>

የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ወያኔ ብቻ ወይስ የውጭ ኃይሎችም ጭምር ? [ፈቃዱ በቀለ ፤ ዶ/ር]

መግቢያ 

dr-fekadu-bekeleይህንን ጥያቄ አንድ ስሙን ልጠቅሰው የማልፈልገው ምሁር በኢሜይል ለብዙ ጓደኞቹ በጥያቄ መልክ ሲያስተላልፍ ለእኔም ስላስተላለፈልኝ ይህንን በሚመለከት ቀደም ብዬ በትንተና መልክ ያቀረብኩ ቢሆንም እንደገና ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ይህችን አጭር ትንተና ለመስጠት ቃጣሁ።

በወያኔና በወጭ ኃይሎች፣ በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮቹ መሀከል ያለውን የእከክልኝ ልከክልህ ግኑኝነት በሚመለከት ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነትና፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቅ ጠበቃ ቆሜያለሁ ብሎ ድምጹን እዚህና እዚያ በሚያሰማው ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ኢትዮጵያዊና፣ በተለይም ምሁር ነኝ በሚለው ዘንድ የተምታታ አቋም አለ። በፕሮፌሽናል ደረጃ ሳይሆን በትርፍ ጊዜውና ደስ ሲለው የሚጮኸውን ሰፊውን ተቃዋሚ ነኝ የሚለውን ኢትዮጵያዊ ትተን ምሁር ነኝ ወደ ሚለውና ካለኔ በሰተቀር የኢትዮጵያ ህዝብ ጠበቃ የለም  ብሎ ድምጹን የሚያሰማውንና በአብዛኛው የዋሁ ኢትዮጵያዊ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘውን በአጠቃላይ ኤሊት ነኝ የሚባለውን አቋም በምንመረምርበት ጊዜ በጣም የተምታታና ከሳይንስና ከሎጂክ ጋር የማይጣጣም ሀታታ እናነባለን። በዚህ ተቀባይነትን ባገኘው ግን ደግሞ ከሳይንስና ከሎጂክ ጋር እንዲሁም ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለውን አስተሳሰብ ስንመረምር፣ ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠበቃ ባይ ነኝ በሚለው በኤሊቱ ዘንድ የወያኔ አገዛዝ በአለፉ 25 ዓመታት በአገራችን ምድር የሚያካሂደው የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ፣ አንድን ህዝብ በብሔረ-ሰብ ከልሎ ጠቅላላው ህዝብ የመንፈስ አንድነት እንዳይኖረው ማድረግና፣ እየተፈራራና እየተጠራጠረ እንዲኖር ማድረግ፣ የአንድን አገር የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል ስርዓት ባለው መልክና በሳይንሳዊ ዘዴ ቀስ በቀስ ተግባራዊ ለማድረግ የማያስችለውን፣ በአጠቃላይ አነጋገር የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል የሚታወቀውን ተግባራዊ ማድረግና፣ አንድን አገር በጠንካራ መሰረት ላይ እንዳትገነባ ማድረግ፣ በተጨማሪም ከውስጥም ሆነ በአካባቢው አገሮች መረጋጋት እንዳይኖር አሸባሪዎችን መዋጋት ነው የዘመኑ ዋና ፖለቲካ ብሎ አገዛዙ በእዚህ ላይ አትኩሮ እንዲያደርግ አስፈላጊ በሆኑ የጦርና የስለላ መሳሪያዎች ማስታጠቅና ማስልጠን፣ እነዚህና ሌሎች አገራችንን ከፍተኛ አደጋ ላይ የጣሏት ነገሮች በሙሉ አገዛዙ ብቻውን እንደሚያደርግ ተደርጎ ነው የሚቀርበው። በአንዳንዶች ድርጅቶችና ምሁሮች አነጋገር የውጭ ኃይሎች ለወያኔ ዕርዳታ የሚሰጡት በጣም ስለሚያፈቅሩትና ስለሚሳሱለት እንጂ ህዝባችንና አገራችንን ለመጉዳትና ለመበታተን አይደለም የሚል ነው። እንዲያውም አንዳንዶች ለማሳመን እንደሚሞክሩት የውጭ ኃይሎች አገራችን እንዳትበታተንና እንደ ዩጎዝላቪያ እንዳትሆን ስጋት አለባቸው ይሉናል። በዚህ ዐይነቱ የጨዋዎች ትንተና እኛንና ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳመን የሚሞክሩት ደግሞ ከዚህ ቀደም በፀረ-ኢምፔሪያሊስትነት የማይታወቀውና ኢትዮጵያ ዛሬ ላለችበት ደረጃ እንድትደረስ አምርሮ ይታገል የነበረው ኢትዮጵያዊ ቢሮክራሲያዊና የቴክኖክራት  ኃይል ብቻ ሳይሆን አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ዋና ጠላት ፊዩዳላዊው ስርዓት ብቻ ሳይሆን ኢምፔሪያሊዝም፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነው ብሎ የትግል አርማ አንስቶ ይታገል የነበረው ኃይል ነው።

ይህ ዐይነቱ የተምታታ ሁኔታና የሃሳብ ጥራት አለመኖር አገራችንን ዛሬ አፍኖ ከያዛት የወያኔ አገዛዝና ፀረ-ዕድገትና ፀረ-ስልጣኔ ፖሊሲው አላቆ የተረጋጋችና ሰላም የሰፈነባት፣ እንዲሁም ህዝቦቿ በሳይንስና በጥበብ እየተመሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ፣ ጠንካራ ህብረተሰብና ለፈጠራና ለትችት የሚያመችት አገር ገንበተው እንደ አንድ ህዝብ ሊኖሩ እንዳይችሉ እንቅፋት የሚሆን አደገኛ አካሄድና አጉል የሪያል ፖለቲካ(Real Politics) ስሌት ነው። እንደሚታወቀው በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሰሉ በብዙ የተወሳሰቡ ችግሩች የተወጠሩ አገሮች እንደዚህ ዐይነቱን የተምታታና ሳይንሳይዊ መሰረት የሌለው ፖለቲካ በመከተል አይደለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ በመገንባት እንደ አንድ ህዝብ ሊተሳሰሩና ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በማስወገድ በውጭው ዓለም ደግሞ ተከብረው ለመኖር የበቁት።

ስለዚህም ይህንን ዐይነቱን እጅግ አደገኛ አቋምና የድህነቱን ዘመን በማራዘም መበታተናችንን የሚያፋጥነውን አጉል ፖለቲካ፣ ግን ደግሞ ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር የማይገናኘውን አቋምና ትንተና የግዴታ መጋፈጠና ማጋለጥ ያስፈልጋል። አንዳንድ ድርጅቶችና ምሁር ነን ባዮች ሁሉንም ነገር ከህዝብ ዕውነተኛ ነፃነትና ብልጽግና ጋር ሳይሆን ከራሳቸው ውስጣዊ ፍላጎትና ስልጣን ላይ ወጥቶ ከመታወቅ ጋር ስለሚያገናኙት ይህ አጉል የፖለቲካ ቫይረስ ተባዝቶ ሰፊውን ወጣት ትውልድ ከማዳረሱና የትግሉን አቅጣጫ ከማዛነፉ በፊት በተቻለ መጠን በሳይንስና በሎጂኩ መንገድ መታገሉ የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በእንደዚህ ዐይነቱ ጥራትነት በሌለው መንገድ ነው ህዝባችን እስከዛሬ ድረስ የሚሰቃየውና በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣት ልጆቹ የሚገደሉትና አገርን ጥለው በመሄድ በየበረሃዉ ህይወታቸውን እንዲያጡ የሚደረገው። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱን አዘናጊና ፀረ-ሳይንስ የትግል ፈሊጥ መጋፈጡና ማጋለጡ የታሪክና የባህል ግዴታ ነው። አንድ ህዝብና አገር በመቅለስለስና በፍርሃት፣ እንዲሁም በዩልኝታ ዕውነተኛ ነፃነትን የተቀዳጀበት ጊዜ የለም። የካፒታሊስት አገሮች እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከውስጥ ሆነው እንደነቀዝ የሚበሏቸውን ዕድገትን የሚቀናቀኑ ኃይሎችን በሳይንሱ ዘዴ በመታገል ነው ወደ ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚና ህብረተሰብ መገንባት የቻሉት። በተጨማሪም የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት፣ የዛሬዋ ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይና እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት በቆራጥነትና በአገር ወዳድ ስሜት በመነሳት እንጂ ከሌሎች አገሮች ፈቃድ በመጠየቅና በመለማመጥ አይደለም።

አንዳንድ ትዝታዎች ከታሪክ ማህደር !

