>
5:33 pm - Friday December 5, 1664

ከስልኩ ጀርባ (አርአያ ተስፋማሪያም)

አቶ መለስ ህገ መንግስቱን ጥሰውና የፕሬዚደንቱን ስልጣን ነጥቀው ካባረሯቸው ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች አንዱ በነበሩት አበበ (ጆቤ) ቦታ ጄ/ል አለምሸት ደግፌ ማእረግ ጭነው ተቀመጡ። “ነጋሶ መታሰር አለበት” ሲሉ ለመለስ ታማኝነታቸው አሳዩ። (የሌሎቹን የኦህዴድ ሹሞች ተመሳሳይ ቃልና ድርጊት ባለፈው ተጠቅሷል)..” አለምሸት የተማሩ ሆኖው ሳለ ..እንዴት እንዲህ አይነት አቋም ያዙ?” የሚለው የብዙዎቹ አስተያየት ነበር። በጋሻ ጃግሬነት ከዘለቁ በኋላ መለስ አንድ ባለ39 ገፅ ፅሁፍ ፃፉና ከፍተኛ ጄኔራሎች እንዲወያዩበት አቀረቡ። “ባለ 5 ነጥብ” የሚለው ይህ ፅሁፍ “ባድመና አካባቢዋን ለኤርትራ እንስጥ” ይላል። ጠንካራ የተቃውሞ አቋም ከያዙት አንዱ ጄ/ል አለምሸት ሆኑ። አሁን በስደት የሚገኝ ኮ/ል ክብሮም የተባለ የአየር ሀይል መኮንን ጋር በመምሪያ ስብሰባ ላይ “”የጓዶቻችሁ አካል ሳይፈርስ አይናችሁ እያየ ሉአላዊ መሬታችን ተላልፎ እንዲሰጥ ካላችሁ የሞት ሞትና ክህደት ነው” አሉ። ..ይህ ከተፈጠረ በኋላ ጄ/ል አላምሸት ለዶ/ር ነጋሶና ብ/ጄ ታደሰ (ጋውና) ስልክ ደወሉ። “ነጋሶ ዛሬ የደወልኩት ይቅርታ ለመጠየቅ ነው። የመለስን ተሃድሶ አምኜ ትልቅ ስህተት ሰርቻለሁ። ከፍ ያለ ይቅርታ አድርግልኝ!?” አሉ። ከአፋቸው ክፉ ቃል የማይወጣው ነጋሶ “እሺ..” በማለት ይቅርታውን ተቀበሉ። ለጄ/ል ጋውና ስልክ ደወሉና ተመሳሳይ የይቅርታ ጥያቄ አቀረቡ። ጋውና በበኩላቸው “አለምሸት ምን አድርጌ ነው ይታሰር ያልከው?..ህገ መንግስቱን እየጣስክ ነው ባልኩኝ?” አሉ። አለምሸትም “በወቅቱ አንተ ያልከው ትክክል ቢሆንም ..ይታሰር ማለቴ ስህተት ነበር። የመለስ አካሄድ የገባኝ አሁን ዘግይቶ ነው” አሉ።..ከዩክሬን በ12 ሚሊዮን ዶላር የተሸመቱ የድምጽ መጥለፊያ ዘመናዊ መሳሪያዎች ተገዝተው የእያንዳንዱ ሹምና ከፍተኛ ጄኔራል ስልክ ይጠለፍ ነበር። የመለስን አጀንዳ ያልተቀበሉ በነወ/ስላሴ ይሰነዝራባቸው የነበረው ማስፈራሪያ “የስዬ እጣ ይገጥማችኋል” የሚል ነበር።..በዚህ መሻከር ውስጥ እያሉ በመቀሌ መለስ ስብሰባ ያካሂዳሉ። ጄ/ል ከማል ገልቹ ሌሎችን አስከትለው ኤርትራ መግባታቸው ተሰማ። የዛኑ እለት መለስ ቀጭን ትእዛዝ ለሳሞራ አስተላለፉ። ሳሞራ በማግስቱ ስብሰባ ጠርተው ከፍተኛ ጄኔራሎችን ሲያብጠለጥሉ ዋሉ። ማእረጋቸው ተገፎ እንዲባረሩ ከተወሰነባቸው አንዱ ጄ/ል አለምሸት ሆኑ። በድምሩ 9 ከፍተኛ አዛዦች ላይ ውሳኔ ተላለፈ። ሳሞራ ጋር ሀይለ ቃል የተመላለሱት ጄ/ል ወዲ አሸብር ለአንድ አመት በቤታቸው የቁም እስረኛ ተደረጉ። አለምሸት ማእረጋቸው ከመገፈፉ ባሻገር ሞራላቸው ተነክቶ ነበር። በአንድ ሴት ኮሎኔል ላይ የተፈፀመውን ግፍ በቀጣይ የምመለስበት ይሆናል..

Filed in: Amharic