>
5:18 pm - Wednesday June 16, 8517

......ወደ ዕውነተኛ ምርጫ ለመሄድ [ገ/ፃዲቅ አበራ]

ethiopia_electionየህወሃት ኢህኣዲግ ቡድን የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት በሃይል ከተቆጣጠረ ወዲህ የዘረኛው ቡድን ፊታውራሪ ኣቶ መለስ ዜናዊ በሌሉበት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው ምርጫ ውጤቱ የታወቀና ተቆጥሮ የተደለደለ መሆኑ ቢታመንም፤ በኦሮሚያ ኣካባቢ የታየው ህዝባዊ መነሳሳትና እንቅስቃሴ ኣስቀድሞ የተጻፈውንና ምርጫ ቦርድ ካዝና ውስጥ የተቀመጠውን ውጤት እንዳለ ይፋ ለማድረግ የሚያስቸግርበት ሁኔታ ተከትሏል።
እርግጥ ነው በኦሮሚያ ክልል የታየውና በመድረክ መሪነት በተለያዩ ዞኖች የተመዘገበው ከፍተኛ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ባይኖርም የዛሬ ኣምስት ኣመቱን ወጤት እንዳለ መድገምና ለተቃዋሚዎች ኣንድ ወንበር ብቻ መልቀቅ እርዳታን ይበልጥ የሚያነጥፍ በመሆኑ ጥቂት ወንበሮችን ለተቃዋሚዎች እንደሚለቁ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ስምና ተሰሚነት ያላቸው ተቃዋሚዎች ሃሳበ ድውያን በሞሉበት ፓርላማ ጫጫታ እንዲፈጥሩ ህወሃት በፍጹም ኣልተዘጋጀም። ሆኖም በመሬት ላይ ያለው ዕውነታ ዶክተር መራራ ጉዲና እና ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ወደ ፓርላማ የሚመለሱበትን መንገድ እየጠረገ ይገኛል። ዓለም ኣቀፉም ማህበረሰብ ከርቀትም ሆነ ከቅርበት እያነበበው ያለው ስዕልም ይሄ በመሆኑ ለህወሃት ያለው ምርጫ የፖለቲካ መሪዎቹን ወደ ፓርላማ መልሶ ከዓለም ኣቀፉ ማህበረሰብ የሚሰፈርለትን ቀለብ መቀበል ይሆናል።
 የህወሃት ኣማካሪዎችም ዶክተር መራራና ፕ/ር በየነ ፓርላማ እንደሚመለሱ በኣደባባይ ምልክት ሰጥተዋል። ቢያንስ  በኣንድና ሁለት  ምክንያቶች ሕወሃት ይህንን ለመቀበል ይገደዳል። ኣንደኛ ከእንግዲህ የዕርዳታ ገንዘብ የለም ማለት፣ መድሃኒትና ነዳጅ የሚገዛበት የውጭ ምንዛሪ ጭምር የለም ማለት ስለሚሆን። ጥቂት ተቃዋሚዎች ፓርላማ እንዲገቡ ፈቅዶ፣ በቀጥታ የሚተላለፉ የፓርላማ ውይይቶችን በማስቀረትና ተቀርጸው የሚተላለፉትንም በመቆራረጥ የተቃዋሚዎችን ፓርላማ መግባት ትርጉም ኣልባ በማድረግ የፈረንጅ ምጽዋት ማግኘቱ የተመረጠ ይሆናል።
በተጨማሪም ‘ስርዓቱ እየተሻሻለ ነው’ በሚል ፈቅደው የሚታለሉና፣ በኣቅም ማነስ የሚወናበዱ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ድጋፍ ስለሚያስገኝ የመሳሪያ ትግል ብለው ብረት ያነሱትን ሃይሎች ተሰሚነትና ተጽዕኖ ይቀንሳል ብለው ሊያምኑም ይችላሉ። ቢያንስ እነዚህን ታሳቢ በማድረግ ዶላሩም እንዳይደርቅ፣ የሃይል ኣማራጩም መሰረት እንዲጠብ ጥቂት የመድረክና፣ ጥቂት የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎችን በቀጣዩ ፓርላማ ማየት የሚጠበቅ ይሆናል።
እዚህ ላይ በደማቁ ሊሰመርበት የሚገባው ምናልባት 10 ቢበዛ 20 የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች  ፓርላማ ቢገቡ፣ ሌላው ቀርቶ ተቃዋሚዎች ያቀረቧቸው እጩዎች በሙሉ ቢያሸንፉ እንኳን  በስርዓቱ ለተንገሸገሸውና ለውጥን ለተራበው ህዝብም ሆነ ለተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎቹ ትርጉም ያለው ፋይዳ ኣይኖረውም። ከፓርላማ ደሞዝ ያለፈ የሚጨምሩት ምንም ነገር እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
