>

የማይዘነጋው ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ! (ቆንጂት ተሾመ)

 

ለጨርቆስና አካባቢው ልጆች አውርቶ የማይጠግበው፤ አዲስ አበባ የማንም አይደለችም የኢትዮጵያውያን እንጂ ሲል የሚሟገተው፤ የብሔር ፖለቲካን እየኮነነ ‹ኢትዮጵያዊ መንፈስን› የሚያቀነቅነው፤ እግር ኳስን መመልከት ቀን ከሌሊት የማይሰለቸው፤ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁሉ የኒውካስል ክለብ እና እንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ሽንፈት የሚያመው፤ የሀገሩ ስደተኞች ጉዳይ የሚያንገበግበው ኢብራሂም ሻፊ አህመድ ይህችን ምድር በሞት ተሰናብቷል።

በሀገር ቤት ለሁለት አስርት ዓመታት በመገናኛ ብዙሀን የሰራው ኢብራሂም፤ የዛሬ ሶስት ዓመት የመንግስትን እስር በመሸሽ ከሀገር ከወጡ የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ጋዜጠኞች አንዱ ነው። በስደት ከኖረባት ኬንያ ሆኖ በማህበራዊ ገጽ ስለ ሀገሩ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና፣ ስለ ስፖርት ሲከትብ፤ ደግሞም ሲሟገት ቆይቷል። የመንግስት ተቃዋሚ ቢሆንም ለሀገሩና ለወገኑ ደግ ህልምና ቅን ልብ ነበረው። አሁን ግን ኢብራሂም ከትልልቅ ሀሳቦቹና ህልሞቹ ጋር ይህችን ዓለም ተሰናብቷል።

ለመጨረሻ ጊዜም ገጹ ላይ ያሰፈረው የቀድሞው የዓለም ኮከብ ተጫዋች ላይቤሪያዊው ጆርጅ ዊሀ በሀገሩ የተካሔደውን ፕሬዝንታዊ ምርጫ ማሸነፉ የፈጠረበትን ስሜት ነው።

ከዘጋቢነት እስከ ብሔራዊ ቡድን አማካሪነት ኢብራሂም ሻፊ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው በስፖርት ጋዜጠኝነትና እግር ኳስ ተንታኝነት ነው። በዋናነትም በኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ ላይ ነው። በኳስ ሜዳ የራዲዮ መድረክም ትንታኔዎችን ያቀርብ ነበር። በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ደግሞ ኢብራሂም በስፖርት አምድ አዘጋጅነት ብቻ ሳይሆን በመጽሔቷ የምክትል ዋና አዘጋጅነት ኃላፊነትን ይዞ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማህራዊ ጉዳዮች ላይም ይጽፍ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም በሲቪክስ ትምህርት መምህርነትም ሰርቷል። በይፋ ባይነገርለትም በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት ኢብራሂም ከሚቀርባቸው አንዳንድ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ጋር የአማካሪነት ስራን ይሰራ ነበር።

የፖለቲካ ሳይንስ ዲግሪውን የተቀበለበትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን የእግር ኳስ ቡድን አሰልጥኗል። ያኔ ተማሪ ቢሆንም አሰለጣጠኑ ግን መደበኛ ሙያው ይመስል እንደነበር የሚውቁት ይመሰክራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የስፖርት ጋዜጠኞችን ቡድን በሚሳተፍባቸው ውድድሮች አሰልጣኝ ሆኖ ይሳተፋል። ውድድሩ ለመዝናኛነት በተዘጋጁ መድረኮች ላይ ቢሆንም እርሱ ግን ቡድኑን ከልቡ ያሰለጥን እንደነበር አብረውት የነበሩት ይናገራሉ።

ኢብራሂም በኢትዮጵያ እግር ኳስ!

