>
5:09 pm - Sunday March 2, 7749

“አገሪቱ እስካሁንም ድረስ የቆየችው በኢህአዴግ ሳይሆን በህዝቡ ጨዋነት ነው” (አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ)

 · ኢህአዴግ፤ ህገ-መንግስቱንም ሀገሪቱንም በራሱ አምሳል ለመፍጠር ነው የሞከረው   · ህዝብ ለ27 ዓመታት በፖለቲካ ጭንቀት ውስጥ አሳልፏል
 · ኢህአዴግ በታደሰባቸው ዘመናት የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ አያውቅም
 · ሰላም የሚሰፍነው በኢህአዴግ አፈና ሳይሆን፤በህዝቡ ብልህነት ነው
 · ኢትዮጵያዊነትና አገራዊ አንድነት የት ጠፍተው ነው የምንተራመሰው?
 · ኢህአዴግ ይቀየራል ወይም የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም
 · በ80 ዓመቴ የዚህች አገር ጉዳይ ያስጨንቀኛል፤የልጆቼ ዕጣ ፈንታ ያሳስበኛል
 ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህውሓት) መሥራቾች አንዱ የሆኑት የ80 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ፤ “የሀገሬ ጉዳይ ያስጨንቀኛል፤ የልጆቼ ዕጣ ፈንታ ያሳስበኛል” በማለት አዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል ድረስ በመምጣት ሙሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ “አገሪቱ በውጥረት ላይ እያለች ምሁራን የዳር ተመልካች ሆነዋል፣ የትግራይ ህዝብ ያለ አግባብ እየተፈረጀ ነው” ያሉት አቶ አስገደ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 27 ዓመታት በፖለቲካ ጭንቀት ውስጥ ማሳለፉን ይናገራሉ፡፡ ከጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት ሃሳብና ስሜታቸውን አውግተውታል፡፡ ሃሳባቸውን ከእነ ስሜታቸው በርዕሰ ጉዳይ ከፋፍለን፣እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡  

 ኢትዮጵያ – የተከመረ ገለባ 
አሁን ኢትዮጵያ የተከመረ ገለባ ሆናለች። የኢትዮጵያ ወጣት ከአጠቃላይ ህዝቡ 70 በመቶ ገደማ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ስራ አጥ ነው፡፡ ይሄ ወጣት ጡንቻውን አሳርፎበት ሊበላበት የሚችል የስራ መስክ የለውም፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ የሚወጣውም ማረፊያ የለውም፡፡  በዚህ መሃል ወጣቱን ለግጭት የሚገፋፋና የሚያቀጣጥል ደግሞ አለ፡፡ ይህ አቀጣጣይ ኃይል፣ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በፌደራሊዝም ያደረጀበት መንገድ ነው፡፡ አሁን አቀጣጣዩ፣ በሀገሪቱ ህዝቦች መካከል እንዲሰፍን የተደረገው የቋንቋ፣ ብሄር ልዩነት ነው፡፡ ደርግ ገዳይ ወታደራዊ መንግስት ነበር፤ነገር ግን በኃይልም ቢሆን አገራዊ አንድነትን አስጠብቆ ኖሯል፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ግን የአገር አንድነት ተፋልሷል፡፡ እየተፈጠረ ያለው የብሄር ግጭት፣ የአንድነት እጦት ውጤት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ መጨረሻው የከፋ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡
በዜጎች መካከል የኢኮኖሚ ልዩነት ተፈጥሯል። ጥቂት ሀብታሞች፣ሚሊዮን ድሃዎች ተፈጥረዋል። ዛሬ ሀገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባችው፣ ሥራ አጥነትና ውርደት በመብዛቱ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ የፖለቲካ ጥያቄ አለን ለሚሉ ወገኖች ቀና ምላሽ አልተሰጠም፡፡ መንግስት በየጊዜው ነገሮችን ለማስተካከል ቃል ይገባል፤ ግን ተግባር ላይ የለበትም፡፡ የኢህአዴግ አመራሮች ቃል ከገቡት ውስጥ 40 በመቶውን እንኳ ቢተገብሩ ሀገር በተረጋጋች ነበር፡፡