በመንግስት ስራ ላይ የሚገኙ የፓርላማ ተመራጮች የፓርላማ ደሞዝ የማያገኙ በመሆናቸው፣ ደሞዝም የሚቆረጠው ስራ ለሌላቸውና፣ በግል ስራ ላይ ለሚገኙ የፓርላማ ኣባላት ብቻ ሲሆን ሁሉም ተመራጮች  ለኣምስት ኣመት የመንግስት ቤት እንደሚሰጣቸው ግን ይታወቃል። ኣስርና ሃያ ተቃዋሚዎች ፓርላማ ገብተው፣ ተቆንጥሮ በሚሰጣቸው ሰዓት የህዝብ በደልና ብሶት ከማስተጋባት ባሻገር ማናቸውንም ህግ ለማስቆምም ሆነ ለማስቀየር ኣንዳችም ኣቅምና ስልጣን ኣይኖራቸውም። በኣስርና ሃያ የፓርላማ ወንበር ብቻ ሳይሆን፣ ያቀረቡት እጩ ሁሉ ቢያልፉ እንኳን መንግስት መለወጥ ኣለመቻል ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ህግ ከመጽደቅ ማቆም ኣይቻላቸውም። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ በሃገርና በህዝብ ዘንድ ኣብይና ኣንገብጋቢ በሆነ ጉዳይ ላይ ፓርላማው እንዲመክርበት ኣጀንዳ የማስያዝም ስልጣን እንዳይኖራቸውም በህግ በግልጽ ተደንግጓል።
በኢትዮጵያ የፓርላማ ምርጫ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ ቢያንስ 274 የፓርላማ ወንበር ማግኘት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ኣጀንዳ ለማስያዝም ሆነ፣ ኣጀንዳ ለመጣል ይህንኑ ያህል ወንበር ማግኘት የግድ ይላል። በዚህ ምርጫ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ማድረጉ የተመሰከረለትና ከተቃዋሚዎች ውስጥ ከፍተኛ ዕጩ ያቀረበው መድረክ በጠቅላላ ለፓርላማ ያቀረባቸው ተወዳዳሪዎች ብዛት 270 ሲሆን፣ መድረክን በዕጩ ብዛት በሩቅ ርቀት የሚከተለው ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ ያቀረበው ዕጩ ብዛት 139 መሆኑን ከምርጫ ቦርድ ይፋዊ መረጃ  መረዳት  ተችሏል።  በተቃዋሚነት የሚታወቁት ወይም ጎልተው የሚሰሙት እነዚህ በመሆናቸው ከመድረክ ቀጥሎ 165 ዕጩ በማቀረብ የሚከተለውን ኢዴፓን ከኢህኣዲግ ጋር ካለው ቅርበት ኣንጻር በተቃዋሚ ዝርዘር ውስጥ ማካተቱ ኣሰፈላጊ ሆኖ ኣልተገኘም።
 መድረክም ሆነ ሰማያዊ ተኣምር ተፈጥሮ ያቀረቡት ዕጩ ሁሉ ቢያልፉ አንኳን የመንግስት ስልጣን  ለመያዝ የሚያስችል ቁጥር የላቸውም።  በመሆኑም እያንዳንዳቸው የፓርላማ ውስጥ ብዙ ደሞዝ የሚከፈላቸው ኣባላት እንዲኖራቸው ከማድረግ ውጭ በሃገሪቱ ፓለቲካዊም፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ምንም ስልጣንም ሆነ ሃላፊነት ኣይኖራቸውም። በኣጭሩ ለማስቀመጥ ተኣምር ተፈጥሮ መድረክም ሆነ ሰማያዊ ያቀረቡዋቸው ዕጩዎች ሁሉ እንዳለ ቢያሸንፉ እንኳን የሕወሓትን ስልጣን ለመቀነስም ሆነ ለመገደብ እንዲሁም ለማረም የሚያስችል ምንም ህጋዊ ቦታና  ስልጣን እንዳይኖራቸው በህግ ታስረዋል።
የመድረክም ሆነ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ሁሉም ቢያሸንፉ የሚለው ምኞት ምድርን ወደ ባህር፣ ባህርን ወደ ተራራ የመለወጥ ያህል ለምድራዊ ፍጡር የማይቻል ተዓምር መሆኑንም ሳንዘነጋ፣ ጥምር መንግስት ቢፈጥሩስ የሚለው ተረት ወደ መጃጃል ይወስዳልና ጉም መዝገኑን ገታ ኣድርገን ወደሚታየውና ምድር ላይ ወዳለው ወደሚጨበጠው ነገር እንመለስ።