የድሮ ታጋዮች ዛሬ የሚያፍሩበትና፣ በአንድ ወቅት ደግሞ ከግራም የበለጠ ግራ በመሆን ደረታቸው ላይ የማጭድና የመዶሻ አርማ ካነቴራ ለብሰው የሚሄዱ እኛ ገና የፖለቲካን ሀሁ ባልሰማንበት ዘመን፣ ፊዩዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኤምፔሪያሊዝም እንዲሁም የብሔረሰብ ምናምን የሚባሉትን ነገሮች ምን እንደሆኑ በማናውቅበት ጊዜ-  ካለምንም ውሽት  እነዚህን ጽንሰ-ሃሳቦች በሙሉ የሰማሁትና የኋላ ኋላ ጉጉት አድሮብኝ በጥብቅ ለመከታተል የቻልኩት አውሮፓ ከመጣሁና ጥቂት ዐመታት ካሳለፍኩኝ በኋላ ነው-  ያስተጋቡ የነበረው እነዚህ ሶስት ጠላቶች የኢትዮጵያ ህዝብ የዕድገት ዋና ጠላቶች ወይንም የጭቆናና የኋላ-ቀር ዋናዎቹ ምክንያቶች ናቸው የሚል ነበር። በመሰረቱ በጊዜው በተማሪው እንቅስቃሴ የተነሱት ጥያቄዎች በዘመኑ በዓለም አቀፈ ደረጃ የሚናፈሰው ነፋስ አካልና ተፅዕኖም በመሆናቸው የኋላ ኋላ ምርምር ለማድረግ ዕድል ላጋጠመን ግለሰቦች የእነዚህ ጽንሰ-ሃሳቦች አነሳስና የፖለቲካ መታገያ መሳሪያዎች ሆነው መቅረባቸው ትክክል አይደሉም ብሎ መናገር በጣም ስህተት ነው። ምክንያቱም በጊዜው በአገራችን ምድር በገሃድ ይታዩ የነበሩት እንደ ድህነት የመሳሰሉትና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ኋላ-ቀርነትና ከዚህ ጋር ተያይዞ አገራችን በረሃብ መታወቋና ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ህይወቱን እንዲያጣ መደረጉ እነዚህ ነገሮች ሊያያዙ የሚችሉት ከስርዓቱ ጋር ብቻ ነው። እንደሚታወቀው አንድ ነገር ካለአንድ ምክንያት በፍጹም ሊከሰት አይችልም። ስለዚህም በጊዜው በግልጽ ይታዩ የነበሩት የኋላ-ቀርነት ምልክቶች በሙሉ የስርዓቱ ገጽታዎች እንደሆኑ ከአገራችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ እዚህ አውሮፓ መጥተን ከአውሮፓው የፊዩዳል ዘመን ስርዓትና የአሪስቶክራሲው መደብና የካቶሊክ ሃይማኖት ጭፍን ዕምነትና አገዛዝ ጋር ከአወዳደርንና፣ በ16ኛው ክፍለ-ዘመን በአንዳንድ የተገለጸላቸው ቀሳውስት ከገበሬው ጋር በመተባበር የሚያደርጉትን ትግል ስናጠና በጊዜው በአገራችን ምድር በተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች የተነሱት ጥያቄዎችና በአገራችን ምድር ለተከሰቱት ችግሮች ተጠያቂዎቹ እነማን እንደሆኑ መነሳቱና፣ በዚህም ዙሪያ ጥናትና ትግል መካሄዱ ትክክል አይደለም የሚል ወይም ይህ ዐይነቱ አካሄድ የዕብዶች የትግል ዘዴ ነው የሚል ካለ ባለፉት ሁለት ሺህ ዐመታት ዘመናዊነትን ለማምጣትና የአንድን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻል የተደረገውን ምሁራዊ ትግል አይ ለማንቋሸሽ የሚፈልግ፣ አሊያም ያልገባው፣ ወይም ደግሞ የአንድ ህዝብ ዕጣ በድሮው መልኩ መቀጠል አለበት፣ አንድ ህዝብ ዕድገትና መሻሻል አያስፈልገውም ብሎ የኋላ-ቀርነት ጠበቃ ሆኖ ለመታገል የሚፈልግ ብቻ ነው። ስለሆነም በእኔ ዕምነት በማያጠራጥር መልኩ አፄ ኃይለስላሴና አገዛዛቸው የኋላ-ቀርነት ቁንጮና ዋናው አራማጅ በመሆናቸው የግዴታ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከግብረአበሮቹ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ግኑኝነት ነበራቸው። በመሰረቱ የአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ነፃነት የሚጠብቅና ጠበቃ  ሳይሆን- በማወቅም ሆነ ባለማወቅ- የውጭ ኃይሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነበር። ስለሆነም አገራችንን እንደ አገር ሊያሰጠራትና ህዝባችንንም እንደ ሰው ተከብሮ እንዲኖር የሚያስችለውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ለመከተል አልቻለም። ውብ ውብ ከተማዎችንና መንደሮችን በመገንባትና የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎቶች በሟሟላት ህዝባችን አገሩን አገሬ ነው ብሎ እንዲጠራና እንዲኮራባት ማድረግ አልቻለም።

አብዛኛው ተቃዋሚ ነኝ የሚለውና በጥሩ የሶይሶሎጂ ትምህርት ያልሰለጠነና የካፒታሊዝምን ዕድገት በየደረጃው ያላጠና፣ ይህንን ከእኛ አገር የኋላ-ቀርነት ሁኔታ ጋር ለማወዳደር ዕድል ያላገኘው፣ ወይም በስንፍና ምክንያት የተነሳ በጥብቅ ጠለቅ ብሎ ለማጥናትና ለማወዳደር ለማይፈልግ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሶስት መሰረታዊ ጽንሰ-ሃሳቦች፣ ፊዩዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም እንዴት ለዕድገት እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ? ብሎ ይጠይቅ ይሆናል።  ፀሐዩ ንጉሳችን እየተባሉ የሚሞገሱትና ኢትዮጵያን ከዘመናዊነት ጋር አስተዋውቀዋታል ተብለው የሚታሙት አፄ ኃይለስላሴስ እንዴት ዕድገትን ይጠላሉ ወይም የዕድገት እንቅፋት ሊሆኑ ቻሉ ? ብሎም ሊጠይቅ ይችል ይሆናል። በዚህች አጭር ጽሁፍ ውስጥ ነገሩን በዝርዝር ለማስረዳት ባይቻልም እንኳ ማንኛውም ሰው እንዲገባው ቀለል ባለ መልክ ለማሳየት እሞክራለሁ።

