>

የጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ ክፍተቶች …[አዜብ ጌታቸው]

ውድ አንባቢያን እንኳን ለአዲሱ አመት በሰላም አደረሳችሁ! እያልኩ የአሮጌውን ዓመት የመጨረሻ መጣጥፍ አልያም የአዲሱን አመት የመጀመሪያ መጣጥፌን ጀባ ልበል፦

ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴን ብዙዎች እንደሚያውቁት አስባለሁ። በተለይ በጉልምስና እድሜና ከዛም ከፍ ባለ የዕድሜ ክልል የሚገኘው ኢትዮጵያዊ አለምነህ ዋሴን ያውቀዋል። በደርግ ዘመን በኢ.ዜ.አ ውስጥ ሲሰራ ለየት በሚለው ጆሮ ገብ ድምጹና ልዩ በሆነው የዜና አቀራረቡ ተወዳጅ እንደነበር ራሴን አንድ ብዬ በማስረጃ ምስክርነት እጠራለሁ።

ዜና-ፋይል! የሚለው የዜና አቀራረብ ፎርማት ሲታወስ አለምነህ ዋሴ፤ ዳሪዎስ ሞዲ፤ ነጋሽ መሃመድ፤ ንግስት ሰልፉን …. የማያስታውስ ካለ እሱ በዛ ወቅት ያለጥርጥር ከኢትዮጵያ ውጭ ነበር ። የዛሬውን አያድርገውና ኢ.ዜ.አ ብቸኛዋ የዜና ምንጫችን ስለነበረች እነ አለምነህን አለማወቅ አይቻልም።

በተለይ አለምነህ ዋሴ ደግሞ በአሜሪካና ኢራቅ ጦርነት ወቅት የሚያቀርበው ዘገባ እንዴት በጉጉት ይጠበቅ እንደነበር ሳስታውስ፤ ዜና ድሮ ቀረ! ለማለት ይዳዳኛል። ስለ አለምነህ የትናንት ሥራ ይህን ያህል ካልኩ ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ ወደ ሆነኝ ወደ ወቅታዊው ሙያዊ እንቅስቃሴው አድምታ ላምራ።

ከጥቂት አመታት በፊት ተቀማጭነቱን በእስራኤል ያደረገው አለምነህ ዋሴ ‘የአለምነህ ዋሴ ዜና” ወይም በምህጻረ-ቃል “አዋዜ” በሚል መጠሪያ በዘመኑ ቴኮኖሎጂ (አፕ) በመታገዝ በአንኳርና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የግሉን ምልከታ እያቀረበ ይገኛል።

ጆሮ ገብ ድምጹና ለየት ያለው የአቀራረብ ስልቱ ሲቀናጁ አሁንም ድረስ አድማጭን የመሳብ አቅማቸው ድንቅ ነው። የአድማጭን ቀልብና ጆሮ ጭምድዶ የመያዝ ጉልበት ያላቸውን እነዚህን ተስዕጦዎቹን እየተጠቀመ የሚያቀርባቸው ትንተናዎችና (የግል ምልከታዎች) ግን አንዳንዴ ሙያው ግድ ከሚለው መርህ ሲያፈነግጡ፤ ሌላ ግዜ ደሞ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ከማስረጃ ይልቅ በግሉ ምናባዊ እይታ ሲታጀቡ ይስተዋላል። ምናባዊ እይታ የደራሲ እንጂ የጋዜጠኛ ትጥቅ አትመስለኝም። ምክንያቱም አንድ ጋዜጠኛ በሚዘግበው ወይም ትንታኔ በሚያቀርብበት ጭብጥ ላይ ምናባዊ እይታውን ሲያክልበት ከጉዳዩ አስኳል ጭብጥ ይርቃል ። ከአስኳል ጭብጡ በራቀ መጠን ደግሞ (fair and balanced) ከሚለው የጋዜጠኝነት መርህም ይርቃል። አለምነህም ላይ ካስተዋልኳቸው ክፍተቶች አንዱ ይህ ነው። በምናባዊ ዕይታ የሚታጀብ ትንተና።

ሌላው በአለምነህ ያየሁት ክፍተት አውቆም ሆነ ሳያውቅ የሥርአቱ ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ መሆኑን ነው። እነዚህ ክፍተቶቹ ደግሞ ሁለት ጥያቄዎች አጭረውብኛል።

