>

ሐበሻ ማን ነው? (በፊሽ ቶክቻው)

 

habesha-imagesበጥንት ዘመን ምናልባት BBC በ DNA ጥናት አረጋግጨዋለሁ እንዳለው የዛሬ 3 ሺ አመት ገደማ ከአሁኗ ሌባንት/ሶሪያ አካባቢ(የመን አይደለም) ወደ ኢትዮጵያ የተደረገ ፍልሰት ነበረ፡፡ በሌሎች ሰነዶች መሰረት በዚህ ወቅት
ባህር ተሻግረው ከአሁኗ ኢትዮጵያ ወይም ኤርትራ የሰፈሩት ነገዶች ስም ሀበሣትና አግዓዚያን ይባሉ ነበር፡፡ (ሸ ፊደል በጥንታዊ የኢትዮጵያ ሴሜቲክ ቋንቋዎች አልነበረም፡፡ ሀበሻ መባል የተጀመረው ሸ፣ቸ፣ጨ፣ኘ፣ . . . .የመሳሰሉ ፊደላት ከኩሽቲክ ቋንቋዎች የሴሚቲክ ቋንቋዎችን ከተቀላቀሉ በኋላ ነው፣ ሀበሻ የተባለውም ከዚያ በኋላ ነው)፡፡

እነኚህ ሁለት ነገዶች ልክ አሁን ሜጫ እና ቱለማ እንደምንላቸው የኦሮሞ ንዑስ ጎሳዎች የተለያየ ስም ይያዙ እንጂ በቋንቋ፣ በባህል፣ በማንነት፣ በዘር ፣ ተመሳሳይ ነበሩ፡፡ እነኚህ መጤዎች ቀይባህርን ከተሻገሩ በኋላ ራሳቸውን
ጠብቀው ከመኖር ይልቅ በአካባቢው ይኖሩ ከነበሩ ነባር ህዝቦች ጋር መቀላቀል ነበር የጀመሩት፡፡ ነባር ህዝቦች ማለት በወቅቱ ኮንቴክስት ኒሎሰሃራ፣ ኦሞቲክና ኩሽቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ማለታችን ነው፡፡ በመሆኑም ሀበሻ የአንድ ብሔር ስም ሆኖ ያገለግል የነበረው መጤዎቹ ከነባሮቹ ጋር
እስከሚቀላቀሉ ባለው ጊዜ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ከተቀላቀሉ በኋላ ስያሜው የሁሉም የጋራ መጠሪያ ነበር የሆነው፡፡
ይህ የቃሉ መሰረተ ታሪክ ነው፡፡

በሀገሪቱ እስካሁን ቅርስ የሚገኝለት የስልጣኔ ታሪክ የሚገኘው ከነዚህ ህዝቦች መምጣት በኋላ ነው፡፡ ያ ማለት ግን የአክሱም ስልጣኔ ባለቤቶች ሴማውያኑ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አክሱም ሲዳከም ስልጣን የያዘው የዛጉዌ ስርወ መንግስት ከአክሱም ግዛት የተነሳ አማፂ እንጂ መጤ ወራሪ አይደለም፤ ያ ማለት ኩሻዊዎቹ አገዎች የአክሱም ስልጣኔ አካል ነበሩ ማለት ነው፡፡ በወቅቱ የአክሱም ስርወ መንግስት የነበሩ ኩሻውያን አገዎች ብቻ ናቸው ወይስ የደቡብ ኩሻውያንን እና ኦሞቲኮችንም ያካትት ነበር የሚለውን በእርግጠኛነት አላውቅም፡፡

በግራኝ አህመድ ወረራ እስከ ባሌ ይደርስ የነበረውን የያኔውን የክርስትያን ግዛት የሀበሻ ግዛት ነበር የሚሉት፡፡ የግራኝ ዘመቻንም ታሪክ ፀሀፊው ሐበሻን የማቅናት ዘመቻ ነበር የሚለው፡፡ በዛኔው ትርጓሜ መሰረት ከሶማሊ፣ አፋርና
ሀረሪ በመለስ ያለው የኢትዮጵያ ግዛት ሐበሻ ነው የሚባለው (ያኔ መደወላቡ የመሸገው የኦሮሞ ጦር በሁለቱም ስር አልነበረም)፡፡