ይህ ደግሞ የሃሳብ ሽሽት እንዳይመስል፣ ኣስፈላጊ ከሆነ ይህንንም ገፋ ኣድርገን ጥቂት እየቃዠን ስለጥምር መንግስት ልናወራም እንችላለን። የሰማያዊና የመድረክ ሁሉም ዕጩዎች  ኣሸነፉ ማለት ግን 270 ሲደመር 139 ኣለመሆኑም በመጀመሪያ ሊሰመርበት ይገባል። በኣንድ ምርጫ ጣቢያ ተደራርበው የሚወዳደሩበት ስፍራ ሲለሚኖር ቁጥሩ እንደሚቀንስ ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል የመድረክና የሰማያዊ የውድድር ሜዳ በኣብዛኛው የተለያየ በመሆኑ፣ የሁለቱ ዕጩዎች ሁሉም ካለፉ፣ በጋራ መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸው ድምጽ እንደሚያገኙ ደግሞ የሚያጠራጥር ኣይሆንም። ሁለቱ ቡድኖች ጥምር መንግስት ፈጥረው በጋራ ሊቆሙ ይችላሉ ወይ የሚለው ጥያቄ በቅድሚያ የሚነሳ ሲሆን፣ የጋራ መንግስት ሁለቱንም ሲለሚጠቅም በዚህ በኩል ብዙ ክፍተት ላይታይ ይችላል። የሁለቱም ፓርቲዎች ሁሉም ተመራጮች ደግሞ በሁለቱ ቡድኖች ፍላጎት ይሄዳሉ ወይ የሚለውም ቸል የማይባል ቢሆንም፣ ሁለቱንም ከጀርባ የሚስብና የሚገፋቸው ሃይል እስከሌለ ጥምር መንግስት የማይመሰርቱበት ምክንያት ኣይኖርም።
ኣሁን  ቅዠቱ ይብቃንና፣ ከደመናው ወርደን መሬት እንርገጥ። ጠመንጃውን የያዙት፣ ጸጥታውን የሚያሽከረክሩት ጄኔራል ሳሞራና ኣቶ ጌታቸው ኣሰፋ፣ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ እንዲሁም በዘረኝነትና በዘረፋ የተቀጣጠለው ሰንሰለት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ከሕወሓት ውጭ የሆነ ቡድን እንኳን ለማየት ለማሰብ ይችላልን?  24 ዓመት የኢትዮጵያን ከፍተኛ ወታደራዊ ሹመትና የጸጥታ ሃላፊነት ይዘው ፣በኣስተሳሰብ ወልደያ መድረስ ያቃታቸው፣ ሁመራን መሻገር የተሳናቸው ከትግራይ ድንበር ውጭ የተፈጠረ ሰው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን ሲይዝ ደማቸውን ኣልፎ ኣጥንታቸውን የበከለው ዘረኝነት ይፈቅድላቸዋልን? ኣቶ ሃይለማሪያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ ፈቅደው የለ እንዴ የሚል የረፈደበት ክርክር የሚያነሱ ካሉ፣ እንደ ህጻን ኣዕምሮ  ንጹህ ለሆነው ህሊናቸው ኣድናቆት ከመስጠት ውጭ የምጨምረው ነገር ቢኖር ፣ የእስረኛው ንጉስ ዙፋን፣ በዙር እንዲደርሳቸው መመኘት ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ ምርጫ ከባድ የሚያደርገው ስልጣን ላይ ያለው የህወሃት ቡድን ከስልጣን ውጭ ራሱን ማሰብ ኣለመቻሉና የኣጼ ዮሃንስን ዙፍን ኣስመሰስኩ በሚል ስካር ውስጥ መውደቁ ጭምር ነው። ይኸው ቡድን ይበልጥ በሃሳበ ድኩማን እየተዋጠና ርስ በርስ እየተፋጠጠ በመገኘቱ ብቻ ሳይሆን ነገን ኣሻግሮ ለማየት ዛሬ ላይ ኣለመድረሳቸውና ትናንት ላይ መቆማቸው ለዘመኑ እንዳይመጥኑ ኣድርጓቸዋል።
ምርጫና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የዶላር ምንጭ በመሆኑ ብቻ በየኣምስት ዓመቱ ስልጣኑን በደም እያደሰ የቀጠለውን ይህንን ቡድን፣ በተኣምር  በምርጫ ማለፍ ቢቻል እንኳን፣ በዘር የተደራጀውን ወታደራዊና የጸጥታ መዋቅር በፕሮግራም ጥልቀት በሃሳብ ምጥቀትና በቃላት ውበት መሻገር ኣይቻልም። ብረትን በብረት እንጂ።
ድንቁርና ተጭኖት፣ የዘረኝነት ኣክሊል ደፍቶ ብረት ነክሶ ብረት የሚያመልከውን ቡድን፣ በሚያመልከው መንገድ ማስተናገድ  ወደ ነጻነት ያደርሰናል ወደ ዕውነተኛ ምርጫም ይወስደናል።
 ኢሳት:-  በሃሳብ መንገድ የቀረበ
Filed in: Amharic