>

​የ​ህወሓት የበላይነት እና የዓረና ውስልትና (ስዩም ተሾመ)

1ኛ) ውስልትና የማን፦ የዓረና ወይስ የሌሎች?

ሰሞኑን የዓረና ማዕከላዊ ኮሚቴ ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ድርጅታዊ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። በመግለጫው መሰረት፣ የዓረና ማዕከላዊ ኮሚቴ “የትግራይ የበላይነት” በሚለው “የፖለቲካ ውስልትና” ዙሪያ መወያየቱን ገልጿል። ጥር 28/2010 ዓ.ም በወጣው መግለጫ መሰረት ይህን “የፖለቲካ ውስልትና” ያለውን ችግር ከነምክንያቱ እንደሚከተለው ገልጿል፡-

“…ቁጥራቸው የማይናቅ ፖለቲከኞች በተለይ ደግሞ የመንግስት ስልጣን የጨበጡ የኢህአዴግ ድርጅቶች “የትግራይ የበላይነት” በሚል ውስልትና ዘመቻ ከፍተው በንፁሃን ተጋሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሱ ቆይቷል፡፡ …በአንድ በኩል የህወሓት መሪዎች ሊያስቆማቸው የሚያስችል ፖለቲካዊ አስተሳሰብና በራስ መተማመን ስለሌላቸው “ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው” እያሉ በትግራይ ህዝብ ብብት ስር ሲደበቁ ይታያሉ፡፡ ህወሓት “ትግራዋይ ሲጠቃ ወደ ህወሓት ይጠጋል” የሚል የተሳሳተ አመለካከቱ አርሞ ህዝብ እንደ ማስያዣና እንደ ቁማር መጫወቻ መጠቀም እንደስልት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፅንፍ የፖለቲካ ተቃውሞ የሚያራምዱ ፖለቲከኞችና ከህወሓት እልህ የተጋቡ የኢህአዴግ ድርጅቶች “የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው” እያሉ በንፁሀን ተጋሩ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡” ከዓረና ትግራይ ማእከላይ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ፥ ጥር 28/2010 ዓ.ም፥ መቐለ


የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ 35 ቀናት የፈጀው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ ከዛሚ ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ “የትግራይ የበላይነት” በሚለው ዙሪያ ከዓረና ፓርቲ ጋር ተመሳሳይ አቋም አንፀባርቀዋል። እንደ አቶ ጌታቸው አገላለፅ “‘የትግራይ የበላይነት’ የሚባለው ነገር ልክ እንደ ‘አያ ጅቦ’ የሚሉት ዓይነት ማስፈራሪያ ነው።” በተመሳሳይ፣ የዓረና ፓርቲ ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ “የትግራይ የበላይነት” የሚባለው ነገር “ውስልትና” እንደሆነ ገልጿል። በዚህ መሰረት፣ “የትግራይ የበላይነት” የሚባለው ነገር ለህወሓቶች “የሞኝ ማስፈራሪያ” ሲሆን ለዓረናዎች ደግሞ “የፖለቲከኞች ውስልትና” ነው። ስለዚህ “የትግራይ የበላይነት” የሚለው በህወሓት ሆነ ዓረና ዘንድ በውሸት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አመለካከት ነው።

ሆኖም ግን፣ ዓረና “የትግራይ የበላይነት” የተባለው ችግር መንስዔው በቀጥታ ከህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ጋር የተያየዘ እንደሆነ በመግለጫው አስታውቋል። ከላይ በቀረበው የድርጅቱ መግለጫ መሰረት፤ አንደኛ፡- የህወሓት መሪዎች “ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው” እያሉ በትግራይ ህዝብ ብብት ስር ይደበቃሉ፣ ሁለተኛ፡- ህወሓት “ትግራዋይ ሲጠቃ ወደ ህወሓት ይጠጋል” በሚል የተሳሳተ አመለካከት የትግራይ ህዝብን እንደ ማስያዣ በመጠቀም የፖለቲካ ቁማር ይጫወታል። በዚህ ምክንያት፣ ሦስተኛ፡- ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ከህወሓት ጋር እልህ የተጋቡ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች “የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው” እያሉ በንፁሀን ተጋሩዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት “እያደረሱ” ይገኛል።