በ ጀምስ ብሩስ ዘመንም ሀገሩና ህዝቡ በዚሁ ስም ነበር የሚጠራው፡፡ የግራኝ አህመድ(አህመድ ገረዌ ይሉታል ሶማሌዎቹ) ወረራን ማክተም ተከትሎ ኦሮሞ የምስራቁንም ሙስሊም፣ የሰሜኑንና የምዕራቡን ክርስትያንም እየገፋ ሲስፋፋ እንደጥንቶቹ ሀበሣትና አግዓዚያን ሁሉ ራሱን ከመጠበቅ ይልቅ በየደረሰበት ሁሉ ተቀላቅሎ መኖርን ነበር የመረጠው፡፡ በዚህም በሂደት በኦሮሞ ህዝብ መካከል የባህል፣ ሀይማኖትና አኗኗር ብቻ ሳይሆን የመልክና ቁመና ልዩነት ሳይቀር እንዲፈጠር ነበር ያደረገው፡፡ የሸዋው ከሰሜኑ
ክርስትያን ጋር ተመሳስሎ ሲኖር፣ የምዕራቡ(ወለጋና ጅማ) ደግሞ ከአካባቢው ህዝብ ጋር ተቀላቅሎ በሂደት የራሱን ፊውዳሊዝም ማዳበር ጀምሮ ነበር፣ የምስራቁ(ሐረርጌ) ደግሞ ከሶማሌዎች ጋር የስነልቦናና ሀይማኖት አንድነትን
ያለው ሲሆን፣ የደቡብ ኦሮሚያና አጎራባቾቹ ደግሞ ከሞላ ጎደል ጥንታዊ ማንነታቸውን አስጠብቀው ቀጥለዋል፡፡ የሚኒልክ መስፋፋት ከጥቂት ሺ የሰሜን ኬንያ ኦሮሞዎች በስተቀር ሁሉንም ኦሮሞዎች ከነልዩነታቸው በአንድ ሀገር ጥላ ስር አሰባሰባቸው፡፡

በ1960ዎቹ ብቅ ያለው የሶሻሊስት ትውልድ ብሔርተኝነትን ሲያቀነቅን ነው ሀበሻ የሚለው ቃል ጥያቄ የበዛባት፡፡ አንዳንድ ኤርትራውያን ሀበሻ አይደለንም ማለት ጀመሩ፡፡ የተወሰኑ የትግራይ ብሔርተኞችም አግዓዚያን ነን በሚል የተለዬ ማንነትን ህዝቡ ላይ ለመጫን ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ይህ ጥረት በደበዘዘ ሁኔታ እስካሁን የቀጠለ ቢሆንም እየተሳካላቸው ግን አይመስልም፡፡ ሀበሻነት ከኤርትራዊነት፣ ከትግራዋይነት ፣ ወይም ከኦሮሞነት ጋር የተደረበ ማንነት መሆኑ መገንጠልን ጨምሮ የትኛውንም ፖለቲካዊ አላማ የሚከለክል ባይሆንም የያኔዎቹ ፖለቲከኞች ግን ለመገንጠልም፣ ብሔርተኝነትን ለማጠናከርም ሆነ ፖለቲካዊ ድጋፍን ለማግኘት ልዩነት ላይ ማተኮር ስለሚፈልጉ ነው፡፡

ለምሳሌ የኦሮሞ ብሔርተኞች የመገንጠል አላማቸውን ለማሳካት እንደ ትግራይና ኤርትራ ተገንጣዮች የቪክቲምሁድ ፖሊቲክስን በስፋት በማራገብ፣ ህዝቡ የተለየ ህዝብነት ስሜት እንዲያዳብር የጋራ ባህሎች፣ እሴቶችና ሀይማኖትን በማጥቃት ላይ ሰፊ ስራ ሰርተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ነበር ሀበሻ ማለት ሴማውያንን ብቻ የሚወክል ቃል እንደሆነ ተደርጎ አዲስ ትርጓሜ የተሰጠው፡፡ ይህ ዘመቻ ኤሊቶችንና ጠረፍ አካባቢ የሚኖሩ ኦሮሞዎችን በተወሰነ ደረጃ ሲማርክ የመሀል አገር ኦሮሞዎች ላይ ግን በቀላሉ ሊሰርፅ አልቻለም(በምዕራብ ያለውን ሁኔታ አላውቅም)፡፡
አሁንም ህዝቡ የአገር በቀል ምርቶችን የሀበሻ ጎመን፣ የሀበሻ ጥድ፣ የሀበሻ ዶሮ፣ . . . . ወዘተ እያለ ነው የሚጠራው፡፡

በዚህም አሁን ድረስ የአስተሳሰቡ አራማጆች በሶሻል ሚዲያዎች ጭምር ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሀበሻን የሴሜቲኮች ብቻ ስም እንደሆነ አድርጎ የማስረፅ ስራ እየሰሩ ነው፡፡ በዚህም ሀበሻ የጋራ ማንነት ስያሜ መሆኑ
እንዲቀር ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ሌሎችስ?

