>

ሕወሃት የሞተው እውነት መስማትና ማየት ያቆመ ዕለት ነው! (ስዩም ተሾመ)

ዛሬ በአዲስ ስታንዳርድ በኩል አፈትልኮ የወጣውን ሰነድ ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ለመመልከት እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የተጠቀሰው ሰነድ የተዘጋጀው በህወሃት/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ሃሳብና ፍላጎት እንደሆነ መረጃዎቹ ያመለክታሉ፡፡ በተመሣሣይ ህገ-መንግስቱን በሚንድ መልኩ ከተዘጋጀው የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት በስተጀርባ ያሉት እነዚሁ ከፍተኛ የህወሃት አመራሮች ናቸው፡፡

እስኪ ለመነሻ ያህል በተጠቀሰው ሰነድ በወቅታዊ የሀገራችንን ሁኔታ የቀረበውን ትንታኔ በከፊል እንመልከት። በመጀመሪያ ደረጃ ለዕቅዱ መነሻ የተደረጉ ሁኔታዎች፤ የፌደራል ስርዓቱን የሚፈታተኑ ክስተቶች እየተስተዋሉ መሆናቸው፣ በየግዜው የሚከሰቱ ግጭቶች በሰውና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሱ መሆኑ፥ ሀገራዊና ከባቢያዊ መልክ እየያዙ መሆኑና ግጭቶቹ የመቆም አዝማሚያ አለማሳየታቸው፣ በዚህ ምክንያት፣ የሕግ የበላይነት እና የሀገሪቱ ፀጥታ አለመከበሩ፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ መሆኑ፣ እንዲሁም የተጠቀሱት ሁኔታዎች የሀገሪቱን የፀጥታ ኃይል ዝግጁነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህ መሠረት፣ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ከመሄዱም በላይ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፥ መንግስታዊ ስርዓት፣ የፀጥታ ተቋማት፥ እንዲሁ የዜጎች ማህበራዊ ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ እያሳረፈ መሆኑ በግልፅ ተጠቅሷል፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር ከላይ በተጠቀሱት ከፍተኛ የህወሃት/ኢህአዴግ አመራሮች መፍትሄ ተብሎ የቀረበው ሃሳብና የተግባር ዕቅድ ነው፡፡  ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ የተቋቋመበት አግብብ፣ እንዲሁም የፀጥታ ዕቅዱ የተዘጋጀበት የዕውቀትና ግንዛቤ ደረጃ እጅግ በጣም አስደንጋጭና አሳፋሪ ነው፡፡ በተለይ የህወሃት እና ደኢህዴን ከፍተኛ አመራሮች በሀገሪቱ ስላለው የፖለቲካ ቀውስ ያላቸው የግንዛቤ ደረጃ ያሳፈራል ብቻ ሳይሆን በጣም ያስፈራል፡፡ ለምሳሌ፣ በሰነዱ ውስጥ በአንደኝነት የተጠቀሰውን እንዲህ ይላል፦

“የፌዴራል ስርዓቱን የሚፈታተኑ ክስተቶች እየተስተዋሉ ነው” የሚለውን አስመልክቶ በፀጥታ ዕቅዱ ውስጥ የቀረበው ዳሰሳ እንዲህ ይላል፡- “የፌደራል ሥርዓታችን የሕዝቦቻችን ዋስትናና ሕልውና መሰረት ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም ፌደራል ስርዓታችን የሕዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ያረጋገጠ፣ ሁሉንም ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የመለሰ፣ “ልዩነታችን ውበታችን ነው” ብሎ አምኖ በመተማመንና በመፈቃቀድ ላይ ያኖረ ሥርዓት መሆኑ [ይታወቃል]። ይሁን እንጂ፣ ፌዴራሊዝም አንድነትን የሚያፈርስ፥ የሚበታትን፥ ፌደራሊዝም በራሱ ችግር ፈጣሪና የሥርዓቱ አደጋ እድርጎ የማየት የተሳሳተ አመለካከት እያደገ መምጣቱ፣…”ለመሆኑ ይህ ስርዓት ይቀጥላል ወይ?” የሚል ስጋትና ብዥታ እየፈጠረ መምጣቱ፣…”

