>

የአስቸኳይ ጊዜ ሕግን በተመለከተ ትኩረት የሚሹ ነጥቦች፤ (ውብሸት ሙላት)

አገራችን፣ ከመስከረም 28/2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ 28/2009 ድረስ የተዳደረችው በተለምዷዊው የሕግ ሥርዓት ሳይሆን ‘በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ’ ነው፡፡ አሁንም በድጋሜ ለስድስት ወራት ያህል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ በእርግጥ ለስድስት ወራትም ይሁን ከዚያ ላነሰ ጊዜ ጸንቶ እንዲቆይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ ይጠበቅበታል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ሲታወጅ፣ፓርላማው መደበኛ ሥራውን ለመጀመር ሁለት ቀናት ሲቀሩት ታወጀ፡፡ አሁንም፣ፓርላማው በእረፍት ምክንያት ሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት ነው የታወጀው፡፡ የ2009ኙም ይሁን አሁን ሲታወጅ፣ለመታወጁ ምክንያት የሆኑት ድርጊቶች በአጋጣሚ ፓርላማው በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት ስለተፈጠሩ ነው ማለትም አስቸጋ ነው፡፡ በ2009 በአማራ ክልል የነበረው ሁኔታ በዋናነት በ2008 ሐምሌና ነሐሴ የተከሰተ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚያን ወቅት ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀም፡፡ ኦሮሚያም ላይ ቢሆን በእሬቻ ጊዜ ያ ሁሉ እልቂት ሲፈጠር ሳይታወጅ ከሳምንታት በኋላ ነው የታወጀው፡፡

አሁንም ቢሆን በአማራ ክልል በተለይም በሰሜን ወሎ አካባቢ የተፈጠረው ችግር ከተረጋጋ በኋላ፣ኦሮሚያም ላይ ቢሆን ቀድሞ ከነበረው በንጽጽር የተሻለ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ወይም ደግሞ ፓርላማው ከመበተኑ በፊትና ከነበረው ሁኔታ የተለየ አዲስ ነገር የለም፡፡

ምናልባት አዲስ ነገር የተፈጠረው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በድንግት የሥልጣን መልቀቂ ጥያቄ በማቅረባቸውና እሱን ተከትሎ የመጣው አዲስ ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ደግሞ መነሻው የእሳቸው የጠየቁበት ሁኔታና ጊዜ እንዲሁም ኢሕአዴግም በፍጥነትና ሕዝቡ ውስጥ ውዥንብር እንዳይፈጥር አድረጎ መፍትሔ መስጠት ስለተሳነው የመጣ እንጂ መነሻው ሕዝቡ አይደለም፡፡

ሕገ መንግሥቱ ስለአስቸኳይ ጊዜ ሕግ፤
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93 ላይ እንደተቀመጠው ከአራቱ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ እንኳን ከተከሠተ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በፌደራል መንግሥቱ ሊታወጅ ይችላል፡፡ እነዚህም፡- የውጭ ወረራ፣ የተለመደውን የሕግ ማስከበር ሥርዓት በመጠቀም ሊቀለበስ ባለመቻሉ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ውስጥ ሲገባ፣ የተፈጥሮ አደጋ እና የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ መከሰት ናቸው፡፡የመጨረሻዎቹ ሁለቱ የተከሰቱት በአንድ ክልል ብቻ ከሆነ ደግሞ አደጋዎቹ የተፈጠሩባቸው ክልል መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ ሊያውጁ ይችላሉ፡፡