1ኛው/ አለምነህ ስለ ወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለው መረዳት ምን ይመስላል?
2ኛ/ ለሃገሩ ፖለቲካ ራሱን የገለለ የውጭ ታዛቢ ወይስ ይመለከተኛል የሚል ተቆርቋሪ? (ይህን የምለው በቅርቡ እባካችሁ ወደ አንድ ጫፍ አትውሰዱኝ የሚል ተማጾኖ ቢጤ ሲያቀርብ ስላደመጥኩት ነው። ሁለቱ ጫፎች እነማን ናቸው? እሱስ ከሁለቱም ጫፎች መሸሽን የመረጠው ለምንድነው፡?

በነገራችን ላይ ይህን ጽሁፍ የጻፍኩት የአንጋፋውን ጋዜጠኛ ስራ ለማጠልሸት አልያም በመሰለኝና በደሳለኝ ስሜት እየተነዳሁ አይደለም። ማስረጃ ይዤ እንጂ። የጽሁፌም ዋና አላማ እንደ አንድ አድማጭ የታዘብኳቸውን ክፍተቶች ማሳየት ብቻ ነው። አስተያየቴን ከተቀበለው መልካም ካልተቀበለውም በጨረታው አይገደድም አይነት መሆኑ ነው።

ወደ መሃል ልዝለቅ፦

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት አለምነህ ዋሴን ከምናስታውስባቸው ስራዎቹ ዋናው የአሜሪካና ኢራቅ ጦርነት ዘገባው ነው።

በዛ ወቅት በማለዳው የኢዜ.አ ዜና አለምነህ  ባግዳድ ጸጥ ረጭ ብላ አድራለች፤ ምድሯን የተቆለመመ ብረት፤ የግንብ ፍርስራሽ፤ አቧራ …… ሞልቶታል  እያለ በአይነ ልቦናችን ወደ ባግዳድ ተጉዘን አዳሯን እንድንመለከት የሚያደርግበትን አቀራረቡን ዛሬም ድረስ በከፊልም ቢሆን አስታውሰዋለሁ። ሰእላዊ ዜናውን ያቀርብልን የነበረው ምናልባት በምስል ያገኘውን የባግዳድን የማለዳ ገጽታ ወደ ቃላት ተርጉሞ፤ አልያም ገጽታውን የዘገበ ዜና ወደ አማርኛ መልሶ ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ አለምነህ በአሜሪካና ኢራቅ ጦርነት የማይረሳ አሻራውን በማሳረፉ ሁላችንም የምንስማማ ይመለኛል። “እጅ መስጠት የለም አሉ ሳዳም ሁሴን”  የሚለው ድምጹ ዛሬም ድረስ ይሰማኛል።

እንዳሁኑ መረጃ ከአንዱ የአለም ጫፍ ወደ ሌላው የአለም ጫፍ በብርሃን ፍጥነት በማይደርስበት በዛን ወቅት አለምነህ ዋሴ የአሜሪካና የኢራቅን ጦርነት እግር በግር ተከታትሎ የሚዘግብልን ከአለም አቀፍ የዜና ዲስፓች ላይና ከእንግሊዘኛ መጽሄቶች ላይ እንደነበር ሲናገር የሰማሁ ይመስለኛል። በግዜው እሱም ከኢ.ዜ.አ የዜና ዲስፓች ሌላ አማራጭ አልነበረውም ። እኛም እሱን ከመስማት በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበረንም። አሁን ግን ግዜው ተለውጧል። እኛም እልፍ ኧእላፍ አማራጭ አለን እሱም እንደዛው።

ወደ ጽሁፌ አስኳል ስገባ፦ አለምነህ ዋሴ “በአዋዜ” ስርጭቱ ከለቀቃቸውና ክፍተት ካየሁባቸው ስራዎቹ ለአብነት ያህል ሁለቱን ብቻ በመጥቀስ ለማሳየት እሞክራለሁ።

1ኛው/ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ሊኖራት የሚገባ ልዩ ጥቅምን ያሚዘረዝርውን ረቂቅ በተመለከተ ያቀረበው ዘገባ ሲሆን፤