አሁን ያለው የፖለቲካ አመለካከት ፍረጃን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ኢህአዴግን የተቃወመ ሰይጣን ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በፖለቲካ ጭንቀት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ኢህአዴግ በጎሳ ላይ የተመሰረተውን ፌደራሊዝም ካዋቀረ ጀምሮ፣ የሀገሪቱ ህዝብ ከጭንቀት ወጥቶ አያውቅም። ይሄ አደረጃጀት በወቅቱ ስልጣንን ለማራዘም ታስቦ ተፈጠረ እንጂ ህዝብ አምኖበት፣ ለህዝብ ጥቅም የተፈጠረ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ፤ ህገ-መንግስቱንም ሀገሪቱንም በራሱ አምሳል ብቻ ለመፍጠር ነው ጥረት ያደረገው፡፡ ይሄ ደግሞ አሁን  የነቃ ማህበረሰብ ሲፈጠር ዋጋ ማስከፈል ጀምሯል፡፡  በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች ዛሬ እየተከበሩ አይደለም፡፡ የገለልተኝነት መርህ ተጥሷል፡፡ እኒህ ጉዳዮች የዚህ ትርምስ መንስኤ ናቸው፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ያለ አግባብ ኢላማ መደረጋቸው ያሳዝናል፡፡
“የትግራይ ህዝብ በዝምታ እየተቃወመ ነው”
የትግራይ ህዝብና ህውሓት አንድ ናቸው፡፡ ህዝቡ የህውሓት መሳርያ ነው፤ የሚል አመለካከት አለ፡፡ ይሄ ግን ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡ እኔም በውስጡ ነው ያለሁት፡፡ አንድ የሚያስተሳስራቸው ነገር ቢኖር፣ የትግራይ ህዝብ ከደርግ ጋር በነበረው ትግል፣ 150 ሺ ልጆቹ ተሰውተውበታል፡፡ ከ126 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፡፡ በራሳቸው ሰርተው አይበሉም። ህዝቡ በጦርነቱ ንብረቱ ወድሞበታል። ሰሜን ጎንደርን፣ ወሎንና ሰሜን ሸዋን ጨምሮ በትግራይ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በጦርነቱ ህይወቱን አጥቷል። የትግራይ ህዝብ እነዚህን ሰዎች ብናገልላቸው፣ የልጆቻችን አፅም ይወቅሰን ይሆን ብሎ ይሰጋ ነበር፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ግን ከ1997 ምርጫ በኋላ ከስሟል፡፡ ግን ህውሓት ትግራይን ዋና ማዕከሌ ነው ስለሚል፣ እያንዳንዱን ዜጋ አቻ በአቻ፣ በስለላ ጠፍንጎ ነው የያዘው፡፡
እውነቱን ለመናገር፣ አሁን ህውሓትን የሚደግፍ ምሁርም የለም፡፡ የትግራይ ህዝብ በህውሓት ልዩ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ብዙ ሰው የኤፈርት ተቋማትን እያየ፣ ህዝቡ ተጠቃሚ ይመስለዋል። እኔ ኤፈርት ውስጥ ሰርቻለሁ፡፡ ድርጅቱ ለህዝቡ ያበረከተው አስተዋፅኦ ቢኖር፣ በቅርቡ ያሰራቸው 11 ያህል ት/ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ተቋም በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ያንቀሳቅሳል፤ ገቢውም በቢሊዮን የሚቆጠር ነው፡፡ ሆኖም መቀሌ እንኳ እስከ ዛሬ የሀብቱ ተካፋይ ሆና፣ ንፁህ ውሃ ጠጥታ አታውቅም። የገጠሩ ክፍል ዛሬም በድህነት የሚማቅቅ ነው፡፡ አሁን ከሌሎች ወገኖች የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ፣ለምን የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው አላመፀም? የሚል ይመስለኛል። እውነቱን ለመናገር፣ የትግራይ ህዝብ ድምፅ የሌለው ከፍተኛ ተቃውሞ እያቀረበ ነው የሚገኘው። በጎንደር ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ፣ ህዝቡ፣ በጥላቻ እርምጃ እንዲወስድ ብዙ ተቀስቅሷል፤ ግን አላደረገውም፡፡ በእምቢተኝነት የእነሱን የከሰረ ፖለቲካ ማክሸፍን ነው የመረጠው፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ዛሬ የትግራይ ህዝብ፣ እነሱ በጠሩት ቁጥር እንደ ወትሮው አይሰበሰብም። ይሄም የተቃውሞ መገለጫ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ፤ ሀገሩ ኢትዮጵያና ወንድሞቹ ህዝቦቹ በልቡ ነው ያሉት፡፡ ዘር ተኮር ትርምሱ ራሱ ኢህአዴግ የፈጠረው ፌደራሊዝም ያመጣው እንጂ ህዝቡ እንደ ህዝብ ችግር የለበትም፡፡ ብዙ ሰው ይሄን  ቢረዳ መልካም ነው፡፡
የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ሁሉ፣ የዚህች ሃገር ባለቤት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ለወደፊትም ኢትዮጵያዊነቱን ለሰከንድም አይጠራጠርም፡፡ የትግራይ ህዝብ ጥንትም በኢትዮጵያ ዳር ድንበር ሁሉ ተንቀሳቅሶ፣ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር አብሮ ይሠራ ነበር፤ ዛሬም እየሠራ ነው፡፡ የኢህአዴግ የብሄር ልዩነት ግንብን አፍርሶ፣ ዛሬም በጉልበቱ ለፍቶ እያደረ ነው፡፡ እርግጥ ነው ከኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋር ተጠግተው ሃብት ያካበቱ ጥቂቶች አሉ፡፡ ምንም ያልነበራቸው ጥገኞች፣ ዛሬ ቢሊየነር ሆነዋል፡፡ እነዚህ ግን ፈፅሞ የትግራይ ህዝብን አይወክሉም፤ ሻይ እያፈሉ፣ ግንበኛ ሆነው፣ “ቆርቆሮ ያለው” እያሉ የሚሰሩ ትግራዮች፣ የትየለሌ ናቸው። ህብረተሰቡ የኢህአዴግ ተላላኪ የሆኑ ጥቂት ቢሊየነሮችን እያየ፣ ሰርቶ አዳሪዎችን በተሣሣተ መንገድ መተርጎም ተገቢ አይደለም፡፡ የትግራይ ህዝብ፣ ልጆቹን ለበጎ አላማ ሰዋ እንጂ ዛሬ ካለው ህውሓት ጋር የግብር አንድነት የለውም፡፡ አሁንም ቢሆን ህዝቡ ዝምታን የመረጠው በመንግስት የሚወሰደው እርምጃ በሙሉ ስለማይጥመው ነው። ህዝቡ እኮ፤ “ተነስ ወገንህ እያለቀ ነው” ተብሎ ተቀስቅሷል፡፡ ህዝቡ ግን አልተቀበለም፤በዝምታ ነው ያለፋቸው፡፡ ህዝቡ ለጥላቻ ቅስቀሳዎች ቦታ የለውም፣ ቦታም እየሰጠ አይደለም፡፡ ይሄን ሌሎች ወገኖቹም ሊረዱለት ይገባል፡፡ ይሄ ህዝብ “በተጫረ ክብሪት ሁሉ አልነሣም” የሚለው፣ ጥቂት ጥገኛ ሙሰኞች ስለማይወክሉት ነው፡፡ ታዲያ ለምን ህዝቡ፣ ከእነዚህ ጥቂት ጥገኞች ጋር ይፈረጃል? ይሄ መሆን የለበትም፡፡
በአጭሩ ለመግለፅ የትግራይ ህዝብ፣ የህወሓት አባል አይደለም፡፡ ህዝቡ እንደ ሌላው ወገኑ ሁሉ ለውጥ ፈላጊ ነው፡፡ ይህን ለውጥ ቢፈልግም ቅሉ፣ በስለላና በአፈና መዋቅሮች ተጠፍሮ የተያዘ ነው። ስለዚህ አማራጩ በዝምታ መቃወም ነው፡፡ በትግራይ ከኢህአዴግ ዘመን ጀምሮ እኮ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተደርጎ አያውቅም፡፡ ህዝቡ በፍረጃ ብዙ ነገሩን አጥቷል፡፡ በዚህ ውስጡ ተጎድቷል፡፡ የትግራይ ምሁራን ዛሬም በህውሓት ባህሪ የተነሳ፣ ከመድረክ ተገልለው ነው ያሉት፡፡ ለዚህ ነው ህወሓት ተተኪ ያጣው፡፡ ወጣት ምሁራንን አያሣትፍም፤ ይፈራል፡፡
እኔ አሁን ምንም በማያውቀው ለፍቶ አዳሪ የትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈፀመው የማግለል እንቅስቃሴ ያሣዝነኛል፡፡ ለምን እንዲህ ይደረጋል? ህዝቡ አንድነትን መስበክ አለበት፡፡ ምሁሩ አገራዊ አንድነት ማስተማር አለበት፡፡ ይቺ ሃገር ተበትና፣ እኛ ምን ልንሆን ነው? እኔ የዚህችን ሃገር ሁኔታ በዚህ እድሜዬ ማሰብ በእጅጉ ያስጨንቀኛል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያዊነትና የአገራዊ አንድነት መንፈስ የት ጠፍቶ ነው፣ የምንተራመሰው? ህብረተሰቡ ይሄን ማጤን አለበት፡፡ መንግስታት ያልፋሉ፤ ይወድቃሉ፤ ሃገርና ህዝብ ግን ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ መንፈስ፣ የወደፊቱን አሻግረን ማየት አለብን፡፡
አንድነት እንዴት ይምጣ?