ከላይ የተገለጹትን፣ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያቶች፣ የሆኑትን ድርጊቶች መከሰታቸውን በማረጋገጥ የማወጅ ሥልጣን የተሰጠው አስፈጻሚው አካል፣በተለይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ ነገር ግን የሕግ አውጭው አካል ዕውቅና ከነፈገው አዋጁ ውድቅ ሆኖ አስፈጻሚው አካል መደበኛውን የሕግ ሥርዓት ብቻ በመከተል ድርጊቱን ማስወገድ አለበት ማለት ነው፡፡ አዋጁ ከጸደቀ ደግሞ በመደበኛው የአገር አስተዳደር ጊዜ ይከበሩ የነበሩ መብቶች፣ አሠራሮች፣ ተቋማት ወዘተ ሊታገዱ ስለሚችሉ እነዚህ የተጋዱትን ነገሮች እና ቦታ አስቀድሞ በማሳወቅ አመራሩ ይቀጥላል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገርን መምራት በባሕርይው ሥልጣንን አላግባብ ለመጠቀም የተጋለጠ ስለሆነ ይሄንን የሚቆጣጠር ቦርድ ይቋቋማል፡፡ ቦርዱ፣አስፈጻሚው ወይንም ሕግ አስከባሪው አካል ያልተገባ ሥልጣን በመጠቀም የዜጎችን መብት እንዳይጥስ ወይንም ከጣሰ ተጠያቂ ለማድረግ ሲባል የሚቋቋም ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በብዙ አገራት የሚደረግና ያለ አሠራር ነው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ፣ የመስከረም አንዱ የሽብር ጥቃትን ተከትሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ አሁንም በሥራ ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በአሜሪካ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የተገደበው የመከላከያ ሠራዊት ቁጥር እና የአገልግሎት ዘመን ብቻ ነው፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገርን መምራት እና ማስተዳደር ከተለመደው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የተለየ የራሱ ዘይቤ አለው፡፡ አሳዛኙ ነገር፣ ይህ አዋጅ የታወጀው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ጠይቀው የፓርቲውም የግምባሩም ሥራ አስፈጻሚ ጥያቄያቸውን ተቀብሎት ነገር ግን የኢሕአዴግ ምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ እስኪያሳልፉ ድረስ፣የፓርቲ አሠራር እና የሕግ ቅድመሁኔታ ብቻ በቀረበት፣ነገር ግን በተግባር ሥልጣናቸውን በለቀቁበት ሁኔታ በአስቸኳይ ጊዜ ሕግ አገርን እንዲመሩ ማድረግ ተጠየቃዊ አይሆንም፡፡

ይህ ጽሁፍም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ንድፈ ሐሳባዊ መነሻዎች እና ዓለማቀፋዊ መርሆቹን በአጭሩ ማቅረብ ነው፡፡ እገረ መንገዱንም የእኛን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚመለከቱትን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎችን በመተንተን ትኩረት የሚሹ ነጥቦችን ማሳየት ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምንነት እና አስፈላጊነት፤
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገርን መምራት በተመለከተ በፖለቲካ ሳይንስ እና በሕግ ሊቃውንት እንዲሁም በፈላስፋዎች ዘንድ የተለያዩ ክርክሮች አሉ፡፡ አገራትም እንዲሁ የተለያዩ አካሔዶችን ይከተላሉ፡፡ የአገራትን የተዘበራረቀ አካሔድ ፍላጎት ለማረቅ የሚበጁ ዓለማቀፋዊ ሕጎች እና መርሆችም ዳብረዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረቱ የአገር ህልውና ነው፡፡ አንድ አገር እንደቀድሞው መኖሩን እንዳይቀጥል የሚያደርግ፣ጸንቶ ያለውን የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚያናጋ፣ በተለመደው የሕግ አሠራር እና አስከባሪ ኃይል ሊመከት የማይቻል ሁኔታ በድንገት ሊጋጥም ይችላል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ ሕግ የሚታወጀው እንዲህ ዓይት አስገዳጅ ሁኔታዎች (Necessity) ሲከሰቱ ነው፡፡ ‘’አስገዳጅ ሁኔታ ሕግ አያውቅም፣ አያከብርምም!’’ እንዲሉ ሕግ የማያውቅን ሁኔታ በሕግ መመከት ወይንም መመለስ አይቻልም፡፡