በመሰረቱ ፊዩዳሊዝም የሚለው ስርዓት  ሰፋፊ መሬትን በሚቆጣጠሩ የመሬት ባላባቶች በአንድ በኩልና በሌላ ወገን ደግሞ  ጭሰኛ በመሆን ካመረተው ምርት አብዛኛውን ለባላባቱ በመስጠት ራሱ የምርቱ ባለቤት እንዳይሆን የተደነገገበት መግለጫ ነው። ባጭሩ ፊዩዳሊዝም ማለት መሬትንና ሌሎች ለማምረት የሚያገለግሉ የማምረቻ መሳሪያዎችን በሚቆጣጠሩና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በማረስና በመገበር የሚኖር ጭሰኛ የሚባል የህብረተሰብ ክፍል የሚገለጽ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ ግኑኘነት የፖለቲካ አወቃቀርንና የኃይል አሰላለፍን እንዲሁም የህብረተሰቡን አስተሳሰብንም ያጠቃልላል። እንደሁኔታው ጭሰኛው ሙሉ በሙሉ የገበሬው ታዛዥ በመሆን ለማድረግ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ በመጀመሪያ ከባላባቱ መደብ ፈቃድ ማግኘት ያለበት ነፃነትን የሚገፍ ስርዓት ነው። ይህ ዐይነቱ ጠበቅ ያለ ስርዓት በአውሮፓ ውስጥ የተለመደ ሲሆን በአገራችን ምድር ግን በባላባቱ መደብና በጭሰኛው መሀከል የነበረው ግኑኝነት የላላ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በባላባቱና በገባሩ የህብረተሰብ ክፍል ብዝበዛን አስመልክቶ የሚካሄድ ወደ ጦርነት የሚያመራ ግጭት አልነበረም። የስርዓቱን የዕድገት ጠንቅነትና የሰፊውን ህዝብ አስተሳሰብ አቆርቋዥነት ሊያሳይና ሊያስተምር የሚችል የህብረተሰብ ክፍልም ባለመኖሩ ስርዓቱ እንደተፈጥሮአዊና፣ ሊለወጥና ሊሻሻል የማይችል ሆኖ የታመነበት ስርዓት ነው።  ከዚህም በላይ መሬትን የሚቆጣጠሩና የገበሬውን የእርሻ ውጤት አብዛኛውን የሚጋሩት የመሬታቸውን ምርታማነት ለማሳደግና የገበሬውን አድካሚ ስራ ለማቃለል የሚወስዱት ምንም ዐይነት እርምጃ ስላልነበረ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ መሻሻል በፍጹም አይታይም ነበር። ራሳቸው ባላባቶችም የፍጆታ አጠቃቀማቸውና አኗኗራቸው በጣም ውስን በመሆኑ ለካፒታሊዝም ዕድገት እንቅፋት ነበሩ ማለት ይቻላል። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት በንግድና በዕደ-ጥበብ የሚገለጽ የምርት ግኑኝነትና  እንቅስቃሴ ስላለነበረ የባላባቱ መደብ በራሱ ተነሳሽነት ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም።  በዚህ መልክ የጠቅላላው አገሪቱ ሁኔታ እዚያው በዚያው የሚንደፋደፍና ውስጣዊ-ኃይል በማግኘት ወደ ተሻለ የአመራረትና የአኗኗር ሁኔታ ለመሸጋገር ያልቻለ ነበር። በዚህ ላይ የንጉሳዊ አገዛዝና በላይነት እንደ ዕምነት በመወሰዱ አገዛዙን መቃወም እንደ ትልቅ ወንጀል የሚቆጠር ነበር። „ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ“ የሚባለው አባባል የንጉሳዊ አገዛዝን ፍጹማዊነት ለማሳየት የሚሰበክና በህዝቡ ጭንቅላት ውስጥ እንደ ዕምነት እንዲያዝ የሚደረግ ቅስቀሳ ነበር። በአጭሩ የፊዩዳሉ ስርዓትና የንጉሳዊ አገዛዝ የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ዕድገት ህጎች የሚቀናቀኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጠንቆች ነበሩ ብሎ መናገር ይቻላል። ድርጊታቸውም በከተማና በመንደር ግንባታዎች የሚገለጹ ሳይሆኑ በቀጨጨ የአኗኗር ዘዴ የሚገለጹና የሰፊውን ህዝብ አስተሳሰብ አፍነው የያዙ በመሆናቸው ለአገሪቱ ሁለ-ገብ ዕድገት ምንም ዐይነት ለውጥ ሊያመጡ አልቻሉም። ይህ ዐይነቱ ባህል አንድ ሰው ፍላጎቱንና ምኞቱን እንዳይገልጽ የሚያደርግ፣ ጥያቄ ለማቅረብ ዕድል የማይሰጥ፣ አስተሳሰብን ውስን በማድረግ አንድ ሰው ተፈጥሮ የለገሰችውን ልዩ ልዩ የጭንቅላት ባህርዮች በመጠቀምና ራሱን በማግኘት አዲስ አስተሳሰብ በማዳበርና አዲስ ነገር በመፍጠር ህይወቱን እንዲያሻሻል ዕድል የማይሰጥ፣ በረቀቀ መልክ በመመራመር የተፈጥሮን ውበት በመቃኝትና ተፈጥሮን በመኮረጅ ከአንድ የኑሮ ደረጃ ወደ ተሻለ እንዲሸጋገር የማያደርግ ጭንቅላትን ቆልፎ የሚይዝ ስርዓት ነበር። በቴክኖሎጂ ዕድገት የሚገለጽ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት ባለመኖሩ ግለሰብአዊ ድርጊትና ነፃነት፣ እንዲሁም ትችትን መሰንዘርና መቀበል የተለመደ አልነበረም። ስለሆነም ለአዲስ ሃሳብ ጭንቅላትን ክፍት ለማድረግ አለመቻል፣ ችክ ብሎ ማምረርና ወዲያው ማኩረፍ፣ ልዩነትን በውይይትና በክርክር ለመፍታት አለመቻል፣ ቶሎ ብሎ ወደ ጠብ ማምራትና አልበገርም ማለት… ወዘተ.፣ የስርዓቱ መግለጫዎች ናቸው። ይህ ዐይነቱ ባህርያችን እስካሁንም ድረስ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን የሚንጸባረቅ ሲሆን በተወሰነ ሃሳብ ዙሪያ ተሰባስበን በጋራ ለአንድ ዓላማ እንዳንሰራ እንቅፋት የሆነ ከፊዩዳሉ ባህል የወረስነውና እስከዛሬ ድረስ የሚከታተለን መጥፎ ባህል ነው። ስለሆነም ይህ ስርዓት የዕድገትና የስልጣኔ ፀር ነው መባሉ ትክክል ነበር።

ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም በጥብቅ የተያያዙና፣ ዘመናዊ የሚባለው ቢሮክራሲም ከኢምፔሪያሊዝም ወደ አገራችን መግባት ጋር ብቅ ሊል የቻለ የዕድገት እንቅፋት እንደሆነ ማየቱ ዛሬ ላለብን የአስተሳሰብ ችግር መነሻ ሊሆነን ይችላል። በመጀመሪያ ደረጃ ማንኛውም ሰው ሊገነዘበው የሚገባው ነገር አለ። አንድ ጽንሰ-ሃሳብ ዝም ብሎ የሚሰጥ ወይም አንዳንድ ሰዎች የተዘበራረቀ አስተሳሰብ ስላላቸው ዝም ብለው የሚወረውሩት ቃል ሳይሆን የአንድ ነገር መግለጫ ስለሆነ ነው። አንድን ነገር በስሙ የምንጠራው የተሰጠው ስም የነገሩን ምንነትና ተግባሩን እንዲሁም አመጣጡን ስለሚገልጽ ብቻ ነው። ለምሳሌ ጠረቤዛን ጠረቤዛ ብለን የምንጠራው አንድ የተወሰነ ተቅዋም ስላለውና ምግብ የምንበላበት ወይም ለመጻፍ ስለሚያመቸን ነው። በተጨማሪም ከዚህ ፍጆታዊ ጠቀሜታ ባሻገር እንደ ጠረቤዛው አሰራር ለቤታችን ውበት ወይም መልክ ይሰጠዋል። ይህም ማለት በህሊናችን ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው። ስለዚህም ጠረቤዛን ጠረቤዛ ብለን እንጠራዋለን። ወደ ኢምፔሪያሊዝም የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ስንመጣም በአበዱ ሰዎች የተሰጠ ሳይሆን ከፍተኛ ዕውቀት ባላቸው ሰዎች  የተሰጠ ብዙ ነገሮችን በማጠቃለል የሚገለጽ ነው። በመሰረቱ ጽንሰ-ሃሳቡ አሉታዊ ሚና ያለው ነው።፡ኢምፔሪያሊዝም የሚባለው ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የሚታወቅ ጽንሰ-ሃሳብ ቢሆንም ትርጉሙ አንድ አገር በሌላ ደካማ ላይ የሚያደርገው ጣልቃ-ገብነትና ወረራ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ሆብሶንና ሌኒን ያዳበሩት የኢምፔሪያሊዝም ጽንሰ-ሃሳብ  ደግሞ በቀጥታ ከካፒታሊዝም ዕድገት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የካፒታሊዝም የመጨረሻው የዕድገት መግለጫ ነው። ጽንሰ-ሃሳቡ በወረራ ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በዓለም-አቀፍ ደረጃ ከምርት ክንዋኔና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መያዝ ጋር፣ እንዲሁም ከፋይናንስ ካፒታሊዝም ዕድገት ጋር መቆላለፍ የሚገለጽ ነው። በተጨማሪም በታወቁት የይሁዲዋ ፈላስፋ ወይዘሮ ሃና አሬንድት አገላለጽ ኢምፔሪያሊዝም ለመስፋፋት ብሎ የሚስፋፋ በቀጥታ ከካፒታሊዝም የምርት ክንውን፣ የሸቀጥ ማራገፍ፣ የጥሬ-ሀብት ፍለጋና ሀብትን ለመዝረፍ የሚያመች የመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ጋር የተያያዘ ሂደት የሚገለጽ ሲሆን፣ በሳቸው አባባል ኢምፔሪያሊዝም የአምባገነን አገዛዝ ወይም ቶታሊታሪያን ዋናው ምንጭ እንደሆነ በደንብ ያብራራሉ። ለምሳሌ ፋሺዝም የካፒታሊዝምና የኢምፔሪያሊዝም ውጤት ሲሆን፣ በሌሎች ቀድሞ በነበሩ ቅድመ-የካፒታሊስት ስርዓቶች ውስጥ ሊወለድ በፍጹም አይችልም።  ይህ ዐይነቱ ስርዓት በተለይም ከሚሊታሪው የኢንዱስትሪ ውስብስብ(Military Industrial Complex) የምርት ክንዋኔ ጋር በመቆላለፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመስፋፋት ዕድገትንና ዲሞክራሲን አጋዥ ሳይሆን አፋኝና ህብረተሰቦችን የሚያዘበራርቅ ነው። ዋናው ዓላማው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሬ-ሀብትን በመቆጣጠርና ወደ ካፒታሊስት አገሮች በቀጥታ እንዲመጡ በማድረግ የተወሳሰበና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የሀብት ክምችት(Capital Accumulation) በጥሬ-ሀብት አምራች አገሮች ውስጥ እንዳይዳብርና ጠንካራ ህብረተሰብ እንዳይመሰርቱ የሚያግድ ነው። ይህ ዐይነቱ በቀጥታ በመዋዕለ-ነዋይ(Direct Investment) ሂደት የሚገለጽ ሲሆን ከመሬቱ ውስጥ የሚወጣው የጥሬ-ሀብት ወደ ውጭ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን ጥሬ-ሀብቱ በሚወጣበት አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የማህበራዊና የአካባቢ ቀውስ ይፈጠራል። በተለይም ጠንካራ ኢንስቲቱሽንና የወዝ አደር የሙያ ማህበርና መንግስታዊ ንቃተ-ህሊና በሌለበት በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎች እንደልባቸው ሀብትን በመዝረፍና መንግስታትን በማባለግ ከፍተኛ የሆነ ባህላዊ፣ ማህበራዊና የአካባቢ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ስለሆነም የዘመኑ ኢምፔሪያሊዝም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በሚሊተሪ፣ በርዕዮተ-ዓለምና በባህል ወረራ የሚገለጽ እጅግ የረቀቀና የተስተካከለ ዕድገትን፣ ነፃነትንና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚቀናቀንና እንዳይፈጠሩም አጥብቆ የሚዋጋ ነው። የካፒታሊስት አገሮች መንግስታትም በዚህ ዐይነቱ ዓለም አቀፋዊ የሀብት ክምችት ገለልተኛ ሆነው እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡ ሳይሆኑ የጥሬ-ሀብት አምራች አገሮችን በተለያዩ የንግድና የኢንቬስትሜንት ስምምነቶች በማሰር ሁኔታዎችን የሚያመቻቹና  በእነዚህ አገሮች ውስጥ ጤናማ ማህበረሰብና ህብረተሰብ እንዳይገነባ የሚያደርጉ ናቸው። በካፒታሊስት አገሮች የተለያዩ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ ይህንን ወይንም ያንን ስም የያዙ በምርጫ ጊዜ አሸነፍው ስልጣን ሲረከቡ ሶሻል ዴሞክራቲክ ወይም ሶሻሊስት ፓርቲ ነኝ የሚለው ከዚህ በፊት ስልጣንን ይዞ ይገዛ የነበረውን ፓርቲ በተለይም የውጭ ፖለቲካውን ገልብጦ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ የሆነ የውጭ ፖለቲካ በፍጹም አያካሄድም። በውስጥ ያለውም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የኃይል አሰላለፍ አንድ ፓርቲ እንደፈለገ የካፒታሊስቶችን ጥቅም የሚጻረር የውጭም ሆነ የውስጥ ፖለቲካ እንዲከተል አይፈቅድለትም። ከዚህ ባሻገር ደግሞ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ህጎችን የሚያረቁት በህዝብ የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ሳይሆኑ በየምኒስትሪዎቹ ውስጥ ሎብይስቶችን በመሰግሰግና ፓርሊያሜንት አካባቢ ቢሮዎችን በመክፈት የየመንግስታት ህጎችን በቅጥታ የሚያረቁትና ተግባራዊ እንዲሆኑም ግፊ የሚያድርጉት፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲሁም በማህበር ደረጃ የተደራጁ የንግድ ሙያተኞች ናቸው ። ብረሰልስ ብቻ ወደ ስድስት ሺህ የሚጠጉ ሎቢይስቶች ቢሮዎች ከፍተው ተጠሪዎችን ያባልጋሉ። ስለዚህም ነው በዘመኑ አጠራር በአብዛኛው የካፒታሊስት አገሮች የውክልና ዲሞክራሲ ሳይሆን ፖስት-ዲሞክራሲ ስፍኗል የሚባለው። ከፓርሊሜንታሪ ዴሞክራሲ ተላቀናል ለማለት ያህል ነው።