-እስከሀያኛው ክፍለዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ድረስ ማህበራዊ፣ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው የሰሜንና ማዕከላዊ ህዝቦች ራሳቸውን ሀበሻ ብለው ይጠራሉ፡፡ ለዘመናት ከሰሜኑ ጋር በክፉም በበጎም ተሳስረው የኖሩት ሴማውንና የሸዋ
ኦሮሞዎች፣ አገዎች፣ቅማንቶች፣ ኢሮቦች፣ . . . .ወዘተ ሀበሻን የጋራ መጠሪያ አድርገው ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡
-የኦሞቲክ ህዝቦች ራሳቸውን በሀበሻነት አይደንቲፋይ ያድርጉ አያድርጉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ከግራኝ አህመድ ወረራ በፊት ግን የሐበሻ ግዛት አካል ነበሩ፡፡ በመሀል አገር ያሉት የደቡብ ተወላጆች ግን ሀበሻነትን ሁሉም የሚጠቀምበት ኢትዮጵያዊነትን እንደሚተካ ቃል እንጂ የተወሰኑ ብሔሮች
መጠሪያ አድርገው አይደለም የሚጠቀሙበት፡፡

-እኔ እስከማውቀው ድረስ ፖለቲከኞች ብለውት ሳይሆን በራሱ ጊዜ እንደህዝብ ሀበሻ አይደለሁም የሚል ብሔር ሶማሊ ነው፡፡ ምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ በሶማሊዎች ዘንድ ሀበሻ ትርጉሙ ከሴሜቲኮችም ጠቦ የአማራ መጠሪያ ተደርጎ ነው የሚያገለግለው፡፡ አማርኛ ቋንቋ በመደበኛ የሶማሊኛ
መድረኮች (በሚዲያዎችም ጭምር) ብዙ ጊዜ አፍ-ሀበሽ ነው የሚባለው፡፡

-ጋምቤላዎችና ቤኒሻንጉሎችም ራሳቸውን ሀበሻ ብለው አያውቁም፡፡

-በሌላ በኩል ሴማዊ የሆኑት ሀረሪዎች ራሳቸውን ሐበሻ ነን አይሉም፡፡

-አረቦች ደግሞ መላውን ኢትዮጵያ ሀበሽ ብለው ነው የሚጠሩት፡፡ በሚዲያ ኢትዮጵያ የሚለውን ቢጠቀሙም ህዝቡ ግን ሀገሪቱንና ዜጎቿን ሀበሽ ነው የሚለው፡፡ አሁን ሁሉም መረዳት እንደሚችለው ኢትዮጵያዊነት ከሀበሻነት የሰፋ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሀበሻነት ከሴማዊነት የሰፋ ነው፡፡ ሴሜቲክ ሳይሆኑ ራሳቸውንሀበሻ ብለው የሚጠሩ በርካቶች ናቸው፡፡ እነኚህን ሴማዊ የሆኑት እና ያልሆኑት በጋራ ራሳቸውን ሀበሻ ብለው የሚጠሩት አንዱ ሌላው ላይ ማንነቱን
ስለጫነ ሳይሆን ቀድሞውንም የጋራ ማንነት እንደነበረና አሁንም ድረስ በሁለቱም ወገን ያሉት ህዝቦች ሀበሻ እኔ ብቻ ነኝ ወይም እሱ ብቻ ነው የሚል አስተሳሰብ እንደሌለባቸው እናውቃለን፡፡

ሆኖም አሁን በተያዘው አካሔድ የብሔርተኛ ኤሊቶች ያላሰለሰ ጥረት ወደህብረተሰቡ ከሰረፀ ሀበሻነት የሴማውያኑ ብቻ መጠሪያ መሆኑ ላይቀር ይችላል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ፖለቲከኞቻችን የህዝቡ አስተሳሰቦች፣ ባህልና እሴቶች አጥንተው በዛ ላይ የተመሰረተ ፕሮግራም ከመቅረፅ ይልቅ
የራሳቸውን ስሜቶች ህዝቡ ላይ መጫን የሚፈልጉ መሆናቸው በተደጋጋሚ ያየነው ነገር ነው፡፡

ፖለቲከኛ ማለት ግን የራሱን የጥበት፣ የጥላቻ፣ የትምክህት፣ . . . ወዘተ ስሜት ብዙሀኑ ህዝቡ ላይ የሚጭን ወይስ የብዙሀኑን ህዝብ ስሜት ተረድቶ ከዚያ አንፃር የሚንቀሳቀስ . . . . . . የእኔ አውቅልሀለሁ ሶሻሊስታዊ
አስተሳሰብ ከነሰንኮፉ ወጥቶልን ህዝቡንና ስሜቱን/ ፍላጎቱን የምናከብረውና የምናገለግለው መ
ቼ ይሆን? ይላል እንግዲ ሳነብ ያገኘሁት …ታሪክ ነው ዝም ብለህ አንብብ ።

Filed in: Amharic