>

የነ ለማን የትግል አካሄድ እንዴት እንመልከተው? (አበጋዝ ወንድሙ)

ለማ መገርሳና አብረውት ባሁኑ ጊዜ በኦህዴድ ውስጥ የበላይነትን የተቀዳጁት ያመራር አባላት፣ የህዝቡን ጩሀት
ለማዳመጥና አንዳንድ እርምጃዎችንም ለመውሰድ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ በኦሮሚያ ክልል ብቻ
ሳይወሰን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃና በውጭ ሃገራት ስደት ላይ ካለው ወገን ጭምር ድጋፍ እያስገኘላቸው እንደሆነ
ግልጽ ነው።
ይሄ የህዝብን ጩሀት ለማዳመጥ መሞከርና አንዳንድ ቀናኢ እርምጃ መውሰዳቸው የተወሰነ የህዝብ ድጋፍ
እንዲያገኙ ማድረጉ ግን፣ እስካሁን ኢህአዴግን በበላይነት ለሚያስተዳደረው ህወሃት በድርጅቱ ውስጥ ያለው
የበላይነት ማብቂያ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ላይ ስለጣለው፣ የነለማን ቡድን ጠልፎ ለመጣል በርካታ
ሙከራዎችን ሲያደርግ ቢቆይም እስካሁን ሊሳካለት አልቻለም።
በተጨባጭ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ካጤንን ኦህዴድ የኢህአዴግ አካል በመሆኑ፣ የነለማ ቡድን የሚያካሂደው ትግል በሀገሪቱ ባለው ህገ-መንግስትና በኢህአዴግ ድርጅታዊ ማዕቀፍ ውስጥ እንደመሆኑ ሊጓዝ የሚችለው ርቀት ውሱን እንደሆነ ነው።
አንዳንድ ወገኖች ይሄን በመዘንጋት ወይንም ነባራዊ ሁኔታውን በቅጡ ካለመረዳትም ሊሆን ይችላል፣ወይንም
ምናልባት በተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ በሚታየው ድክመት ተስፋ በመቁረጥ፣ የራሳቸውን ምኞት ኦህዴድ ላይ
እስከ መጫንና (project በማድረግ)፣ ይሄን ቢያደርግ ያንን ቢያደርግ ወደሚል አጀንዳ ቀረጻና የቅደም ተከተል አካሄድ እስቀመቀየስ ሲደርሱ የምናየው ።
በሌላ ወገን ደግሞ እነለማ በእናት ድርጅታቸው ኢህአዴግ ውስጥ ሊያደርጉት የሚችሉት ትግል ውሱን ቢሆንም
ለአጠቃላይ ህዝባዊ ትግል ሊኖረው የሚችለውን አስተዋጽኦ አኮስሶ፣ የዋህነት ካልሆነ ከነሱ ምን ይጠበቃል!
ወይንም አንዳንዱ ደግሞ ጭሩሱኑ የህወሃት ተልአኮ የተሰጠውና የህዝባዊ እንቅስቃሴውን ለማለዘብ የታቀደ
መሰሪ አካሄድ ነውና፣ እንኳን ለሚያደርጉት ትግል ድጋፍ ልንሰጥ ተላላኪነታቸውን ከስር ከስር ነቅሰን እያወጣን
ማጋለጥ ነው መሆን ያለበት የሚል ውዥንብርም ይደመጣል።
ከላይ እንዳልኩት የነለማ ቡድን በድርጅቱ ውስጥ በሚያደርገው ትግል ውሱን ይሁን እንጂ ፣ብዙዎቻችን
ለምንመኛት የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣ የዜጎች መብት የሚከበርባትና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን
ዕውን ለማድረግ ለሚደረገው ረጅም ትግል ግን ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ነገሮችን ከወዲሁ እንዳደረገና፣
ለዚህም ያደረሰው ህዝባዊ ትግል ግለቱን እየጨመረ እስከሄደ ድረስ ተጨማሪ ግብአቶች ሊያበረክት እንደሚችል
መገመት ይቻላል።

ከዚህ አንጻር በኔ ግምት መልካም ግብአት ከምላቸው ውስጥ ምሳሌ ብጠቅስ፣ ህወሓት ለ 26 ዓመት
የበላይነቱን ማስጠበቂያ ዋና መሳሪያ አድርጎ ይጠቀምበት የነበረውን፣ በኦሮሞና አማራ ማህበረሰብ መሃል
ጥርጣሬና አለመተማመን፣ ከፍ ሲልም ጥላቻ በመዝራት የተገነባውን የክፍፍል አጥር ፣ የነለማ ቡድን የፖለቲካ
አመራሮችን፣የሃይማኖት አባቶችንና የባህል አምባሳደሮችን ይዞ ባህርዳር ድረስ በመሄድ፣ከአማራው ማህበረሰብ
ጋር ወንድማማችነታቸውንና እህታማችነታቸውን ባደሱበት ታሪካዊ ጉዞ ብትንትኑን ማውጣታቸው አንደኛው
ትልቅ ድል ነው።
ሌላው በኔ ግምት የነለማ ቡድን ትልቁ አስተዋጽኦ በሻእቢያ የተጎነጎነውን፣ ሀውሃትም ሆነ ሌሎች የብሔር
ድርጅቶችን ጨምድዶ ይዞ ብዙ እዳ ያስከፈለንን ኢ -ታሪካዊ ትርክት ድባቅ በመምታት፣ የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር፣በኢትዮጵያ ሃገራዊ ግንባታም ሆነ እድገት ፣እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ነጻነቷን ጠብቃ
እንድትኖር ያደረገውን አኩሪ ተጋድሎ ትክክለኛ ስፍራውን እንዲይዝ በማድረግ ላይ ያሉት አካሄድ ነው።

