በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 12 መሰረት “የመንግስት አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት አለ” እንዳይባል ባለፉት አስር አመታት ሙስና እና ብልሹ አሰራር ምን ያህል እንደተንሰራፋ መንግስት ራሱ ጠንቅቆ ያውቃል። በአንቀፅ፡-11 መሰረት “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም” እንዳይባል በቅርቡ በእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ላይ የተፈፀመውን ግፍና በደል መጥቀስ ብቻ በቂ ነው።
እንደ ማዕከላዊና ቅሊንጦ ባሉ እስር ቤቶች በፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣…ወዘተ ላይ የሚፈፀመውን የስቃይ ምርመራና እንግልት የሚያውቅ በአንቀፅ፡-10 መሰረት “የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች” በጭራሽ እንዳልተከበረ ይመሰክራል። በመጨረሻም፣ ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፀረ-ሽብር አዋጁ እየተዳኘ ባለበት ሁኔታ በአንቀፅ፡-9 መሰረት “የሕገ-መንግስቱ የበላይነት ተረጋግጧል” ሊባል አይቻልም።
ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከአምስቱ (5) መሰረታዊ መርሆች ውስጥ አራቱን (4) እየጣሰ ይገኛል። ለዚህ ሁሉ ዋና መነሻ ምክንያቱ ደግሞ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 ላይ የተጠቀሰው “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ ነው። ይህ መርህ፤ አንደኛ፡- በፅንሰ-ሃሳብ ደረጃ ከተቀሩት አራት የሕገ-መንግስቱ መርሆች ጋር በቀጥታ ይጋጫል። ሁለተኛ፡- የህወሓትን የፖለቲካ አመለካከትና የስልጣን የበላይነት የማስቀጠል ዓላማ ያለው ነው፣ ሦስተኛ፡- ተግባራዊ ሲደረግ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ይጣሳሉ።
ስለዚህ ሕገ-መንግስቱ ካልተሻሻለ፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በማንኛውም አግባብ ተግባራዊ ከተደረገ በዜጎች ላይ የሚፈፀመው የመብት ጥሰት ይቀጥላል። ለምን እና እንዴት የሚለው ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከታለን።
መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተደነገጉበት የሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል ሁለት መሰረት የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች፤ በንዑስ አንቀፅ 39(1) “በራስ የመወሰን፥ የማስተዳደር፣ ቋንቋና ባህሉን የማሳደግ መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 40(3) መሰረት “የመሬት ባለቤትነት መብት”፣ እንዲሁም በንዑስ አንቀፅ 43(1) መሰረት “የልማት መብት” እንዳላቸው ይጠቅሳል። በአጠቃላይ በሕገ-መንግስቱ ከተዘረዘሩት 31 መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ውስጥ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ሦስት መብቶች ብቻ ነው ያሏቸው።
በእርግጥ እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ የተጠቀሱት የብሔር መብቶች ይኖሩታል። ብሔሮች እንደ ግለሰቦች የራሳቸው ሃሳብና አመለካከት የላቸውም። ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት መብቶች ሌላ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃቶች የሏቸውም። እንደ ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ስላልሆነ “ሰብዓዊ መብቶች የሉትም። በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ምሉዕ መብት ያለው ግለሰቦች እንጂ ብሔሮች አይደሉም።
“ሉዓላዊነት” (Sovereignity) ማለት “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት ነው”። በዚህ መሰረት፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል። በሕገ-መንግስቱ ከተዘረዘሩት 31 መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ውስጥ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ሦስት (3) መብቶች ብቻ ሲኖራቸው እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ እንደ ግለሰብና እንደ ብሔር ተወላጅ ሁሉም መብቶች (31) መብቶች ይኖሩታል።
በሕገ መንግስቱ መሰረት የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ምሉዕ መብትና ነፃነት ስለሌላቸው የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን አይችሉም። እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ ግን ምሉዕ መብትና ነፃነት ስላለው የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት መሆን ሊኖረው ይገባል። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8(1) መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው” ይላል። በንዑስ አንቀፅ 8(2) ደግሞ “ሕገ-መንግስቱ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ሉዓላዊነት መገለጫ ነው” እንደሆነ ይገልፃል።
በመሰረቱ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል ባለ መብት ብቻ ሳይሆን ባለስልጣን ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ ሉዓላዊ ስልጣን ያለው አካል በሀገሪቱ መንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ይኖረዋል። ስለዚህ፣ የሀገሪቱ መንግስት ተጠሪነቱ ለዚህ አካል ይሆናል። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት፤ የሀገሪቱ ዜጎች መብትና ነፃነት አላቸው፣ ብሔሮች ደግሞ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው።
ዜጎች ምሉዕ መብት አላቸው፣ መብታቸውን የመጠየቅ (ሉዓላዊ) ስልጣን ግን የላቸውም። ብሔሮች ደግሞ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን አላቸው፣ የሚጠይቁት ምሉዕ መብት ግን የላቸውም። በሕገ-መንግስቱ መሰረት ዴሞክራሲያዊ መብቱና ነፃነቱ የዜጎች ነው፣ ፖለቲካዊ ስልጣንና መብቱ ግን የብሔሮች ነው!
