትሸከም? 

ለመሆኑ ይህ የውጭ ሀገር ዜች በኢትዮዽያ መሬት እንዲገዙና በባለቤትነት እንዲይዙ የሚጋብዘው አዋጅ እንዴት ሀገር መሸጫ ሊሆን ይችላል? ለዚህ የእራኤል እና ፍልስጤም ተሞክሮ ሸጋ ምሳሌ ነው፦ 

እስራኤል እንዴት ዳግም ተመሰረተች?

እስራኤላውያን ሀገራቸው ፈርሳ፣ በዓለም ዙሪያ ተበትነው ለ2 ሺህ አመታት ያህለ ኖረዋል። የኦሪት አማኞቹ የጥነተ እስራኤላውያን ምድር ወደ አረብነት ተቀይራ ነበር። ታዲያ እስራኤላውያን በጥንታዊ አባቶቻቸው ምድር እንደገና ለመሰባሰብና የተነጠቋት ሀገራቸውን ለመመለስ ታገሉ። ሁለት ሺህ አመታትን ከፈጀው ትግላቸው መካከል ሀገራቸውን መልሰው ያቆሙበትን የቅርብ ሂደት (Immediate cause) ብቻ እንጥቀስ። እስራኤል ወደ ፍልስጤም ተቀይራ ነበር። የወቅቱ የፍልስጤም ገዥዎች ደግሞ ቱርኮች ነበሩ። ለእስራል መልሶ መቋቋም የሚታገለው የጽዮናዊነት ንቅናቄ የቱርኩን መሪ ሱልጣን አብዱል ሐሚድን በፍልስጤም ለእስራኤላውያን ማረፊያ የሚሆን ብርኩማ መሬት እንዲሰጣቸው ጠየቀ። ሱልጣኑ ፈቃደኛ አልነበሩም። በወቅቱ የነበረው የጽዮናዊነት ንቅናቄ መሪ ቴዎዶር ኸርዚል በፍልስጤም መሬት ቢሰጡት በምትኩ ቱርክ በውጭ ሀገራት ያሉባትን ብድሮች ጽዮያውያኑ እንደሚከፍሉ ሊያግባባቸው ሞከረ። በአውሮፓ የሚኖሩ ጽዮናውያን ባለጸጋ ነጋዴዎች ነበሩና ይህንን ማድረግ ይችሉ ነበር። ሆኖም የቱርኩ መሪ “አንድ ጋት መሬት እንኳን አልፈቅድላችሁም” አሉ። 

ጽዮናውያኑ በዚህ ተስፋ አልቆረጡም። “ሰው የሌለውን ሀገር፣ ሀገር ለሌላቸው ሰዎች! – Land without people,  for people without land!” በሚለው መፈክራቸው ታጅበው አሁንም በፍልስጤም የእግራቸው መርገጫ ምድር ለማግኘት ኳተኑ። እንደ ቱርክ ሁሉ በወቅቱ በአካባቢው ሰፊ ተፅዕኖ የነበረውን የእንግሊዝን መንግሥት ጠየቁ። “ፍላጎታችሁ መሬት ከሆነ በመካከለኛው ምስራቅ በፍልስጤም ሳይሆን በአፍሪካ ዩጋንዳ እንድትሰፍሩ ፈቅደናል” ተባሉ። እንግሊዝ ይህንን ማለቷ ዩጋንዳ በቅኝ ግዛቷ ስር ስለነበረች ነው። ነገር ግን እስራኤላውያኑ “በአባቶቻችን ሀገር በአፅመ ርስታችን ካልሆነ በስተቀር አንቀበልም” አሉ። 