ሻአቢያ የራሱ የሆነ ነጻ ሀገር ለመመስረት ባካሄደው ትግል ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ፈጥሮት የነበረው ኢ -ታሪካዊ
ትርክት፣ ማለትም የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ምንም አይነት ታሪካዊ ግንኙነት እንዳልነበረው ፣ አለ
የሚባልም ከሆነ በቅኝ ገዢና ተገዥ መሃል ያለ ነው የሚል ሕያው ታሪክን በአፍጢሙ የደፋ ትርክት ነበር።
ይሄን ታሪካዊ ክህደት ተአማኒ ለማድረግም፣ የብዙ ሺ አመታት ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያ ትላንት የተፈጠረችና
የመቶ ዓመት እድሜ ያላት ናት የሚል በፍጹም ቅጥፈት ላይ የተመሰረተ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማካሄድ በርካታ
የብሄር ድርጅቶችን ለማወናበድ በቅቶ ነበር።
በጉርአ ፣ጉንደትና ሰዓጢ፣ ኢትዮጵያን ከወራሪ የታደጉ ጀግና ኢትዮጵያውያን የልጅ ልጆች የሆኑት ህወሃቶች
የዚህ ኢ -ታሪካዊ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ በመሆን ወንድማማች ህዝብ ከመለያየት አልፎ፣ መቶ ሚልዮን ህዝብ ወደብ
አልባ አድርጎ እስቀማስቀረት የደረሰ ታሪካዊ ስህተት እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል።
እርግጥ ቀድመው የህወሃት የፖለቲካና የውትድርና ባለስልጣናት (ስዬ፣ጻድቃን፣አበበ ተ/ሃይማኖትና በተለይ
ገብሩ አስራት)ድርጅቱ ውስጥ በነበሩበት ወቅት የሰሩትን ታሪካዊ ስህተት የተቀበሉና እርምት ለማድረግ የሞከሩ
ቢሆንም፣ ህወሃት ግን አስካሁንም ድረስ ይሄንን ስህተቱን ተቀብሎ ሃላፊነት ሲወስድ አይታይም።
ኦነግም ሆነ ሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኞች (አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ ) የዚህ የሻእቢያ ኢ -ታሪካዊ ትርክት
ምርኮኛ በመሆን፣ የ ኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጵያን በመገንባትም ሆነ ለረጅም ጊዜ አንድነቷን ለመጠበቅ
በተደረገው ትግል የነበረውን ወሳኝ ሚና በመካድ፣ ልክ እንደ ሻእቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት በቅኝ ገዢና
ተገዥ መሃል ያለ ነውና የሚቛጨውም ነጻ ኦሮሚያን በመመስረት ነው የሚል አካሄድ ብዙ ዕዳ አስከፍሎናል።
የነለማ ቡድን ይሄንን ከታሪክ ጋር ፈጽሞ የማይገጥም አካሄድ በመናድ የኦሮሞ ህዝብ የ ኢትዮጵያን ሃገራዊ
ማንነት ለመገንባትም ሆነ እስካሁንም ነጻነቷን አስከብራ ለመቆየትና ለወደፊትም ለምታደርገው ጉዞ፣ የኦሮሞ
ሕዝብ የነበረውንና ለወደፊትም የሚኖረውን ሚና በሚገባ ያገናዘበ ፣ በድፍረትና በሙሉ ልብ የሚያቀርቡት
አመለካከትና ትንተና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነትና የነጻነት ትግል ትልቅ አስተዋጽዖ አለው።
በመጨረሻም ያለፈውን ዓመት የነለማ ቡድንን አካሄድ ስናጤን፣ኦህዴድ የኢህአዴግ አካል መሆኑን ተገንዝበን፣
ሊያደርግ የሚችለው እንቅስቃሴም ዉሱን መሆኑን፣ዉሱንም ሆኖ ግን ለፍትህ ለነጻነትና ለዴሞክራሲ ለሚደረገው ትግል ጠቃሚ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ እስካሁን ለወሰዷቸው ገንቢ እርምጃዎች እውቅና ሊሰጣቸውና ሊበረታቱ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።የወሰዷቸው ገንቢ እርምጃዎች ደግሞ ያለ ሰፊው ሕዝብ እንቅስቃሴና ግፊት የማይታሰብ በመሆኑ የህዝቡ ትግል ቀጣይነት እንዲኖረው እነሱም ወደዃላ እንዳይሉ ሁላችንም እንደየ አቅማችን ብናግዝ የተሻለው አማራጭ ነው የሚል እምነት አለኝ።

 

Filed in: Amharic