>
5:16 pm - Monday May 23, 2107

የችግሩ ምንጭ ራሱ የብሔር ፌደራሊዝሙ ነው (አቤነዘር ይስሃቅ)

የብሔር ፌደራሊዝም ከግጭት በቀር ምንም አይነት መፍትሄ ማምጣት የማይችል አወቃቀር መሆኑን ባለፉት 26 ዓመታት አይተናል። የተለያዩ ሁለት ሀገሮች ይመልስ “የድንበር ላይ ግጭት” የተለመደ ሆኗል። በአማራና በትግራይ፣ በኦሮሞና በሶማሌ፣ በኦሮሞና በደቡብ . . .ክልሎች መካከል ያለው ግጭት የብሔር ፌደራሊዝም ያመጣውና መፍትሄም ሊሰጠው ያልቻለውና የማይችለው ነገር ነው።

በቀድሞ ዘመን አርብቶ አደሮች በግጦሽ መሬት የተነሳ መጋጨታቸው የተለመደ ነበር። እንደነዚህ አይነት ግጭቶች የአርብቶ አደሮችን የአኗኗር ዘይቤ በመለወጥ መቅረፍ ይቻላል። በብሔሮች መካከል ያለን የድንበርና መሬት ይገባኛል ግጭት ግን በዚህ መልኩ ማስወገድ አይቻልም። በአርብቶ ወይም አርሶ አደሮች መካከል በገጠሪቱ ኢትዮዽያ የሚከሰቱ ግጭቶች መሰረተ ልማቶች ሲስፋፉ፣ ትምህርት ሲስፋፋ፣ ከተሞች ሲመሰረቱና ሲስፋፉ ወዘተ ይወገዳል። በተቃራው በብሔሮች መካከል አሁን ያለውን “የድንበርና የመሬት ይገባኛል” ግጭትን በዚህ መልኩ ማስቀረት አይቻልም። ጉዳዩ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም በላይ “ማንነቴ” ከሚል አስተሳሰብና ዕምነት ጋር ስለተቆራኘ በቦታው ላይ መሰረት ልማትን በማስፋፋት መፍትሄ መስጠት አይቻልም።

በወልቃይት የተነሳ በአማራዎችና በትግሬዎች መካከል ያለው ጉዳይ፣ በምስራቅ ኦሮሚያ በኦሮሞዎችና በሶማሌዎች መካከል ያለው የይገባኛል ግጭት. . .ከታሪክ፣ ከማንነት፣ ከባሕል፣ ከመሬት ይገባኛል፣ ከሰብአዊነትና ከሕልውና ጋር የተያያዘ ጉዳይ ስለሆነ በብሔር ፌደራሊዝም አወቃቀር ስር ተሆኖ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም። የችግሩ ምንጭ ራሱ መፍትሄ መሆን አይችልም።

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት ከብሔር ፌደራሊዝሙ ጋር ተደማምሮ “የድንበርና የመሬት ይገባኛል” ግጭቶች እየተባባሱ እንጂ እየበረዱ አይሄዱም። ይሄ የብሔር ፌደራሊዝሙ አንዱ መግለጫ ባሕሪው ነው።

አሁን ያለውን ግጭት ማስወገድ የሚቻለውም በሕዝበ ውሳኔ ሳይሆን ለአስተዳደርና ለልማት አመቺ የሆነ አወቃቀርን ስንመሰርት ብቻ ነው። ይሄ አወቃቀር ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዳያስተዳድሩ አይከለክልም። በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ፣ ባሕላቸውን እንዳይጠብቁና እንዳያሳድጉ አይከለክልም። የሚዋቀሩት አስተዳደሮች ኢኮኖሚን፣ ልማትን፣ የተፈጥሮ ሀብትንና አቀማመጥን፣ የሰዎችን አሰፋፈርንና አኗኗርን ታሳቢ ያደረገ ስለሚሆን የሚጎዳ ግለሰብም ይሁን ብሔር አይኖርም።

በተቃራኒው የብሔር ፌደራዚም በብሔሮች መካከል ሰላምንንና መረጋጋትን ማምጣት አልቻለም። አይችልምም። የግለሰቦችንም መብት ይደፈጥጣል። አሁን ያለው አወቃቀር አንድን ኢትዮዽያዊ የሚያውቀው በሆነ ብሔር ሥር ከገባ በኋላ እንጂ እንደግለሰብ ዕውቅና አይሰጠውም። እናም ለሀገሪቱ ሰላም፣ ለብሔሮች ዕኩልነትና መከባበር፣ ለግለሰቦች መብት መከበር. . . ትክክለኛ መፍትሄ የሆነውን አወቃቀር መተግበር ግድ ይላል።

አሁን በብሔሮች መካከል “በድንበርና በመሬት ይገባኛል” የተነሳ የተከሰቱትን ግጭቶችንና ደም መፋሰሶችን ሊያስቀር የሚችለው ለልማትና ለአስተዳደር አመቺ በሆነ ሁኔታ የሚደረገው አወቃቀር ነው። አለበለዚያ ልክ ኤሪትሪያና ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ እንደሚጋጩት ሁሉ ትግራይና አማራ፣ ኦሮሞና ሶማሌ . . . ሁል ጊዜ እንደተናቆሩ ይኖራሉ።

Filed in: Amharic