2ኛው/ በቅርቡ በኦሮሚያ የተጠራውን የአምስት ቀን የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ ጋር አያይዞ በጃዋር መሃመድ እንቅስቃሴና ማንነት ላይ ያቀረበው ትንተና/ምልከታ ነው

በተናጥል ልያቸው፦

1ኛ/ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖራትን ልዩ ጥቅም የሚደነግገውን ረቂቅ በተመለከተ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገና ለኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ቅርበት ያለው የታመነ ምንጭ ለአዋዜ በተለይ አቀብሏል ብሎ እሱም ለኛ ያቀበለንን ዘገባ ሳደምጥ፤ ወዲያውኑ በአይምሮዬ ያጫረው ጥያቄ አለምነህ ስለ ወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይም ስለ ህውሃት መራሹ መንግስት ያለው መረዳት ምንድነው ? የሚል ነው።

አለምነህ ዘገባውን ሲጀምር ፤ ለኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ቅርብ የሆነው፤ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው “ታማኝ ምንጩ” በኦሆዴድ የቀረበው ረቂቅ እንዳስደነገጠው ገለጸልኝ ይልና የረቂቁን ይዘት ይተነትናል፦

በትንተናው ፡ የአዲስ አበባን ስም ከመቀየር ጀምሮ፤ የኦሮሞ ተወላጅ ሁሉ ከሊዝ ክፍያ ነጻ እንዲሆን፤ በተቃራኒው የሌላው ብሄር ተወላጅ እጥፍ ሊዝ እንዲከፍል፤ በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ዋና ዋና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ ሃላፊዎች የኦሮሞ ተወላጆች እንዲሆኑ ፤ መንገዶች በኦሮሞኛ ቋንቋ እንዲሰየሙና …. ሌላም ሌላም ይዘረዝራል።

ህውሃት፤ ብአዴን፤ ኦሆዴድና ደህዴን እያንዳዳቸው በ5 ወንበር የሚወከሉበት ባለ 20 ወንበሩ የኢሃዴግ ስራ አስፈጻሚ በዚህ ረቂቅ ላይ ውይይት አድርጎ ድምጽ በመስጠት እንደሚወስን ይጠበቃል። ይላል በተለይ ለአዋዜ ከታማኝ ምንጩ የተላከው መረጃ።

ይቀጥላል፦  ህውሃትና ብአዴን አንድ ላይ ሆነው የኦሆዴድን የይገባኛል ጥያቄ እንደሚቃወሙ ይጠበቃል ይልና ደቡብ ህዝቦች ግን እስካሁን አቋሙ አልታወቀም ሲል ታማኝ ምንጩ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሜ ውሳኔን አጓጊነት አድምቆ የነገረውን ዘግቧል።  በመጨረሻም ስለ ድምጽ አሰጣጡ የራሱን አረዳድ በማከል “ በድምጽ አሰጣጡ ሂደት 20ው አባላት እኩል 10 ለ 10 ከሆኑ ጠ/ሚንስትሩ ያሉበት ወገን አሸናፊ ይሆናል” ሲል ይነግረናል።

ይህ በሆነ በማግስቱ ማለትም Jun 17, 2017 ለጆሮ ባበቃው ዘገባው ደግሞ ፤ እንደተፈራው ሳይሆን የኦህዴድ የይገባኛል ጥያቄ ውድቅ ሆነ ብሎ ይኽው ታማኝ ምንጩ የነገረውን እሱም ለኛ ነገረን። ታዲያ ምን አጠፋ ? ምንም? እኔም እኮ አጠፋ አላልኩም።

ጥያቄ ግን አለኝ፤ አለምነህ ስለ ኢህአዴግና በውስጡ ስላሉት 4 ድርጅቶች መስተጋብር ያለው መረዳት ምንድነው? 4ቱም ድርጅቶች እውን እኩል መብትና ጉልበት አላቸው ብሎ አስቦ ይሆን ታማኝ ምንጩ የነገረውን የስራ አስፈጻሚውን ውሳኔ እንደ ዋንጫ ጫወታ አጓጊ አድርጎ ለማቅረብ የሞከረው ? እውን አንድም ጉዳይ ቢሆን ያለ ህውሃት ይሁኔታ ሊተገበር ይችላል ብሎ ያስባልን? የሚሉ ጥያቄዎችን ላነሳ ተገድጃለሁ።

