>
5:31 pm - Sunday November 12, 6705

ዘረኝነትና መዘዙ!

”…ግቢያችን የብረት በር ነው። እንድንከፍተው የፈለጉ ሰዎች በሩን ደበደቡት። ታላቅ እህቴ የእናታችንን ትካዜ ለማረሳሳት፤ የኣትክልት ዓይነቶች እያቀራረበች ነበር። እህቴ የበሩን መደብደብ በመስማቱዋ የምትሰራውን ኣቁማ ለመክፈት ሄደች።

”ማነው?” በትህትና ጠየቀች።

”ክፈች!!” ሃይለኛ ቃል ኣምባረቀባት።
”…በዚያ ጊዜ እንዲህ የተገደለ ታድሏል ይባላል። በጥይት በሩ ላይ ጭንቅላቱዋን በርቅሰው ጥሏት። የሰማነው የጥይት ጩኽት፣ መላ ቤታችንን ኣናጋው። በዚያን ጊዜ የነበረንን ስሜት ለመግለጽ ያዳግተኝ ይሆናል። ግማሻችን ተንቀጥቅጠናል፣ ወይም ፈዝዘናል፣ ኣለያም ወደበሩ ሄደናል። ኣራት የሚሆኑ ሚሊሺያዎች መሳሪያና ባንጋ ይዘው ገቡ። ባንጋ ማለት ቆንጨራ ይዘው ገቡ። ሁላችንንም ግቢያችን ውስጥ ኣንድ ቦታ ሰበሰቡን። ኣንበረከኩን። ኣንድ በኣንድ እያነሱ በጥይት ይቆጥሩብን ጀመር። አናቴ ልጆቼን ኣትግደሉ በማለት ስትጮህ በባንጋ ኣንገቱዋን ቆረጡት። ያን ጊዜ ነበር የደመ- ነፍስ መፍጨርጨር የጀመርነው። ቢሆንም ማናቸውም ሊተርፉ ኣልቻሉም። ለምን አግሬን ባባንጋ ቆርጠው፣ ይሄን የግራ ጡቴን ቀድደው፣ ጥለውኝ እንደሄዱ ኣይገባኝም። የዚያች ተወልጄ ያደግሁበት ግቢ ውስጥ፣ እናቴን፣ እህቴን፣ የእህቴ ባልና ልጆቹዋን ባለበቴና ልጆቼ በኣሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው ሬሳቸው ናባራንጎ ወንዝ ተጣለ። ራሴን ሳውቅ ራሴን እንዳጠፋ እንኩዋን ኣልተፈቀደልኝም። ከዚያ በሁዋላማ ለወሬ እኔ ተረፍኩ እንጂ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ከኣፕሪል እስከ ጁላይ 1 ሚሊዮን ቱትሲ የሁቱ ሰለባ ሆነ።”
(ይህን የተረከልኝ የወቅቱ ሰለባ የነበረው ቻርለስ ንኮሮንኮ ነው። ቻርለስ ንኮሮንኮን ያገኘሁት ኬኒያ ነበር። በወቅቱ ይሄኑኑ ቃለ መጠይቅ በሃገር ቤት በሚታተመው ኢትኦጵ መጽሔት ላይ ለህትመት በቅቶኣል። ቅጽ 1 ቁጥር 1. 1991 ዓ/ም።)
”ገንዘብ የምትሰጠኝ ከሆነ በመሳሪያ አገድልሃለሁ”
”…ትልቁና ኣሰቃቂው እልቂት የደረሰው በጸሎት ላይ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳሉ በባንጋና በጥይት ያለቁት ሰላሳ ኣምስት ሺ ቱትሲዎች፣በጥይት የመሞት ዕድሉን ያገኙት፣ ጎረምሳዎቹ አንጂ ኣሮጊት፣ ህጻናት፣ ነፍሰጡሮች ኣቅመ ደካሞች ያለቁት በባንጋ ወይም በሜጫ ነው። በተሳለና