>

ከደብረ ሊባኖስ ገዳም የ“ውሻ ገደል” መንደር ከ2ሺ በላይ ነዋሪዎች ይነሣሉ

አዲስ አድማስ
ከደብረ ሊባኖስ ገዳም የ“ውሻ ገደል” መንደር ከ2ሺ በላይ ነዋሪዎች ይነሣሉ
ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ዕድሜ ባስቆጠረው ደብረ ሊባኖስ ገዳም አካባቢ የተቆረቆረው መንደር ወደ ከተማነት በመለወጡ፣ የገዳሙ ታሪካዊና መንፈሳዊ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን መንግሥት፣ ነዋሪዎቹ ከቦታው የሚነሡበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች አስታወቀ፡፡

• ከ60 እስከ 70 ሚሊየን ብር ካሳ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ይፈጸማል
• የገዳሙ ታሪካዊና መንፈሳዊ ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል ተባለ
• መካነ ቅርሱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየታሰበ ነው – ክልሉ

ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ዕድሜ ባስቆጠረው ደብረ ሊባኖስ ገዳም አካባቢ የተቆረቆረው መንደር ወደ ከተማነት በመለወጡ፣ የገዳሙ ታሪካዊና መንፈሳዊ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን መንግሥት፣ ነዋሪዎቹ ከቦታው የሚነሡበትን ሁኔታ እንደሚያመቻች አስታወቀ፡፡

ማኅበረ መነኰሳቱ “ፍኖተ ጽድቅ” በሚሉትና በተለምዶ “ውሻ ገደል” እየተባለ በሚጠራው የደብረ ሊባኖስ ገዳም መግቢያ አካባቢ በሚገኘው መንደር፣ በነዋሪዎችና በገዳሙ መካከል ስላለው ግንኙነት፣ ስምንት አባላት ያሉት አጥኚ ቡድን ያካሔደው የዳሰሳ ጥናት፤ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ኂሩት ወልደ ማርያም ባሉበት ለፌዴራልና ለክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መቅረቡ ታውቋል፡፡

“የነዋሪዎቹ መበራከት ለገዳሙ ህልውና አስጊ ሆኗል፤ ጉዳዩ እልባት ይሰጠው፤” የሚል አቤቱታ፣ የገዳሙ አስተዳደር ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ ላለፉት አራት ወራት ከተለያዩ ተቋማት በተውጣጡ ምሁራን፤ መንደሩ፥ ከገዳሙ ሥርዓት፣ ከአስተዳደርና ሰብአዊ መብት፣ ከጸጥታና ከብዝኃ ሕይወት ጥበቃና ክብካቤ አንጻር የፈጠረው ችግር ተጠንቶ መቅረቡን፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርና ቱሪዝም መምሪያ ዋና ሓላፊ፣ መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ አስረድተዋል፡፡

መንደሩ፣ በገዳሙ ጥንታዊ ይዞታ መሀል መስፋፋቱ ችግር መፍጠር የጀመረው ከ50 ዓመት በፊት ሲሆን የገዳሙ አቤቱታ ከ17 ዓመታት በላይ ሲቀርብ እንደቆየ ያወሱት መጋቤ ሰላም ሰሎሞን፤ በካሳና በምትክ ቦታ አሰጣጥ ጉዳይ ላይ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋራ መግባባት ሳይቻል ቀርቶ፣ እስከ አሁን ተግባራዊ ሳይደረግ መዘግየቱን ጠቁመዋል፡፡

“ከቤተ ክርስቲያኒቱ ታላላቅ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መካነ ቅርሶች አንዱ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ነው፤” የሚሉት ዋና ሓላፊው፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አቤቱታውን ተቀብሎ፥ ከሚኒስቴሩ የጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተውጣጣ የምሁራን ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ካለፈው ሚያዝያ አንሥቶ፣ሙሉ ጊዜ በመውሰድ፣ የችግሩን ሥር መሠረት ማጥናቱን ገልጸዋል፡፡