በሃገር ውስጥም በውጪም የአገር አንድነት ጉዳይ በእጅጉ የሚያሳስባቸው አሉ፡፡ በውጭ ያሉ ምሁራን እዚያ ሆነው ከሚብሰከሰኩና በሃገር ፍቅር ናፍቆት ከሚቃጠሉ፣ ወደ ሃገር ቤት የሚገቡበት ሁኔታ ተመቻችቶ፣ አገራቸውን ለማዳን መዋጮ ማድረግ አለባቸው፡፡ ፍረጃዎች ቀርተውና ሃገርን የማዳን አጀንዳ ቅድሚያ ተሰጥቶት፣ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን ማዋጣት አለበት፡፡ ኢህአዴግ ወደዚህ አስተሳሰብ ካልገባ ዋጋ የለውም፡፡ ችግሩ ኢህአዴግ በምሁራን የተደራጀ ሃይልን አይፈልግም፡፡ ግን ሃገርን ለማዳን ሲሉ የግድ ወደዚህ ሃሳብ መምጣት አለባቸው፡፡
የህወሓት የበላይነት ምንጩ? 
ሕወሓት በትግሉ ወቅት ራሱ ብቻ ብሄራዊ አጀንዳ ይዞ፣ ወደሰራው የኢትዮጵያ ህዝብ መግባት እንደማይችል ያውቅ ነበር፡፡ ኢህዴን ደግሞ በባህሪው ተጠፍጥፎ የተሠራ፣ በወቅቱ የህወሓት መሣሪያ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ በጊዜው ኢህዴን ለአማራ ህዝብ ወኪል እንዲሆን ቢፈለግም ህዝቡ አልተቀበለውም፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ ኢህአፓን ይወደው ነበር፡፡ ኢህዴን እንደ ከዳተኛ ነበር የታየው፤ ከኢህአፓ ስለወጣ፡፡ ህዝቡ የቱንም ያህል ቢሰበክም ኢህዴንን መቀበል አቃተው፡፡ ኢህአፓ በአንፃሩ ቅቡልነት እያገኘ መጣ፡፡ እዚህ ጋ አንድ ሳልጠቅሰው የማላልፈው፣ ኢህዴን ዛሬ የህገ መንግስቱ መሰረት የሆኑት የብሄር ብሄረሰብ አጀንዳ፣ የመገንጠል መብት ጉዳይ፣ የኤርትራ መገንጠልን ሳይቀበል እየተከራከረ ነበር እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የተጓዘው። ድርጅቱ በባህሪው፣ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን ነበር፡፡ በኋላ በህውሓት ተፅዕኖ ይሄን አቋሙን ቀየረ፡፡ የበላይነቱ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው፡፡ ይሄን “አባታዊነት” ብንለው ይሻላል፡፡
በሌላ በኩል በሳይንሳዊ መንገድ የተደራጀውን የደርግ ወታደር የመበተኑ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ልምዳችን የሽምቅ ውጊያ እንጂ ሳይንሳዊ አልነበረም፤ ከወታደሩ ጀምሮ ሌሎች የደርግ ቢሮክራሲዎች በተለያየ መንገድ በህውሓት የፖለቲካ አቋም ተመታ፡፡ ይሄን የተቃወምነው የህውሓት አባላት፣ አብረን ተመታን፤ ከድርጅቱም ለቀን ወጣን፡፡ ህውሓት ሙሉ የመንግስት መዋቅሩን ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ እኔ በወቅቱ የፋይናንስና ሎጅስቲክ ኃላፊ ነበርኩ፡፡ የብአዴን ኃይል 2500 ያህል ነበር። ይሄን አውቃለሁ። ሲቪል አላደራጁም ነበር። ስልጣን በሽምቅ ተዋጊዎች የመያዝ አጋጣሚ ተፈጠረ። ህውሓት በአንፃሩ ጥቂት ለስልጣን ያዘጋጃቸውን፣ ከወታደር ጥቃት እየደበቀ ነው ለስልጣን ያበቃቸው። ኦህዴድም ቢሆን በ300 ያህል ምርኮኛ ወታደሮች የተደራጀ ነበር፡፡ ህውሓት በአጠቃላይ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰቡ፣ በሰው ኃይሉ፣ በፖሊሲው — በሁሉም የበላይ ነበር፡፡ በተግባርም ያ የበላይነት ነው የተፈጠረው፡፡ አሁንም ይህ አብዮታዊ ዲሞክራሲና በ1983 የተቀመጠው ፖሊሲ እስካለ ድረስ የህውሓት የበላይነት ይቀጥላል ማለት ነው፡፡