ኢብራሂም በእግር ኳስ ጋዜጠኝነት ህይወቱ የሰራባቸው ኢትዮ ስፖርትና ኳስ ሜዳ የእግር ኳስ ግጥሚያ የራዲዮ ዝግጅት በአብዛኛው ለባህር ማዶ እግር ኳስ ሽፋን የሚሰጡ ናቸው። ይሁንና የኢብራሂም የእግር ኳስ እውቀት በባህር ማዶ ስፖርት ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም። የሀገር ውስጥ ጨዋታዎችን በአካል ተገኝቶ የሚከታተልና በቂ ግንዛቤና መረጃዎችም ያሉት ጋዜጠኛ ነው። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ተጽዕኖ ከሚያሳርፉ ጥቂት የስፖርት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነበር።

ኢብራሂም በውጭ ሀገር የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውንን በማፈላለግና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲጫወቱ በማድረግ ተሳትፎ ነበረው። የውጭ ሀገር አሰልጣኞች በሚፈለጉበትና በሚጠሩበት ጊዜም የቀደመ ታሪካቸውን በማሰስ ለፌዴሬሽኑ ያቀርብ ነበር።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ አቋም ይዘው ድምጻቸውን ከሚያሰሙ ጋዜጠኞች መካከልም አንዱ ነው። በተለይም ደግሞ በብሔራዊ ቡድን ውስጥ እንደ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን በተንታኝነትና ያልተገለጸ አማካሪነትም ጭምር የላቀ ተሳትፎ ነበረው።

ለአብነት ያህልም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞው ውስጥ የነበረውን ሚና መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተሳትፎ ሲጀምር ጀምሮ ሰፊ ዘገባዎችና ትንታኔዎችን ጽፏል። ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፎ ተጋጣሚዎቹም ሲታወቁ በየሳምንቱ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ለቡድኑ ውጤታማነት ጠቃሚ መረጃዎችን ሰጥቷል፤ የተጋጣሚዎቹን ቡድኖች በጥልቀት በመመልከትና በመዳሰስ ለኢትዮጵያ ቡድን የሚሻለውን መንገድ ለማሳየት ሞክሯል።

በአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤታማ ለመሆን የሚያዋጣውን አሰላለፍ ጭምር በመጠቆም ከዘጋቢነትም በላይ ለአሰልጣኞችና ተጫዋቾች የአማካሪነት ሚና ነበረው። እርሱ ቀድሞ የሚጠቁማቸው ታክቲኮችና የአሰላለፍ ዘዴዎች በቡድኑ ተግባራዊ ሲሆኑም ይታያል።

አሰልጣኞቹ እንዲህ ማድረግ አለባቸው ብሎ የሚሰጣቸው አስተያየቶች በአብዛኛው ተአማኒነት አግኝተው ተተግብረዋል። ለአብነት ያህልም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡድን አባል የሆኑት አበባው ቡታኮና ሲሳይ ባንጫ ላይ የተወሰደው የቅጣት ውሳኔ አንደኛው ማሳያ ነው።

ሁለቱ ተጫዋቾች ከናይጄሪያ ጨዋታ በኋላ እርስ በእርስ መደባደባቸው በሰፊው ተዘግቦ ነበር። ኢብራሂም ሻፊ ግን ከሌሎች በተለየ መልኩ ተጫዋቾቹ ላሳዩት የጨዋነት ጉድለት በቀጣይ ጨዋታ ከቡድኑ መታገድ አለባቸው የሚል አቋሙን አንጸባረቀ። በእርግጥም እርሱ እንዳለው ተጫዋቾቹ ላይ ቅጣት ተላለፈባቸው።

ኢብራሂምና ኢትዮጵያዊ መንፈሱ!

