>

ሠርገኛ መጥቶም በርበሬ ቀንጣሽ ጠፋ [ህይወት እምሻው]

Hiwot Emishaw(በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች በሙሉ የተወሰዱት ከዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ‹‹ሰሚ ያጡ ድምፆች›› መፅሀፍ ነው፡፡ )

—————————
ስንቱ መከረኛ ወገኔ ዛሬም ፤

‹‹አዬ ክፉ ዘመን ይቅር አይነሳ፣
አርጉዝ ላሜን ሸጥኳት- ለሁለት ቀን ምሳ›› እያለ አጣዳፊ አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ሲገልፅ፤

‹‹ድርቁን ረሃብ ከመሆኑ በፊት ተቆጣጥረነዋል!››

‹‹የውጪ እርዳታ አንፈልግም!›› ሲባል ተከርሞ፤ በዚህ ሳምንት ከወራት በፊት በጓሮ በር ቤተመንግስት ይመላለሱ የነበሩት የእነ እንትና እርዳታ ድርጅት ተወካዮች መቼ እለት በይፋ በቴሌቪዥን ታዩ፡፡

ይሄን ባየሁ ጊዜ ፤ ‹‹ከወራት በኋላ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ድርቅ ከቁጥጥር አመለጠ እንዴ?››

‹‹ረሃብ ሆነ እንዴ?››

‹‹በድንገት የውጪ እርዳታ አስፈለገን እንዴ›› ብዬ አሰብኩ፡፡

ለነገሩ ይሄም ከመሆኑ በፊት እርዳታ እንዲያመጣም ፣ የፖለቲካ ኪሳራ እንዳያመጣም የታሰበበት የሚመስለው የቀይ መስቀል የእርዳታ ጥሪ ግራ ሲያጋባኝ ነበር፡፡

ቀይ መስቀል እርዳታ ለሚገባቸው እርዳታ በመጠየቅ እና የፖለቲካ ስሌቱን ባለማዛባት መካከል ተሰንጎ የፃፈው የ‹‹ወገን ለወገን›› ጥሪ ሲያስገርመኝ ነበር፡፡

‹‹በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ›› የምትለዋ ቃል በቀይ መስቀል ሳይሆን በባለ ቀይ እስኪብርቶ አራሚዎች የገባች ፖለቲካዊ አረፍተ ነገር ስለምትመስለኝ ታስደምመኝ ነበር፡፡

መቼም ‹‹አንዳንድ›› የምትለዋን ቃል ታሪካዊ ምንጭ የሚውቁ ሰዎች በዚህ ሃሳቤ አይወቅሱኝም፡፡

የሆነው ሆኖ፤ ነገሩ ሁሉ እንዲህ በፖለቲካ ባልዲ ውስጥ ሲቦካ ያ መከረኛ ህዝብ ግን በረሃብ ይሰቃያል፡፡

ኮሚቴው እነ እንትናን በማያስበላ አኳሃን ማንን ምን ብሎ እርዳታ እንደሚጠይቅ ሲያሰላ፣ ይሄ ዛሬም ቀን ያልወጣለት ህዝብ መከራውን ይቆጥራል፡፡

ነጥቡ ይሄ ነው፡፡

መንግስት ማጣፊያው አጥሮት እግሩን ሲለብስ ጭንቅላቱን እየበረደው፣ ጭንቅላቱን ሲለብስ እግሩን እየበረደው ‹‹ገመና›› ለመሸፈን ሲገዳደር ፤ ያ አይለፍልህ ያለው ህዝብ በረሃብ ይቆላል፡፡

ለነገሩ ጥንቱንም የኮሚቴን ስራ የሚያውቀው ረሃብተኛ ህዝብ ለዚህ ነው እንዲህ ብሎ የገጠመው፡፡

‹‹አስራ አምሰት ኮሚቴ ቢያናፋ ቢያናፋ፣
በሰማይ ደመና በምድር ዝናብ ጠፋ›› ፡፡

ለዚህ ነው የምድር ላይ አስተዳዳሪው ‹‹በድርቅ እና በረሃብ መካከል ያለው የትርጉም ልዩነት›‹ በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ሲጠመድ፤ ዘንድሮም ለጠኔ የተማገደው ህዝብ ሰማይን አንጋጦ እያየ፣ የሰማይ አስተዳዳሪውን ‹‹ደመናውን ዝናብ አርግልኝ›› ብሎ የተማፀነው፡፡

እየተማፀነም እንደዚህች አይነቷን አንጀት የምታላውስ ግጥም የገጠመው፡፡

‹‹ እርሻ በደመና ይመረት በነበር፣
ይሄን ክፉ ዘመን እሻገረው ነበር››፡፡

ለዚህም ነው ፤ ፉርሽ በሆነ ‹‹ራሳችንን ችለናል፤ የተራቡብንን ለመመገብ የውጪ እርዳታ አንፈልግም›› በሚል ሀተታ መሃከል፤ ‹‹የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ›› አስተዳዳሪውን ለይቶ የሚያውቀው ረሃብተኛ ህዝብ እንዲህ ብሎ የገጠመው፡፡

‹‹ እናቴን ጠላኋት፣ እህቴን ጠላኋት፣
ፈረንጇን ብቻ ነው- ዛሬስ የወደድኳት›.፡፡

‹‹በአሜሪካን ስንዴ በፈረንጇ ክክ፣
አሸጋግረውናል ከአመት እስከ አመት››፡፡

…ሲሆን ሲሆን፤ እንደሚነገረን ከሆነ፣ ሩብ ምእተ አመት፤

ባይጠግብ እንኳን፣
ባያማርጥ እንኳን፣
ሶስቴ ባይሆን እንኳን፣
አንዴ በልቶ የሚያድር ህዝብ ለመፍጠር በቂ ጊዜ ነበር፡፡

እሺ ያም አልሆነም፡፡

ቀድሞ መዘጋጀቱ ቀርቶ፣ ሰርገኛ መጥቶም በርበሬ ቀንጣሽ አልተገኘም፡፡

ቢያንስ ፤ የተቸገረ ሳይዘገይ አንዲረዳ፣

የተራበ ሳይረፍድ አንዲበላ፣

የፖለቲካ ስሌቱን ለጊዜው ተወት አድርጎ በይፋ፤ ‹‹ዛሬም ህዝባችን ተርቧል፡፡ ዛሬም ህዝባችንን መመገብ አልቻልንም፡፡ መግቡልን›› ማለት ማንን ገደለ!?

Ethiopian droughts

Filed in: Amharic