በሾለ ባንጋ…ከዚያ በሁውላማ በጥይት ለመሞት ገንዘብ ለሁቱ ሚሊሺያዎች መስጠት ኣለብህ። እነሱም ለመሞት የትኛው እንደሚሻልህ ያስመርጡሃል። ”ገንዘብ የምትሰጠኝ ከሆነ በመሳሪያ አገድልሃለሁ፣ ኣለበለዚያ የምገድልህ (የምትሞተው) በባንጋ ነው እያሉ ስለቱን እያብለጨለጩ ያሳዩሃል። ኣብሮህ የነበረው አጅህ ወይም አግርህ በባንጋ ተቆርጦ ለተወሰነ ደቂቃ የተለየውን ኣካልህን ትመለከተዋለህ። ህይወት ከነፍስህ አስክትለይ። ኣሁን አኔ አከሌ የምለው ዘመድ አንደሌለኝ ሳውቅ የመኖሬ ትርጉም ግራ ያጋባኛል። ከጣት ጣት ይበልጣልና ሁልጊዜ ያንን ኣሰቃቂ ዕለት ሳስታውሰው የእናቴ ኣሟሟት አንደ – ፊልም ትርኢት ህይወት ዘርቶ መጀመሪያው ረድፍ ድቅን ይልብኛል።
”…እስከ ምሽቱ ፫ ሰዓት እህቴም ከባለቤቷና ከልጆቿ፣ እኔም ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር በመሆን እናታችን ጋር እራት የመመገብና ኣብረ የመቆየት ባህል ኣለን።.ኣባቴ በህይወት ባለመኖሩ እናታችን ብቻዋን እንዳትሆን በማሰብ ቤተሰብም መስርተን ኣልራቅናትም። የ ”ቴጎኔስት ባጋሶራ መንግስት” በቱትሲ ጎሳዎች ላይ አያደረሰ የነበረውን ዕልቂት፣ ብናውቅም ስለግል ኑሮኣችን እንጂ በቱትሲነታችን ይደርስብናል የምንለው ስጋት ኣልነበረም። ብናስበው አንኩዋን ከምንኖርበት ኣካባቢ ወደየት አንሄዳለን?…ተወልደን ያደግነው፣ ቤተሰብም የመስረትነው፣ አዚያው ቡታሬ ውስጥ ነው። መጥፎ ነገር ቢከሰት አንኩዋን ከቡታሬ ንቅንቅ የምንል ኣይመስለንም። ለእናታችን ሁለት ነን። እኔና – እህቴ። እህቴም ትዳር ኣላት።ታላቄ- ነች። የኣምስት ልጆች እናት። የመጀመሪያዋ ሴት ልጅዋ የ24 ስትሆን፣ የመጨረሻዋ ደግሞ የ9ኣመት ወንድ ልጅ ነው። እኔም ሶስት ልጆች ነበሩኝ። ኣንድ ሴት፣ ሁለት ወንድ። የመጀመሪያዋ እድሜዋ 17 ሲሆን የመጀመሪያ ዓመት ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበረች። ሁለተኛዋ 13ዓመቷ፣ ሶስተኛዋ ኣስረኛ ዓመቷ።
”…ይህ ቀን ነው እንግዲህ የማልረሳው። እየተወያየን የነበርነው ስለተገደሉ ጎሳዎቻችን ሲሆን ከተገደሉትም ውስጥ ዘመዶቻችን ይገኙበት ነበር። ብቻ ቤታችንን ያለወትሮው የዝምታ ድባብና የሓዘን ጥላ ኣጥልቶበታል።እምቡር – እምቡር የሚሉት ህጻናቶች ኣንዳች የሰሙ ይመስል፣ ኣደብ ገዝተዋል። ያም ቢሆን ኣልፎ-ኣልፎ ድፍ የሚል ተኩስ እንሰማለን።እናታችን ስቃ – የምታስቅ ነበረች፤ በዚህ ቀን ግን ተክዛለች። ብዙ ሆነን ብቻዬን የቀረሁበት ዕለት።