ኢብራሂም በእግር ኳስ ስፖርት ፍቅር ያበደ ቢሆንም ለሀገሩ ኢትዮጵያ ያለው ስሜት ግን ቅድሚያውን ይይዛል። በስደት ከሀገር ከወጣ በኋላ በተለይ የኢትዮጵያና ህዝቦቿን እያንዳንዷን ነገር ይከታተላል። በስክነት አስቦም ያመነበትን እውነት ይገልጻል። በጣም የሚያስደንቀው ሰብዕናው ደግሞ ሀገሬ ለስደትና እንግልት ዳረገችኝ ብሎ እንዲህ ሆንኩኝ ብሎ ያማረረበት ጊዜ አለመኖሩ ነው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢብራሂምን የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ ይነሳዋል። ህመሟ ያመዋል፤ ችግሯ ያስጨንቀዋል። አንድነቷን ሁሌም ይሰብካል። በሀይማኖት፣ በብሔርና በጎሳ ሊከፋፍሏት የተነሱትን ሁሉ ይወቅሳል። የተሳሳቱ የመሰለው ጊዜም ምክሩን ከመለገስ ወደኋላ አይልም።

ኢትዮጵያዊነትን ያቀነቅናል። ይህን አስተሳሰብ ከሚራምዱት ጋር አብሮ ይዘምታል። ስለኢትዮጵያ አንድነት የሚሰብኩ ጀግኖችን ደጋግሞ ያወድሳል። ለድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ያለው ፍቅር የመነጨውም ከዚሁ ስሜት በመነሳት ነው።

ኢብራሂም በተለያዩ ጉዳዮች ከፍተኛ ልዩነት ቢኖረውም በኢትዮጵያዊነት ግን አንድ ሆኖ ይገኛል። በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር አይደራደርም። እንደ እርሱ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ምሬት ያላቸው ብዙ ወዳጆች ቢኖሩትም ኢትዮጵያን ሊቆርሱ ባሰቡ ጊዜ ግን… ሀገሩን በብሔርና ሀይማኖት ሊከፋፍሉ በሚራመዱ ጊዜ ግን… ይለያቸዋል፤ ይቃወማቸዋልም። ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› የሚለው ብሒል ኢብራሂም ጋር ፈጽሞ አይሰራም። ለዚህም አንድ ማሳያ ለመግለጽ እወዳለሁ።

ኃይሌ ገብረስላሴ ከአትሌቲክስ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ላይ አልፎ አልፎ የሚሰጣቸው አወዛጋቢ አስተያየቶች ላይ የሰላ ትችት ከሚያቀርቡ ጸሐፊዎች መካከል ኢብራሂም አንዱ ነው። ኃይሌ ከፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነቱና ኢትዮጵያዊነትን ከማቀንቀኑ ጋር በተያያዘ ብሔርተኞች ፈተና በሆኑበት ጊዜ ግን ኢብራሂም ለጀግናው አትሌት ወግኖ ተገኝቷል። ተቺዎቹንም አፍ የሚያዘጉ የመልስ ምቶችን ሰንዝሯል። ኃይሌን በበቂ ሁኔታ ግን አልተከላከልኩለትም ብሎ ይጸጸት ነበር።

ከዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከእኔ ጋርም ለመጨረሻ ጊዜ መልዕክት የተለዋወጥነው ከአራት ወራት በፊት ከኃይሌ ገብረስላሴ ኢትዮጵያዊ መንፈስ አራማጅነት ጋር በተያያዘ ነበር። ኃይሌ አትሌቲክስ መሪነት ከመጣ በኋላ ለስፖርቱ ውጤት ኢትዮጵያዊነትን ለማስረጽ የሚያደርገው ጥረት ብሔርተኝትን የሚያራምዱ ወገኖች የሚደግፉት አልሆነም። በተለያዩ አቅጣጫዎችም ጫና ስለፈጠሩበት በፈቃዱ ኃላፊነቱን ሊለቅ ስለመሆኑ ተወርቶ ነበር። እንደነገ መግለጫ ሰጥቶ ሀላፊነቱን ይለቃል ከተባለበት እለት አንድ ቀን በፊት ማታ ላይ የኢብራሂም መልዕክት ደረሰኝ።

