>
5:18 pm - Friday June 15, 2604

ኢህአዴግን እየሰጉ ከኢህአዴግ ተስፋ የማድረግ ፖለቲካ (መሃመድ እንድሪስ)

ከአንድ ሳምንት በፊት በምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ላይ አተኩሮ በሚሰራ የምርምርም ተቋም አስተባባሪነት በተዘጋጀ ሴሚናር ላይ ፅሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡ ሴሚናሩ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስን በሚመለከት ነበር፡፡ ዋና ትኩረቴ ደግሞ የአንድ ፓርቲ ፍፁም የበላይነት ባለበት አገር የዴሞክራሲ ሽግግር ሊካሄድ የሚችልባቸው አማራጮች ላይ ነው፡፡በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ሲስተም ኢህአዴግ በየወቅቱ በተለያየ አገላለፅ ሲያቀርበው ይስተዋላል፡፡ እንደ ፓርቲ ስርአት ብዙሀን ፓርቲ (Multi Party system) እንደሆነ ሲቀርብ እንሰማለን፡፡ ለዚሀ ደግሞ መነሻው በኢትዮጵያ ከ70 በላይ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ነው፡፡ Multi Party system በመሰረቱ ብዙ ፓርቲዎች ላሉበት የፖለቲካ ሲስተም የተሰጠ ስያሜ ሳይሆን ለስልጣን በሚደረግ የምርጫ ፉክክር ከሁለት በላይ ፓርቲዎች ወደስልጣን የመምጣት እድል ኖሯቸው በውድድሩ ግን በርካታ ፓርቲዎች የሚሳተፉበትን የፓርቲ ስርዓትን የሚገልፅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ወደስልጣን የመምጣት እድል ያለው ተቃዋሚ ፓርቲም ሆነ ለዛ የሚሆን ፍትሀዊ ምርጫ ባለመኖሩ ይህ ስያሜ ጥቅም ላይ ማዋል አንችልም፡፡

በምርጫ 2002 ማግስት አቶ ሬድዋን ሁሴን በምርጫው ውጤት ኢህአዴግ ስላስመዘገበው ውጤት ሲናገሩ ‘አሁን ኢህአዴግ Dominant Political Party ሆኗል’ የሚል ሀሳብ ይዘው ቀርበው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የፓርቲ ስርአት ግን አሁንም በዚህ የሚገለፅ አይደለም፡፡ አንድ ፓርቲ ዶሚናንት ፓርቲ ለመባል ሁሌ ፍትሀዊ ምርጫ እየተካሄደ አንድ ፓርቲ ሁለቴ እና ሶስቴ በተከታታይ እያሸነፈ የበላይነቱን ማስጠበቅ ሲችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ የኢህአዴግ ተደጋጋሚ የበላይነት ምንጩ ደግሞ በዚህ የሚገለፅ አይደለም፡፡ ኢህአዴግን በተሸለ መልኩ ሊገልፀው የሚችለው Dominant Authoritarian Party የሚለው ነው፡፡ በዚህ የፓርቲ ስርአት ተቃዋሚዎች በህግ ደረጃ እንዳይሳተፉ ባይታገዱም አንድ ፓርቲ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያሉ የመንግስትንም ሆነ ህዝባዊ ተቋማት በመጠቀም የበላይነቱን በማያስነካ ሁኔታ የጨዋታ ሜዳ ውስጥ የሚገባበት ስርአት ነው፡፡ ምናልባት እንደሚሻሻል የሚጠበቀውን የምርጫ ህግን ተከትሎ አዲስ አወቃቀር ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ ማድረጉን ሳንረሳ፡፡ ይህ የፓርቲ ስርአት ከቅኝ ግዛት ወይንም ከወታደራዊ አገዛዝ ተላቀው ወደ ፓርቲ ፖለቲካ በተሸገሩ በርካታ አገራት የነበረ እና አሁንም ያለ ነው፡፡