የአገርን ሕልውና አደጋ የሚጥል ነገር ቢከሰት እና ሕጋዊ አካሄዶችን መከተል ደግሞ አደጋውን የማያስወግድ ከሆነ ሕጋዊ ያለሆነ መንገድን ተከትሎም ቢሆን አገርን ማትረፍ ተገቢ ነው የሚሉ አሉ፡፡ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የጣለ አስገዳጅ ሁኔታ ሲከሰት አስፈጻሚው አካል ማንኛውንም መንገድ በመከተል ከቀውስ አውጥቶ ወደ መደበኛው አመራር የመመለስ ሥልጣን ሊሰጠው ይገባል የሚሉም አሉ፡፡ የቀውስ ጊዜ አመራር ስለሆነ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይመራ ይችላል፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት እና የሕግ የበላይነት ሳይሆን የአስፈጻሚው አካል የበላይነት የሚሰፍንበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቀውስ ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት የሚወጡ ሕጎች የአስቸኳይ ጊዜ ሕጎች ይባላሉ፡፡ ዓላማቸውም በአጭሩ ሕግ አልባ የአመራር ሥርዓትን ሕጋዊ የማድረግ ነው፡፡

በርካታ አገራትም እና ዓለማቀፉ ማኅበረሰብም በእንዲህ ዓይነቱ ወቅትም ቢሆንም ምን መደረግ እንዳለበት እና እንደሌለበት የሚገልጹ ሕጎችን አሏቸው፡፡ በእርግጥ እንደ ሲዊትዘርላድ የአስቸኳይ ጊዜ እንዴት መመራት እንዳለበት ሕግ አያስፈልግም፤ ፕሬዚዳንቱ ትክክል ነው ብሎ ያመነበትን ነገር በሙሉ የማድረግ ሥልጣን አለው የሚሉም አሉ፡፡ ይህ እንግሊዛዊው ፈላስፋ፣ ቶማስ ሆብስ፣ እንደሚለው ‘የንጉሡ ወይንም የመሪው ዋና ተግባር የአገርን እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ በመሆኑ ያልተገደበ ሥልጣን ሊኖረው ይገባል፤ እንደውም ሌዋታን እንደሚባለው የባህር ውስጥ ኃይለኛ እና ፈርጣማ ሊሆን ይገባዋል’ የሚለውን ፍልስፍና የተከተለ ነው፡፡

ቶማስ ሆብስ ‘መገደብ ያለበት የዜጎች መብት ነው’ ባይ ነው፡፡ ይህ ፈላስፋ ሐሳቡን ያቀረበው ለመደበኛው እና ለሠላሙ ጊዜ ቢሆንም የሚስማማው ግን ለአስቸኳይ ጊዜ ነው፡፡ በአንጻሩ ጀርመን ደግሞ ከሂትለር አድራጎት በመማር እጅግ በጣም ጥብቅ አሠራርን በሕገ መንግሥቷ አስቀምጣለች፡፡

በዴሞክራሴያዊ አገራት የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ ዋና ዓለማ ዴሞክራሲው ላይ የተቃጣ ጠላትን ለመከላከል ነው፡፡ በተለይም የአዋጁ መነሻ የተፈጥሮ አደጋ ወይንም በሽታ ካልሆነ ዴሞክራሲ ራሱን ለመጠበቅ ጠላቶቹን መዋጋት መቻል አለበት የሚሉም አሉ፡፡ በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በብዙ ምክንያት ሊታወጅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቁልፍ የሆነው ጉዳይ ለማወጅ የሚያስችል አስገዳጅ ሁኔታ አለ ወይንስ የለም የሚለው ነው፡፡ በተለይም በበርካታ የላቲን አሜሪካ እና የአፍሪካ አገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው በሥልጣን ላይ ያለገደብ ለመቆየት ሲባል እንደሆነ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

