>

“የህወሓት የበላይነት” እንጂ “የሕግ የበላይነት” ብሎ ነገር የለም። (ስዩም ተሾመ)

በአማርኛ “መብት” (right) የሚለውን ቃል አንድ ሰው በአንድ ነገር ወይም ጉዳይ ላይ የሚፈልገውን ለማድረግ ሆነ ላለማድረግ የሚያስችለው ስልጣን ነው። ስለዚህ፣ ነፃነት ሁሉን-አቀፍና ምሉዕ የሆነ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ሲሆን መብት ደግሞ ነፃነትን የማስከበር “ስልጣን” (authority) ነው።

ነፃነት በራስ ፍላጎት (free will) የመንቀሳቀስ፣ አማራጭ መንገድን የመወሰና፣ በራስ ምርጫ የማሰብ፣ ማድረግና የመኖር መብት እንደመሆኑ መጠን ከኃላፊነት ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ስለዚህ፣ ሕይወትን በነፃ ፍላጎትና ምርጫ ለመምራት የሚያስፈልገው ነፃነት የሚገኘው ለተግባራዊ እንቅስቃሴያችን “ኃላፊነት” (responsibility) መውሰድ ስንችል ነው።
ጀርመናዊው ፈላስፋ “Nietzsche (pdf)” አገላለፅ፣ ኃላፊነት መውሰድ የሚችሉት ግለሰቦች (individuals) ብቻ መሆናቸውን “Only individuals have a sense of responsibility” በማለት ይገልፃል። ስለዚህ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በራሳቸው ኃላፊነት (responsibility) መውሰድ አይችሉም። በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው መብትና ነፃነት የላቸውም። ራሳቸውን-በራሳቸው የማስተዳደር፥ የመምራት አቅምና ስልጣን የላቸውም። በመሆኑም ለመንግስት በውክልና አሳልፈው የሚሰጡት መብት ሆነ ስልጣን የላቸውም።

በዚህ መሰረት፣ የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8(1) ላይ “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” የሚለው ፍፁም ስህተት ነው። ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- በራሱ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ከ31 ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ውስጥ ሦስቱ ብቻ ያሏቸው የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ምሉዕ መብት (የሉዓላዊ) ስልጣን ባለቤቶች ሊሆኑ አይችሉም። ሦስት መብቶች ብቻ ሰጥተው የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን አይችሉም።

በዚህ መሰረት፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርህ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ መርህ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ከመሆኑ በተጨማሪ ከተቀሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች፥ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር ይጋጫል።

የኢትዮጲያ ዜጎች በተፈጥሮ ምሉዕ መብት አላቸው። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት መብታቸውን የመጠየቅ ሉዓላዊ ስልጣን የላቸውም። የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በሕገ-መንግስቱ መሰረት የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው። ነገር ግን፣ እንደ ግለሰብ ፖለቲካዊና ምክንያታዊ ፍጡር አይደሉም። ስለዚህ መብታቸውን እንዲከበር በራሳቸው አይጠይቁም። ግለሰቦች የራሳቸውም ሆነ የማህብረሰቡን (የብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ) ጥያቄ ሲያነሱ “ፀረ-ሰላም፥ ፀረ-ልማትና ፀረ-ዴሞክራሲ…” ተብለው ይፈረጃሉ፣ “ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃል ለመናድ…” በሚል በፀረ-ሽብር አዋጁ ይከሰሳሉ።

በአጠቃላይ በሕገ-መንግስቱ መሰረት የፖለቲካ መብት ያላቸው ዜጎች ሲሆኑ የፖለቲካ ስልጣን ያላቸው የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ናቸው። የኢትዮጲያ ዜጎች የማይጠይቁት ምሉዕ መብት ሲኖራቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ደግሞ የማይጠቀሙበት ሉዓላዊ ስልጣን አላቸው።

የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ (ተፈጥሯዊና ፖለቲካዊ) መብቶች በሕገ-መንግስቱ ዋስትና ቢሰጠውም እንዲከበር መጠየቅ አይችሉም። ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በሕገ-መንግስቱ መሰረት የስልጣን የበላይነት ቢኖራቸውም መብታቸው እንዲከበር በራሳቸው መጠየቅ አይችሉም። የብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ጥያቄ ዜጎች (ግለሰቦች) መጠየቅ አይችሉም።

ይህ “በብሔር ሉዓላዊነት” ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ከተገለፀው የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ጋር የሚፃረር ነው። የእያንዳንዱ ሰው ዓላማና እንቅስቃሴ ያለውን አንፃራዊ ነፃነት ማሳደግ እና/ወይም ፍርሃቱን መቀነስ ነው። ነገር ግን፣ “በብሔር ሉዓላዊነት” ላይ የተመሰረተው ፖለቲካዊ ስርዓት የዜጎችን ነፃነት የሚገድብና ፍርሃታቸውን የሚጨምር ነው። እንደ መንግስት የዜጎች መብትና ነፃነት ከማስከበር ይልቅ በተደጋጋሚ የሚጥስ ነው።