ይህንን አልፈን ወደ ሶስተኛው ዓለም መንግስታት ደግሞ ስንመጣ አብዛኛዎቹ መንግስታት ራሳቸውን ችለው በራሳቸው ፍልስፍናና ህሊና የሚንቀሳቀሱ አይደሉም። ስለሆነም በየመንገስታት ቢሮክራሲ ውስጥ የካፒታሊስት አገሮችን፣ በተለይም የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም ጥቅም የሚያስጠብቁ ሰዎች ቀድሞውኑ ተኮትኩተው ከፍተኛ ስልጣንን ስለሚይዙ እነዚህ ኃይሎች በቀጥታ የየአገራቸውን ጥቅም ሳይሆን የካፒታሊስት አገሮችን ጥቅም ነው የሚያስጠብቁት። ስለሆነም የካፒታሊስት አገሮች የራሳቸውን ሰዎች በመንግስት መኪና ውስጥ አሰልጥነው በማስገባት በገዢው መደብ ዘንድ መተማመን እንዳይፈጠር ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠርና ህዝቡ ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርጋሉ። በዚህ መልክ የሶስተኛው ዓለም መንግስታት በቀጥታ የካፒታሊስት አገሮች ታዛዥና አፈ-ቀላጤ በመሆን ወደ ውስጥ ማንኛውንም የማህበራዊና የምሁራዊ እንቅስቃሴ አፍነው ይይዛሉ። ነገሩ ገፍቶ የሚሄድ ከሆነ ደግሞ በማሰርና በመግደል የተቀሰቀሰውን ትግል ለማብረድ ይሞክራሉ። በዚህ ድርጊታቸው የበለጠውን አምባገነናዊ በመሆንና ለዕድገት የሚያመቹ ማንኛውንም ምሁራዊ እንቅስቃሴዎችን በማፈን የካፒታሊስት አገሮች ተጠሪነታቸውን ያረጋግጣሉ። ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ንቃተ-ህሊና እንዳይዳብርና ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት አገሩን እንዳይገነባ በሚሆን በማይሆን ነገር ጠምደው በመያዝ አስተሳሰቡን ያዘበራርቁበታል። ከዚህ ስንነሳ በካፒታሊስት አገሮችና በጥሬ-ሀብት አምራች አገሮች መሀከል ያለው ግኑኝነት የጌታና የሎሌ ዐይነት ግኑኝነት ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ዛሬ በብዙ የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ያለው አምባገነናዊና ፋሺሽታዊ ስርዓት ከዚህ ዐይነቱ ግኑኝነት ውጭ አይደለም። ዋናው ዓላማውም ድህነትን ማስፋፋትና የህዝቡን አስተሳሰብ አዳክሞና አዘበራርቆ አቅመ-ቢስ ማድረግ ነው። ጠቅላላው ህዝብ አገርና ህብረተሰብ የሚለውን አስተሳሰብ ከጭንቅላቱ ሰርዞ በማውጣት እንደ አንድ ነፃ ህዝብ እንዳይኖርና ታሪክን እንዳይሰራ ማድረግ ነው። የካፒታሊስት አገሮችም ዋናው ፍላጎት ይህ ሲሆን እንደዚህ ዐይነቱን አገዛዝ በማንኛውም ነገር መደገፍና በድርጊቱ እንዲገፋበት ማድረግ ነው።

ይህ ዐይነቱ ስርዓት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ መልኩን በመቀየር በውስብስብ ነገሮች በመገለጽ የብዙ አገሮችን ዕድል ወሳኝና ጦርነት ቀስቃሽ ለመሆን ቻለ። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነትን በመቀዳጀትና በሱ ቁጥጥር ስር ሊውሉ የሚችሉ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖችን በመፍጠርና በእነዚህ ኢንስቲቱሽኖች አማካይነት የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለውን፣ በመሰረቱ በቴክኖሎጂና በሳይንስ የሚደገፍን ዕድገት ሳይሆን በርዕዮተ-ዓለም የተሸፈነን(Neo-Liberal and Neo-Classical Economy Policy) ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ በየአገሮች ውስጥ ያለ የጥሬ-ሀብትና በመዋዕለ-ነዋይ ስም የሚካሄድ ትርፍ ወደ ውጭ እንዲወጣ በማድረግ በየአገሮች ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት እንዲስፋፋ ለማድረግ በቃ።  ከአንድ አገር ህዝብ ፍላጎት ጋር የማይጣጣሙና የዕድገት አጋዥ ሊሆኑ የማይችሉ እንደ ኮካኮላ፣ የሲጋራ ፋብሪካ፣ የብስኩት፣ የቢራ ፋብሪካና ቀላል የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች የዚህ ዐይነቱ የተዘበራረቀ የዕድገት መግለጫዎች ሲሆኑ፣ የፍጆታ ዕቃዎቹ ለተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የታቀዱና ይህንን የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ከጠቅላላው የህብረተሰብ ክፍል በመነጠል በአሜሪካን የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ እንዲሽከረከር በማድረግ ብሔራዊ ስሜት እንዳይኖረው ማድረግ ነው። ይህ ዓይነቱ የፍጆታ አጠቃቀም(Consumption Pattern) ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የተስፋፋና እዚያው በዚያው ኢንፎርማል ኢኮኖሚ(Informal Sector) ከሚባለው መስክና ከእጅ ወደ አፍ ከሚመረተው(Subsistence Economy) የምርት ክንዋኔ ጋር በመጣመር በካፒታሊዝም ሎጂክ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንዋኔ እንዳይካሄድ ያገደ ጣልቃ-ገብነትና የኢምፔሪያሊዝም መስፋፋት መግለጫ ነው። ይህ ዐይነቱ ሂደት በተለይም ወደ ውስጥ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በንግድና በአልባሌ መስኮች ላይ ብቻ እንዲሰማራ በማድረግ ከውስጥ ብሄራዊ ከበርቴ እንዳያድግ ያገደና የሚያግድ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ነው። በአንዳንድ የአሜሪካን የዘመናዊነት ተመራማሪዎች(Modernization theortecian)  ዕምነትና፣ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ከሶስተኛው ዓለም አገሮች የሚመጡ ተማሪዎች  ጭንቅላት ውስጥ ተቋጥሮ እንዲያዝ በሚሰብኩት ፍላጎት መሰረት  የአፍሪካ አገሮችና የተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ሁለ-ገብ የሆነ በመጀመሪያ ደረጃ ባህላዊ ዘመናዊነትንና ጭንቅላትን ያስቀደመ ዕድገት ሳይሆን የሚያስፈልጋቸው አንድ የተወሰነ ኤሊት ብቻ በመኮትኮት በዚህ አማካይነት ቀስ በቀስ ዕድገት ሊመጣ ይችላል ብለው ያስተምራሉ። ይህም አካሄድ  ዕውነተኛው የዕድገት መንገድ ተደርጎ በመወሰዱና ይህንንም የተዛባና ከሳይንስ ጋር በፍጹም ሊጣጣም የማይችል አስተሳሰብ ሊዋጋ የሚችል ኃይል ብቅ ማለት ስላልቻለ እስከዛሬ ድረስ አገራችንና አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በድህነት እንዲማቅቁ ተፈረደባቸው።

ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣና በተለይም በመንግስት መኪና ላይ ያለውን ተፅዕኖ ስንመለከት የሲቪልና የሚሊታሪ ቢሮክራሲውን በማሰልጠንና የአገዛዙ መሰረት በማድረግ፣ በአንድ በኩል ወደ ውስጥ ብዝበዛን ሲያጠናክርና የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ ህብረተሰቡን ቆልፎ ሲይዝ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሚያስፈልግበት ጊዜ የመንግስት ግልበጣ በማድረግ አንድ መንግስት መፈጸም ያለበትን ተግባር እንዳያከናውን ያደረገና የሚያደርግ ስርዓት ነው። እንደሚታወቀው እንደተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮችም የኛም አገር ዘመናዊ የመንግስት መኪና አወቃቀር ከታች ወደ ላይ ከኢኮኖሚው ዕድገትና ከምሁራዊ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ እያደገ የመጣና የጠቅላላውን የአገሪቱን ዕድገት ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ሳይሆን ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊዝም ጋር በሺህ ድሮች በመቆላለፉ የዕድገት አጋዥና ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዲዳብር የሚያግዝ አልነበረም። ስለዚህም ነው በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተዋቀረው የመንግስት መኪና ከኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎትና ብሔራዊ ዕድገት ጋር የተያያዘ ሳይሆን የወጭው አካል ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር የሚቻለው። ስለዚህም ነው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አብዮቱ ሲፈነዳ አሜን ብሎ ያልተቀበለውና በጠቅላላው ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ነፃ ኢኮኖሚ ሊያስገነቡ የሚችሉ የአብዮቱ ድሎች እንዲጨናገፉ አብዮቱን የሚቀናቀኑ ኃይሎችን ሁሉ በማስታጠቅ አጠቃላይ ጦርነት ያወጀብን።

በአብዮቱ ወቅት ወደ ውስጥ በተለያዩ ኃይሎች የተከሰቱትን የማያስፈልጉ ሽኩቻዎችንና ምስቅልቅል ሁኔታዎችን ወደ ኋላ በመተው፣ አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ህዝቡ የተቀዳጃቸው እንደ መሬት ላራሹ የመሳሰሉት ድሎችና ዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባርነት ተመንዝረው ህዝባችን ያለ የሌለውን ኃይሉን በአገር ግንባታ ላይ እንዳያውል የታገደው በውጭ ኃይሎች፣ በተለይም በአሜሪካንና በእንግሊዝ እንዲሁም በተቀሩት የሰሜን አትላንቲክ የጦር አባል አገሮች በህዝባችን ላይ ጦርነት ስለታወጅብን ነው። እነዚህ የውጭ ኃይሎች ህዝባችን ብሔራዊ ስሜቱ አድጎ አገሩን በጸና መሰረት ላይ እንዳይገነባ ለማድረግ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የነፃ አውጭ ኃይሎች ነን የሚባሉትን የብሔረሰብ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በማስታጠቅና የገንዘብ ዕርዳታ በማድረግ የወታደራዊዉን አገዛዝ ከውስጥም ከውጭም ወጥረው እንደያዙት በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በአገራችን ምድር በጊዜው በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር የተካሄዱት የወንድማማች ህዝብ ርስ በርስ መተላለቅ በስተጀርባ ሲአይኤና ሌሎች የስለላ ድርጅቶች እንደነበሩበት ይታወቃል። እንደሚባለው የውጭው ርዕዮተ-ዓለም ወደ አገራችን በመግባቱ ሳይሆን የርስ በርስ መተላለቅ ሊፈጠር የቻለው፣ ወደ ውስጥ የአብዮቱ ድሎች በተለይም በሚሊቴሪውና በሲቪል ቢሮክራሲው ዘንድ ግንዛቤን ባለማግኘታቸውና፣ ይህም የህብረተሰብ ክፍል ገና ብሔራዊ ስሜቱ ያደገ ባለመሆኑ በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ተራማጅ ነኝ በሚለው ዘንድ አብዮቱ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኝ በጥንቃቄ ባለመካሄዱና የፊዩዳሉን መደብ የሚያስቆጣ ስር-ነቀል የመሬት ላራሹ ተግባራዊ መሆን እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ በመደመር በጊዜው ለተከሰተው አስከፊ ሁኔታ ተደራራቢ ምክንያቶች ሊሆኑ ቻሉ። በተጨማሪም የተወሰነው የተማሪው ንቅናቄ አካል የነበረው አርቆ የማሰብ ኃይል በጣም ደካማ ስለነበር  ድርጊቱን በቅጡ ለመመርመርና  ከአደገኛ ተግባሩ ሊቆጠብ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ መሰባሰብና አብሮ መታገል የሚገባው ተራማጅ ነኝ ይል የነበረው ኃይል በዚህ ጨቅላ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ጠቅላላውን የህዝብ ኃይል መበተን ቻለ። በአጠቃላይ ሲታይ ተራማጅ ወይም የለውጥ ፈላጊ ኃይል በሚባለው ዘንድ ህብረተሰብአዊና ፓለቲካዊ ንቃተ-ህሊና ስር የሰደደ ባለመሆኑ፣ ድርጊቱን ከራሱ የስልጣን ፍላጎት ውጭ ማየት አልቻለም። ይህ ዐይነቱ የኃይል መከፋፈል ለውጡን ለሚጠሉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አመቺ ሁኔታ ፈጠራላቸው።  እንደሚታወቀው አገራችን የረዥም ጊዜ አገር ታሪክ አላት ቢባልም ምሁራዊ እንቅስቃሴ የሚባለው ከ1950ዎች ዓ.ም ጀምሮ ብቅ ያለ በመሆኑና ይህም ቢሆን በሰፊ መሰረት ላይ የተገነባ ባለመሆኑና አመለካከቱም በጣም ውስን በመሆኑ አብዛኛውን ምሁር ተብሎ የሚጠራውን ያቀፈ አልነበረም። በአገራችን ምድር በሁሉም መልክ የሚገለጽና አገሪቱን ሊያዳርስ የሚችል ምሁራዊና ህብረተሰብአዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ አብዮቱን ለማዳከመና ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችን ለመምታት በጣም የሚያመች ነበር።  አብዛኛው ዘመናዊ የሚባሉት ነገሮች አዲስ አበባ ብቻ ይካሄዱ ስለነበር  ከ90% በላይ የሚሆነው ህዝባችን ንቃተ-ህሊናውን ለማሳደግ የሚያስችለው የትምህርት፣ የቲያትርና ልዩ ልዩ ጭንቅላትን የሚያዳብሩ ትምህርታዊ ነገሮችን የማግኘት ዕድል አልነበረውም።

ከዚህ ሀተታ ስንነሳ የተቀረውን ትተን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጀምሮ  አሜሪካንና ግብረ አበሮች ደካማ አገሮች ራሳቸውን እንዳይችሉ የተከተሉትንና የሚከተሉትን በግልጽና ግልጽ በአልሆነ መልክ የሚካሄደውን ፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ፖሊሲያቸውን በጥብቅ ለተከታተለ አሜሪካንና ግብረአበሮቿ በምንም ዐይነት የዕድገትና የሰላም አራማጆች ሆነው አያውቁም። ነበሩም፣ ናችውም ብሎ ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር ካለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን እንደተካሄደና እንደሚካሄድ የማያውቅ ብቻ ነው። ከኢራን እስከ ጓቴማላ፣ ከብራዚልና እስከቺሌ ድረሰ የተደረጉት የመንግስት ግልበጣዎችና የአምባገነን መንግስታት አነሳሶች፣ እንዲሁም የቬትናም ጦርነት በአጭሩ የሚያረጋግጡት የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝም ዐይን ያወጣ ተግባር እንጂ ዲሞክራሲያዊ ባህርዩን አይደለም። ይህንን በሚመለከት በዐይናችንን ከምናየው በሻገር ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ የድሮና አሁን በየጊዜው የሚወጡት ሊትረቸሮች በሚገባ ያረጋግጣሉ። ዛሬ በተለይም በአፍሪካ ምድር አምባገነን በመባል የሚታወቁት አገዛዞች በሙሉ አነሳሳቸውና የውስጥ ፖሊሲያቸው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ከግብረ-አበሮቻቸው ጋር በጥብቅ የተያያዙ እንደሆነ አያሌ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የአፍሪካን አምባገነን አገዛዞች በአፈጣጠራቸው ጭራቆችና የዕድገት ተቀናቃኝ ኃይሎች ናቸው ተብሎ በተናጠል የሚቀርበውጥ ጥናትና የሚሰጠው የቃለ-ምልልስ ገለጻ በመሰረቱ ሳይንሳዊ አይደለም። ይህንን ካልኩኝ በኋላ ወደ ዛሬው በአገራችን ምድር ወደ ሰፈነው አምባገነናዊና ፋሺስታዊ አገዛዝ ልምጣ። ወያኔ ብቻውን የሚገዛ ኃይል ወይስ የውጭ ኃይሎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ አገዛዝ ? ይህንን በደንብ ጠጋ ብለን እንመልከት።

ወያኔ ለማን ነው ጠበቃ የቆመው? የትኞቹ ኃይሎችስ ናቸው ከበስተጀርባው የቆሙት ?

አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት ለዕድገት ጠንቅና ለዲሞክራሲያዊ ነፃነት አለመኖር ዋናው ጠላቶች ፊዩዳሊዝም፣ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምና ኢምፔርያሊዝም ናቸው ብለናል። እዚህ ላይ ከሞላ ጎደል ስምምነት ያለ ይመስለኛል። አብዮቱ ከፈነዳና ከተቀለበሰ በኋላ ግን እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች እንደዋና ጠላቶች አድርጎ መውሰድ በፍጹም አይቻልም። የፊዩዳሊዝም የማቴሪያል መሰረቱ ሙሉ በሙሉ ስለተደመሰሰ እንዲሁም ፖለቲካዊ መዋቅሩ ተገርስሷል። ስለዚህ ይህንን እንደምክንያት ወስደን የኋሊት ጉዞ በመጓዝ በአረጀ የትግል መሳሪያ ልንታገል አንችልም። ስለሆነም ለዛሬው ችግራችን ዋናው ምክንያት የሆነውን ቆፍሮ በማውጣት ላይ የሚያተኩር መሆን አለበት። እንደሚባለውና እንደሚታመንበት ለአንድ ህምም ሆነ ህብረተሰብአዊ ችግር በቂ ምክንያት አለ። የችግሩን ዋና ምንጭ ሲታወቅ ብቻ ነው መፍትሄ መስጠት የሚቻለው። ይህንን በሚመለከት አዲስ ባወጣሁት መጽሀፌ ላይ በሰፊው ስላተትኩ አልመለስበትም።

ያም ሆነ ይህ በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት አንድ ጉዳይ አለ። ይኸውም አንድ የውጭ ኃይል ለአገራችን ዕድገትንና ነፃነትን የሚመኝ ከሆነ መስራት ያለበት ከተገለጸላቸውና ዕውነተኛ ነፃነትንና ዕድገትን ከሚያመጡ ብሔራዊ ኃይሎች ጋር እንጂ ስልጣንን ዋና ዓላማው አድርጎ የጦር ትግል ከሚያካሂድና አንድ ወንድማማች ህዝብ ወደ ርስ በርስ ጦርነት እንዲያመራ ከሚያደርግ አሸባሪ ኃይል ጋር አይደለም። በዚህ ረገድ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ አገራችንን ለማዳከም ፀረ-ዲሞክራሲያዊና ተገንጣይ ኃይሎችን በሃሳብና በማቴሪያል እንዲሁም በገንዘብ ሲደግፉ ኖረዋል። ስለሆነም ትላንትናም ሆነ ዛሬ አገራችን እንድታድግ፣ እንድትረጋጋና፣ ህዝባችንም ዕውነተኛ ነፃነትን እንዲቀዳጅ በፍጹም አይፈልጉም። ይህንን ማድረግ ማለት በራስ ላይ ዘመቻ እንደማካሄድ ይቆጠራል። ከሄጄሞኒ(Hegemony) ቲዎሪ አንፃር  ስንነሳ፣ ለአንድ የሶስተኛው ዓለም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘን ሁለ-ገብ ዕድገት መደገፍ ማለት ቀስ በቀስ የራስን የበላይነት እንደማጣት ይቆጠራል ማለት ነው። አንድ አገር የጠነከረ ብሔራዊ ኢኮኖሚና በሁሉም መስክ የተማረ ኃይልና የአገሩን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ የህብረተሰብ ኃይል ካላት ከውጭው ኃይል ጋር የመደራደር ኃይሏ ይጨምራል። አገሩንም የሚወክለው ኃይል በድፍረት የሚፈልገውንና የማይፈልገውን፣ ለአገሩ ዕድገት የሚያዋጣውንና የማያዋጣውን በግልጽ ስለሚናገርና ስለሚደራደር ይህንን ዐይነቱ የህብረተሰብ ክፍልና መንግስት እንዲፈጠርና እንዲጠነክር መፍቀድ ማለት የራስን መቃብር እንደመቆፈር ይቆጠራል። ስለሆነም በውጭው ኃይልና እንደኛ ባለው አገር ጋር ያለውን ግኑኝነት ከዚህ አንፃር በመነሳት ነው መገምገምና መረዳት ያለብን። እንዲያው በአጉል ጥላቻ ላይ የተመረኮዘ ቅስቀሳ የትም አያደርሰንም። በሌላ ወገን ደግሞ በውጭው ኃይል ላይ የሚሰጠውን ክሪቲካል ትንተናና ገለፃ የአክራሪዎችና የግራ-ቀደሞች አስተሳሰብ ነው እያሉ ለማንቋሸሽና ስም ለማጥፋት መሞከር በተጨባጭ ሲታይ ዕውነተኛ ስልጣኔና ዲሞክራሲያዊ ነፃነት እንዳይመጣ አጥብቆ እንደመታገል ይቆጠራል። በተለይም በአንድ ወቅት ግራ ነን ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ በሚሉት ዘንድ ይህ ዐይነቱ የፀረ-ዕድገትና የፀረ-ዲሞክራሲ ዘመቻ እየተስፋፋ መጥቷል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለጤናማ ትንተናና ውይይት እንቅፋት ለመሆን በቅቷል ማለት ይቻላል።

ያም ሆነ ይህ ወያኔ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው በእንግሊዝ፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች ድጋፍ እንደሆነ የታወቀ ነው። አፀነሳሱና አነሳሱ ከኢትዮጵያ የህብረተሰብ አወቃቀር ድክመት ጋር የተያያዘና የአገራችን ኋላ-ቀር ዕድገት ውጤት ቢሆንም፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ይደገፍ የነበረው ሻቢያ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ስልጣን ላይ ቁጥጥ ብሎ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲውን ተግባራዊ እንዲያደርግ እንደረዳው ግልጽ ነው። በሌላ አነጋገር ለወያኔ መፀነስ፣ መወለድና ማደግ የውስጥ ተጨባጭና ህሊናዊ ነገሮች ዋናው ምክንያት ቢሆኑም፣ ሊጠናከር የቻለውና የዲሞክራሲና የነፃነት ጠላት ሊሆን የበቃው በአካባቢው በሚገኙና በውጭ ኃይሎች አማካይነት ነው። ከዚህ ስንነሳ ወያኔ ስልጣን ሲይዝ እንደ ዋና ቅድመ-ሁኔታ ከቀረቡለት ነገሮች የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትንና(IMF) የዓለም ባንክን የተቅዋም ፖሊሲ ማስተካከያ(Structural Adjustment Program) ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ነው። የዚህ ፖሊሲ ዋና ዓላማ ደግሞ የገበያ ኢኮኖሚን ማስፋፋት በሚል ስም በፖሊሲው አማካይነት የህዝብ ሀብቶች በግለሶብች ቁጥጥር ስር ውለው የተወሰኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሀብታም ሊሆኑ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በተጨማሪም የመንግስቱ ሚና በሞኔተሪ ፖሊሲ ላይ ብቻ በማትኮር ወደ ውስጥ ሰፋ ያለ የአገርን የውስጥ ገበያ ሊያሳድግና ሊያስፋፋ በሚችልና የሰውን ኃይልና የአገርን የተፈጥሮ ሀብት ለማንቀሳቀስ በሚችለው ሂደት ላይ በምንም መንገድ አለመሳተፍ ነው። ከዚህም ባሻገር ሰፊውን ህብዝ ለማድኸየት ሲባል ሀብትን ከደሀው ወደ ሀብታሙ የህብረተሰብ ክፍል ለማሸጋሸግ የግዴታ ለማህበራዊ መስክ የሚወጡ ድጎማዎችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ነው። በዚህ መልክ የውስጥ ሀብት በፍጹም ሊዳብር አይችልም። አገርም ልታድግና ህዝብም ሊሰባሰብና ብሔራዊ ስሜት ሊያድርበት አይችልም። እንደሚታወቀው ለአንድ አገር ዋናው የዕድገት መሰረት ወደ ውስጥ ያተኮረ ሳይንሳዊና ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተል ሲሆን፣  አንድ አገዛዝ በውጭ ኃይልና በኢንስቲቱሽኖቹ እየተመከረና እየታገዘ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያወጣና ተግባራዊ የሚያደርግ ከሆነ በመሰረቱ የአገሩን ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም። ከዚህም በላይ በአንድ አገር ውስጥ አንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በውስጥ የህብረተሰብ ኃይሎች መጠናትና ለክርክር መቅረብ የሚችል መሆን አለበት። ይህንን አስመልክቶ ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ በውስጥ ኃይሎች የተደረገ ክርክርና ወያኔም በራሱ ተነሳሽነት ምሁሩን ጋብዞ እንወያይ ያለበት ጊዜ የለም። ስለሆነም ወያኔ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደ አሽከር በመሆን በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በኢንስቲቱሽኖቹ የቀረበለትን ፖሊሲ ነው። ይህም ማለት ፖሊሲው ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የሚፃረርና የዕድገትና የስልጣኔ ተቀናቃኝ ነው። በብዙ አገሮች ተሞክሮ በጥናት እንደተረጋገጠውና በዐይናችንም እንደምናየው በውጭ ኃይሎችና አማካሪ ኩባንያዎች የሚረቀውና የሚደገፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ድህነትን ፈልፋይ ነው። በከተማዎች ብቻ ሳይሆን፣ በጠቅላላው በአንድ አገር ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገትን በማምጣት ለህብረተሰብ መወዛገብና ለሌሎች እንደ ጎሳና ሃይማኖት ለመሳሰሉት ነገሮች ያለመግባባትና የግጭት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ሰፋ ያለ አንድን አገር የሚያዳርስ የስራ-ክፍፍል ለመዳበር ስለማይችልም፣ አብዛኛው ህዝብ ሀብትን በማይፈጥር ጥቃቅን የምርትና የአገልግሎት መስኮች ላይ በመረባረብ ኑሮውን ለማሻሻል አይችልም። ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን(Basic Needs) የማግኘት ዕድሉም በጣም እየጠበበ ይመጣል። ስለዚህም ነው ዛሬ በአገራችን ምድር ድህነትና ረሃብ ሊስፋፉ የቻሉት። በፖሊሲውም አማካይነት ነው ከተማዎች ካለ ዕቅድ የሚሰሩትና ህዝባችንም የተዝረከረከ ኑሮ እንዲኖር የተገደደው። በአንፃሩ ግን ፖሊሲውም በቀጥታ ወያኔና ግብረአበሮቹን የረዳና በሀብት እንዲናጥጡ ያደረገ ነው።