ወደዋናው ርዕሴ ስመለስ

Dominant Authoritarian Party ባለበት ሁኔታ ወደዴሞክራሲ ለሚደረግ ሽግግር ሶስት ትላልቅ ሀይሎች ጉልህ ድርሻ ይጫወታሉ፡፡ የመጀመሪያው ፓርቲውን አሳታፊ የፖለቲካ መድረክ እንዲፈጥር ጫና የሚያሳድሩ የውጭ መንግስታት መኖር ነው፡፡ ይህንንም በአገራችን በምርጫ 97 ወቅት ሜዳውን ክፍት በማድረጉ ረገድ የአውሮፓ እና አሜሪካ ሚና የጎላ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ባሉት ወቅቶች ግን ይህ ነው የሚባል ጫና ካለመኖሩ ጋር የፕሬዝደንት ኦባማ ጉብኝት ኢትዮጵያን ‘ዴሞክራሲያዊ’ ሲል እስከመግለፅ በመደረሱ በዚህ በኩል የሚጠበቅ የለውጥ ተስፋ ጠባብ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ በራሱ በፓርቲው ውስጥ በሚፈጠር የሀሳብ እና የስልጣን ልዩነት የሚኖር መሰንጠቅ እና ውስጣዊ ተቃውሞ ማንሰራራት ነው፡፡ Acemoglu and Robinson ይህን መሰሉን አጋጣሚ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ለማካሄድ ለሚሹ በአነስተኛ ዋጋ ሊያሳኩበት የሚችሉበት መንገድ ሲሉ ይገልፁል፡፡ አነስተኛ ዋጋ ያስባለውም ከውስጥ የሚነሱት ተቃውሞ መሰል እንቅስቃሴዎች የራሱ የፓርቲውን መዋቅር፣ ሚዲያ፣ ሀብት እና የሰው ሀይል በመጠቀም የሚካሄድ ፉክክር በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ከውስጥ በሚፈጠር ተቃዋሚ ኬንያ፣ ማሌዥያ፣ ቦትስዋና፣ ሜክሲኮን ጨምሮ በርካታ አገራት ወደተሸለ ፉክክር ያለበት ዴሞክራሲያዊ ስርአት መሻገር ችለዋል፡፡

ሶስተኛው መንገድ ያልተቋረጠ ማህበረሰባዊ ንቅናቄ (Social Movements) መኖር ነው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ባጡበት ሁኔታ ውስጥ ይህ የለውጥ አማራጭ ከ5 አመታት ወዲህ የሚታይ ውጤት እያስመዘገ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በተለየ ሁኔታ በኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ንቅናቄዎች መሬቱን ለገዢው ፓርቲ ምቹ ባለማድረግ ከህዝብ የሚወግን አመራር ብቻ እንደ አማራጭ መውሰድ ግድ ሆኗል፡፡ ማህበረሰባዊ ንቅናቄ በሁለተኛው ላይ እንደተጠቀሰው ለውጥን በአንፃራዊነት ቀላል በሚባል ዋጋ ሊያመጣ የሚችል መንገድ ነው፡፡ የነዚህ ሁለት አማራጮች ስኬታማነት አንዱ ምንጭ ከራሱ ከገዢው ፓርቲ የሚቀዳ ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ከውስጥ በሚፈጠር ተቃዋሚ እና ማህበረሰባዊ ንቅናቄዎች በሚፈጥሩት ጫና በሚያደርገው የስልጣን ማካፈል ሂደት ህልውናውን ሙሉ በሙሉ እንደማያጣና ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ያስመዘገባቸውን መልካም ፍሬዎች ማስጠበቁን ስለሚተማመን ነው፡፡

