>
5:13 pm - Tuesday April 19, 2310

‹‹የመጀመሪያው የቁንጅና ውድድር በኢትዮጵያ››153ኛ ዓመት መታሰቢያ

አምደ ጽዮን ምንሊክ

ከዛሬ 153 ዓመታት በፊት (መስከረም 19/1857 ዓ.ም) በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቁንጅና ውድድር በጎንደር ተካሂዶ ነበር፡፡

የመስቀል በዓል በዋለ በሁለተኛው ቀን፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጰያ (ምናልባት የመጀመሪያው) የቁንጅና ውድድር በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡ ከልደታ ምሥራቅ ለአበራ ጊዮርጊስ ሰሜን ከሆነችው በቀሃ ወንዝ አጠገብ፣ አጤ ሰቀላ ላይ ከምትገኘው ኮረብታ ላይ የንጉሠ ነገሥቱ ሸራ ድንኳን ተተከለ፡፡ ከጧቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ የከተማውና የገጠሩ ሕዝብ በዓሉ ወደሚከበርበት ሜዳ ይጎርፍ ጀመር፡፡

አራት ሰዓት ሲሆን ምርጥ መሳሪያ የያዙ ወታደሮችና አጋፋሪዎች ሰልፈኛውን ለማስተናበርና ፀጥታውን ለማስከበር በበዓሉ ሜዳ ተሰማሩ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፊታውራሪ ገብርዬ በሰራዊታቸው ታጅበው ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ አጤ ሰቀላ ደረሱና የዙፋኑን አቀማመጥ ተመለከቱ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ንጉሠ ነገስቱ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ በፈረሶች በሚሳብ ሰረገላ ላይ ተቀምጠው ሊቀ መኳስ ዮሐንስ ቤል ባሰለጠናቸው ወታደሮች ታጅበው መጥተው በዙፋናቸው ላይ እንደተቀመጡ እምቢልታና መለከቱ ተብላላ፤ አጅብር አጅብር፣ ውጋው ውጋው እያለ ነጋሪት ይጎሰም ጀመር፡፡

ዘፋኞች ይዘፍናሉ፤ አዝማሪዎች ይዘምራሉ፤ ወታደሮች ይጨፍራሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ይዞታ ተድላና ደስታ ሆኖ ሲደባለቅ በመካከሉ ለውድድሩ የታጩት ወይዛዝርት ጥልፍ ቀሚሳቸውን እያንሰረተቱ፣ ተቀብተውና ተኳኩለው ወደተዘጋጀላቸው ቦታ ያልፋሉ፡፡

ቀጥሎም ምርጫው በሚፈፀምበት ጎል እየገቡ ውበታቸውና ደም ግባታቸው፣ የላሕየ ገፃቸው አወራረድ፣ የፀጉራቸው ስሬት፣ የቁንዳላቸው ርዝመት፣ ሽንጣቸው፣ ዳሌያቸውና ተረከዛቸው እየተመረመረ የምርጫው ስነ ስርዓት ይጀመራል፡፡ እንዲህ እየተደረገም ከሰቀልት ወረዳ ከመቋሚያ ማርያም የመጣችው ትውልዷ ከመቄት አዝማቾች ወገን የሆነች የደጃዝማች ይልማ አሰፋ ልጅ፣ ጣይቱ ይልማ አንደኛ ስትሆን፣ ከጎንደር አዲስ ዓለም የመጣችው የመሐመድ ኩርማን ሚስት የሼህ መሀመድ ጌታ ልጅ፣ ተዋበች ደግሞ በፀጉሯ ማማር፣ በቁንዳላዋ አወራረድና መርዘም ሁለተኛ ደረጃን አገኘች፡፡

ከዚህ በኋላ ፊታውራሪ ገብርዬና ሊቀ መኳስ ዮሐንስ ቤል የምርጫውን ውጤት ለንጉሠ ነገሥቱ ለመንገር ወደ ዙፋኑ ቀረቡ፡፡ ወዲያውም ጣይቱ ይልማ አንደኛ፣ እንዲሁም ተዋበች መሀመድ ጌታ ሁለተኛ መሆናቸውን ከገለፁ በኋላ ተመራጮቹ ከዙፋኑ ፊት በመቅረብ እጅ እየነሱ ሽልማታቸውን ተቀብለው የበዓሉ ፍፃሜ ሆነና እንደተለመደው በሰባት ሰዓት ለመሳፍንት፣ ለሊቃውንት ለመኳንንትና ለካህናት የምሳ ግብዣ ተደረገ፡፡

ከውድድሩ በኋላ ኦርማኤል (ወርመር) የተባለው በጋፋት የመድፍ ሰራተኞች አለቃ አንደኛ የወጣችውን ጣይቱ ይልማን በሚስትነት አግብቶ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወልደዋል፡፡ ጋይንት ውስጥ አሁንም በኦርማኤል ስም የሚጠራ መሬት አለ፡፡

(የመረጃው ምንጮች ፡ ገሪማ ታረፈ (የቋራው አንበሳ አባ ታጠቅ ካሣ) እና ጳውሎስ ኞኞ (አጤ ቴዎድሮስ))
—————
በምዕራቡ ዓለም ደግሞ ዘመናዊ የቁንጅና ውድድር መቼ መካሄድ የጀመረው በ1831 ዓ.ም በስኮትላንድ እንደሆነ የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ ተደርጎ በነበረው ውድድር ያሸነፈችው ከገዢ መደብ አባላት የሆነች ሴት እንደነበረች ተፅፏል፡፡

በ1847 ዓ.ም በአሜሪካ የቁንጅና ውድድር ለማድረግ ተሞክሮ ብዙ ሳይጓዝ መቋረጡም ይነገራል፡፡ ውድድሩ በመላው ዓለም በስፋት እየታወቀ የመጣው ግን በ1881 ዓ.ም በቤልጂየም ከተካሄደው የቁንጅና ውድድር ወዲህ እንደሆነ ማስረጃዎቹ ያመለክታሉ፡፡

ያም አለ ይህ በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር የተከናወነው የቁንጅና ውድድር ኢትዮጵያውያን በዚህኛውም ዘርፍ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደምንሰለፍ ጠቋሚ ነው፡፡
ለመሆኑ እኛ ያልጀመርነውና ቀደምት ያልሆንበት ምን ነገር አለ?!

Filed in: Amharic