በጣም የሚገርመው ነገር እነዚህ ሰዎች ላለፉት 25 አመታት ሀገሪቱና ህዝቡን በዚህ የተሳሳተ ግንዛቤና አቅጣጫ መምራታቸው ሳያንስ፤ የፈፀሙትን ስህተት መረዳት አለመቻላቸው፣ ስህተታቸውን ሲነግሯቸው አለመስማታቸው፣ “ተሳስታችኋል” ያሏቸውንም ለእስር፣ ስደት፥ የአካል ጉዳትና ሞት መዳረጋቸው፣ አለማወቃቸው ሳያንስ ዙሪያቸውን በኣላዋቂዎች መክበባቸው፣ …በዚህ ምክንያት ሀገሪቷን አሁን ካለችበት የፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት ውስጥ መክተታቸው፣ ከዚህ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት ይህን ችግር በፈጠረው ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብና የፖለቲካ አመለካከት መመራታቸው፣… በተለይ ህወሃት/ኢህአዴግ በራሱ “ቆሞ-ቀር” መሆኑ ሳያንስ ሌሎችን ሌሎችን አባል ድርጅቶች ቆመው እንዲቀሩ ያለ የሌለ አቅማቸውን መጠቀማቸው፣ … በአጠቃላይ መውደቃቸው ላይቀር ህዝብና ሀገር ይዘው መውደቃቸው፡፡


እንዲህ በምሬት የምናገረው በእብሪት አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ ሺህ ግዜ ተናግራችሁ፥ “ይሆናል፥ መሆን አለበት” ብላችሁ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምላችሁ በመለስ ዜናዊ ስም ተገዝታችሁ አንዴ እንኳን ትክክል መሆን ስለተሳናችሁ ነው፡፡ አሁን ይህን የምፅፈው  “ላለፉት 25 አመታት መሳሳታችሁን፣ አንዴም እንኳን ከስህተታችሁ መማር የተስናችሁ” መሆናችሁን ለመናገር አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ “አንድ የፖለቲካ ቡድን ለምንና እንዴት እንዲህ እውነትን ማየትና መስማት ይሳነዋል?” የሚለውን በዝርዝር ለማሳየት ነው፡፡ እርግጥ ነው አውቃለሁ “ህወሃት ለምን እንዲህ እንደሆነ የማወቅ ፍላጎቱና ድፍረቱ ቢኖራቹህ ኖሮ አሁን ካላችሁበት ደረጃ ላይ አትደርሱም ነበር፡፡  ይህ ግን እኔን ከመናገር አያግደኝም፡፡ ስለዚህ ህወሃት/ኢህአዴግ እውነት ማየት ሆነ መስማት የተሳነው ለምንና እንዴት እንደሆነ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ በአጭሩ ህወሃት እውርና ደንቆሮ የሆነው ዙሪያውን በአወቅን ባይ ጥረዝ-ነጠቆች በመክበቡ ምክንያት ነው፡፡ ለምንና እንዴት የሚለውን ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡

ህወሃት የሞተው የተማረ ሁሉ ይደግፈኝ፣ ተቃዋሚ አያሳየኝ ያለ ዕለት ነው! 

እንደ ማንኛውም ዜጋ ምሁራን የመንግስት ስልጣንና ኃላፊነት ተረክበው መስራት ይችላሉ። ይህ ሲሆን እንደ ማንኛውም ባለስልጣን የመንግስትን ሥራና ተግባር ደግፈው ሃሳብና አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ። የመንግስት ተሿሚ ወይም ባለስልጣን ካልሆኑ ግን የሕዝብን ድምፅ ተቀብለው የማስተጋባት ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው።

