>

ይቅርታ ጠያቂው መንግሥት ነው ወይስ እስረኞች? (ውብሸት ሙላት)

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በስብሰባው ለአገራዊ መግባባት እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል እስረኞችን በምሕረት እንደሚለቅ ገለጸ፡፡ ውሎ ሲያድር “በምሕረት ሳይሆን በይቅርታና ክስ በማቋረጥ” እንደሆነ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በኩል አሳወቀ፡፡ ከዚያም ጉዳያቸው በክስ ላይ የሚገኙትን በተመለከተ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክሳቸውን ያቋረጠላቸው ሲሆን የተፈረደባቸውን ደግሞ ይቅርታ እየጠየቁ እንዲፈቱ መንግሥት አሳውቋል፡፡

በይቅርታ አሰጣጥ አዋጅ፣ቁጥር 840/2006 አንቀጽ 3 መሠረት የይቅርታ ዓላማ የሚከተለው ነው፡፡ ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡፡ “የይቅርታ አሰጣጥ ዋና ዓላማ የሕዝብ የመንግሥትና የታራሚዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል መንግሥት የወንጀል ጥፋተኞች የተጸጸቱና የታረሙ መሆኑን በማረጋገጥ ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡” በመሆኑም እንደ ሕጉ፣ ማንኛው እስረኛ በይቅርታ ለመፈታት በጥፋቱ አምኖ መፀፀት እና ይህንንም በፊርማው በማስደገፍ በጽሑፍ መግለጽ ይጠበቅበታል፡፡

በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 15 መሠረትም ይቅርታ የሚያቀርበው ሰው በወንጀል ተከስሶ ጥፋተኛ የተባለው ነው፡፡ የይቅርታ ጥያቄው የሚነሳው በታራሚው ነው፡፡ በእርግጥ ጥያቄውን ከታራሚው በተጨማሪ የታራሚ ባለቤት፣ የቅርብ ዘመድ ወይም ጠበቃ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ በይቅርታ ጥያቄውም የተስማማ መሆኑን በፊርማ ማረጋገጥ ግድ ነው፡፡

የሰሞኑን የእስረኞች አፈታትን በሚመለከት፣ በይቅርታ ለመፍታት አስቀድሞ የወሰነው መንግሥት እንጂ እስረኞች አይደሉም፡፡ አስቀድሞ ይቅርታ እንዲደረግላቸው እስረኞቹ ቢጠይቁ ኖሮ በጥፋታቸው ተፀፅተው ነው ማለት ይቻላል፡፡ መፍታቱን የወሰነው መንግሥት ከሆነ ግን አስገድዶ አስረኞችን ተፀፀቱ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ በተጨማሪም መፀፀታችሁን ተናገሩ፣ግለጹ፣ፈርሙ ማለትም ተገቢም አይደለም፡፡

መንግሥት ለአገራዊ መግባባት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል እፈታለሁ ካለ፤ እስረኞችን “መፀፀታችሁን በፊርማችሁ ከገለጻችሁ ነው የምፈታችሁ” ማለት እንደምን አድርጎ አገራዊ መግባባትን ይፈጥራል? ሲጀመርም የሚመስለው፣ ይቀርታ ጠያቂው መንግሥት እንጂ እስረኞች አይደሉም፡፡ የይቅርታውን ሒደትም የጀመረው መንግሥት እንጂ እስረኞች አይደሉም፡፡
በመሆኑም፣መንግሥት እስረኞችን በይቅርታ ለመፍታት “አስቀድማችሁ በወንጀላችሁ ተፀፅታችሁ ፈርሙ” ማለት የተነሳበትን ዓላማ ስለማያሳካ የሚሻለው በአዋጅ በምሕረት መፍታት ነው፡፡ የሚሻለውም ምሕረት እንጂ ይቅርታ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ወንጀል ተከስሰው የማይፈቱ እስረኞች ካሉም አድልኦ ይሆናል፡፡ እኩልነትንም ይጥሳል፡፡ በየጊዜው እየነጠሉ መፍታትም እንዲሁ ችግሩን የበለጠ ከማባባስ ባለፈ እርባና አይኖረውም፡፡ ፋይዳም አይኖረው፡፡ በአገሪቱ ላይ እየታየ ያለውን ችግርም አይቀርፈውም፡፡

Filed in: Amharic