>

የኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል ዓይነት ምርጫ አለው ወይ? (ከይኄይስ እውነቱ)

 

በመሪር አገዛዝ ወይም በባርነት ቀንበር ሥር የሚገኝ ሕዝብ ለነፃነት የሚያደርገው ትግል ተቃውሞ  የሚቀርብበትን የፖለቲካ ሥርዓት ዓይነት፣ የአገዛዝን ባህርይ ግምት ውስጥ ያስገባና ተቃውሞው ወይም የሚደረገው ዓመጽ ለዚኹ የሚመጥን መሆን ይኖርበታል፡፡ ከኀልዮ ወይም ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ በገቢር ምድር ላይ ያለውን ጽድቅ (እውነታ) ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሰላማዊ እና በኃይል ወይም በትጥቅ የተደገፈ በሚል ክፍፍል ነጭና ጥቁር አድርጎ በማቅረብ ሰላማዊው ስኬትን ያስገኛል፣ በተቃራኒው በኃይል የሚደረገው ዓመፃን ይወልዳል እንጂ መፍትሄ አይሆንም የሚል የመጨረሻ መደምደሚያ ላይ መድረስ ትክክል አይመስልም፡፡ አንደኛውን መንገድ ብቻ ወስዶ ለስኬት ዋስትና አድርጎ መውሰዱም ስህተት ላይ ሊጥለን ይችላል፡፡ በእርግጥ ኃይልን መሠረት አድርጎ የሚካሄድ ትግል የሚፈለገውን ዓይነት መንግሥተ ሕዝብ (እኩልነት፣ የሕግ የበላይነት እና ፍትሕ የሚሠፍንበት ሥርዓት) ለመመሥረት ያስችላል ወይ የሚለው በአገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ካሉ ተሞክሮዎች አኳያ ኹላችንን ሥጋት ውስጥ ይከተን ይሆናል፡፡ የሚፈለገው ግብ ላይ ለመድረስ ግን ሙሉ በሙሉ ዝግ የሆነ መንገድ ነው ማለት አይደለም፡፡ በተበታተነ ሰላማዊ ትግል ኹሌ በአገዛዙ አውሬዎች ጥይት ማለቁ ትክክለኛ የትግል ስልት ነው ወይ? ዙሪያ ገባ ያሉ ታሳቢዎችን (ከላይ እንደተጠቀሰው የፖለቲካው ሥርዓት ዓይነት፣የትግሉ አንኳር ጥያቄዎች÷ ዓላማና የሚፈለገው ውጤት፣ ተቃውሞው የመላ ሕዝብ ወይስ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፣ የሕዝብ ንቃተ ኅሊና÷ ተነሳሽነት÷ አንድነትና ኅብረት፣ በገዢውም ሆነ በተቃዋሚዎች በኩል ያለው የኃይል አሰላለፍ÷ አቅምና ብቃት፣ ሌሎች አገራዊ ተጨባጭ እውነታዎችና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ወዘተ.) በጥንቃቄ መፈተሸና ማስላትን ይጠይቃል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ባመዛኙ የጦርነት ታሪክ ነው የሚል ስምምነት ካለ፣ ይህ ታሪክ በጋራ ባህልና ሥነ
ልቦና እንደሚንፀባረቅ የሚታመን ከሆነ፣ ኅብረተሰባችን ጀግንነትን በዋናነት ከጦር ሜዳ ውሎ ጋር ማያያዙም እውነት ከሆነ፣ ሰላማዊ ለሚባለው ትግልም በአብዛኛው እንግዳ ከሆነ፣ ዋናው አማራጭ የኃይል/የትጥቅ ትግል ሆኖ ይታያል፡፡