በጥናቱ ከተጠቆሙት ችግሮች መካከል፥ በንግሥ በዓላት ወቅትና ምእመናን ሱባኤ በሚይዙባቸው ጊዜያት ዝርፊያ፣ ድብደባና አስገድዶ መድፈር መፈጸም፤ ከገዳሙ መንፈሳዊ አገልግሎት ጋር የሚቃረኑ የመጠጥ ቤቶችና ሆቴሎች መስፋፋት፤ የሴተኛ አዳሪነትና የሕገ ወጥ ቪድዮ ቤቶች መበራከት ይገኙባቸዋል፡፡ በገዳሙ የሚገኙ የቆሎ ተማሪዎችንና መናንያንን በከተማ ባህሎች በማማለልና በማላመድ ከትምህርታቸውና ከገዳማዊ አኗኗር ተለይተው በመንደሩ እንዲውሉ ተደርገዋል፤ ይላል ጥናቱ፡፡

በአካባቢው፣ ከመንፈሳዊነት ጋራ ተቃርኖ ያላቸው እንደ ሲጋራ ማጨስ፣ ጫት መቃም፣ በጾም ወቅት እርድ መፈጸምና ኳስ ጨዋታዎችንና ያልተገቡ ፊልሞችን ማሳየት፣ በስፋት እየተለመደና የአካባቢውም ዋነኛ ችግር እየሆነ መምጣቱም ተጠቁሟል፡፡ በመናንያንና በቱሪስቶች ላይ ወከባና ስርቆት ይፈጸማል፤ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ግዢና ሽያጭም ይከናወናል የሚለው ጥናታዊ ሪፖርቱ፤የገዳሙን ጥበቃዎች እስከ መደብደብና መሣሪያ እስከ መቀማት የደረሱ የከፉ ችግሮች መኖራቸውን ይገልጻል፡፡

“የገዳሙ አጠቃላይ መልክአ ምድር በራሱ፣ ሥፍራው ለምናኔ እንጂ ለዓለማውያን ሰዎች መኖሪያ እንደማይሆን ማረጋገጫ ነው፤” ያለው ጥናቱ፣ መንደሩ፥ ለዓለማዊ ሕይወት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችንና ተቋማትን ለማሟላት አመቺ እንዳልሆነ ያብራራል፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃና መጸዳጃ ቤት ባለመኖሩ፣ አካባቢው ለበሽታና ወረርሽኝ እንደተጋለጠም ይጠቁማል፡፡ መንደሩ በፕላን ያልተሠራ፣ አብዛኞቹ ቤቶችም ወደ ገዳሙ በሚወስደው የአስፋልት መንገድ ዳርቻ በእጅጉ ተጠግተው የተሰሩ በመሆናቸው ለትራፊክ አደጋ የተጋለጡ ናቸው፤ ብሏል፡፡

በአጠቃላይ መንደሩ በሒደት ተስፋፍቶ ወደ ከተማነት እየተለወጠ መምጣቱ፣ የገዳማውያኑን መንፈሳዊ አኗኗርና ተግባራት ከማወኩም በላይ የገዳሙን ቀጣይ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደከተተው ጥናቱ አመላክቷል፡፡

መንደሩ በፀበልተኞች ማረፊያነት እንደተቆረቆረ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፤ በ1968 ዓ.ም በዕድገት በኅብረት መርሐ ግብር ወደ አካባቢው የዘመቱ ወጣቶች፣ የሠሯቸው በርካታ ቤቶች፣ ለመንደሩ መስፋፋት ቁልፍ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጥናቱ ጠቅሷል፡፡ በመንደሩ ከነበረው የቀበሌ መዋቅር፣ ገዳሙ በ1980 ዓ.ም. ከተረከባቸው በተጨማሪ በርካታ የግል ቤቶች እንደተገነቡና በገዳም የሚተዳደሩት ቤቶች ቁጥር እያነሱ እንደመጡ ተጠቅሷል፡፡ በመንደሩ የቦታና የቤት ሽያጭ እንደሚካሔድና የግንባታ ፈቃድ የሚሰጠውም፣ በፍኖተ ጽድቅ በተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ገዳሙ የሚገኝበት የደብረ ጽጌ ወረዳ አስተዳደር፣ በመንደሩ ምንም መንግሥታዊ ሚና እንደሌለውና ከባለይዞታዎች የቦታና የቤት ግብር እንደማይሰበስብም የጥናቱ ሪፖርት አረጋግጧል፡፡

