>
5:16 pm - Wednesday May 23, 8390

አቶ ምላስ ዜናይን እያጣደፍህ የጠራህ አቤቱ ድንቅ ነው ስራህ! ግጥሎት(ግጥምና ጠሎት) (በ.ስ)

 

አቤቱ ውሃን አየር ላይ ያረጋህ
ከቀዳሚ ትውልድ ፤እስከ ከዳሚ ትውልድ ዘመንህን የዘረጋህ
በጃርት ወስፌ ጠንቁለህ ፤ያሞራን አይን ያፈሰስህ
ካላጣኸው እጄጠባብ፤ ኤሊን ድንጋይ ያለበስህ
ካልቸገረህ ወጣትነት፤ አዳምን ባርባ ዐመት ያስረጀህ 
በህዳር በሽታ ዘመዶቼን የፈጀህ

ሀቅ ሀቁን ልንገርህ፤ እንደሌሎች ሳልሸነግል
ድሃ ሲጠልይልህ፤ ሃብታሞችን ምታገለግል
በሊብያ ምድረበዳ፤ባርያ ምታስፈነግል

ያባቴ አምላክ ያያቴ
አቤቱ እድል ፋንታየ፤አቤቱ እድል ስፕራይቴ
ርዳኝ
ወደ ዶላር ክምር ንዳኝ
ድህነቴ ለዘላለም፤ አስጎንብሳ ከምትከዳኝ
የቺስታነት ዘመኔ፤እንደቁመቴ ይጠር
ለዘላለም ከምትቦዝን፤ ለኔ ሚሆን ስራ ፍጠር
ከሻኪሶ የወርቅ መስክ፤ድርሻየን ሸርፈህ እጠር
ወይ ፈረንጁን አራራልኝ ፤save the children ልቀጠር

ያ ካልሆነም አንደበቴን ፤ነቢይነት አስተምራት
አድርገኝ መላከ መንክራት
ኩርማን ልቤን ውሰድና፤ባዱኛ በዝና አስክራት
በበጎች ሀብት አምበሽብሸኝ ፤ በመባ ባስራት በኩራት
ይሄ ሰንበሌጥ ምመን ፤ ከፊቴ ይውደቅ ይነሳ
ልፎግረው በምላሴ ፤ልገርስሰው በዳበሳ
እንደ አባባ ማርግ ፤እንደ ፍልስጤም ዳንሳ

አቤቱ ድንቅ ነው ስራህ! አቤቱ ድንክ ነው ስራህ
በዳይኖሰር መቃብር ላይ፤ የሰውን ህይወት የዘራህ
አቶ ምላስ ዜናይን እያጣደፍህ የጠራህ
ሙጋቤን ከጥልቅ እንቅልፍ ፤ወደ ወታደር እቅፍ የመራህ
የነጂዎቻችን እጣ ፤ከኒህ ጋራ ይደመር
በርካሽ የገዙን ሁላ፤ ፍጣሚያቸው አይመር
አሳልፈህ ስጣቸው፤ ለሪህና ላይዛመር፤

ጠሎተን እንኩዋን ባትሰማው፤ አደራ ባርክልኝ ግጥሜን
በተቀረ ርሳኝ ልርሳህ ፤ድምስስ አድርገው ስሜን
አሜን ብያለሁ አሜን
አሜን!

Filed in: Amharic