የአማራን ሕዝብ የህልውናን ትግል ችቦ ለኩሶ የጀመረው ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ከአፋብን ሙሉ በሙሉ ለመልቀቅ መወሰኑን አስታወቁ-!!!
ለአፋብን ፖሊት ቢሮ(ሥራ አስፈፃሚ)
ጉዳዩ—ከአፋብን አባልነት ስንብት ስለመጠየቅ
ጥቅምት 17፣ 2019 ዓ.ም
ይህ ደብዳቤ የምፅፈው በታላቅ ሀዘን ነው። የዚህ ሐዘን ምንጭ የምንታገልለት ፀረ—ጄኖሳይድ የህልውና ትግል የገጠመው የሞራል ልዕልና መናጋት፣ የርዕዮት ዓለም ቅልበሳ፣ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ ክስረት ብቻ ሳይሆን ፣ የፋኖን ትግል ከሞላ ጎደል ለብቻው ተሸክሞ የሚገኘው የአማራ ደሃ ገበሬ ያለበት ሁኔታ ነው።
የአማራ ደሃ ገበሬ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሀብቱንም ነፍሱንም ለዚህ ትግል እየገበረ እንደሚገኝ የዕለት በዕለት ምስክር ነኝ። አምላክ ብቻ በትክክል ለሚያውቀው ለዚህ ውለታው የተሰጠው ምድራዊ ምላሽ፣ በደሙ የገነባው አፋብን “በአማራ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ (ጄኖሳይድ) ከፈፀሙ ድርጅቶች ጋር ትብብር ፈጠረ” የሚል ዱብ እዳ መሆን አልነበረበትም። ነገሩ ሁሉ “በሬ ከአራጁ ጋር” እንደሚባለው ሆኖበታል።
የፋኖ ትጥቅ ትግል፣ ለረዥም ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ማንነትን መሠረት አድርገው የተፈፀሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች ተደማምረው ያፈነዱት ድንገተኛ ህዝባዊ አመፅ ነው። ከዚህ በፊት በሀገራችንም ሆነ በውጩ ዓለም እንደፈነዱት ድንገተኛ ህዝባዊ አመፆች ሁሉ፣ ይኸኛውም ማዕከል ያልነበረው እና በአማራ ክልል የ85 ከመቶ ድርሻ ያለውን ደሃው ገበሬ መሠረት አድርጎ የተከሰተ ነበር።
ይህ እውነታ የተለያዩ አካላት ህዝባዊ አመፁን ለራሳቸው ጠባብ ዓላማ ማስፈፀሚያነት እንደ መሣሪያ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ኃይል አድርገው እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል። ከእነዚህ አካላት መካከል አንዱ የሆነው ሕወሓት አፍቃሪው ብአዴን/ሕወሓት በአገዛዙ ውስጥ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ፣ በሚዲያው እና በዲያስፖራው ከ30 ዓመታት በላይ የተገነባ ኔትወርክ ያለው ስብስብ ነው።
ይህ ስብስብ ከሌሎች አካላት በተለየ መልኩ፣ ፋኖ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ ራሱ በቀጥታ የሚቆጣጠረው ፋኖን ለማደራጀት ሙከራ አድርጎ አልሳካለት ሲለው፣ በቀጣይነት፣ በመላው አማራ ክልል ብቅ ብቅ ያሉትን የፋኖ አደረጃጀቶችን ለመጥለፍ ለዓመታት የተንቀሳቀሰ ነው። ከብዙ ልፋት ቦኃላ ጠለፋው ተሳክቶለትም፣ “ግዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ፣ ለሶስት አሥርት ዓመታት በዘለቀው የሕወሓት አገዛዝ ዘመን ጥርስ አልባ ሆኖ የኖረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ግዜ በአፋብን ውስጥ ዋነኛው የፖለቲካ እና የህዝብ ግንኙነት ሥራዎች መዘውር እና ድምፅ ሆኗል።
የአማራ ፋኖ የህልውና ትግል ማውጠንጠኛ ሕወሓት ስሪቱ ህገ–መንግስት ነው። የዚህ ህገ–መንግስት የታሪክ ንባብ፣ የፖለቲካ ርዕዮት እና ራዕይ አማራን :-
“አፄያዊ ወራሪ፣ ነፍጠኛ (imperial expansionist)”፣ ቀሪዎቹን ኢትዮጰያዊያንን “ተወራሪ ሉዓላዊ ብሄር ብሄረሰቦች(sovereign nations and nationalists)” ብሎ የፈረጀውን የፋሺስት ጣሊያን የጥላቻ እና የፈጠራ ታሪክ (revisionist history) የተቀበለ እና እንደ ፈራረሱት ሶቨየት ህብረት እና ዩጎዝላቪያ ትናንሽ ነፃ ሀገራትን የሚያዋልዱ መንግስታዊ መዋቅሮችን የፈጠረ ነው።