ጨቋኝ ስርዓትን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ኃይል ስለ ቀድሞ ታሪኩ፣ አሁን ላይ ስላለው ሥራና አሰራር፣ ወይም ስለ ወደፊት አቅጣጫና ዕቅዱ ለመግለፅ አስፈላጊ የሆነ መንግስታዊ መዋቅርና ተቋማት አሉት። ለዚህ ተግባር የተመደበ የሰው ኃይልና ካፒታል ይኖረዋል። ስለዚህ፣ ምሁራኑ የመንግስትን ሥራና ተግባር አጎልቶ በመናገርና በመመስከር የአፈ-ቀላጤ እንዲሆኑ አይጠበቅም።

ከዚያ ይልቅ፣ የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት በማህብረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አጉልቶ በማውጣት የግንዛቤና አመለካከት ለውጥ እንዲመጣ መስራት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት እንዲስተካከሉ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።

ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች አንፃር ሲታይ ምሁራን በሙያቸው ችግሮችን ቀድሞ የመለየትና መፍትሄያቸውን የመረዳት ብቃት አላቸው። የፖለቲካ ስልጣን የሚጨብጡ ሰዎች ግን ሕዝብን የማደራጀትና የመቀስቀስ አቅም እንጂ ከምሁራን የላቀ ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ስላላቸው አይደለም። በመሆኑም እንኳን በትጥቅ ትግል የመንግስት ስልጣን የያዘ ቀርቶ በሕዝብ ምርጫ የመጡ የመንግስት ኃላፊዎች የሕዝብን ፍላጎትና ጥያቄ ለመገንዘብ የሚያስችል በቂ አቅምና ዕውቀት የላቸውም።

እንግሊዛዊው ፈላስፋ “John Stuart Mill” ስለ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አመሰራረትና አሰራር በሚተነትነው መፅሃፉ የምሁራንን ድርሻና ኃላፊነት እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

“….a fair sample of every grade of intellect among the people which is at all entitled to a voice in public affairs. Their part is to indicate wants, to be an organ for popular demands, and a place of adverse discussion for all opinions relating to public matters, both great and small; and, along with this, to check by criticism, and eventually by withdrawing their support, those high public officers who really conduct the public business.”  Representative Government, Ch.5: Page  59

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የፖለቲከኞች መደበኛ ስራ ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር ነው። የምሁራን ድርሻ ደግሞ የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና የመንግስት ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማስቻል ነው። ለዚህ ደግሞ በፖለቲካ ቡድኖች እና በምሁራን መካከል ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ መቀጠል አለበት።

ከዚህ አንፃር፣ ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጓቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እና በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየትና የሚስተካከሉበትን የመፍትሄ ሃሳቦችን በመጠቆም ነው። የፖለቲካ ስልጣን ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ ከምሁራን የተሰጣቸውን ሃሳብና አስተያየት ተቀብለው የሀገሪቱንና ሕዝቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል የፖለቲካ አመራር መስጠት፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ስርዓቱን ማሻሻል ነው።

በዚህ መሰረት፣ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ከተወጡ በመንግስት ሥራዎችና አስራሮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ወዲያው ይስተካከላሉ። መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል። ስራና አሰራሩ ግልፅነት እና ተጠያቂነት ይኖረዋል። የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጡ የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ይሆናል።

ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ በሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ይኖራል። ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ለዘላቂ ልማት፣ ለአስተማማኝ ሰላም እና ለዳበረ ዴሞክራሲ መሰረት ይሆናል። ነገር ግን፣ ምሁራን ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ማምጣት አይቻልም።