የወያኔ አገዘዛ በአጠቃላይ ሲታይ ከአንድ ብሔረሰብ የተውጣጣ በመሆኑ ስትራቴጂክ የሚባሉ መስኮችን ገንዘብ በርካሽ ወለድ ከባንክ በመበደር ከዚህ ቀደም በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩ ሀብቶችን በራሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ በቃ። በዚያው መጠንም እያደገ ሲመጣ ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ታታሪ ግለሰቦች ከገበያው ተስፈናጥረው እንዲወጡ በማድረግ ወደ ውስጥ በግለሰብ ታታሪነትና ፈጠራ ላይ የተመሰረተ የካፒታሊዝም እንቅስቃሴ እንዳይካሄድ አገደ። የተቀሩትን የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች ስንመረምር ደግሞ ወደ ውስጥ ሀብት ሊያፈሩ የሚችሉ ሳይሆኑ ወደ ውጭ የጥሬ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል የሚካሄዱ የምርት ክንዋኔዎች ናቸው። የአበባ ተከላ፣ የስኳር አገዳ ተከላና ምርት፣ የሰሊጥና የኑግ ምርት እንዲሁም ቡናና ሌሎች በጥሬ ሀብት ላይ የተመረኮዙት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚባሉት በሙሉ የስራ መስክ ፈጣሪዎችና የአገር ውስጥ ሀብት(National Wealth) እንዲዳብር የሚያደርጉ ሳይሆኑ አገሪቱ ራሷን እንዳትችልና ሰፋ ያለ ብሔራዊ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ናቸው። በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚካፈሉት የውጭ አገር ሀብታሞች የሚባሉት በሙሉ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የምርት ክንዋኔ የሚያካሄዱ ሳይሆኑ በአበባ ተከላና በፍራፍሬ ምርት ላይ የተሰማሩ ናቸው። እንደነዚህ ዐይነት የምርት ክንዋኔዎች ደግሞ ምንም ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋፅዖ የላቸውም። በአንፃሩ የውስጥ ገበያና የአገር ውስጥ ከበርቴ እንዳያድጉ የሚያደርጉ ናቸው።  በመሰረቱ እነዚህ የውጭ መዋዕለ-ነዋዮች የሚባሉት፣ 1ኛ) የምርት ክንዋኔዎቹ ከተቀሩት የኢኮኖሚ መስኮች ጋር የተያያዙ አይደሉም። ይህም ማለት የሚመረቱት የጥሬ-ሀብቶች ሳይፈበረኩ(Unprocessed) እንዳሉ ወደ ውጭ የሚላኩ ወይም የሚወጡ ናቸው። በዚህ መልክ በአጠቃላይ ሲታይ የተሳሰረና የተደጋገፈ የምርት ክንዋኔ  ወይም ሂደት (Value-added Chain) ይበጠሳል። ወይም ርስ በርሱ የተያያዘ የኢኮኖሚ ክንዋኔ አይኖርም ማለት ነው። የ2ኛ) የስራ መስክ የመክፈት ኃይላቸው በጣም ደካማ ነው። ተቀጥሮ የሚሰራው ደግሞ አነስተኛ ደሞዝ ስለሚከፈለው ከኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር ሚናው በጣም ውስን ነው ማለት ነው። በሚያገኘው ደሞዝ ደግሞ ፋብሪካ ውስጥ የሚመረቱትን ወይም ራሱ የሚያመርታቸውን ሳይሆን ገዝቶ የሚጠቀመው ከሌሎች ዘመናዊ ኢኮኖሚ ከሚባለው ዘርፍ ጋር ባልተያያዙ መስኮች የሚመረቱ ምርቶችን ነው። 3ኛ) እንደዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ክንዋኔ የፕላንቴሽን ኢኮኖሚን በማስፋፋት ከውስጥ ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት እንዳይመጣ ያግዳል። ስለሆነም በካፒታሊስት አገሮች በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የፍጆታ አጠቃቀምና የሀብት ክምችት ዘዴ የሚያግዝ ሲሆን፣ ወደ ውስጥ ደግሞ ለምለም መሬቶች የህዝቡን ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ ሰብሎች እንዳይዘራባቸውና እንዳይመረትባቸው ይደረጋሉ። በዚህም ምክንያት አገር ቤት ውስጥ የእህል እጥረት ሲከስት፣ በቁጥር እየጨመረ ከሚሄደው ህዝብ ጋር የሚመጣጠን በቂ ምግብ ገበያ ላይ እንዳይቀርብ ያግዳል። 4ኛ) ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ የምግብ እጥረትን ማስከተሉ ብቻ ሳይሆን ኢንዱስትሪዎች የጥሬ-ሀብት እንዳያገኙ ይደረጋሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ የተወሳሰበ የአገር ውስጥ ገበያ(Home Market) እንዳያድግ ያግዳል። 5ኛ) አገዛዙ ከእንደዚህ ዐይነት የውጭ ከበርቴዎች ጋር በመቆላለፍ በአገር ውስጥ ብሔራዊ ባህርይ ሊኖረውና በኢኮኖሚው መስክ ሊሰማራ የሚችል የአገር ውስጥ ከበርቴ እንዳይዳብር ያግዳል። 6ኛ) ይህ ዐይነቱ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ያለውን ድህነትና ዝርክርክነት የባሰውኑ ያጠናክረዋል። በተጨማሪም ጥበባዊ የሆኑ ከተማዎችና መንደሮች እንዳይገነቡ ያግዳል። 7ኛ) የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል አትኩሮው እንዲቀየር በማድረግ ብሔራዊ ስሜቱ እንዳይዳብር ያደራግል። በዚህ መልክ ጠቅላላው አገሪቱ ከውስጥ ስትዳከም ለውጭ ወረራ አመቺ ትሆናለች ማለት ነው። ስለሆነም  በውጭውና በአገር ውስጥ ያለውን የኢኮኖሚ ትስስርና የድህነትን መጠናከርና ጥገኝነት መግለጽ የሚቻለው በዚህ መልክ ነው። የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችም ዋና ተግባር አገዛዙ በዚህ ዐይነቱ ድህነትን ፈልፋይ ፖሊሲው እንዲቀጥል መገፋፋት ነው። ጭቆናውን እንዲያጠናክር ማንኛውንም ነፃነት አፋኝ የሆኑ ህዝቡን መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች በሙሉ ያቀርቡለታል። በሁሉም መልክ የሚገለጽ ኋላ-ቀርነት በሰፈነበት አገር ደግሞ ይህ ዐይነቱ በአገዛዙና በውጭ ኃይሎች መሀከል ያለው የእከክልኝ ልከክልህ መደጋገፍ እንደትክክለኛ ድርጊትና ዕርዳታ ተደርጎ ይቆጠራል። ስለሆነም የወጭ ኢንቬስተሮች የሚባሉትን ሚና ትርፍን ወደ ውጭ በማውጣት ብቻ በገምገም መረዳት የሚቻል ሳይሆን፣ ለአንድ አገር ብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ የቴክኖሎጂና የሳይንስ ምጥቀት፣ የባህል ዕምርታና የህብረተሰብ መተሳሰርና መጠናከር ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋፅዖች ከስሌት ውስጥ የከተትንና መተንተን የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። በራሱ የሚንቀሳቀስና ከሌላው የኢኮኖሚ መስክ ጋር የማይተሳሰር የኢኮኖሚ ዘርፍ ለዘረፋና ለአምባገነን አገዛዞች የሚያመች ነው። ማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከጠቅላላው የኢኮኖሚ ፕላኒንግ ሲይሰተም ጋር ሲዋሃድ ብቻ ነው ኢኮኖሚያዊ ትርጉምነቱን መረዳት የሚቻለው። ያም ሆነ ይህ የውጭ ዕርዳታና መዋዕለ-ነዋይ አገራችንን ከድህነትና ከጥገኝነት ሊያላቅቁ በፍጹም አልቻሉም።