እንደኔ እይታ፤ አለምነህ ለስራ አስፈጻሚው ቅርብ ያለው ታማኝ ምንጩ የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ አድርጎታል። ከህውሃት መራሹ መንግስት ጋር ለ26 አመታት በነበረን ቆይታ በግልጽ ካወቅናቸው ባህሪው አንዱ፤ በመንግስት ሚዲያ ከሚነገር ይልቅ በሌላ የዜና አውታር ቢቀርብ ህዝብ ሊቀበለው ይችላል ብለው ያሰቡትን አዘናጊ ወሬ ሆን ብለው እንደሚያሾልኩ ነው።

በዚሁ መሰረት ለኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ቅርብ የሆነው የአለምነህ ታማኝ ምንጭ፤ አስደንጋጭ ያለውን የረቂቁን ይዘት ስሜን ደብቅልኝ ብሎ አቀበለው(ሆን ብሎ አሾልኮ ሰጠው)። አለምነህም በተለይ ለአዋዜ የደረሰው በሚል እንዳለ ለኛ አቀበለን። የሃገሩ ህልውና የሚያሳስበው ኢትዮጵያዊ ዜጋ የአለምነህን ዘገባ ሲያደምጥ፤ ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል?  በሚል ቁጭት ሊብከነከን እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓልና ፤ አስደንጋጩ የተባለው ዜና በተደመጠ በማግስቱ ይኽው የአለምነህ ታማኝ ምንጭ “የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አስደንጋጩን ረቂቅ ህግ ውድቅ አደረገው” ብሎ የምስራቹን አቀበለው። አለምነህም አሁንም ለኛ አቀበለን።

ልብ በሉ! ቀደም ሲል ህውሃትና ብአዴን አንድ ወገን ሆነው የኦሮሚያን የይገባኛል ጥያቄ ይቃወማሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ደቡብ ህዝቦች ግን እስካሁን አቋሙ አልታወቅም የሚል ስጋትን ያንቀረዘዘ ዘገባ አድምጠናልና፤ አሁን ደግሞ ህውሃትና ብአዴን ደቡብ ህዝብንም ከጎናቸው አሰልፈው አዲስ አበባን ከተጋረጠባት አደጋ እንደታደጓት ሲነገረን በደስታ ጮቤ እየረገጥን አበጃችሁ..! አንበሶች…! ብለን እንድናጨበጭብ ተጠብቋል። ይሁንና ህውሃትን በቅጡ የሚያውቀው ኢትዮጵያዊ እንኳን ሊያጨበጭብ ….።

እንግዲህ ይህ በህውሃት ተደርሶ፤ በህዋህት ዳይሬክተርነት ተቀናብሮ በቀረበልን የፕሮፓጋንዳ ድራማ አለምነህ ዋሴ በማያውቀው መንገድ ታማኝ ምንጬ ባለው ግለሰብ ተመልምሎ ተዉኗል ባይ ነኝ። ለዚህም ነው አለምነህ የአገዛዙ ሰዎች የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ ሆኗል የምለው። ለዚህም ነው ለስራ አስፈጻሚው ቅርብ የሆነው የአለምነህ ታማኝ ምንጭ ታማኝነቱ ለአለምነህ ወይስ ለሥራ አስፈጻሚው? የሚል ጥያቄ ልናነሳ ግድ የሚለው።

እንደኔ፤ እንደኔ! ህውሃት ጠፍጥፎ በሰራቸው ሶስቱ ድርጅቶች ላይ ያለውን ፍጹም የሆነ የበላይነት በአግባቡ የሚረዳ ሰው ፤ የስራ አስፈጻሚው ውሳኔ እንደ ዋንጫ ጨዋታ አጓጊ ሊሆንበት አይችልም። ለዚህም ነው አለምነህ ስለ ኢህአዴግና በውስጡ ስላሉት ድርጅቶች መስተጋብር ያለው መረዳት  ምንድነው? በማለት ለመጠየቅ የተገደድኩት። ይህን በዚህ ላብቃ።