”…የዚህ ሁሉ እልቂት መንስኤው ምን አንደሆነ ታውቃለህ?…ሌላ ኣይደለም። ሩዋንዳ ነጻነቱዋን ያገኘችው እ/ኤ ኣቆጣጠር በ1962 ነው። ከዚያ በፊት በቤልጂየሞች ቅኝ ስንገዛ የኖርን ህዝቦች ነን። ቤልጂየሞች በ1951 ህዝቡን አርስ- በርስ ለማፋጀት አንዲህ ማለት ጀመሩ። ”ቱትሲዎች የመጡት ከኣቢሲኒያ ነው። እነሱን ከዚህ የማስወጣት ስራ የእናንተ ነው” ሲሉ ለሁቱዎች ሰበኩ። በፊት ተግባብቶና -ተጋብቶ የኖረውን ህዝብ ለሁለት የሚከፍለውን ክብሪት ለኮሱ። ሩዋንዳ ነጻነቱዋን ያገኘችው በ፩፱፰፪ ነው። አንደ ኤ.ኣቆጣጠር። ታዲያ በዚህ ኣጭር ጊዜ ውስጥ ሶስት መሪዎች ተለዋውጠውባታል። ሁሉም ሁቱዎች ናቸው።የሚኒስትር ማዕረጎች የእነሱ ቢቻ ነው።ወደታች የወረድክ አንደሆነ ትምህርት፣ ህክምና የማግኘት መብት የጠበበ ነው።የሩዋንዳ መሪዎች ”… የመጣህው ከኣቢሲኒያ ነው ወደ ኣቢሲኒያ ቀጥል ይሉታል። እኛ ከኣቢሲኒያ ለመምጣታችን ምንም ማረጋገጫ የለንም፤ በታሪክም ሆነ በምንም የምናውቀው የለም። ይህንን ስለመባላችንም የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀዋል ብዬ ኣልገምትም። ካቢላ ከመራሹ ቱትሲና ከተቀናቃኙ ጋር በጀመረው ጦርነት የብዙ ኣፍሪካ መሪዎች ለካቢላ ያደርጉትን ተቃውሞና ድጋፍ በዜና ማሰራጫ አከታተል ነበር። የአናንተም መለስ ዜናዊ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባላት ጦርነት ሳቢያ እያካሄደች ባለው ወታደራዊ ሁኔታ የተነሳ፣ ”ሰራዊት ወደ ክንሻሳ መላክ ኣንችልም። በማንኛውም መልክ ድጋፌ ኣይለይዎትም።” ይሄ ነበር የመለስ ዜናዊ መልዕክት ለርስ- በርስ የሁቱና – ቱትሲ ቅራኔና ጭፍጨፋ ወቅት። መለስ ዜናዊ በሁቱና ቱትሲ የዘር ማጥፋት አርምጃ ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኣለበት ባይ ነኝ። ምክንያቱም ቱትሲን ለሚወጋ ሁሉ ያለኝን ሁሉ ለማቅረብ አሞክራለሁ ያለው መለስ ዜናዊ ነበርና።(ካቢላም መለስም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። መለስ ዜናዊ ለኩሶት የሄደው የዘር መርዝ ሃገራችንን አያመሳት ሲሆን፣ ሎሬት ካቢላም ሃገራቸው ዛየርም በዘር በመባላት ላይ ትገኛለች።)
በሃገራችን በወያኔ ስርዓት የተዘራው የዘር መርዝ፣ ለስርዓቱና ለባንዳዎች…ለጊዜና ለስልጣን ማቆያ ይበጅ ካልሆነ፤ ለቀሪው ህብረተሰብ ጠቀሜታ የለውምና ዘርን ለሰው ሳይሆን፤ ለጥራጥሬ መጠቀሙ ተገቢ መሆኑን መጠቆሙን ኣንዘነጋውም። ”ውሃ ቢወቅጡት አምቦጭ..” አየሆነብን አንጂ። በኣንጻሩም፤ቻርለስ የተረከልን ቁስል ዘረኝነት ያመጣው መዘዝ ነው። ዘረኝነት ክፉ ደዌ በመሆኑ፣ በደዌው የተለከፉ እንዲምራቸው ደጋግመን የነቻርለስ ንኮሮንኮን ኣስከፊ ትዝታ፥ ማስነበብ ግድ ይለናል። ዘር ያመጣው ጣጣ ነውና።ዘረኝነት የሚያመጣውን መዘዝ በተገቢው ማስተዋል፤ ሜጫ ከመሳል ያድናልና!!

 

 

 

Filed in: Amharic