ይህ ዐይነቱን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግና ዘረፋን ለማጠናከር ደግሞ አገዛዙን በሚሊታሪ ቴክኖሎጂዎች ማስታጠቅ ዋናው የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ተግባር ነው። የፀጥታው መስክ ውስጥ ስርጎ በመግባትና በማማከር አምባገነናዊ ባህርዩን ማጠናከርና በህዝባችን ላይ ግልጽ ጦርነት ማካሄድ፣ ዕድገትን ማጨናገፍ፣  ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ፣ በአገሪቱ ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት በመነሳት ህዝባችን አቅመ-ቢስ እንዲሆን ማድረግ፣ ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ-ገብነት ተነጥሎ በፍጹም የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ስለዚህም ነው የውጭ ኃይሎች  ቢያንስ የግንቦቱ 97 ዓ.ም ምርጫ ውጤት ከከሸፈ በኋላ ባለፉት 12 ዐመታት አገዛዙ የበለጠ ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ህዝብ፣ እንዲሁም ፀረ-ዕድገት እየሆነ ሲመጣ ዝም ብለው የሚመለከቱት። ከአንድ ዐመት ጀምሮ የሚካሄደውን ህዝባዊ ተቃውሞና አገዛዙ በህዝባችን ላይ የሚያካሂደውን ፋሺሽታዊ ጭፍጨፋ ካለምንም ተቃውሞ ዝም ብለው የሚመለከቱት ወያኔ እነሱ የሚፈልጉትን ስራ ስለሚሰራላቸው ነው። ከዚህ ስነሳ የውጭ ኃይሎችን ሚና በሚመለከት በአገር ቤት ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚ ነኝ በሚባለው ኃይል ዘንድ ከፍተኛ የግንዛቤ ጉድለት አለ። ጩኸትና ስለማዊ ሰልፍ ስለተደረገ፣ የመንግስታትን ተጠሪዎች ወይም ፓርሊሜንቴርያኖችን ማነጋገር ስለተቻለና ግብዣም ተደርጎ ገለጻ ስለተሰጠ የውጭ ኃይሎች በአገዛዙ ላይ የፖለቲካዊና የዲፕሎማሲ ጫና ማድረግ የሚፈልጉና፣ ይህ አላዋጣ ሲል ደግሞ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በማድረግ በአገዛዙ ላይ ግፊት ለማድረግ የሚችሉ የሚመስላቸው ብዙ የዋህ ኢትዮጵያውያን አሉ። ይህም የሚያረጋግጠው  በአጠቃላይ ሲታይ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጨናገፉትን ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችና ለብሔራዊ ነፃነት የተደረጉትን ትግሎች በቅጡ እንዳልከታተለና ጉዳዩም እንዳልሆነ ነው።  ስለሆነም በአገራችን የሰፈነውን ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ጭፍጨፋ ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ከሰፉኑ አምባገነናዊ አገዛዞችና የብዝበዛ ስርዓቶች ጋር ማያያዝ ከተቻለና፣ ወደ ኋላ ተጉዞ  ለዲሞክራሲና ለነፃነት የተደረጉትን ትግሎች መመርመር ከቻለ ምናልባት የተሻለ ስዕልና ግንዛቤ ማግኘት ይቻል ይሆናል።

ያም ሆነ ይህ ከላይ የተጠቀሰው በወያኔና በውጭ ኃይሎች መሀከል ያለው ግኑኝነት የኢምፔሪያሊዝም መግለጫዎች ሲሆኑ፣ ግኑኝንቱና በአገራችን የሰፈነው ጭቆናዊ አገዛዝ ከአሜሪካንና ከተቀረው የኢምፔርያሊስት ኃይሎች ትስስር ውጭ በፍጹም ሊታዩ አይችልም። ስለሆነም የአገራችንን በፓለቲካና በኢኮኖሚ እንዲሁም በባህልና በማህበረሰብ መዳከም ከውጭው ዓለም ጣልቃ-ገብነት ውጭ አውጥቶ ማየት ከፍተኛ የስትራቴጂ ስህተት ነው። እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የአውሮፓው አንድነት የመሳሰሉት የሶስተኛው ዓለም አገሮች በጥሬ-ሀብት አምራችነት ብቻ ተወስነው እንዲቀሩ የሚሰብኩና የሚደግፉ ድርጅቶች በመሆናቸው እነዚህን የመሳሰሉት ድርጅቶች የዲሞክራሲና የነፃነት አራማጆች ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። የተቃዋሚ ኃይሎች መሪዎች ነን የሚሉት ተጠሪዎች እዚህ አውሮፓ እየመጡ ለአውሮፓው አንዳንድ የፓርሊያሜንት ተጠሪዎች ገለጻ ሲያደርጉ የማይረዱት ነገር የአውሮፓው  አንድነት አዲስ አበባ ውስጥ ትልቅ ቢሮ እንደሌለውና አገር ቤት ውስጥ ምን ነገር እንደሚካሄድ እንደማያውቁ አድርገው በመቁጠር ነው። እንደሚታወቀው የአውሮፓው  አንድነት አዲስ አበባ ትልቅ ቢሮ ሲኖረው፣ ተጠሪዎቹም ከወያኔ ጋር ሽር ጉድ የሚሉና ከዚህ አንዳንድ ልዑካን በሚሄዱበት ጊዜ ልዩ ዐይነት መስተንግዶ ከሴት-ልጃገረዶች ጭምር የሚቀርብላቸው ናቸው። በዚህ መልክ ነው ወያኔ የውጭ ኃይሎችን የያዘውና በህዝባቸን ላይ የሚቀልደው። ይህንን ጉዳይ በጥብቅ ለመከታተል የማይፈልገው ተቃዋሚ ነኝ የሚባለው ኃይል እዚህ እየመጣ እሮሮ ሲያሰማ በእርግጥም የአውሮፓውን አንድነት የዲሞክራሲና የብልጽግና አራማጅ አድርጎ በመቁጠርና የዋሁን ታዳጊ ወጣትና ህዝባችንን በማታለል ነው።

ከዚህ ስንነሳ፣ ይህ ጸሀፊ በአሜሪካንና በተቀረው የካፒታሊስት አገሮች ላይ ግልጽ የሆነ ዘመቻ እንዲካሄድ ቅስቀሳ እንዲደረግ ባይፈልግም፣ መታሰብ ያለበት ጉዳይ የግዴታ ብሔራዊ ስሜት ያላቸውና የዕውነተኛ ዕድገት አጋዥ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ማደራጀትና ማጠናከር አለባቸው ብሎ ያምናል። ይህ ካልተቻለ ደግሞ ምሁር ነኝ፣ የግዴታ የኢትዮጵያ ነገር ያገባኛል በሚለው ኃይል ዘንድ ግልጽ ክርክር መካሄድ አለበት። ሜዳው ዝም ተብሎ ለአሳሳች ኃይሎች መለቀቅ የለበትም። ይህንን ማድረግ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ድርጊትንና ኃይሎችን ማገዝ ብቻ ሳይሆን የድህነቱንም ዘመን እንዲራዘም አስተዋፅዖ ማበርከት ነው። አንድ አገር በግልጽና በድፍረት የሚታገልላት ምሁራዊ ኃይል ከሌላትና፣ የተወሰነው ኃይል የግንባር ቀደምትነቱን ቦታ ይዞ እዚህና እዚያ በመንቀሳቀስ ወጣቱን የሚያሳስት ከሆነ በቀጥታ ይህ ዐይነቱ ኃይል ጥቅሙ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተያያዘ አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ መስመር መለየትና ግልጽ ውይይት ማድረግ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው። ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው፣ ግልጽ ውይይ የማይደረግበትና፣ ሀቀኝነት የጎደለው ትግል የመጨረሻ መጨረሻ አንድን ህዝብ ነፃ ሊያወጣውና ዲምክራሲያዊ ስርዓት መስርቶ ዕውነተኛ ዕድገትን ሊያጎናጽፍ አያስችለውምና።

ፈቃዱ በቀለ            

fekadubekele@gmx.de

Filed in: Amharic