በጥናቱ ማጠቃለያ በተደረገው የቤቶች ቆጠራ፣ መንደሩ በአሁኑ ወቅት 602 ያህል ቤቶች እንደተገነቡበት የታወቀ ሲሆን ከእኒህም መካከል 315 ቤቶች በግል የተያዙ፣ 277 በገዳሙ ባለቤትነት በኪራይ የሚተዳደሩ፣ የተቀሩት 10ሩ ደግሞ ልዩ ልዩ የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫዎች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በመንደሩ አባወራዎችን ጨምሮ 2ሺ263 ነዋሪዎች እንዳሉና ከቋሚ ነዋሪዎች መካከል፥ መንደሩን ያቀኑ ነባር ባለይዞታዎች፣ ፀበልተኞች፣ በገዳሙ በጉልበት ሥራ የሚያገለግሉ፣ ጡረተኞች፣ መናንያን፣ የመንግሥት ሠራተኞችና በግብርና የሚተዳደሩ እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡

የ“ፍኖተ ጽድቅ” መንደር ነዋሪዎች፣ ተገቢው ካሣ ከተሰጣቸው ለገዳሙ ክብር ሲሉ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለቀው ለመውጣት ተነሣሽነት ማሳየታቸው፤ የዞንና ወረዳ መስተዳድሩም፣ በአካባቢው ለተነሺዎች ቦታ ለማዘጋጀት መፍቀዱ፤ የተነሽዎች ቤትና ንብረት የዋጋ ግምት ተደርጐ ከነመጓጓዣቸው የሚያስፈልጋቸውን ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ካሣ ክፍያ ለማመቻቸትና ወደ ገዳሙም መጠቃለል የሚፈልጉትን ለማቀፍ ደግሞ የገዳሙ አስተዳደር መወሰኑ፣ “መልካም አጋጣሚዎች ናቸው፤” ብሏል ጥናቱ፡፡

ጥናቱ ባለፈው ዓርብ ለቋሚ ሲኖዶሱ እንደቀረበና ለተነሺዎች የሚከፈለው ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን ብር የካሣ ክፍያ በቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲፈጸም ይኹንታ መገኘቱን መጋቤ ሰላም ቀሲስ ሰሎሞን ገልጸዋል። “በምክረ ሐሳቡ መሠረት ለሚወሰነው ውሳኔና የአፈጻጸም ተግባራዊነት ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትተባበር መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አረጋግጠዋል፤” ብሏል ጥናቱ፡፡ ምትክ ቦታ የማዘጋጀቱ ተግባር በክልሉ ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ በኩል ተፈፃሚ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋና ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ገዳሙ በክልሉ ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ የጥንታውያንና ታሪካውያን ቅርሶች መገኛ ከሆኑ ስፍራዎች አንዱና ዋነኛው እንደሆነ የተናገሩት፣ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሓላፊ፣ ገዳማዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ የቱሪስት መስሕብነቱ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ በቢሮው ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ጠቁመው፣ መካነ ቅርሱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየታሰበ እንደሆነም ለአጥኚ ቡድኑ ገልጸዋል፡፡
የ“ፍኖተ ጽድቅ”(ውሻ ገደል) መንደር ነዋሪዎች ከተነሡና ችግሩ መፍትሔ ካገኘ በኋላ፣ የአካባቢው መንግሥታዊ አካል ለገዳሙ ሙሉ ይዞታ የተረጋገጠለት የባለቤትነት ካርታ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

በተከለለው የገዳሙ ይዞታ፣ ሥርዓቱ በሚፈቅደው አግባብ፣ ደንብና መመሪያ በማዘጋጀት፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱንና ቱሪዝሙን በተጣጣመ መልኩ ለማስቀጠል የታቀደ ሲሆን የመንፈሳዊና የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት መሠረተ ልማት ሥራን ብቻ ለማከናወንና የግል ወይም የኪራይ ቤቶች ይዞታ በቦታው ላይ እንዳይቀጥል ለማድረግ ገዳሙ ግዴታ እንደሚገባም ለማወቅ ተችሏል። addisadmassnews

Filed in: Amharic