ምሁርና ወጣት የማይወድ ድርጅት 
ብአዴን እና ኦህዴድ በትግሉ ወቅት ከነበራቸው የሰው ኃይል ይልቅ በብዙ እጥፍ ከስልጣን በኋላ የመጣው ይበልጣል፡፡ አብዛኛው አሁን በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ያለው አዲስ የሰው ኃይል ነው። ህውሓት ከዚህ አንጻር ራሱን በራሱ ገድሏል። ነባር ታጋዮቹን ነው ይዞ መቀጠል የመረጠው። ምሁራንን አይፈልግም፡፡ አዲስ ወጣት ኃይል፣ ወደ ፊት ማምጣት አልቻለም፡፡ አሁን ከኦህዴድና ከብአዴን መገዳደር የገጠመው፣ በዚህ ራስን በራስ የማጥፋት እንቅስቃሴ ነው፡፡ ህውሓት በእንቅስቃሴ የተዳከመው፣ በራሱ ስህተት ነው፡፡ የሱ አስተሳሰብ ግን ዛሬም የሀገሪቱ ገዢ ሀሳብ ነው፡፡ እነ አቶ ለማ መገርሳም ሆኑ እነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዛሬም በዚህ አስተሳሰብ ስር ናቸው፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ አልወጡም፡፡ እኔ በበኩሌ፣ ኢህአዴግ ይቀየራል፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡
የሃገሩ ጉዳይ የማይጨንቀው ምሁር
የምሁራኑን ሚና ካነሳን አይቀር፣ የዛሬዎቹን ብቻ ሳይሆን የቀድሞዎቹን ማየት አለብን። የድሮ ምሁራን  6ኛ ክፍል ሆነው ስለ ሀገር ጉዳይ ይቆረቆራሉ፡፡ ዛሬ ባለ ሶስተኛ ዲግሪውም ስለ ሀገሩ የማይጨነቅበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል። የቀድሞ ምሁራን ስለ አርሶ አደሩ፣ ስለ ነጋዴው፣ ስለ እናቶች፣ ስለ ህብረተሰቡ –መብት ያሰላስላሉ። የዛሬዎቹስ? ትንሽ ክፍተት እንኳ አግኝተው፣ ራሳቸውን ከመድረኩ ማግለልን ነው የመረጡት። አሁን ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወደ አንድነት ማምጣት ያቃታቸው ምንድን ነው? ምሁሩ ስለ ሀገሩ ማሰብ መጨነቅ ማቆሙ ነው፡፡ የስርአት ለውጥ እኮ በየጊዜው ነው የሚያስፈልገው። በዚህ ረገድ ምሁራኖቻችን፣ ምርምርና ጥናት አድርገው ሲሞግቱ አናይም፡፡ እኔ ይህቺ ሀገር ከጠፋች የት እንደምኖር ይጨንቀኛል። አብዛኛው ምሁር ግን ይሄ አይጨንቀውም፡፡ እርግጥ ነው፤ ጥቂት ወጣት ታጋይ ምሁራን አሉ፡፡ ፊት ለፊት የሚናገሩ፣ የሚያውቁትን ምሁራዊ ሀቅ የሚገልጹ። አብዛኛው ምሁር ግን በዝምታ መኖርን ነው የመረጠው፡፡ ለምሳሌ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲና በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ከ5 ሺህ በላይ መምህራን አሉ፤ ግን አንድም ቀን ስለ ሀገሪቱ ውጥረት ሲያወሩ አናይም፡፡