ከምክንያት-ውጤት ግንኙነት (cause-effect relationship) አንፃር ሲታይ፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ከህወሓት ጋር እልህ የተጋቡ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች “የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው” ከማለታቸው በፊት የህወሓት መሪዎች “ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ [ናቸው]” በማለት ከትግራይ ህዝብ ብብት ስር ተደብቀዋል። በዚህ ምክንያት፣ “በንፁሀን ተጋሩዎች ላይ ጉዳት ከመድረሱ” በፊት ህወሓት “ትግራዋይ ሲጠቃ ወደ ህወሓት ይጠጋል” በሚል የተሳሳተ አመለካከት የትግራይ ህዝብን እንደ ማስያዣ ተጠቅሞ በክልሉ ተወላጆች ላይ ቁማር ተጫውቷል።

በዚህ መሰረት፣ ከሁሉም በፊት “የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው” የሚል አቋም ያራመደው ማን ነው? ህወሓት ነው! ከሁሉም በተለየ “ትግራዋይ ሲጠቃ ወደ ህወሓት ይጠጋል” በሚል በንፁሃን ላይ በሚፈፀም ጥቃትና ጉዳት የፖለቲካ ትርፍና ድጋፍ የማጋበስ ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ማን ነው? ህወሓት ነው! ስለዚህ “የትግራይ ህዝብና ህወሓት አንድ ናቸው” ለሚለው አመለካከት ሆነ በተጋሩዎች ላይ ለደረሰው ጥቃትና ጉዳት ተጠያቂ ማን ነው? ህወሓት ነው! ስለዚህ በንፁሀን ተጋሩዎች ላይ ለደረሰው ጥቃትና ጉዳት መነሻ ምክንያቱ ህወሓትና ህወሓት ሆኖ ሳለ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን እና ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ተጠያቂ ማድረግ ምን ይባላል? ውስልትና!

2ኛ) የትግራይ የበላይነት ወይስ የህወሓት የበላይነት?  

በዓረና ድርጅታዊ መግለጫ “የትግራይ የበላይነት”፤ የህወሓት መሪዎች በአንድ በኩል፣ የህወሓት ተቃዋሚ ኃይሎች በሌላ በኩል ሆነው “ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ [ናቸው]” በማለት የሚያራምዱት የተሳሳተ አመለካከት ውጤት እንደሆነ ተገልጿል። ስለዚህ እንደ ዓረናዎች አገላለፅ “የትግራይ የበላይነት” የሚለው ሁለት ትላልቅ ሀይሎች “ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ አንድ [ናቸው]” የሚል አቋም በማራመዳቸው ምክንያት የተፈጠረ የተዛባ አመለካከት ነው። ነገር ግን፣ የአንድ ወገን የበላይነት መኖርና አለመኖር የሚለካው በአንድ ወይም በከሌላ የፖለቲካ ድርጅት አቋምና አመለካከት አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ፣ የአንድ ወገን የበላይነት የሚረጋገጠው በፖለቲካ ቡድን፥ ድርጅት፥ ፓርቲ ወይም መደብ አማካኝነት ነው።

በመሰረቱ “ትግራይ” ማለት በውስጡ ሕዝብ የሚኖርበት፣ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ያለውና በአንድ መስተዳደር ስር የሚገኝ ግዛት ነው። “የትግራይ ሕዝብ” ማለት ደግሞ በትግራይ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚገኙና በአንድ መንግስት ስር የሚተዳደሩ ጠቅላለ ሰዎች ናቸው። በሕገ-መንግስቱ መሰረት፣ “የትግራይ ክልል” ከዘጠኙ የሀገሪቱ ክልሎች አንዱ ሲሆን “የትግራይ ሕዝብ” እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብትና ስልጣን አለው። “ህወሓት” ደግሞ የትግራይን ክልልና ሕዝብ በማስተዳደርና መምራት ላይ ያለ የፖለቲካ ቡድን ነው።

በዚህ መሰረት፣ “የትግራይ የበላይነት” ሲባል መሰረቱን ትግራይ ባደረገ የፖለቲካ ቡድን፥ ድርጅት፥ ፓርቲ ወይም መደብ የተዘረጋ የአንድ ወገን የስልጣን የበላይነትንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት (poltical system) ነው። “ትግራይ” እንደ ጂኦግራፊያዊ ክልል ሆነ እንደ ሕዝብ የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት አይችልም። ምክንያቱም ሕዝብ ወይም ክልል በራሱ እንደ አንድ የፖለቲካ ቡድን፥ ድርጅት፥ ፓርቲ ወይም መደብ የራሱን የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋትና ማስተዳደር አይችልም።