ሦስተኛውን አማራጭ ሞከሩ። ይህኛው አማራጭ ከፍልስጤም ገበሬዎች መሬት እየገዙ በአካባቢው መስፈር የሚል ነበር። ተሳካም። የፍልስጤም ሕግ መሬት ለውጭ ሀገር ዜጋ መሸጥን የሚከለክል ባለመሆኑ ከቤት መስሪያም በዘለለ ጽዮናውያን ነጋዴዎች ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎችን እየገዙ ማልማት ጀመሩ።  ቀጥሎ “ማሳችን ጠባቂ” በሚል ታጣቂዎችንም ማስቀመጥ ጀመሩ። የእርሻ ማሳዎች ሀጋናህ የተባለው የጽዮናውያኑ ህቡዕ ወታደራዊ ድርጅት ማደራጃና ማሰልጠኛ ሆኑ። በፍልስጤም የሚሰፍሩ እስራኤላውያን ቁጥር ቀስ በቀስ እየጨመረ መጣ። የመጀመሪያዋን የአይዳውያን ከተማ ቴላቪቭን ከ123 አመት በፊት በ1902 መሰረቱ። ከዚህ በኋላ ሀጋናህ በሁለቱም የአለም ጦርነቶች ተሳትፎ ያገኛቸው ድሎች እና የእስራኤላውያንን የሃይል ሚዛን የማስጠበቅ አቅሙ በመጎልበቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፍልስጤም የሁለት መንግሥት ስርዓትን ፈቀደ። በአንድ በኩል የፍልስጤም መንግስት በሌላ በኩል የእስራኤል መንግስት እየተቧቀሱም፣ ለጎሪጥ እየተያዩም ቆሙ። በውጭ ባለሀብቶች ተይዞ የነበረው እየሩሳሌም እና አካባቢው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተይዞ እንዲቀጥል ሲወሰን የናጊቭ በረሃን ጨምሮ 55 ከመቶ የሚሆነው የፍልስጤም መሬት ለጽዮናውያን ተሰጠ። 44 ከመቶ የሚሆነው ደግሞ ለአረቦች ተሰጠ። በዚህም ጽናውያኑ ዳግም የሀገር ባለቤት ሆኑ። 

እስራኤላውያን በዲፕሎማሲና የፖለቲካ ጥያቄ የተከለከሉትን በግዥ የወሰዱት የአባቶቻቸውን አፅመ ርስት ነው። እኛ ኢትዮዽያውያን ደግሞ አባቶቻችን በደም እና በአጥንት ከቅኝ ግዛት ጠብቀው፣ በሰላም እንዳንጭበረበር ሕግ ሰርተው ያቆዩንን ሀገር፥ ሕግ ሽረን ሕግ በመስራት ለሽያጭ ገበያ ይዘናት ቀርበናል።

የኬንያው የሕግ ሊቅ እነ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ ጸረ ቅኝ ግዛትን እተሰበኩ ባለበት፣ የቡርኪናፋሶው መሪ ካፕቴን ኢብራሒም ትራኦሬ አውሮፓውያንን ከሀገራቸው እያስወጡ ባለበት፣ ከዘመነኛው ቅኝ ገዥነት (Neocolonialism) ጋር አንገት ለአንገት እየተናነቁ ባለበት በዚህ ዘመን ጸረ ኢትዮጵያው የኢትዮዽያ መሪ አዋጅ አውጆ ቅኝ ገዥን ጋብዟል። ለመሆኑ ታላሚ ተጋባዦች እነማን ይሆኑ?

አዲሱ የአረብ ወራራ

ከአመታት በፊት የተባበሩት አረብ ኢምሬት ኩባንያዎች ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል። የከተማዋን ኗሪዎች እያፈናቀሉ ታላላቅ ሕንፃዎችንም ገንብተዋል። ከእነዚህ መካከል ኤግል ሒልስ የተባለው ኩባንያ አንዱ ነው። ኤግል ከእሪ በከንቱ እስከ ለገሀር ዜጎችን አፈናቅሎ በርከት ያሉ ሕንፃዎችን አንጿል። በዚህ ምክንያት ጠላ እና ቆሎ በመሸጥ ይተዳደሩ የነበሩ እናቶች መድረሻ አጥተዋል። ቤታቸው ፈርሶ አንድም ሕንፃ ተገንብቶበታል ሌላም ሸርተቴ መጫዎቻ ተርቶበታል። ዛፎች ተሰርተውበት የሰው ሰራሽ ደን አካልም ሆኗል። ተፈናቃዮች በበኩላቸው ከእድር እና ማህበሮቻቸው ተናጥበው ባይተዋር ሆነዋል። ከዚህ ሲከፋም ፈፅሞ ማረፊያ አጥተዋል። የወንዞችና የወንዞች ዳርቻ ልማት፣ ሸገርን ማስዋብ ወዘተ በተባሉ አፍራሽ ውጥኖች ሁሉ ኗሪዎች ተፈናቅለዋል። ታሪካዊው ቡፌ ደላግርን ጭምር  የአረቡ ኩባንያ ግፊያ አናጥቦታል።