እኔ የሚደንቀኝ ህገ መንግስቱ፣ የትምህርት ማዕከላት የፖለቲካ ማራመጃ አይሆኑም ይላል፤ ግን እነ ህውሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድና ደህዴን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተወካይ አስቀምጠው አባላት ሲመለምሉ፣ አንድም የህግ ምሁር ሲቃወም አላየንም። ይሄ ክሽፈት ነው፡፡ የትኛውም ምሁር፣ ይሄን ጥስት ሲቃወም አልተመለከትንም፡፡ በዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ፓርቲዎቹ ተመሳሳይ ተግባር ሲፈጽሙ ምሁራኑ ድምጽ አላሰሙም፡፡ ለእኔ አብዛኛው ምሁር፣ሀገራዊ ፍቅሩን አጥቷል፤ ጥቅመኝነት አጥቅቶታል፡፡ ወደ ኢህአዴግ የሚመጡ ምሁራን ደግሞ ደካማ ናቸው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ ዋስትና ያለው ስራ ለማግኘት ነው ፓርቲውን የሚቀላቀሉት፡፡
በአጠቃላይ ምሁራኑ ለህዝባቸው ውለታ አልዋሉም፤ ሚናቸውን አልተወጡም፡፡ ሀገሪቱን ከትርምስ ለማዳን እየሞከሩ አይደሉም፡፡ ምናልባት ጥቂቶች እየተንቀሳቀሱ ሊሆን ይችላል፤ ግን የእነሱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችን በተመለከተ፣ በመሰረቱ ኢህአዴግ ሽማግሌ አይወድም፤ ያሉት ሽማግሌዎችም ከሱ አይወጡም። እኔ በ80 ዓመቴ፣ የዚህች ሀገር ጉዳይ ያስጨንቀኛል። የልጆቼ ዕጣ ፈንታ ያሳስበኛል፡፡ የዚህች ሀገር ሸክም ላለመሆን ብቻ ነው የምናገረው። ምሁራኑም ስለ ሀገራቸው ካልቆሙ፣ የሀገር ሸክም ከመሆን አያመልጡም፡፡
“ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ የለችም“ 
ኢህአዴግ፤ ”እኔ ከሌለው አገሪቱ፣ አገር አትሆንም” ይላል፡፡ ሌሎችም ተቀብለው ያስተጋቡታል፤ ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም፡፡ ዛሬ አገሪቱ ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ብዙ ፖለቲካ አዋቂዎች አሏት። ገለል ብለው የቆዩ ቢሆንም ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ፣ ለሀገራቸው ደማቸውን መስጠት ይችላሉ። አሁንም ቢሆን እኮ በኢህአዴግ አይደለም ይህቺ ሀገር የቆየችው፤ በህዝቡ ጨዋነት ነው፡፡ ሰላም የሚሰፍነው በኢህአዴግ አፈና የሚመስላቸው ወገኖች አሉ፤ ይሄ ስህተት ነው፡፡ ሰላም የሚሰፍነው በህዝቡ ብልህነት ነው፡፡ “ከኢህአዴግ በኋላ ሀገር ምን ትሆናለች?” የሚለው የራሱ የኢህአዴግ ሃሳብ ስለሆነ፣ ቅቡልነት የለውም፡፡
ተሃድሶና የፀረ ሙስና ዘመቻ
ተሃድሶ ያለ አስተሳሰብ ለውጥ ዋጋ የለውም። ኢህአዴግ በታደሰባቸው ዘመናት የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቶ አያውቅም፡፡ ዛሬም አጀንዳው፣ የመለስን ራዕይ ማስፈፀም ነው፡፡ መተካካቱም ወደ ኋላ ተመልሷል፡፡ ሙስናን በተመለከተ አቶ መለስ ራሳቸው፣ ”ሙስናን ከመሰረቱ እናጥፋ ከተባለ ኢህአዴግ አይኖርም” ብለው ነበር፡፡ ስለዚህ ሙስናን ከመሰረቱ ለማጥፋት ከተፈለገ ውጤቱ ይታወቃል ማለት ነው፡፡ እናም በሙስና የሚመቱ ሰዎች ትልቅ ስልጣን ያላቸው አይደሉም፡፡ ቦታ የሌላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የተሃድሶውም የሙስና ዘመቻውም ግልፅ አይደለም፡፡   

Filed in: Amharic