ስለዚህ “የትግራይ የበላይነት” ሲባል የህወሓት የፖለቲካ መሪዎችና ልሂቃን የራሳቸውን የስልጣን የበላይነት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የዘረጉት ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። “የትግራይ የበላይነት” የሚለው “የህወሓት የበላይነት” ከማለት የዘለለ ትርጉምና ፍቺ ሊሰጠው አይችልም። በፖለቲካ ሳይንስ “የአንድ ወገን የበላይነት” እንጂ “የአንድ ሕዝብ የበላይነት” የሚባል ነገር የለም፣ ሊኖር አይችልም፣ ኖሮ አያውቅም። ስለዚህ፣ በፖለቲካ አነጋገር “የትግራይ የበላይነት” ማለት ከትግራይ የመጣው ህወሓትና የህወሓት አባላትና ደጋፊ የሆኑ ልሂቃን የበላይነት ማለት ነው።

“‘የአንድ ቡድን የበላይነት’ ማለት በአስተዳደራዊ መዋቅሩ ውስጥ ያሉ የስልጣን እርከኖችን መቆጣጠር አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ የፖለቲካ ሳይንስ የሚለው የአንድ ቡድን የበላይነት የሚረጋገጠው፤ አንደኛ:- አስተዳደራዊ ስርዓቱ የሚተዳደርበትን የህግ ማዕቀፍ በራስ ፍላጎትና ግንዛቤ መሠረት በማፅደቅና ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡ አሁን ሀገሪቱ የምትተዳደርበት ህገ መንግስት በዋናነት በህወሓት ፍላጎት እና የፖለቲካ አቋምና አመለካከት መሠረት የተረቀቀ፥ የፀደቀና ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ነው። ስለዚህ፣ “The Class Domination Theory of Power” በሚለው የፖለቲካ ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት፣ “የህወሓት የበላይነት” መኖርና አለመኖር የሚረጋገጠው ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች፥ ድርጅቶች፥ ፓርቲዎች፥ ክልሎች፥ መስተዳደሮች፥ …ወዘተ የሚተዳደሩበት ስርዓትና ደንብ ከመወሰን አንፃር ነው፡-

“Domination by the few does not mean complete control, but rather the ability to set the terms under which other groups and classes must operate.” Elites, political elites and social change in modern societies; Revista De Sociologia, Nº 28 (2013) pp. 31-49

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ “የህወሓት የበላይነት” መኖሩና አለመኖሩን ማረጋገጥ የሚቻለው ሁሉም የፖለቲካ ተቋማት፥ ቡድኖች፥ ድርጅቶች፥ ክልሎች፥ …ወዘተ የሚመሩባቸውን መርሆች፥ ሕጎችና ደንቦች ከመወሰን አንፃር ባለው ድርሻ ነው። በመሆኑም “ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች፥ ድርጅቶች፥ ፓርቲዎች፥ ክልሎች፥ መስተዳደሮች፥ የሚተዳደሩበትን መንግስታዊ ስርዓትና ድንብ ከመወሰን አንፃር የህወሓት ድርሻና ሚና ምን ይመስላል?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።

ሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የሚተዳደሩበት መንግስታዊ ስርዓት በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የማያውቅ የፖለቲካ ልሂቅ ያለ አይመስለኝም። የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጨምሮ፣ የፌደራል ስርዓቱና ተቋማት፣ እንዲሁም የክልል መንግስታትና ተቋማት የሚተዳደሩበት ሕግ፥ ስርዓትና መዋቅር በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው። የፌደራሉና ክልል መንግስታት በሕገ-መንግስቱ መሰረት የተቋቋሙ ናቸው። በመሆኑም በፌደራልና ክልል ደረጃ የሚወጡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች፣ የተቋማት ሥራና አሰራሮች፣… በአጠቃላይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ ለሕገ-መንግስቱ ተገዢ መሆን አለባቸው። በመሆኑም አሁን ባለው ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ የህወሓት የበላይነት መኖሩ አያጠራጥርም።