በአንፃሩም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የኅብረተሰባችን ክፍሎች ሰላማዊ ትግልን በመርህ ደረጃ እንደሚመርጡ ይታመናል፡፡ ይህ መንገድ የሚመረጥበት ምክንያት መሥዋዕትነት የማይከፈልበት ስለሆነ አይደለም፤ ድልን በፍጥነት የሚያረጋግጥ ስለሆነም አይደለም (እንደውም በተቃራኒው ውጤቱ ከኃይል ትግል አኳያ አንፃራዊነት በጣም የሚዘገይ እንደሆነ ይታሰባል)፤ በአንፃሩም ይህን አቋም መያዝ ፈሪነትም አይደለም፡፡ ለሰብአዊነት፣ለሕሊና፣ለሞራል፣ ለእውቀት የሚመች ሥልጡን መንገድ በመሆኑ እንጂ፡፡ ይልቁንም ለሰላማዊ ሽግግር አስተማማኝ መንገድ ይሆናል፣ በጉልበት የሚቆም የአገዛዝ ሥርዓት አዙሪትን ያስቀራል ከሚል እምነትም የመነጨ ይመስለኛል፡፡ የዚህ አስተያየት አቅራቢ ምርጫም ሰላማዊው የትግል ስልት ነው፡፡ ይህ መንገድ ቢያንስ አገርና ሕዝብ አለኝ ብሎ በሚያስብ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ውስጥ የሚሠራበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የወያኔን አገዛዝ ባህርይ በተረዳኹበት መጠን እና በርካታ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ካሰለፍኹ በኋላ የሚከተለውን ሃሳብ ለማቅረብ ተገድጄአለሁ፡፡ ወረድ ብለን እንደምናየው በኢትዮጵያ ሰፍኖ የሚገኘው አገዛዝ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ አገዛዙ አንዳች የመንግሥትነት ጠባይ የለውም፡፡ የገጠመን ባላጋራ ተቃውሞ በተነሳበት ቁጥር እንደ ቅኝ ገዢ ኃይል ያለምንም ርህራሄ ሕዝብን የሚጨፈጭፍና ቀን ከሌሊት አገራዊ ሀብትን በመዝረፍ ላይ የተሰማራ ነው፡፡

ከፍ ብለን ካነሳነው ሃሳብ አንፃር ኢትዮጵያና ሕዝቧን የገጠማቸው ፈተና ሕዝብንና አገርን በጠላትነት ፈርጆ
ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን በመናድ ሕዝቧን ለማያቋርጥ ሰቆቃ፣ ሞት (የጅምላ ጭፍጨፋ) ፣ እስራት፣ ስደት፣ችጋር፣ እንግልት፣ ባጠቃላይ ለፖለቲካና ማኅበረ ኢኮኖሚያው ምስቅልቅል የዳረገ የወያኔ ትግሬ አገዛዝ ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያን በጎሣ አጥር ከልሎ አንድነቷን ያናጋ እና እንደ ጠላት አገር ማባሪያ በሌለው ዝርፊያ የተጠመደ የኅዳጣን አገዛዝ በዓለማችን ከነበሩ ወይም ካሉ ሌሎች አምባገነን ወይም ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ጋር የሚያመሳስለው ገጽታ ቢኖረውም እንደማናቸውም አምባገነን ወይም ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የሚታይ አይደለም፡፡ በምንገኝበት 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚገዛውን አገርና ሕዝብ በፍጹም ጠላትነት ፈርጆ በሥልጣን ላይ የተቀመጠ አገዛዝ በእኔ እውቀት ወያኔ ብቸኛ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እስከ የሌለው ድንቁርናና ዝርፊያውም እንዲሁ አቻ የለውም፡፡ ስብስቡ በሱፍና ክራቫት የተጀቦኑ ተራ የጫካ ወንበዴዎች ጥርቅም ሲሆን፣ ሚመራውም በጫካ ሕግ ነው፡፡ ለአፈና አገዛዙ የገነባውም የወያኔ ሠራዊት፣የወያኔ ደኅንነት እንጂ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አልነበራትም/የላትምም፡፡ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ተቋም አልነበራትም/ የላትምም፡፡ በግድያው የአንበሳውን ድርሻ ቢወስድም ሕዝብን ዕለት ዕለት እየጨፈጨፈ ያለው አግአዚ የተባለው የወያኔ ትግሬ ልዩ ጦር ብቻ ነው የሚል ካለ እጅግ ተሳስቷል፡፡ በእኔ እምነት ይህ እኩይ እና ዕቡይ
ቡድን ለሥልጣኑና ዝርፊያው ሲል እስከ መጨረሻው ይገድላል፡፡ ለዚህ ድርጊቱ ከሩብ ምእተ ዓመት በላይ ተሞክሮ አለን፡፡
ሁኔታዎች አሁን ተለውጠዋል የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ አዎን ተለውጠዋል፡፡ ወያኔ በውስጥም በውጭም
ተዳክሟል፡፡ ሕዝባችንም በሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዘናት በቃኝ ብሎ በአገዛዙ ላይ ተነስቷል፡፡ ዕለት ዕለትም ለነፃነቱ እየወደቀ ነው፡፡ ይህ ትግል ግን በአንድነት/በኅብረት የሚደረግ ባለመሆኑ የሚከፈለውን መሥዋዕትነት እጅግ ውድ ከማድረጉ በተጨማሪ ለአገዛዙም ፋታ የሚሰጥ ሆኗል፡፡ ትግሉ በአማራ እና በኦሮሞ አካባቢ እየተባለ በፈረቃ እስከ መቼ ይዘልቃል፡፡ መቼ ነው ሕዝባዊ ዓመጹ ኢትዮጵያው (አገር አቀፍ) የሚሆነው? አንድ በእርግጠኛነት መናገር የሚቻለው ጉዳይ ግን ወያኔ ከአቋሙ አንዲት ስንዝር ፈቅ አለማለቱ ነው፡፡ ይህ ቀጣፊ ቡድን መቼም እንደማይለወጥ በምን ቋንቋ ቢነገረን ነው የሚገባን?
ስለዚህ የትግሉ ስልት መውደቅ ብቻ ሳይሆን አውሬውን መጣል ካልተጨመረበት የወያኔን ማንአለብኝነትና
ዕብሪት ያስተነፍሰዋል ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ተቃዋሚ በሚባሉ ቡድኖች አሁንም ለውጥ የለም፡፡ ስልታዊ አንድነት/ኅብረት ለመፍጠር የግል አጀንዳቸው ተብትቦ ይዟቸዋል፡፡ አገርና ሕዝብን የሚያስቀድም እውነተኛ ተቃዋሚ ድርጅት ካለ የተበታተነውን የሕዝብ ተቃውሞ/ዓመጽ በዚህ በአሥራ አንደኛው ሰዓት ያላስተባበረ/ያላቀናጀ መቼ ነው አገርንና ሕዝብን ለመታደግ የሚነሳው? ዛሬ ኢትዮጵያውያን ወላጆች ለነፃነታችን ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን የከፈሉ ለጋ ልጆቻቸውን ለመቅበር ፈተና በገጠማቸው ሰዓት ከተቃዋሚዎች የሚፈልጉት የውግዘት መግለጫ አይደለም፡፡ ከጎናቸው እንዲሰለፉ እንጂ፡፡