አማራ ላይ ያነጣጠሩት ህገ–መንግሥታዊ የፈጠራ ታሪክ፣ ፖለቲካዊ ፍረጃ፣ የደቦ ጥላቻ ስም፣ ኢኮኖሚያዊ አድልኦ ፣ ማህበራዊ ማግለል እና ሥነ ለባናዊ ወከባ ተደማምረው ጄኖሳይድ እንደሆኑ በርካታ አኬልዳማዎችን ታቅፈን የምንኖረው እኛ ሰለባዎቹ ብቻ ሳንሆን፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ምስክርነት የሰጠበት ተጨባጭ ክስተት ነው። የሀገራችን ህገ–መንግስት የጄኖሳይድ ምንጭ መሆኑ በደም የተፃፈ እውነታ ነው። የህገ–መንግሥቱ መንፈሳዊ ምንጭ ደግሞ ሕወሓት ነው። ኦህዴድ/ብልፅግና ተቀባይ እና አስቀጣይ ነው። የአማራ የህልውና ትጥቅ ትግል በቀጥታ የሚታኮሰው ከኦህዴድ/ብልፅግና ጋር ይሁን እንጂ ወደ ምንጩ ስንሄድ ከሕወሓት ጋር እየተደረገ ያለ ትግል ነው።
የአማራን የህልውና ትጥቅ ትግል ከዚህ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ አውዱ ዝቅ አድርጎ ከኦህዴድ/ብልፅግና ጋር ብቻ የሚደረግ ትግል እና በኦህዴድ/ብልፅግና መወገድ ብቻ ሁሉም ችግሮች እንደሚፈቱ አድርጎ ለመቃኘት በብአዴን/ሕወሓት በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት መነሻ ሃሳብ የጄኖሳይድ ክህደቱ (genocide denial) መሆኑ ግልፅ ሊሆን ይገባል። ጄኖሳይዱ ሳይካድ ወደ ጄኖሳይዱ ምንጭ መሄድ አይቻልም።
አማራ ሆኖ በገለልተኛ የዓለም አቀፍ ተቋማት ምስክርነት የተሰጠበትን የአማራ ጄኖሳይድ መካድ፣የብአዴን/ሕወሓት ክስረት ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይም ሞራላዊ እንደሆነ ማሳያ ነው። አማራነት የሥጋ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነም ይጠቁመናል። ለነገሩ፣ የአማራን በደል መካድ ለብአዴን/ሕወሓት አዲሱ አይደለም። መንፈሱም፣ ማንነቱም፣ ታሪኩም ነው። የአርባ ጉጉ ጭፍጨፋ ግዜ ሲናገር የነበረው መቼም የሚረሳ አይደለም። የአሁኑን የተለየ የሚያደርገው በአማራ የህልውና ትግል ስም ክህደቱን ማስቀጠሉ ነው።
በዚህ ቡድን ሴራ አፋብን “ትብብር ለህውልና” የተባለው ሕወሓት ስሪት ስብስብ ውስጥ ገብቷል። “ትብብሩ” ሕወሓት በ2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሲቃረብ “የፌድራል ኃይሎች” በሚል መጠሪያ ያቋቋመው የትሮይ ፈረሱ እንጂ አዲስ ተቋም አይደለም። አዲሱ ነገር የአፋብን መቀላቀል ብቻ ነው። “ትብብሩ” ያኔም ዛሬም ፀረ–አማራ እና ፀረ–ኢትዮጵያ ነው። ከ”ትብብሩ” ሰባት ድርጅት መካከል አፋብን አንድ ድምፅ ብቻ ይዞ በፖለቲካ ሊለውጠውም ሆነ ሊመራው እንደማይችል እና ሕወሓት በ”ትብብሩ” ውስጥ ያለውን ወታደራዊ በላይነት መቼም ቢሆን አሳልፎ እንደማይሰጥ ለማወቅ ሊቅነትን አይጠይቅም።
በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርክ ሩቢዮ አንደበት “ተገንጣዮች” ተብሎ የተነገረው ይህ እውነታ ነው። ይህ እውነታ በሌሎች ጉዳዮች የማይስማሙትን አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይናን አስማምቷል። ምክንያቱ እንቆቅልሽ አይደለም። በተለያዩ ምክንያቶች የዓለማችን ልዕለ ኃያላን የኢትዮጵያን መበታተን ማየት አይፈልጉም። ያን ነው እየተከላከሉ ያሉት።
የውጮቹ የታያቸውን ሀገራዊ አደጋ አፋብን ሳይታየው ቀረ ተብሎ በታሪክ መመዝገቡ፣ በ1969 ዓ.ም ሱማሊያ ኢትዮጰያን ስትወር፣ “ጭቁን ጭቁንን አይወጋም፣ ደርግ ነው ቀዳሚ ጠላታችን” ብለው ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ከፈፀሙት ተርታ አሰልፎታል። የዚህ ባለቤት ጠላፊው ብአዴን/ሕወሓት ነው። “ትብብሩ” ከመመሥረቱ በፊት፣ ጭምጭምታውን ሰምተን ስለነበር፣ ብዙሃኑ የአፋብን አባላት ምንም የምናውቀው ነገር እንደሌለ ፍንትው ባለ ቋንቋ አሳውቀናል። ይህን እውነታ ማንም ሊቀማን አይችልም። ለህዝብም፣ ለታሪክም፣ ለራሳችንም መፅናኛችን ነው።
ከዚህ ስብስብ ጋር መቀጠል እንደማልችልም እንደማልፈልግም መላ የአፋብን አባላት የሚያውቁት ሐቅ ነው። ስብስቡም እኔ በአባልነት መቀጠሌን እንደማይፈልግ በዚያው ልክ ይታወቃል። ለሁለታችንም ሆነ ለድርጅቱ መፍትሄው የእኔ መልቀቅ ነው። ስለዚህም፣ በድርጅታችን ህገ ደንብ መሠረት ከአፋብን አባልነት እንድለቅ ይፈቀድልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለኹ።
ክብር ለሰማዕታት !!!
ዘላለማዊ ክብር ለፈጣሪ !!!
እስክንድር ነጋ፣
ጥቅምት 17፣ 2019 ዓ.ም።
አዲስ ሚዲያ




