‹‹ስለ ኃይሌ የሚባለው ነገር እውነት ነው ግን?›› ሲልም ጠየቀኝ። ወሬው ለኔም በጣም አስደንጋጭና ያልጠበኩት ነበር። ሀገር ቤት ያለን ጋዜጠኞች ያልሰማነውን ወሬ ቀድሞ መስማቱ እያስገረመኝ መረጃውን አጣርቼ እንደማሳውቀው ነገርኩት።

‹‹እውነት ካደረገው ራሴን መቼም ይቅር አልለውም። ምክንያቱም በበቂ ሁኔታ አልተከላከልኩለትም›› በማለትም በጸጸት ስሜት ማልቀሱንም ነገረኝ።
‹‹ፌዴሬሽኑ በ25 ዓመት ታሪኩ አሁን ገና ነው መሪ ያገኘው›› ሲልም በእነ ኃይሌ አመራር ተስፈኛነቱን ገለጸልኝ።
የዚያኑ ምሽት የተናፈሰውን ወሬ አጣርቼ ከሰአታት በኋላ ኢብሮን ደግሜ ፈለኩት። ሰአቱ እኩለ ለሊት ቢያልፍም እርሱ ግን አልተኛም። በመስመር ላይ ነበረ። ኃይሌ እንደተባለው በዘረኝነት ተግባሮች ተማሮ ኃላፊነቱን እንደማይለቅ ከታማኝ ምንጮች ማረጋገጤን ነገርኩት።

‹‹አላህ ይስጥሽ! አሁን በቃ እቅልፌን ልተኛ›› አለና ተሰናበተኝ። በማግስቱም ኃይሌ ገብረስላሴ ለቀቀ የሚል ዜና አልበረም። ኢብሮ ቢያንስ በዚህ ጉዳይ እንቅልፍ አያጣም ብዬ ስለ እርሱ ደስ አለኝ።

ኢብራሂም የቅርብ ወዳጆቹ ስሜት!

ኢብራሂም ሻፊ ለሞት የዳረገው የእግርና የወገብ ህመም ለረጅም ጊዜ አብሮት የቆየ ነው። በ1997 ዓ.ም በፖሊስ ኃይሎች የደረሰበት ድብደባ መንስኤነት ነው። በስደት በኖረባት ኬንያ የረባ ህክምና ሳያገኝ በስቃይ መሞቱ የሚያውቁትን ሁሉ አሳዝኗል። እርሱን በቅርበት የሚያውቁት ወዳጆቹ ህልፈተ ህይወቱን ሲሰሙ የፈጠረባቸው ስሜት በተለይ በማህበራዊ የገጽ ድሮች ላይ ገልጸዋል። የሁሉም ስሜቶች ጋዜጠኛው የነበረውን የላቀ የመንፈስ ልዕልና እና ኢትዮጵያዊ መንፈስን የሚያረጋግጡ ናቸው። ለብዙዎችም በመልካም አርአያነት የሚጠቀስ ሰብዕና ባለቤት መሆኑን የሚያስረዱ ናቸው።

ኢብራሂም ሻፊ ያለውን እውቀትና የሙያ ልምድ ሳይሰስት መስጠት የሚወድ፤ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነትም የተመሰገነ መሆኑን የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የምመሰክረውና ብዙዎችም የሚያውቁት እውነት ነው። በሐሳብ ልዩነት ከሚሟገታቸው ሰዎች ጋር እንኳ ያለው ግንኙነት ጤናማ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ላመነበት እምነት እስከመጨረሻው የሚታገልና የራሱን መንገድ ይዞ የሚጓዝ በመሆኑ ሁሌም ሲታወስ እንዲኖር ያደርገዋል።

ነፍስህ በሰላም ትረፍ ኢብሮ!

Filed in: Amharic