በመቀጠል የሀገር እድገትና ብልፅግና መርህን ይቃረናል። ምክንያቱም የሀገር እድገትና ብልፅግና የሚረጋገጠው የለውጥና መሻሻል መንፈስ ሲኖር ነው። የለውጥና መሻሻል መንፈስ የሚኖረው የግለሰቦች መብትና ነፃነት ሲከበር ነው። “በብሔር ሉዓላዊነት” ላይ የተመሰረተው ፖለቲካዊ ስርዓት የዜጎችን መብትና ነፃነት አያከብርም።

ይህ የፖለቲካ ስርዓት፤ “ኢትዮጲያ የተመሰረተችው ከብዙሃንነት ይልቅ በአህዳዊ አንድነት ላይ ነው፣ እንደ ሀገር ካሉን አኩሪ የድል ታሪኮች ይልቅ አስከፊ በደሎችን በመዘርዘር፣ “ኢትዮጲያዊነት” ከወደፊት አብሮነት ይልቅ “በአማራ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ነው!” በሚል የታሪክ ክህደት ላይ የተመሰረተ ነው።

ይህ የኢትዮጲያን ታሪክ እና የዜጎቿን መብት የሚክድ ፖለቲካዊ ስርዓት በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ህወሓት) መሪነት የተዘረጋ ነው። የህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በዘውግ ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። በትጥቅ ትግል ወቅት ድርጅቱ ከራሱ አመራሮችና ልሂቃን ምንም ዓይነት የተለየ ሃሳብና አስተያየት እንዲነሳ የማይፈቅድ ነው። ይህንን የቀድሞ የህወሓት (TPLF) መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንደሚከተለው ገልፀውታል፡-

“…the prevalence of the TPLF at this stage of the struggle was attained by its rigorous mobilization of the people based on the urge of ethno-nationalist self-determination on the one hand and the enforcement of strict internal discipline of its rank and file that able to take on rival forces decisively.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991)፣ Page 151 – 152.

የህወሓት የፖለቲካ አቋምና ድርጅታዊ ባህል በሕዝቦች መካከል ልዩነትን የሚፈጥር፣ የማይለያዩ ነገሮችን በመለያየት የተመሰረተ እንደመሆኑ የመጨረሻ ውጤቱ “የመለያየት ኃይል” (separative power) መሆኑ እርግጥ ነው። ይህ ፖለቲካዊ ኃይል ከዜጎች መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ይልቅ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚውል ነው።

በእርግጥ ህወሓት ራሱን የትግራይ ሕዝብ ተወካይ አድርጎ ቢያቀርብም የድርጅቱ የትግል ስልትና ዓላማ ከሕዝብ እኩልነትና ተጠቃሚነት ይልቅ የልሂቃኑን የስልጣን የበላይነት የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ህወሓት እንደ ድርጅት የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ስለሌለው በትጥቅ ትግል ወቅት የተፈጠረውን የወገንተኝነት፥ ተበዳይነት፥ ጥላቻና ጠላትነት ስሜት ከውስጡ ማውጣት አልቻለም።

በዚህ መሰረት፣ በራስ-ወዳድነት (egoism) በተሞላ “አሮጌ ነፍስ” እየተመራ፣ “የጭቆና ፈረሶችን” እየጋለበና “የዕልቂነት ነጋሪቶችን” እያስጎሰመ ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ቡድን ነው። “በብሔር ሉዓላዊነት” ላይ የተመሰረተው ሕገ-መንግስት፣ እሱን ተከትለው የተዘረጋው መንግስታዊ መዋቅርና ተቋማት፣ የሚወጡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች፣ የፍትህና ፀጥታ ተቋማት አደረጃጀት፣ …ወዘተ ሁሉም የህወሓትን የበላይነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት በአራት አባል ድርጅቶች ጥምረት የተፈጠረ ቢሆንም ሥራና ተግባሩ የሚመራው በህወሓት የፖለቲካ መርህና መመሪያ ነው።  በፌዴራሉ መንግስት ስር ያሉት የፍትህ፥ ፀጥታና የደህንነት ተቋማትና መዋቅር ዋና አገልግሎታቸው የህወሓትን የበላይነት ማስቀጠል ነው።

በእርግጥ በሁሉም ደረጃ የሚወጡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች ለሕገ-መንግስቱ ተገዢ መሆን አለባቸው። ነገር ግን፣ የሕገ መንግስቱ ትርጉምና ፋይዳ የህወሓትን የፖለቲካ አመለካከት ተግባራዊ በማድረግና የራሱን የስልጣን የበላይነቱን ማስቀጠል ነው። ስለዚህ ለሕገ መንግስቱና ለመንግስታዊ ስርዓቱ ታማኝ መሆን በራሱ ለህወሓት ተገዢ መሆን ነው። በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት “የህወሓት የበላይነት” እንጂ “የሕግ የበላይነት” ብሎ ነገር የለም።

Filed in: Amharic