2ኛ ሌላው የአለምነህን ሙያዊ ክፍተት ያስተዋልኩበት ሥራው፤ በቅርቡ በኦሮሚያ ከተጠራው የአምስት ቀን የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ ጋር በተያያዘ ስለ ጃዋር መሃመድ ባቀረበው የግል ምልከታው ነው።

አለምነህ በኦሮሚያ የተጠራው የ5 ቀን የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ያቀረበው ይህ ዘገባ/ምልከታ (ዘገባና ምልከታ) አብዛኛው ክፍል ኦብዘርቨር የተሰኘው የዜና አውታር ከሁለት አመት በፊት ስለ ጃዋር መሃመድ ማንነት፤ ስብዕናና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያቀረበውን ጽሁፍ መሰረት ያደረገ ነው። ሲጀመር አለምነህ ስለ ጃዋር መሃመድ ለማወቅ ከሁለት ዓመት በፊት በኦብዘርቨር የተጻፈን ጽሁፍ መሰረት ማድረግን ለምን እንደመረጠ አልገባኝም፡፤ ምክንያቱም ጃዋር ራሱ ከጻፋቸው ጽሁፎችና በተለያየ ግዜ ከሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ብቻ በመነሳት ከኦብዘርቨር በበለጠ ጃዋር ጃዋር የሚሸት ምልከታ ሊያቀርብ ይችላልና ነው።

ለምሳሌ ጃዋር በአካባቢው ካሉት ሰዎች ማንም ቢሆን ሊቃወመው እንደማይፈቅድና ደፍሮ የተቃወመም፤ እጣ ፈንታው መባረር እንደሆነ ኦብዘርቨርን ጠቅሶ የቅጂ ቅጂ ከሚያስደምጠን፤ በጃዋር የተባረሩት የቅርቡ ሰዎችን ኦርጅናል ጽሁፍ ጠቅሶ ቢጽፍ ለጃዋር ማንነት የበለጠ ቅርበት ያለው ስራ ሊሰራ ይችል ነበር እላለሁ። (እዚህ ውስጥ ብዙ መረጃዎች ነበሩ)

የሆነው ሆኖ ከሁለት አመት በፊት በኦብዘርቨር ስለ ጃዋር በተጻፈውና በአለምነህ ዘገባ በድጋሚ በተነገሩት የጀዋር የማንነት መገለጫዎች በአብዛኞቹ እስማማለሁ። የማልስማማው አለምነህ ስለ ጃዋር ባቀረበው የራሱ ምልከታ ላይ ነው።

አለምነህ ጃዋርን ሲገልጸው፤ የገጽታ (ፕሮፋይል)ግንባታ ማስታወቂያ እየሰራለት እስኪመስል ድረስ አወድሶታል።

“ከዚህ ቀደም በዲያስፖራ ታሪክ ሆኖና ተደርጎ የማያውቅ ልዩ ኃይል መሆን የቻለ የፖለቲካ ሰው መሆኑ ግን እሙን ነው፡” በማለት እጅግ በጣም የተጋነነ ጠንካራ ስብዕና አላብሶታል።  ክፍተቱን ማሳየት እንጂ ምክንያቱን መመርመር የጽሁፌ አላማ አይደለምና ለምን ብዬ አልጠይቅም።

በነገራችን ላይ አለምነህ የተዋጣለት የማስታወቂያ ስራ ባለሙያ እንደሆነም አውቃለሁ። የንግድ ማስታወቂያ በባህሪው ግነትን ያዘወትራል ።  ለዚህ አባባሌ መገለጫ የሚሆን ራሱ አለምነህ(ይመስለኛል) የሰራው አንድ ማስታወቂያ ትዝ ይለኛል።

ማስታወቂያው የተሰራው “ባለ ጋሻ” የተሰኘውን ክር ለማስተዋወቅ ነበር ። እናም ማስታወቂያው ሲጀምር  “ ብዙዎች የልብስ ማማሩ ከስፌቱ ነው ይላሉ! እኛ ግን ከክሩ ነው እንላለን….” በማለት ነበር ለአንድ ልብስ ማማር ከስፌቱ ይልቅ የሚሰፋበት ክር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የሚያስተዋውቀው፡፤ ይህ ወደ ውሸት የሚጠጋ ግነት በራሱ ማስታወቂያው ከሰው ትውስታ እንዳይጠፋ ስለሚያደርግ ስለ ክር ስናስብ ባለ ጋሻ ክርን እንድናስብ ያደርጋልና ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። እኔም ከረዥም ግዜ በኋላ ላስታውሰው የቻልኩት በዚሁ ግነቱ መሆኑን ልብ ይሏል።