የኢትዮጲያ ዜጎች የማይጠይቁት መብት አላቸው፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የማይጠቀሙት ስልጣን አላቸው። የኢህአዴግ መንግስት ዘወትር ስለ ብሔር መብትና እኩልነት ይደሰኩራል። የፖለቲካ መብትና ነፃነታቸውን የጠየቁ ዜጎች እንደ ጠላት እያደነ ለእስር፥ ስደት፥ ስቃይ፥ መከራ ይዳርጋል። የሕዝቡ ጥያቄ ፖለቲካዊ ውጥረትና አጣብቂኝ ውስጥ ሲከተው ደግሞ ልክ እንደ ዛሬው “የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ” ብሎ ይወስናል።
ነገ የሀገሪቱ ዜጎች የፖለቲካ መብትና ነፃነታቸው እንዲከበር ያለ ገደብ መጠየቅ ይችላሉ? አይችሉም! ምክንያቱም በሕገ-መንግስቱ የተደነገገ መብት እንጂ መብታቸው እንዲከበር የመጠየቅ “ስልጣን” የላቸውም። የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የዜጎች መብትና ነፃነት እንዲከበር መጠየቅ ይችላሉ? አይችሉም! ምክንያቱም ብሔሮች እንደ ሰው በራሳቸው ማሰብና መናገር አይችሉም። እንደ ሰው ማሰብና መናገር ቢችሉ እንኳን የሚጠይቁት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የላቸውም።
ኢትዮጲያ የኢትዮጲያዊያን ናት! በሀገራቸው እና መንግስታቸው ላይ ሙሉ መብትና ስልጣን ያላቸው ዜጎች ናቸው። ብሔር የባህልና ቋንቋ ውጤት እንጂ ሰብዓዊ ፍጡር አይደለም። በራሱ አያስብም፥ አይጠይቅም፥ አይናገርም! የማያስብ፥ የማይጠይቅ፥ የማይናገር ግዑዝ ማህበራዊ ፍጡሩ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ሊሆን፥ መሆን አይችልም።
“የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” በሚል የዜጎችን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለራሱና ለራሱ ብቻ ያደረገው ህወሓት ነው። “የብሔሮች መብትና እኩልነት” በሚል የሞኝ ፈሊጥ የኢትዮጲያዊያንን መብትና ነፃነት እየገፈፈ ያለው፣ ዜጎች በሀገራቸውና መንግስታቸው ላይ ያላቸውን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት በመግፈፍ ሀገር-አልባ አድርጎ፣ በማን-አለብኝነት ሰብዓዊ መብትና ክብራቸውን እየገፈፈ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ ነው። በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 መሰረት ለብሔሮች የተሰጠው ሉዓላዊ መብትና ስልጣን በዜጎች እጅ እስካልገባ ድረስ ጨቋኝና ጭቆናን ከዚህ ሀገር አይጠፋም።