Dominant Authoritarian Party ዝግመታዊ በሆነ ለውጥ ስልጣን ለማጋራት ፍቃደኛ ሆኖ በምርጫ ወደፉክክር ቢገባ እንኳን በአብዛኛዎቹ ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ መቀጠል ይችላል፡፡ ለአብነት ያህልም በ19 አገሮች ላይ በተካሄደ አንድ ጥናት በአስራ አንዱ ፓርቲው ቀጣዩን ምርጫ ማሸነፍ ሲችል በ8 አገሮች ደግሞ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ህልውናውን ግን አስጠብቆ ጥሩ ተሸናፊ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በሁለቱም ሁኔታ ውስጥ ግን ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር መካሄድ ተችሏል፡፡ በስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ከስልጣን ቢወርድ ወይንም ስልጣን ቢያካፍል ሊያጋጥመው የሚችለው እጣ ፈንታ ሁኔታ ፓርቲው ስልጣን ለማጋራት በሚኖረው ፍቃደኝነት ላይ ወሳኝ ተፅእኖ ማሳደሩም የሚጠበቅ እውነታ ነው፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ተጨባጭ ምዕራባውያን ስለዴሞክራሲ ሽግግር ጫና የሚያደርጉበት ደረጃው ቀንሷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከውስጥ የሚፈጠርን የተቃውሞ እንቅስቃሴ እና ማህበረሰባዊ ንቅናቄዎችን ብልሀት በተሞላበት መልኩ ከመጠቀም ውጭ ሌላ አማራጭ አይታይም፡፡ ከውስጥ የሚፈጠር ተቃዋሚ ሀይል በረዥሙ ታስሮ የተለቀቀ እንደሆነ ቢታመንም እንኳ በገመዱ ልክ ተጉዞ መመለስ እንዳይችል መገፋፋት ፖለቲካዊ ብልህነት ነው፡፡ በተለይ ማህበረሰባዊ ንቅናቄዎች የሚያመጡት ለውጥን በልዩ ብልሀት መጠቀም ይጠይቃሉ፡፡ በብልሀት የመጠቀማችን ትልቅ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ለውጡ የሁሉንም ተጠቃሚነት እንዲያመጣ በሚያስችል እና የአገርን ህልውና በማይፈታተን መልኩ እንዲካሄድ ማገዝ ሲቻል ነው፡፡ ንቅናቄዎቹን ሙሉ ለሙሉ ለፖለቲካ ፓርቲ አስረክቦ (በኦሮሞ ትግል እየታየ እንደመጣው) ህዝቡን የፓርቲዎች ፉክክር አዳማቂ ማድረግም አደጋ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ አካባቢ አይሎ የሚገኝ የለውጥ እንቅስቃሴን የዚያን አካባቢ የበላይነት ለማስጠበቅ የሚደረግ የተናጠል አንቅስቃሴ አድርጎ በጥርጣሬ ማየትንም ማቆም ይጠይቃል፡፡ በተለይም አገራዊ አንድነትን ከማጠናከር አኳያ ኢትዮጵያዊነት ዋና አጀንዳ መሆን ሲጀምር ‘የናንተ ኢትዮጵያዊነት ማስመሰል የኛው ብቻ ያልተኳኳለ እውነተኛ መንፈስ’ ከሚል ራስን ጠልፎ የመጣል አካሄድ ማራቅ ግድ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የአንድ ፓርቲ ፍፁም የበላይነት ባለበት ሁኔታ ያ ፓርቲ የቀደሙ ፍሬዎቹን እንዲሰበስብ ማድረግ ለፓርቲውም በአገራችንም ከመንግስት መንግስት ተመጋጋቢ ሽግግር ከማስለመድ አኳያ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ በሌላ አነጋገር የለውጥ አማራጮቹ እውን እንዲሆኑ የኢህአዴግን ትልቁ የፖለቲካችን ባለድርሻነትና የለውጡ አካል መሆኑን ቢመርም መዋጥ ግድ ነው፡፡