በዚህ መሰረት፣ በየትኛውም የኢትዮጲያ ክፍል የሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ የፌደራሉና ክልል መንግስታትና ተቋማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚመራበት ሕግና ስርዓት በሙሉ በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው። ከላይ በተጠቀሰው “The Class Domination Theory of Power” በሚለው የፖለቲካ ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት የህወሓት የበላይነት መኖሩ አያጠራጥርም። የሕገ መንግስቱ መሰረታዊ ፋይዳ የህወሓትን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ተግባራዊ ማድረግ ነው። ለሕገ መንግስቱና ለመንግስታዊ ስርዓቱ ታማኝና ተገዢ መሆን በራሱ ለህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ታማኝና ተገዢ መሆን ነው። ሌሎች የኢህአዴግ መንግስት አባል ድርጅቶች ከህወሓት የፖለቲካ አቋምና መመሪያ ካላፈነገጡ በስተቀር የህወሓት የበላይነት ማስቀጠያ፥ መገልገያ፥ መጠቀሚያ ናቸው።

3ኛ) የህወሓት ተቃዋሚዎች ወይስ አገልጋዮች? 

አሁን ባለው ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ የትግራይ/ህወሓት የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ስለመኖሩ በመርህና በተግባር ደረጃ ማረጋገጥ ይቻላል። የህወሓት የበላይነት የተመሰረተው በፖለቲካ ስልጣንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ላይ ብቻ ሳይሆን በለየለት የአስተሳሰብ ጥንባት ላይ እንደሆነ ለመገንዘብ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ሃላፊ ሜ/ር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልዳረጋይ ወራይና ከተባለ መጽሄት ጋር ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ ማንበብ ብቻ ይበቃል። ነገር ግን፣ ይህን ዓይን ያወጣ “የህወሓት የበላይነት የለም” እያሉ በሌላ በኩል “የህወሓት ተቃዋሚ ነኝ” ከማለት የባሰ ውስልትና አለ እንዴ?

ከላይ በፅሁፉ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው፣ “የትግራይ/ህወሓት የበላይነትን” በተመለከተ የዓረና እና የህወሓት አቋምና አስተያየት አንድ ዓይነት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከትግራይ ሕዝብ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ ህወሓትና ዓረና የሚያንፀባርቁት ሃሳብና አስተያየት አንድና ተመሳሳይ ነው። ከሞላ-ጎደል “ሁሉም” የትግራይ ልሂቃን ማለት ይቻላል፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ የደረሰን ችግር ከመጠን በላይ በማጋነን ያራግቡታል። ለዚህ ደግሞ የዓረና ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው ድርጅታዊ መግለጫ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

በአንፃሩ በዋናነት በህወሓት አባላትና ደጋፊዎች የሚመሯቸው የደህንነት እና የመከላከያ ሰራዊት በሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦች ላይ ከመጠን ያለፈ በደልና ጭፍጨፋ ሲፈፅሙ አብዛኞቹ ዝምታን ይመርጣሉ ወይም ደግሞ ይህን የፈፀሙትን የፀጥታ ኃይሎች በማወደስ፣ የተፈፀመውን በደልና ጭፍጨፋ ያጣጥላሉ። የሀገሪቱ ጦር ሰራዊት “የህወሓትን የበላይነት” ለማስቀጠል በሚያደርገው ጥረት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ሲያፈናቅል ለማውገዝ ቃላት የሚያጥረው የፖለቲካ ፓርቲ ትላንትና ደርሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቀሉ ብሎ ማራገብ በራስ ላይ ጥላቻ እንደ መስበክ ይቆጠራል።