የፓሪስ ዝቅተኛ መለኪያዎች፤
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት አገራት ሊከተሏቸው የሚገቡ ዘጠኝ መርሆችን የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ሪፖርተሮች በአንድ ወቅት አቅርበዋል፡፡ እነዚህም፡- የሕጋዊነት መርህ (የሚያስቀጡ ድርጊቶች ከነቅጣት መጠናቸው አስቀድሞ ማሳወቅ)፣ ማወጅ፣ የታወጀውን ነገር በዝርዝር ማሳወቅ፣ ጊዜውን መወሰን፣ ልዩ እና አስገዳጅ ስጋት መኖር፣ የእገዳውና የድርጊቱ መመጣጠን፣ ያደረገ አድልኦ አለማድረግ፣ የርምጃው አደጋውን ለመቅረፍ የሚችል መሆን፣ አዋጁ ከዓለማቀፍ አሠራሮች ጋር መጣጣሙ ናቸው፡፡

እነዚህ ጥቅል መርሆች ሲሆኑ የበለጠ ዘርዘር ባለ መልኩ የሰብኣዊ መብት እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ብሎም ወደ ቀደመ የአመራር እና የአስተዳዳር ዘያቸው ሊመለሱ የሚችሉበትን መንገድ የሚያሳየው የፓሪስ ዝቅተኛ መለኪያዎች (The Paris Minimum Standards) የሚባለው ነው፡፡

ዓለማቀፉ የሕግ ማኅበር፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሰብኣዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ኮሚቴ በማቋቋም ለስድስት ዓመታት አስጠንቶ እንደገና ለሁለት ዓመታት አስከልሶ አገራት እንደ ዝቅተኛ መሥፈርት እንዲጠቀሙበት፣ ሌሎች ተቋማትም ለክትትል እና ቁጥጥር ይረዳቸው ዘንድ እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም. በርካታ አንቀጾች ያሉት ሰነድ አውጥቷል፡፡ ዝቅተኛ መሥፈርት መባላቸው አገራት ቢችሉ ከእዚህ በተሻለ፣ካልሆነ እና ዝቅ ካሉ ደግሞ ከእዚህ ዝቅ እንዳይሉ መለኪያ እና ማነጻጸሪያ በመሆናቸው ነው፡፡

የፓሪሱ ሰነድ፣ የአንድን አገር መኖር አደጋ ውስጥ የጣለ ወይንም ለመጣል የቀረበ ሁኔታ ሲከሰት አስፈጻሚው አካል ማወጅ እንደሚችል ነገር ግን በተቻለ ፍጥነት እና በአጭር ጊዜ የሕግ አውጭውን ይሁንታ ማግኘት አለበት፡፡ በእኛም ሕገ መንግሥት ፓርላማው በሥራ ላይ ከሆነ በ48 ሰዓታት፣ በዕረፍት ጊዜው ከሆነ ደግሞ በ15 ቀናት ውስጥ መጽደቅ አለበት እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ጊዜ ፓርላማውን ለመጥራት ወይንም አጀንዳ ለማስያዝ የሚፈጀውን ጊዜ ከግምት ለማስገባት ነው፡፡ ፓርላማው ካላጸደቀው በአዋጁ መሠረት የወጡ መመሪያዎችም ይሁን ድርጊቶች ውድቅ ስለሚሆኑ በፍጥነት ማስጸደቁ ለአስፈጻማው አካል ጠቃሚ ነው፡፡

በ28/01/2009 ዓ.ም. አውጆ ፓርላማው በ30/01/2009 ዓ.ም. ሥራ ከጀመረ እንደሕገ መንግሥቱም ይሁን እንደፓሪሱ ሰነድ መንፈስ አስራ አምስት ቀናት እንደ መብት ማየት የሚቻል አይመስልም፡፡አሁንም ቢሆን፣አንድም ፓርላማው በሥራ ላይ በነበረበት ወቅት ከነበረው ብዙም አዲስ ነገር የሌለ በመሆኑ ፓርላማው ለእረፍት ከመበተኑ በፊት አስቀድሞ ማወጅ ይቻል ነበር፡፡ ከታወጀ በኋላም ከእረፍት መጥራትም ይቻል ነበር፡፡