የሰሞኑ ሀገር ሻጭ አዋጅ አረቦቹ የእነኝህ ሕንፃዎች ብቻ ሳይሆን ሕንፃዎቹ ያረፉበት መሬትም ጭምር ቋሚ ባለቤቶች እንዲሆኑ የሚያስችል ነው። ወደፊትም እያንዳዳቸው ሕንፃዎች እንደ ኢምባሲ ሉዓላዊ የማይሆኑበት ምክንያት አይታየኝም። እዚህ ላይ ነው የእስራኤልና ፍልስጤም ተሞክሮ የሚሰራው።

በአዋጁ መሰረት ባለፉት አመታት በተገነቡትም ሆነ ወደ ፊት በሚገነቡት አዲስ አበባ ብሎም መላ ኢትዮዽያ የአረብ ወረራ ሰለባ ትሆናለች። የዘመናት ፍላጎታቸውም ይሳካል።

የአረብ ፍላጎት

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ የሚዋኘው ቀይ ባሕር ላይ ነው። ቀይ ባሕር የአረብ ቀለበት ውስጥ እንዲገባ ይፈለጋል። ቀለበቱ ዙር እንዳይሞላ ያስቸገረቺው ኢትዮዽያ ነች። ከኢትዮዽያም በተለይ የሰሜን ኢትዮዽያ ሕዝብ። በአቅራቢያ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን ለአረብ ፖለቲካም ሆነ ስነ ልቦና የተመቹ ናቸው ወይም ራሳቸው አረቦች ናቸው። ኤርትራ በከፊል አረብ ሆናለች። የአረባዊ ፖለቲካ አስመራ ውስጥ ያለው ቦታ በቀላል የሚገመት አይደለም። በአንፃሩ ኢትዮዽያ የአረብ ሊግ አባል አለመሆን ብቻ ሳይሆን በሀይማኖት፣ በባሕል፣ በትውፊትም ሆነ በስነ ልቦና ከአረብ የራቀች ነች። ይልቁንም ከአረቦቹ ታሪካዊ ጠላት እስራኤል ጋር የታሪክ፣ የስነ ልቦና፣ የባህል ወዳጅነት አላት።

በመሆኑም 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአማራ ነገስታት እና አርበኞች ትግል የተገታውን የአረብ ወረራ ለማስቀጠል አሁን ምቹ ጊዜ ያገኙ ይመስላል። ኢትዮዽያን በገንዘብ የሚሸጥላቸው የኢትዮዽያ መሪ አግኝተዋል። አዋጅ አርቅቆ በማጽደቅ በሕጋዊነት እንዲወሩ አመቻችቶላቸዋል። ይህ ለኢትዮዽያ ብቻ ሳይሆን ለመካከለኛው ምስራቅ፣ ለአውሮፓ እና ለአሜሪካ ፖለቲካም ጠንቅ ነው። የአረብ ወረራ በፖለቲካ፣ በኃይማኖት፣ በባህል እና በምጣኔ ኃብት መነፅር ቢታይ ዳፋው ከኢትዮዽያ ባሻገር ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ የሚመታ ነው።

በነገራችን ላይ የሱዳን እና የሶማሊያን እየፈረሱ መምጣት፣ የደቡብ ሱዳንን ውጥረት እና የኢትዮዽያን የአንድነት ስጋት ስንጨምርበት ጅምር ወረራውን ይበልጥ ያፋጥነዋል።

በአጠቃይ አብይ አሕመድ እንደ ግራኝ አሕመድ ሆኗል። ኢትዮዽያ አጼ ልብነ ድንግልን ትሻለች። ገላውዲዎስን ትፈልጋለች። ልጆቿን ኩባ ድረስ አዝምታ ለአሜሪካ ጥቅም ያዋጋች ሀገር ክርስቶፎረስ ዳጋማን ታማትራለች።

Filed in: Amharic