ወደ ዋናው ነጥብ ልመለስ፤ አለምነህ እንደ ባለጋሻው ክር ማስታወቂያ የኦሮሚያ ክልል የተቃውሞ እንቅስቃሴ ድሩም ማጉም ጃዋር መሃመድ ነው በሚል ያቀረበው ግነት የተጣባው ትንታኔ ግን እንደ ንግዱ ማስታወቂያ አበጀህ ብለን የምናልፈው አይደለም። አለምነህ ምነካው ..? የሚል የአግራሞት ጥያቄ የሚያጭር እንጂ!።

አለምነህ አድማው በጃዋር አቃጅና ነዳፊነት፤ በቄርዎች አስፈጻሚነት የሚከናወን እንደሆነ ሲያቀርብ ፤ ጃዋር ራሱ ስለ አድማውና ስለ ቄሮዎች የተናገረውን ያደመጠ አልመሰለኝም። ጃዋር አድማውን ያቀዱትም የተገበሩትም ቄሮዎች መሆናቸውን ግልጽ አድርጎ ተናግሯል። ክሬዱትንም ሙሉ ለሙሉ የሰጠው ለነሱ ነው። አለምነህ ግን ቄሮዎቹን የጃዋርን
ትዕዛዝ አስፈጻሚ አድርጎ ክሬዲታቸውን አሳንሷል። ይህ ደግሞ መረጃን በወጉ ያለመሰለቅ የፈጠረው ክፍተት ይመስለኛል።

አለምነህ ጃዋርን መካቡን ይቀጥልና፤

“ይህ እውቀቱን፤ የኮምፒውተር ቁልፍና ሚዲያ የታጠቀ የዲያስፖራ ባለስልጣን አታጋይ፤ ከአስር ሺህ ኪሎሜሮች ርቀት ላይ ሆኖ በኦሮሚያ ክልል የምትገኘውን አንዲት የሶፍት ፔፐር መሸጫ መደብርን ወይም አንድ ባለ 3 ጎማ ባጃጅን እንድትንቀሳቀስ ወይም እንዳትንቀሳቀስ የማዘዝ ወይም የመሰማት ኃይል እንዳለው እያሳየ የሚገኝ ነው፡፤” ይለዋል፡፤

ይህ ደግሞ አለምነህ የግል ምልከታውን ሊጠቀስ በሚችል መረጃ አልያም ሊቀርብ በሚችል ማስረጃ ከማስደገፍ ይልቅ፤ ምናባዊ እይታውን በመቀላቀል ከዋናው ጭብጥ የራቀበት ክፍተቱ ነው። በምናብ አብረነው ወደ ኦሮሚያ ክልል ተጉዘን በጃዋር ትዕዛዝ የተዘጋች ሱቅና አንድ ስራ ያቆመች ባጃጅ እንድናይ እየጋበዘ የጃዋርን ኃያልነት ሊያሳምነን ይሞክራል። ይህ  የታሪክ ቀመስ የፈጠራ ስራ (ድርሰት) አቀራረብ ስልት እንጂ አንድ ጋዜጠኛ እውነታን እንደወረደ የሚዘግብበት አልያም በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን የግል ምልከታ የሚያቀርብበት ስልት አይደለም።

በእርግጥ የምናወራው ስለ ድርሰት ቢሆን ኖሮ አለምነህ የጃዋርን የአዛዥነት እጅ ከ10 ሺህ ኪሎ ሜትሮች በላይ አርዝሞ ከአሜሪካ ተዘርግቶ ሻሸመኔ ላይ ያለች ሱቅን እንዲዘጋ ማድረጉ ምንም ችግር ባልኖረው ። ምክንያቱም ደራሲው የምናባዊ ጉዞው ካፒቴን ራሱ ነውና ሙሉ ነጻነት አለው። አንድ ጋዜጠኛ ግን እንዲህ ሆነ ወይም እንዲህ ነው፤ በሚል ለሚያቀርበው  ጭብጥ የሚታይ የሚዳሰስ ማስረጃ ማቅረብ ግድ ይለዋል። እዚህ ላይ የሚታየው የሚዳሰሰው ማስረጃ ደግሞ ጃዋር የአድማው መሪም፤ አቃጅም አለመሆኑን በእራሱ አንደበት መመስከሩ ነው ። ታዲያ አለምነህ ምነካው? ብል ይፈረድብኛል ትላላችሁ?