የሀገሪቱ ፖለቲካ ዋና ችግር የህወሓትን የበላይነት በማስቀጠል ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርዓት ሆኖ ሳለ “የትግራይ/ህወሓት የበላይነት የለም” ብለው ከህወሓት ጋር የሚጨፍሩ የፖለቲካ ቡድኖች በሙሉ የእብድ አጫፋሪዎች ናቸው። ነገር ግን፣ የዓረና ፓርቲ አባላትና አመራሮች “የትግራይ/ህወሓት የበላይነት አለ” የሚሉ ወገኖችን በውስልትና የሚከስሱበት ምክንያት ምንድነው? በመሰረቱ የዓረና አባላትን ጨምሮ አብዛኞቹ የትግራይ ልሂቃን “የትግራይ/ህወሓት የበላይነት” መኖሩን መገንዘብ የተሳናቸው ህወሓት ራሱ የበላይነቱን ለማስቀጠል ሲል በፈፀመባቸው የአስተሳሰብ በደልና ጭቆና ነው። በመሆኑም “የትግራይ/ህወሓት የበላይነት የለም” የሚለው አቋም በራሱ የህወሓት ጭቆና እና አፈና ውጤት ነው። ስለዚህ ዓረናን ጨምሮ ተመሳሳይ የፖለቲካ አቋም የሚያራምዱ የፖለቲካ ቡድኖች የህወሓት የበላይነት ያፈራቸው ጭንጋፍ ፖለቲኮኞች ናቸው።

በመሰረቱ የህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የራሱ የሆነ መጀመሪያና መጨረሻ አለው። የህወሓትን የበላይነት ማስቀጠል ማለት የድርጅቱን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት መጨረሻ ላልተወሰነ ግዜ ማራዘም ወይም ማስቀጠል ነው። በዚህ መልኩ፣ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በዘላቂነት ለማስቀጠል አዲስ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዳይፈጠር ማድረግ ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ የተለየ ሃሳብና አመለካከት እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት፣ የህወሓት የበላይነትን በዘላቂነት ማስቀጠል የሚቻለው በማህብረሰቡ አባላት ላይ ከፍተኛ ሽብርና ፍርሃት በመፍጠር የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችን በማጥፋት ነው።

እንደ ምክንያታዊ ፍጡር እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ የሆነ ግንዛቤና አመለካከት አለው፤ በራሱ ሃሳብና ፍላጎት፣ ምርጫና ፍቃድ መንቀሳቀስ ይችላል። በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ አዲስ የሕይወት ጅማሬ ነው። ስለዚህ የህወሓትን የበላይነት ማስቀጠል የሚቻለው በትግራይ ሕዝብ ስም የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን ግለሰቦች በማጥፋት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ተገዢ የሆነ ልሙጥ የፖለቲካ ማህብረሰብ በመፍጠር ነው።

በዚህ መሰረት፣ የህወሓት የፖለቲካ ስልጣንና የበላይነት የተመሰረተው ከማህብረሰቡ ውስጥ “ግለሰቦችን” (individuals) በማጥፋት አዲስ የፖለቲካ ጅማሬን በማስወገድ ነው። የህወሓት የበላይነት እንዲቀጥል አዲስና የተለየ ሃሳብ የሚያፈልቁ ግለሰቦች በነፃነት መንቀሳቀስ፥ ማሰብ፥ መናገርና መፃፍ የለባቸውም። ለዚህ ደግሞ የሃሳብና አመለካከት ነፃነትን የሚገድቡ የሕግ አዋጆችን በማውጣት የሕግ-የበላይነትን መናድ፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነትን መጣስ፣ ተጠያቂነትና የሕግ-የበላይነት የጎደለው ሥራና አሰራር መዘርጋት፣ በዚህም የክልሉ ሕዝብ በፍርሃት ቆፈን እንዲያዝ ያደርጋል።

በአጠቃላይ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ልሙጥ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት እንዲኖራቸው የተደረገው ህወሓት በፈጠረው የፍርሃት ቆፈን ምክንያት ነው። ግለሰቦች የራሳቸውን ሃሳብና አመለካከት በመተው፣ በአንድም ሆነ በሌላ በመልኩ የህወሓት የአቋምና አመለካከት እንዲያራምዱ ተደርገዋል። በዚህ መሰረት፣ “የህወሓት የበላይነት” የሚለውን “ትግራይ የበላይነት”፣ ሕዝብና የፖለቲካ ቡድንን መለየት እንኳን ተስኗቸዋል። በመሆኑም፣ በተቃዋሚ ስም የህወሓትን የበላይነት ለማስከጠል አበክረው እየሰሩ ይገኛሉ። በእርግጥ ዓረናዎች የህወሓት አገልጋዮች እንጂ ተቃዋሚዎች አይደሉም። የህወሓት የበላይነት ያልተገለጠለት የፖለቲካ ቡድን የእኩልነት ትርጉምና ፋይዳ አይታየውም።

Filed in: Amharic