ኢህአዴግ የትኞቹን ፍሬዎች ያስጠብቅ

Samuel Huntington በታዳጊ አገራት የሚገኙ መንግስታት በትምህርት እና ሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ለውጥ ካመጡ ስልጣናቸውን ለረዥም ግዜ አስጠብቀው ማቆየት እንደሚችሉ ማመናቸው አንድ ትልቅ ቁም ነገር በመርሳታቸው የመጣ መሆኑን ይናገራል፡፡ ይኸውም ባህላዊ እና ዝግ የሆነው የፖለቲካ ስርአታቸው አዲስ ለሚፈጠረው የተማረ እና ኢኮኖሚ ውስጥ ሚና ላለው ትውልድ የሚመጥን መሆን ሲያቅተው ሙሉ መዋቅራቸው ሊፈርስ እንደሚችል መዘንጋታቸው፡፡

ኢህአዴግ በአሁን ሰአት ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ብቻ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ አመለካከት እና የመንግስት አደረጃጀት ያስተዋወቀ የፖለቲካ ሀይልም ነው፡፡ ይህ አመለካከት እና የመንግስት አደረጃጀት ፓርቲው በስልጣን ላይ ኖረም አልኖረም ጠንካራ ደጋፊ እንዳለው የሚቀጥል ነው፡፡ በቋንቋው የተማረ፣ በቋንቋው በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚያገለግል፣ በቋንቋው የሚዳኝ እና ባህሉን የሚያስፋፋ አዲስ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ በየአመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ በፊት የትምህርት እድል የሌላቸው አካባቢዎች ፈጣን በሆነ መልኩ ወደመድረኩ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በየክልሉ ያሉ የፖለቲካ ተቋማት ለወጣቶች ጥሩ የፖለቲካ እና አመራር ሰጪነት ማሰልጠኛ መድረኮች ሆነዋል፡፡ በፌዴራል ስርአቱ ላይ ኢህአዴግ መወቀስ ካለበት በተግባር የሚጠበቀውን ያህል መጓዝ አለመቻሉ ነው፡፡ የክልል ፓርቲዎችን የማዕከላዊ መንግስትን ፕሮግራም ከማስፈፀም በሂደት በራሳቸው እንዲቆሙ ባለማድረጉ ነው ሊተች የሚገባው፡፡ ለአዲሱ ትውልድ የሚሆን አዲስ የፖለቲካ ሜዳ ባለማመቻቸቱ፤ ባሉት የፖለቲካ መድረኮች ተሞክሮ የወሰዱትን እንደቀድሞው አስፈፃሚ ብቻ አድርጎ የማስቀረት ድብቅ ፍላጎቱ ነው ስህተቱ፡፡ አሁን የተነሱት ህዝባዊ ንቅናቄዎች የራሱ የፌዴራል ስርአቱ የፈጠራቸው የፖለቲካ ተሳትፎ አማራጭ አድርጎ በመቀበል ወቅቱ የሚጠይቀውን ለውጥ ለማድረግ አለማሰቡ ነው ኢህአዴግ ሲወገዝ ፌዴራል ስርአቱም አብሮ እንዲወገዝ ያደረገው፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያስተዋወቀውን አዲስ ሞዴል እስከስኬቱ ድረስ ለማሻገር አቅም እና ፍላጎት ማጣቱ እንጂ በራሱ የፌዴራል ስርአቱ አልነበረም ስህተቱ፡፡

