>

ኢትዮጵያ የሁላችንም ትሁን፤እኩል ይዝነብልን (እንዳለጌታ ከበደ)

ከ‹ያልተቀበልናቸው›….መጽሐፍ አንዱን ነጥብ እነሆ!

ጀምቦሮ፣ በንጉሥ ምኒልክ ዘመን፣ ንጉሡ ግዛታቸውን ለማስፋፋት በመጡ ጊዜ፣ የተመሰረተች ከተማ ናት፡፡ ከተማ አይደለችም፤ ገጠር ናት፡፡ ገጠርም አይደለችም፡፡ ከተማ ለመሆን ዳዴ ማለት የጀመረች ከተማ ቀመስ ገጠር ናት፡፡ የሰሜን ሸዋ ሰዎች፣ ከመቶ ሰላሳ ዓመት በፊት አቅኚ የነበሩትን እነፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን፣ራስ ወልዴንና ሌሎችንም ተከትለው መጡ፡፡ በቦታው ሰፈሩ፡፡

አሁን የአቅኚዎቹ ውሉዶች ቋንቋቸው ተቀይጧል፤አማርኛቸው ከጉራጊኛ ጋር ተደባልቋል፡፡ ከቀደሙ ዘመዶቻቸው – ከቅም ቅም አያቶቻቸው ጋር- አይገናኙም፡፡ ከዚህ ወደዚያ የሚሄድ የለም፡፡ ከዚህም ወደዚያ የሚሄድ የለም፡፡ ግንኙነቱ ተቋርጧል፡፡ ልቅሶ አይደራረሱም፡፡ ሰርግ አይጠራሩም፡፡ አሁን፣ እነዚህ የአንኮበር ደም ያላቸው ግለሰቦች፣ ጀምቦሮ ተወልደው፣ ወላጆቻቸውም፣ የወላጆቻቸው ወላጆችም ተዋልደው፣ አዲስ ማንነት ገንብተዋል፡፡ ከሁለቱ ብሄሮች ሁለት ሁለት ቃል ወስጄ አማጉራ ብዬዋለሁ፡፡

የተዋሃዱ ቢመስሉም፣ ሙሉ ለሙሉ ግን ነባሩን ማኅበረሰብ አልመሰሉትም፡፡ እንደአካባቢው ተወላጅ ቅመ አያቶቻቸው በዐይናቸው አይተውት የማያውቁትን የእንሰት ተክል ይተክላሉ፤ ቆጮ ይመገባሉ፤ እንደ አካባቢው ነባር ነዋሪ ገጆ ይቀልሳሉ፤ ከብት ያረባሉ፤ አዝርዕት ይተክላሉ፡፡ መስቀል በዓል መጣ ብለው እንደ ማኅበረሰቡ ሞቅ አድርገው ይደግሳሉ፡፡ ልጆቻቸውን ለጋብቻ ይሰጣጣሉ፤ ይቀባበላሉ፡፡ የሚያገሉትም ሆነ የሚያገላቸው ወገን የለም፡፡ ጠብና አምባጓሮ በመሐላቸው የለም፡፡ እንኳንስ እርግጫ፣ፍጥጫና ጫጫታ ሊሰማ፣ ግልምጫ በመሐላቸው የለም፡፡

ነባሩ ማኅበረሰብም ከጠጅ ጋር መተዋወቅ የጀመረው በእነዚህ ሰዎች አማካይነት ነው ይባላል፤ አንድ ሁለት ጠጅ ቤቶች አሉ፤ጠጅ ቤቶቹ በአግዳሚ ወንበር የተሞሉ ናቸው፡፡ ወንበሩ ሁሉንም እኩል ያስተናግዳል፡፡
‹ዕዳ ከፋይ› ከሚለው መጣጥፍ የተወሰደ፡፡

ተረፈ መምሕር ነው፡፡ የአምስት ዓመት የማስተማር ልምድ አለው፡፡የተመረቀው ሀዋሣ መምሕራን ኮሌጅ ነው፡፡ ተረፈ ከሐመሮች ጋር ብዙ ዘመኑን አሳልፏል፡፡ ስለ ሐመሮች ሲያወራ ስለ ልጅነት ትዝታው ወይም ደግሞ ስለ ሕጻን ልጁ እንደሚተርክ ወጣት ነው፡፡ ‘አቦ! ሐመሮች ደስ የሚሉ ሰዎች ናቸው!’ አለኝ፣ ‘ጣጣ የላቸውም፤ ፍቅር ናቸው!’…መምሕሩ ጎጆ ከቀለሰ አምስት ዓመቱን ይዟል፡፡መኪናው ላይ ካሉት ነዋሪዎች ጋር ሲያወራ አይቼው የብሄሩ ተወላጅ መሆን አለመሆኑን ጠይቄው ነበር፡፡

‘አይደለሁም! … ግን እዚህ ነው የተወለድኩት – ሐመሮች እምብርት ስር፡፡ እናቴ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ናት፡፡ አባቴ ደግሞ አማራ ነው፡፡ ለንግድ መጥተው ተግባብተውና ተጋብተው እኔን የወለዱኝ እዚሁ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከአንዲት የኦሞ ወንዝ ልጅ ጋር ተጋብቼ አሁን የወንድ ልጅ አባት ሆኛለሁ…’ አለኝ፡፡

እየነገረኝ ያለውን ነገር እየሰሙ ያሉ ሌሎች በአማርኛ ቋንቋ መግባባት የሚችሉ ተሳፋሪዎች፣ ሣቅና ፈገግታ ተለዋወጡ፡፡
‹ክራሞት› ከተሠኘው መጣጥፍ የተወሰደ፡፡
……
…ኢትዮጵያ የሁላችንም ትሁን፤ኢትዮጵያ ጥቂት ብሄሮች፣ጥቂት ምሁሮችና ጥቂት ታጋዮች ኮሚቴ መስርተው የሚመሯት አገር አይደለችም፤እኩል ይዝነብልን፤ለጥቂቶች ሲዘንብ አይደለም ለተቀረው ማካፋት ያለበት፤ጥቂቶች ሲጠግቡ አይደለም የተቀሩት እንደተመፅዋች ‹ትራፊ› በጀት ሊበጀትላቸው የሚገባው፡፡

‹ሰምና ወርቃዊ ኑሮ› ከሚለው መጣጥፍ የተወሰደ፡፡

Filed in: Amharic