አገዛዙን በትጥቅ ትግል ለመገዳደር በርሃ የገባችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ ባዶ እጃቸውን ከወያኔ ጋር
እየተፋለሙ የሚገኙ ወጣት ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ የእናንተን ደጀንነት ይጠባበቃሉ፡፡ ብረት ነካሽ መሆን አምሯችሁ ሳይሆን የወያኔ አገዛዝ በጥላቻውና በድንቁርናው ምክንያት ከተለመዱት አምባገነን አገዛዞች (“conventional tyrants”) የተለየ እንደሆነ በማመናችሁ ይመስለኛል ትጥቅ ትግሉን በተጨማሪ አማራጭነት የያዛችሁት፡፡ መቼም ወያኔ አጥፍቶ መጥፋት ተልእኮው ነው፣ የሚከፈለውን መሥዋዕትነት እንቀንስ፣ ዕድሉን እንስጠው በሚል ምክንያት ከሆነ እስከ መቼ? ምን ያህል ወጣቶችን ደም ለጠማቸው ወያኔዎች እንገብር? ወያኔ እንዲያንሠራራ ክፍተት ከሰጠነው መሥዋዕትነቱ የከፋ እንደሚሆን መቼም አትዘነጉትም፡፡ ወያኔ ለሥልጣን እና ዝርፊያው ሲል ኢትዮጵያን እበታትናታለኹ በሚል ማስፈራሪያ ላገር ፍቅር ያለንን ስሱነት የአገዛዙን ዕድሜ ለማራዘም ሲጠቀምበት ኖሯል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ማስፈራሪያና ሥጋት እስከ መቼ የባርነት ዘመናችንን እናራዝማለን?

ስለዚህ ሰለማዊውንም ሆነ በኃይል የሚደረገውን ሕዝባዊ ተቃውሞ መቀጠል ኢትዮጵያን የገጠማት የውስጥ
ባላጋራ ባህርይ የሚያስገድደን በመሆኑ፣ የአገዛዝ ሥርዓትን ከኢትዮጵያ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅሎ መንግሥተ ሕዝብ ለመትከል የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ይዘን ከመታገል ጀምሮ በውስጥም በውጭም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን አቅማችን የፈቀደውን ኹሉ ለማድረግ ዘግይተናል ከሚባል በቀር ጊዜውም ሆነ ሰዓቱ አሁን ነው፡፡
የኢትዮጵያ አምላክ እንደ ውኃ የፈሰሰውን የልጆቻችንን ደም ከንቱ አያድርግብን፡፡

Filed in: Amharic