>
5:14 pm - Thursday April 20, 6924

በኢትዮጵያ ህዝብ ለመከበር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማክበር ብቻ በቂ ነው! (ቋጠሮ)

እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ ሃገሩን የሚወድ ህዝብ ያለ አይመስለኝም። በወያኔ የዘር ፖለቲካ የተለከፉትም ሳይቀሩ ዘረኝነት ያለው አፋቸው ላይ እንጂ ልባቸው የኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊነት ነው።  የሃገሩን ልዋላዊነት እስካስጠበቁለት ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ መሪዎቹን ብዙ ይታገሳል። በኢትዮጵያ ህዝብ ለመከበርና ለመወደድ ኢትዮጵያን መውደድና ማክበር ብቻ በቂ ነው።

ልብ በሉ ቴዲ አፍሮ በህዝብ ልብ ውስጥ የገባው በሥራዎቹ ኢትዮጵያን በማክበሩና ኢትዮጵያዊነትን በማድመቁ ብቻ ነው ። ገዳይ የሚባለው መንንግስቱ ኃይለማሪያም እንኳ ዛሬም ድረስ በጥፋቱ ከሚወቅሱት ባላነሰ መጠን፤ ለሃገሩ ባለው ፍቅር የሚያወድሱት አሉ።

የቅርቡን እንኳ ብንጠቅስ ለማ መገርሳ ከወያኔ ጋር ለበርካታ አመታት መስራቱን ያስረሳችለትና በሚገርም ፍጥነት ክብርና አድናቆት ያተረፈቺለት “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” የምትለው ንግግሩ ነች።

የወያኔዎች አስተሳሰብ ግራ የሚገባው ለዚህ ነው። ኢትዮጵያን ማክበር በዚህ ፍጥነትና በዚህ መጠን የሚያስከብር መሆኑን እንኳ እያዩ ሊለወጡ ሲሞክሩ አይታትዩም። በቆርጦ ቀጥል ፕሮፓጋንዳቸው ህዝብን ለማሳመን ከሚሯሯጡ ይልቅ ህዝብ የሚያከብረውን ቢያከብሩ፤ ህዝብ የሚወደውን ቢወዱ እኮ ቀስ በቀስ የህዝብን አመኔታ ባገኙ ነበር። የማይወጡበት አዘቅጥ ውስጥም ባልገቡም ነበር።

መለስ ዜናዊ እንኳ ይህን ግልጽና ቀላል ነገር መረዳት አቅቶት ሳይሆን በደሙ ውስጥ የሚንተከተከው ከአያት ቅድመ አያቱ የወረሰው የባንድነት ታሪኩ እየጎፈነነው ነው። አዎ የኢትዮጵያ ህዝብ ለገዳይም፤ ለሙሰኛም፤ ለዘራፊም፤ ለአምባገነኖችም የይቅርታ ልብ እንዳለው በርካታ የታሪክ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። አገሩን ለሸጠ ባንዳ ይቅርታ የለውም። የመለስ ዜናዊ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የመትጋቱም ሚስጥር ይኽው ነው።ኢትዮጵያና  ኢትዮጵያዊነት ከጠፋ አሳፋሪው የባንድነት ታሪክ አብሮ ይጠፋልና። ለዚህም ነው በትረ ስልጣኑን በጨበጠ ማግስት ባንዲራዋን ጨርቅ ብሎ በማጣጣል የጥፋት ጉዞውን አንድ ብሎ የጀመረው። በዛው ቅጽበት ከህዝብ ተቆራረጠ።

የማይገባኝ ግን የአርበኞች ልጆች እንደሆኑ የሚነገርላቸው የወያኔ መሪዎችም በዚሁ በመለስ ዜናዊ ልክፍት መያዛቸው ነው። ያደቆነ ሴይጣን ሳያቀስ አይለቅም እንዲሉ ይኽው ልክፍታቸው ድህረ መለስም ቀጥሏል። አሁን ደግሞ ጭራሹኑ አገር በቀል ቀኝ ገዢ ሆኑና የጥፋታቸው እርከን ከይቅርታ በላይ ሆነ ።  ይብላኝ ለነሱ እንጂ ኢትዮጵያዊነት አቦ ለማ መገርሳ እንዳሉት የማይለቅ ሱስ ነው።

በነገራችን ላይ በቴዲ አፍሮ የባህርዳር ኮንሰርት ላይ ባንዲራዋን ከበው በሚደንቅ ስሜት የሚጨፍሩትን ለጋ ወጣቶች  የተመለከተ እውነትም ኢትዮጵያዊነት ልዩና መግነጢሳዊ ኃይል እንዳለው አምኖ ለመቀበል አይቸገርም። ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሌት ተቀን በሚሰራ መንግስት ውስጥ ያደጉ፤ ኢትዮጵያዊነትን እንዲያደበዝዝ በተቀረጸ ሥርዓተ ትምሀርት ያለፉ ለጋ ወጣቶች  በኢትዮጵያነት ፍቅር እንዲህ ሲንዘፈዘፉ ማየት ያስደንቃል። እውነትም ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው።ለዚያውም በደም የሚተላለፍ ሱስ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ከቋጠሮ : quatero.net

 

Filed in: Amharic