እወጃው ጸንቶ መቆየት ያለበት የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ለሚፈጀው ጊዜ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ከፍተኛው ጣሪያም በሕገ መንግሥቱ መቀመጥ እንዳለበት ይገልጻል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዚህ ሰነድም ይሁን በሌሎች እንደተገለጸው የሚያካልለው አካባቢ ወይንም መልክአ ምድር መለየት አለበት፡፡ ችግር በሌለበት ቦታ ወይንም አካባቢ ማወጅ ተገቢ አይደለም፡፡ መርሁ፣ችግሩ ባለበት ቦታ ብቻ ማወጅ ሆኖ ችግሩ ሰፍቶ የሚያካልለውም ቦታ ከሰፋ የሚፈጸምበትን ወሰን መጨመር ነው፡፡ ለምሳሌ ችግር የተፈጠረው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ከሆነ እዚያ አካባቢ ብቻ፣ እንዲሁም ኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ዞኖች አካባቢም ከሆነ መጣል ያለበት እነዚህ አካባቢዎች ብቻ እንጂ በሌሎች ክልሎች አይደለም እንደ ማለት ነው፡፡

አሁንም ቢሆን ለምሳሌ፣ትግራይ፣አፋር፣ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ሐረሪ፣አዲስ አበባና ድሬዳዋ፣ደቡብ፣ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያሳውጅ ችግር መከሠቱን ሕዝብ አያውቅም፡፡ በፓሪስ መርህ ቢሆን እነዚህ ክልሎች ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ችግሩ ሲከሰት መጨመርን እንጂ አስቀድሞ መከለልን እንደመለኪያ አይወስድም፡፡

አገራት ያሉባቸውን ዓለማቀፋዊ ግዴታዎችም በዚህ ሰበብ ቀሪ ማድረግ እንደማይችሉ ይገልጻል፡፡ የኢትዮጵያን በአስረጅነት ብንወስድ፣ ዓለማቀፉን የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ስምምት ፈራሚ ናት፡፡ በዚህ ስምምነት ካሉባት ግዴታዎች መካከል አንዱ የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ ማወጇን ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ማሳወቅ ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜም እንኳን የማይታገዱትን መብቶች ማክበር ደግሞ ሌላው ነው፡፡ የማይታገዱት መብቶች ደግሞ በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ላይ ከተዘረዘሩት ስለሚሰፉ እነዚህንም መጨመር ይጠበቅባታል፡፡ ፈራሚነቷ እንዚህንም ጭምር እንድታከብር ግዴታ ጥሎባታል፡፡

አዋጁ፣ሕግ አውጪውን እና የዳኝነት ተቋማቱን የሚያግድ፣ የሚያፈርስ እንዲሁም በነጻነት መሥራታቸውን የሚያደናቅፍ መሆን የለበትም፡፡ ሕግ አውጪውን የሚየስፈርስ ምክንያት ቢፈጠር እንኳን በፍጥነት ምርጫ መደረግ አለበት፡፡ ይህንን በተመለከተ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በተወሰነ መልኩ ግር የሚል አቋም ተከትሏል፡፡ በአንቀጽ 93 መሠረት በማናቸውም መልኩ ሊታገዱ የማይችሉ ነገሮችን ሲዘረዝር የአገሪቱን መንግሥት ሥያሜ እና ሦስት መብቶችን ይዟል፡፡

በመሆኑም ከመብት በተጨማሪ የመንግሥትን ሥያሜ ማካከተቱ ሊታገዱ የሚችሉት መብቶች ብቻ አለመሆናቸውን ያመላክታል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ሌሎች መዋቅሮች እና ተቋማት ሊታገዱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያጸድቀው እና የሚያራዝመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ስናይ ሊታገድ የማይችል ተቋም ነው ማለት ይቻላል፡፡