አለምነህ አሁንም ጃዋርን መካቡን ሲቀጥል፤ ኦብዘርቨር የተሰኘው የዜና አውታር ጃዋርን የኦሮሚያን እንቅስቃሴ እንዲግለበለብ ያደረገ ሲል እንደገለጸው ይነግረንና፤ በማስከተለም “ አሁን ደግሞ ሌሎች ያቀጣጠሉትን ከማግለብለብ አልፎ እራሱን የቻለ ነበልባል ሆኗል” በማለት ኦብዘርቨር ከሰጠው የውዳሴ እርከን ሽቅብ አምዘግዝጎ ከአግለብላቢነት ወደ ነበልባልነት ያሸጋግረዋል ።  ለዚህም አባባሉ ስሜቱን እንጂ መገለጫ አልቀረበም።

አለምነህ ይህን ዘገባ ያቀረበው የ5 ቀናቱ አድማ በተጀመረ በ2ኛ ቀን ነው፡፤ ጃዋርን በዚህ ደረጃ ለመካብ ያነሳሳው ምክንያት ምናልባት እንደ ሁላችንም አድማው በታሰበለት መርሃ-ግብር ለአምስት ቀናት እንደሚቀጥል ያሳደረው እምነት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ምልከታውን አንድ ቀን ለማዘግየት ቢችል ኖሮ የምልከታው ይዘት ፍጹም የተለየ ይሆን እንደነበር ጥርጥር የለኝም፡፤ ምክንያቱም ምንም እንኳ እነጃዋር የ5ቀኑ አድማ በሁለት ቀን ውስጥ በስኬት ተጠናቋል ቢሉም፤ ስኬቱ ምንድነው ? ለሚለው ጥያቄ መልስ አልተገኘለትምና አለምነህም ውዳሴውን ቀነስ ያደርጋል አልያም ጭራሹንም ስራውንም አያቀርብም ብዬ አስባለሁ።

አዲስ አበባ የሚታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ “በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የተጀመረው የንግድ አድማ 4ኛ ቀኑን ይዟል ” በማለት ያወጣው ዜና ጃዋር ከቄሮዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው። ምናልባት ይህን የአዲስ አድማስን ዘገባ አለምነህ ሲያነብ አድምቆ የጻፈው የጀዋር የአድማ መሪነት ገድል መጠን ያለፈ መሆኑን ይረዳል ብዬ እገምታለሁ። እዚህ ጋ ችኩልነትም ሌላው ክፍተቱ መሆኑ ነው፡፤ ( በአንድ ወቅት ድምጻዊ ጌድዮን ሞተ ብሎ የዘገበውንና ይቅርታ የጠየቀበትም አጋጣሚ በዚሁ ሙያዊ ክፍተት መገለጫነት ሊጠቀስ የሚችል ነው።)

አለምነህ በተለይ ከአገር ጉዳይ ጎን ለጎን እያዛነቀ የሚያቀርብልን አንኳር የአለም አቀፍ ዜና ዘገባዎችና ሪፖርቶች የተዋጣላቸው ናቸው።  ትኩረቱን ሁሉ በአገሩ ጉዳይ ላይ ብቻ  በማድረጉ የምድራችንን ጉልህ ክስተት ለመከታተል ግዜ ላጠረው ኢትዮጵያዊ ጠቃሚ የመረጃ ስንቅ ናቸውና በርታ ለማለት እሻለሁ። በነዚህ አለም አቀፍ ዘገባዎች ላይ ሊከሰት የሚችል ክፍተትም ሆነ ስህተት ቢኖር እዳው ገብስ ነውና አሳሳቢ አይሆንም።