ሰሞነኛ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ፌዴራሊዝሙ የፈጠረው ተናዳፊ ትውልድ ማሳያ ተደርጎ እንዲወሰድም በር መከፈቱ ኢህአዴግ ሊወደስባቸው የሚችሉ መልካም ፍሬዎቹን ሳይቀር አመድ እያለበሳቸው ይገኛል፡፡ ፓርዎቹ የስልጣን ጦርነት የሚያካሂዱት የንፁሀንን ሕይወት እንደምሽግ ተጠቅመው መሆኑ ከግጭቶቹ መንግስት እጁን ንፁህ ማድረግ የሚችልበት እድል የለም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በተቃዋሚው ጎራም ቢሆን ግጭቶቹን በተካረረ መልኩ ለቅስቀሳ መጥቀሙ እውነታውም ፌዴራሊዝም ያመጣው የብሄሮች ግጭት ነው አያስብለውም፡፡ ኢትዮጵያ በፌዴራል ስርአት እየተዳደረች በኦሮምያ ክልል ከሚኖረው አጠቃላይ ህዝብ 13 በመቶው የሌላ ብሄር ተወላጅ ነው፡፡ ከ2 ሚሊየን የማያንሱ አማራዎች የዚሁ አካል ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ሶስት ብቻ ይመስል ነገሮች የተያዙበት አግባብ ኢ-ሞራላዊም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የማእከላዊ እስታቲስቲክስ ባለስልጣን መረጃዎች ስብጥሩን ስለሚገልፁ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልሻም፡፡ ትልቁ እውነታ ግን የፌዴራል ስርአቱ መሬት ላይ መኖሩ የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት ሊያጠፋው አለማቻሉ መታወቁ ላይ ነው፡፡ እነዚህን መሰል ግጭቶች እንደዛሬ ማህበራዊ ሚዲያ ከመስፋፋቱ በፊት የተለመዱ ክስተቶች ሲሆኑ የሰው ህይወት በመጥፋቱ ከማዘን ውጭ በሞት ላይ ፖለቲካዊ ፉክክር አልተለመደም ነበር፡፡

እንደማሳረጊያ

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ‘ያልተረጋጋች አገር’ ሊያስብላት የሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ በፍጥነት እየገባች ይመስላል፡፡ አመራሩ እና ተቋማቶቹ እርስርበርስ የማይናበቡና በከፍተኛ ደረጃ ቅቡልነታቸውን አጥተዋል፡፡ በሁሉም መስመር ያሉ ልሂቃን የርስ በርስ ተቃርኖ ውስጥ ገብተው የጋራ እርምጃ መውሰድ አልቻሉም፡፡ በተለምዶ ውጤታማ የነበሩ ልማዳዊ፣ ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ እሴቶች በፖለቲካዊ ግለት ተሸፍነው ሚናቸው ደብዝዟል፡፡ መፍትሄ አፍላቂዎች ከመጥፋታቸውጋ የሚሰነዘሩ የመፍትሄ ሀሳቦቸም አካታችነት ይጎድላቸዋል፡፡ ባልተረጋጋች አገር ውስጥ መፍትሄ የሚሰጠው ያጣ ህዝብ ደግሞ ተስፋ በመቁረጥ የአገር መረጋጋትን ብቻ ይመኛል፡፡ መረጋጋቱ በባሌም ይሁን በቦሌ ወደሚል ከሄደ ደግሞ ወታደር እስከመናፈቅ ሊጓዝ ይችላል፡፡ ያንን ለማስቀረት ከፓርቲው ውስጥ ያሉ የለውጥ ተስፋዎችን እድል ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ ኢህአዴግም የለውጥ ጥያቄው አገራዊ ለውጥን ከመናፈቅና የሚገባውን ከመጠየቅ እንጂ የፓርቲው የመኖር እና የመሞት ጉዳይ አድርጎ መውሰዱን በማለዘብ ሂደቱን ካለገዘ ማንም አትራፊ አይሆንም፡፡ እዚህም እዚያም እንዲነሱ የሚደረጉና በአጋጣሚ የሚነሱ ግጭቶችን የብሄር ግጭት አድርጎ የማቅረብ አቅጣጫ የሳተ ፖለቲካዊ ስሌታችንን በማረቅ ለለውጡ ተባባሪ በመሆን በጠቆረው መፃዒያችን ተስፋ ልንረጭበት እንችላለን፡፡

ተስፋ ማድረግ ደጉ!

Filed in: Amharic