እዚህ ላይ ለማንሳት የተፈለገው ዋናው ነጥብ የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ በባሕርይው አስፈጻሚውን አካል ሉዓላዊ እና ከሕግ በላይ በማድረግ አንባገነንነትን ስለሚያበረታታ ሌሎች ተቋማት እንደማይታገዱ በግልጽ መቀመጥ አለበት፡፡

ግብጽ እ.አ.አ. ከ1958 እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ በአስቸኳይ ጊዜ ሕግ ነው የተመራችው፤ ፕሬዚዳንት ሳዳት ከመገደሉ በፊት ካሉት የተወሰኑ ጊዜያት በስተቀር፡፡ አልጀሪያ የ1991ን የምርጫ ውጤት ተከትሎ በታወጀው ሕግ ለበርካታ ዓመታት በወታደራዊ ሕግ ሥር ቆይታለች፡፡

እንዲህ ዓይነት አካሔዶችን ለመግታት ቁልፍ የዴሞክራሲ ተቋማት መታገድ እንደሌለባችው በሕገ መንግሥቱ ሊገለጽ ይገባው ነበር፡፡ መታገድ የማይችሉት በግልጽ ተዘርዝረው ከተቀመጡ ቀሪዎቹ ሊታገዱ መቻላቸውን ስለሚያመለክት፡፡

የፓሪሱ መለኪያ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ የዳኝነት ተቋሙ በአስቸኳይ ጊዜ የሚኖረው ሚና ነው፡፡ ሥልጣኑና እና ሚናው የአስቸኳይ ጊዜ አውጁን ሕገ መንግስታዊነት ማረጋገጥ፣ እየተወሰደ ያለው ርምጃ ከአዋጁ ጋር የሚጋጭ ወይንም የማይጋጭ መሆኑን መቆጣጠር እንዲሁም መታገድ የሌለባቸው መብቶች እንዳይጣሱ የመከታተል ተግባር አለው፡፡

በእኛ አገር ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊነቱን የሚያረጋግጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ የመርማሪ ቦርዱ ደግሞ የሚወሰዱትን እርምጃዎች ሕጋዊነት እና ተመጣጣኝነት ይከታተላል፡፡ ተጥሰው ሲገኙ ርምጃ እንዲወሰድ እና ለፍርድ እንዲቀርቡ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የፍርድ ቤቶች ሥልጣን ይህ አጣሪ ቦርድ እንዲቀርብ በሚያደርግለት ክስ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የ1966ቱን ዐብዮት ተከትሎ ደርግ ሥራ ላይ ባዋለው ወታደራዊ ሕግ (Martial Law) ከመደበኛ ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የተላለፉ በርካታ ሥልጣኖች እንደነበሩ እናውቃለን፡፡

የነጻ የዳኝነት ተቋምን የሚያጠፋ ብሎም ለአስፈጻሚው አካል የሚወግን ፍርድ ቤት እንዳይኖር ለመከላከል እንዲረዳ አገራት ለዳኝነት ተቋማቸው ጥበቃ ማድረግ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ በመሆኑም በደርግ ጊዜ እንደነበረው ከመከላከያ ሠራዊቱ ጉዳዮች ውጪም ያሉ ጉዳዮችን የሚዳኝ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በአስቸኳይ ጊዜ ሰበብ እንዳይቋቋሙ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገር ስትመራ አሳሳቢ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የእስረኞችን ሁኔታ ነው፡፡ ሕግ አስከባው ግለሰቦችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይይዛል፤ ሰውነትን ይፈትሻል፤ ንብረትን ይበረብራል፡፡ በ48 ሰዓትም ፍርድ ቤት ላይቀርብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ጠበቃ የማማከር እና ሕክምና የማግኘት መብትን የሚከለክል መሆን የለበትም፡፡ የተያዙ ሰዎችንም በተቻለ ፍጥነት የት እንደሚገኙ ጭምር ለቤተሰብ ማሳወቅ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡

በፓሪሱ መለኪያ መሠረት በማናቸውም ሁኔታ የተያዘ ሰው በ30 ቀናት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት ያሳያል፡፡ አንዳንድ አገራት በአምስት ቀናት ውስጥ መቅረብ እንዳለባቸው ደንግገዋል፡፡

አሁን ሥራ ላይ በዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ውስጥ አንዱ የተያዙ ሰዎች ጠበቃ የማግኘት መብት ነው፡፡ በተለይ ለፖሊስ ቃላቸውን ከመሥጠታቸው በፊት ጠበቃ ጋር እንዴት መመካከር እና ማግኘት እንዳለባቸው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት ትልቅ ሓላፊነት ነው፡፡ ጠበቃ በራሱ መቅጠር ለማይችል ሰው ተከላካይ ጠበቃ የመመደብ ድርሻ የዚህ መሥሪያ ቤት በመሆኑ ነው፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ የማይታገዱ መብቶች፤
ስለአስቸኳይ ጊዜ ሲነሳ መታወስ ያለበት የመብት ‘ገደብ’ ሳይሆን ‘እገዳ’ ነው፡፡ ‘ገደብ’ በማናቸውም ጊዜ ማንም ሰው በመብቱ ሲገለገል ማለፍ የሌለበት ወሰንን የሚያመለክት ነው፡፡ ለምሳሌ ማንም ሰው የፈለገውን ሐሳብ የመግለጽ መብት ቢኖረውም መሳደብ ወይንም ስም ማጥፋት ግን አይችልም፡፡ የመንቀሳቀስ መብት ቢኖረውም ያለፈቃድ ከሌላ ሰው ግቢ ውስጥ መግባት አይችልም፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ‘ገደብ’ ናቸው፡፡

እገዳ ሲባል ግን በአጠቃላይ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመንቀሳቀስ ወዘተ መብትን መከልከል ነው፡፡ ለተወሰኑ ቀናት በተወሰኑ ቦታዎች የሚገኙ ሰዎች ከቤታቸው ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ ቢከለከሉ ይህ ‘እገዳ’ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ ዓለማ የተወሰኑ መብቶችን በማገድ መደበኛውን የሕግ ሥርዓት ማስፈን ነው፡፡ በመሆኑም በእንዲህ ዓይነት የቀውስ ወቅት ሰዎች እጅግ በርካታ መብቶቻውን እንዳይጠቀሙ ሊከለከሉ ይችላሉ፡፡ መርሁ፣ የማይታገዱትን መብቶች በሕገ መንግሥት ማስቀመጥ ነው፡፡ ከዚያ የተፈጠረውን ቀውስ ለማስወገድ የሚጠቅሙ መብቶችን መርጦ መከልከል ነው፡፡ ቀውሱን ለማስወገድ ምንም ፋይዳ የማይሰጡ ክልከላዎች ተገቢነት የላቸውም፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ላይ በተገለጸው መሠረት ፈጽሞ ሊታገዱ የማይችሉ የግለሰብ መብቶች ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም ልዩነት ያለማድረግ ወይም የእኩልነት እና ከኢሰብኣዊ አያያዝ የመጠበቅ መብቶች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለታወጀ ብቻ ከእነዚህ ውጪ ያሉ መበቶች ይታገዳሉ ማለት አይደለም፡፡

አንቀጽ 93(4)(ለ) ላይ እንደተገለጸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተከሰተውን ችግር ለማስወገድ በሚያስፈልገው ደረጃ መጠን መብቶችን ሊያግድ እንደሚችል ነው የገለጸው፡፡ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የሆነው የጎርፍ አደጋ ቢሆን ሰዎችን ያለፍርድ ትእዛዝ ማሳር ወይንም በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት የመቅረብ፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማገድ ችግሩን ለማስወገድ የሚፈይደው ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ እገዳ የሚጣልባቸው መብቶች በዝርዝር ተለይተው መታወቅ እና ችግሩን ለማስወገድ የሚረዱ ብቻ መሆን አለባቸው፡፡