ነገር ግን ብዙ ያልጠገጉ ፈውስ ናፋቂ ቁስሎች እዛም እዛም በፈነዳዱባት፤ ብዙ ምርቅ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ ባላገኙበት በሃገራችን ፖለቲካ ዙሪያ የምናቀርበው ምልከታም ሆነ ዘገባ ፍጹም የሆነ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑን አለምንነህን ለሚያክል አንጋፋ ጋዜጠኛ ልመክር አይዳዳኝም።

በተለይ ዘገባውም ሆነ አመለካከቱ የሚቀርበው እንደ አለምነህ ባሉ ተሰሚነትን ባዳበሩ ታዋቂ ሰዎች ሲሆን ደግሞ እያንዳንዷ ቃልና አረፍተ ነገር ሚዛን ላይ ልትቀመጥና በማስረጃ ልትፈተን ግድ ስለሚል ከቃላት ምርጫ ጀምሮ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄም በዛው መጠን ከፍ ሊል ይገባል። እንደ እኔ ያለ ተራው ሰው ያሻውን ቢል ያን ያህል ጎጂም አሳሳችም አይሆንም።

በመሆኑም ከዚህ በመነሳት በመደምደሚያዬ ላይ ለአለምነህ እንደ ምክርም ባይሆን ሊያስብበት ይገባል የምላቸውን ጉዳዮች ልጠቁም እወዳለሁ።

1ኛ በግል የሚደርሱህን መረጃዎች በተለይም ከአገዛዙ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ  ግንኙነት ካላቸው ወገኖች የምታገኘውን መረጃ እንደወረደ ከመልቀቅህ በፊት ብትመረምረው፡፤

2ኛ ቅራኔ እንደ እንጉዳይ በፈላበት ማህበረሰብ ውስጥ አንዱን ወገን ማወደስ በራሱ ሌላውን ማኮሰስ ተደርጎ ይወሰዳልና በግለሰቦች ስብዕና ላይ ያለህን ምልክታ ከማቅረብ ተቆጥበህ በአንኳር የጋራ ጉዳዮች ላይ ብቻ ብታተኩር።

3ኛ/ ባለህ እውቅናና የሥራ ልምድ በየትኛውም አለም ጥግ ያለውን ኢትዮጵያዊ ለቃለ መጠየቅ ጋብዘህ ማነጋገር ትችላለህና ከፈረሱ አፍ እንደሚባለው ኦርጂናል ስራዎችን (በአገር ጉዳይ ላይ) ለማቅረብ ብትሞክር ።

እንደ መደምደሚያ

የጽሁፌ መነሻ የሆነኝን ጃዋር መሃመድን በጨረፍታም ቢሆን ሳልመለከት ማለፍ ተገቢ አልመሰለኝም፡፤ አዎ ጃዋር ኦብዘርቨርም እንደታዘበው ራስ ወዳድ፤ አምባገነን፤ አደጋ የሚሰጋ(ፈሪ ላለማለት ይመስለኛል) የሚሉት ባህሪያት ይገልጹታል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ጃዋር፤ ወጥ የሆነ አቋም የሌለው፤ በአንድ እጁ ለአክራሪ እስላምና እያጨበጨበ፤ በሌላ እጁ ለአክራሪ ብሄርተኝነት (ኦሮሞነት) ማጨብጨብ የሚፈልልግ። ቢሆንለት ኦሮሞ ሁሉ ሙስሊም እንዲሆን የሚፈልግ ሰው ነው። ጃዋር መላ በጠፋው ግዜ ከአንድነት ሃይሉ ጋር አብሮ ስለመስራት ይሰብካል፤ ጉልበት በስተሰማው ግዜ ኦሮሞ ፈርስት ብሎ ያውጃል። ባጠቃላይ ብዙ ነገር የተዘበራረቀበትና አድማጩ ሊሰማው የሚፈልገውን ብቻ እየመረጠ የሚደሰኩር ስለመሆኑ እላይ እታች ሳንል በተለያዩ ሶስት ቋንቋዎች የሰጣቸውን ቃለ መጠይቆች ማድመጡ በቂ ይመስለኛል። የአማርኛ፤ የእንግሊዘኛና፤ የኦሮሞኛ አመለካከቶች ያሉት የሚገርም ፖለቲከኛ ነው ጃዋር።አበቃሁ!

ቸር ይግጠመን

አዜብ ጌታቸው

azebgeta@gmail.com

Filed in: Amharic