በአጠቃላይ፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ምሁራን ሕግ አውጪዎች የሚያፀድቋቸውን አዋጆች፣ የሕግ አስባሪዎች አሰራርና የፍትህ ስርዓቱ ገለልተኝነትን፣ የሕግ አስፈፃሚዎች የሚያሳልፏቸውን የአፈፃፀም መመሪያዎችና ደንቦች፣ በአጠቃላይ የመንግስት አካላት ሥራና አሰራርን አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ከሙያው አንፃር መተንተን፣ የተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦችን እያነሱ መወያየትና በመንግስትና ሕዝቡ ዘንድ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መጠቆም አለባቸው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ መሰረታዊ ችግር ያለባቸው አዋጆች፥ እቅዶችና ውሳኔዎች በተለያዩ የመንግስት አካላት ተግባራዊ ሲደረጉ እያዩ በዝምታ የሚያልፉ ሰዎች እንደ ምሁር ያለባቸውን ማህበራዊ ግዴታ አልተወጡም። ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ምሁር ያለውን ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ በተለይ የመንግስትን ስራና አሰራር የመተቸት ማህበራዊ ግዴታ አለበት።

ምሁራን በዜጎች ማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣት፣ እንዲሁም የመንግስት ስራና አሰራር ማሻሻል የሚችሉት፣ በአጠቃላይ እንደ ምሁር የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉት ራሳቸውን ከመንግስት ሲነጥሉ ነው። ልክ እንደ የመንግስት ተሿሚ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመንግስትን ሥራና ተግባር በመደገፍ፣ ጥሩን እያጋነኑ፥ መጥፎውን እየሸፋፈኑ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ በዜጎች ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰትን በማጣጣል የመንግስትን ጥሩ ምግባር አጉልተው ለማውጣት የሚጥሩ ከሆነ፣ በሕዝብና መንግስት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ የከፋ ነው።

ምሁራን በደጋፊነት ስም ራሳቸውን ከመንግስት ጋር ማጣበቃቸው በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት “John Stuart Mill” እንዲህ ገልፆታል፡-

“….There are no means of combining these benefits except by separating the functions which guarantee the one from those which essentially require the other; by disjoining the office of control and criticism from the actual conduct of affairs, and devolving the former on the representatives of the Many, while securing for the latter, under strict responsibility to the nation, the acquired knowledge and practised intelligence of a specially trained and experienced Few.” Representative Government, Ch.5: P.59 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ምሁራን የተለያዩ የመንግስት አካላት የሚያሳልፋቸው የብዙሃኑን እኩልነትና ተጠቃሚነትን የማያረጋግጡ እቅዶችና ውሳኔዎች እንዳይሻሻሉ፣ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚገድቡ አዋጆችና ደንቦች ማሻሻያ እንዳይደረግባቸው፣ የሕዝብ ጥየቄዎችና ቅሬታዎችን እንዳይሰማ፣ እንዲሁም የመንግስት ኃላፊዎች ያለባቸውን የግንዛቤ እና የብቃት ማነስ ችግር እንዳይቀርፉ እንቅፋት ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ምሁራን የመንግስትን እርምጃዎችን በመደገፍ ብቻ ሳይሆን ሙያተኝነት ስም ገለልተኛ መስለው ለማለፍ መሞከራቸው በራሱ በህዝብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን እንደመደገፍ ይቆጠራል። ስለዚህ፣ በገለልተኝነት (neutrality) ስም መንግስትን ከመተቸት የሚቆጠቡ ምሁራን “የመንግስት ደጋፊ ነን” ከሚሉት በምንም የተለዩ አይደሉም። ምክንያቱም እንደ ምሁር ከማህብረሰቡ የተጣለባቸውን ግዴታና ኃላፊነት አልተወጡም።

ስለዚህ ሁሉም ምሁራን በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማንሳት የግንዛቤና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚያስከትሉትን ጭቅጭቅና ውዝግብ በመፍራት ማህበራዊ ግዴታቸውን የማይወጡ፣ በተለይ ደግሞ የሕዝብ ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን እያጣጣሉ፣ የመንግስትን ስራና ተግባር እያጋነኑ የሚያቀርቡ፣ ከመንግስት ኃላፊዎች በላይ የመንግስት ጠበቃና ደጋፊ ለመሆን የሚቃጣቸው ሰዎች “ምሁር” ለሚለው የክብር ስያሜ አይመጥኑም።

Filed in: Amharic