ስለሆነም በሚታገዱት መብቶች እና የተፈጠረውን ችግር በማስወገድ መካከል በሚኖረው መመጣጠን ላይ አጽንኦት መሥጠት ተገቢ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ በጭራሽ የማይታገዱ መብቶችን ቢዘረዝርም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ በግልጽ የታገዱ እና ያልታገዱትን ማሳወቅ ይገባል፡፡

በዓለማቀፉ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት መሠረት በሕይወት የመኖር መብት ሊታገድ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ የዚህ ስምምነት ፈራሚ ከመሆኗ በተጨማሪም ለአተረጓጎምም እንደመስፈርት ለመጠቀም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13(2) መሠረት ራሷ ላይ ግዴታ ጥላለች፡፡ ስለሆነም በዚህ ስምምነት ላይ የተገለጹትን የማይገደቡ መብቶችንም ጭምር ማክበር አለባት ማለት ነው፡፡

በሕይወት የመኖር መብት ላይ የሚኖረውን ገደብ በተመለከትም መለኪያው በወንጀል ሕጉ ላይ በተቀመጠው “ሕጋዊ መከላከል” የሚለው መሆን ያለበት፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 78 እና 79 ላይ እንደተገለጸው ማንም ሰው የራሱን ወይንም የሌላ ሰውን ጥቅም ከጉዳት ለመከላከል ሲል በሌላ በምንም መንገድ ማስወገድ የማይችለው ድረጊት የሚፈጸምበት ከሆነ ከመጠን ያላለፈ የአጸፌታ ኃይል መጠቀም አልሞት ባይ ተጋዳይነት ስለሚሆን የተፈቀደ ነው፡፡ ከመጠን ያለፈ ከሆነ ግን ወንጀል ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ ሕጋዊ መከላከል ማለት በግድ የራስን ሕይወት ወይንም ንብረት ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ የሌላ ሰው መብትን ለመከላከል ሲባል የሚወሰደው ርምጃንም ይጨምራል፡፡ በመሆኑም የወንጅል መከላከል ሥራ ላይ የተሰማሩ የሕግ አስከባሪ አካላት የመጀመሪያ ተግባራቸው ምንም ዓይነት ኃይል ከመጠቀማቸው በፊት በሌላ መንገድ ወንጀሉን ለመቀልበስ የሚቻልበትን ሁኔታዎች መሟጠጥ አለባቸው፡፡ ቀጥሎ፣ የሚጠቀሙት የኃይል ርምጃ የወንጀል ድርጊቱን ለማስቆም የሚያስችል ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡

የወንጅሉ ድርጊት ተፈጽሞ ከሆነ ግን የኃይል ርምጃው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከሚያስፈልገው መጠን ማለፍ የለበትም፡፡ ለምሳሌ ፋብሪካን ለማቃጠል የሚመጣን ሰው በኃይል ማስቆም የሚቻል ሲሆን ቃጠሎው ተፈጽሞ ከሆነ ግን የሕግ አስከባሪ አካላት ተግባራቸው በቁጥጥር ሥር ማዋል ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የሕግ አስከባሪ አባላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ቢሆን የሰው ሕይወት ሲጠፋ መታየት ያለበት ከወንጀል ሕጉ አንጻር ነው፡፡

በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ የሚታወጀው የአገርን ህልውና ወይንም የተወሰኑ ሕዝቦችን ሕይወት የሚፈታተን አስገዳጅ ሁኔታ ሲከሰት ቢሆንም የግለሰቦች መብት ደግሞ አላግባብ የሚጣስበትን ሁኔታ መቀነስ ተጠያቂነትን ማስፈን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው

Filed in: Amharic