ከይኄይስ እውነቱ
ማሽቃበጥ የሚለው ቃል በጥቅሉ ዐንጓች÷አድር ባይ÷ እወደድባይ÷ በማያገባው ገብቶ የሚዘባርቅ ብለን ልንፈታው እንችላለን፡፡ በዚህ አስተሳሰብና ድርጊት የተጠመደን ሰው ደግሞ አሽቃባጭእንለዋለን፡፡ ባለፉት አምሳ ዓመታት አገር ከማፍረስና ከማዋረድ፣ ሕዝብን በማያቋርጥ ሰቈቃ ውስጥ በማኖር በደል ከፈጸሙናእየፈጸሙ ካሉ አገዛዞችና የአገዛዝ ቊንጮዎች እኩል ለአገር ጠንቅ የሆኑት አድር ባዮች መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እነዚህ እኔ ከሞትኹ ሰርዶ አይብቀል ባዮች ባገርና በሕዝብ ጥፋትውስጥ የምቾት ጥጋት ፈላጊዊች ሲሆኑ፣ እምነትም ሆነ መርህ የሌላቸው አረመኔ ደንታ ቢሶች ናቸው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ጉዶች ከቤተሰብ እስከ ኅብረተሰብ እንደ ዕንጉዳይ በዝተው የአገዛዞችን በተለይም አገራችን ላይ የሠለጠኑትን ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዞችን ህልውና በማራዘም የሚልዮኖችን ሕይወት ሲኦል አድርገውታል፡፡
በዚህ ርእሰ ጉዳይ እንድጽፍ ያስገደደኝ ርጉም ዐቢይ ‹ባልተፈጸመ ምርጫ› በኢትዮጵያ የሥልጣን መንበር ላይ በጉልበት ያላንዳች ኀፍረት መቀጠሉ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ፣ ‹የእንኳን ደስ አለህ› መግለጫ ተሸቀዳድመው የሚያዥጎደጉዱ የግል ተቋማትን መልእክት በየኦፊሴል ድረ ገጻቸውና ባገኙት መድረክ ሁሉ ሲቀባጥሩ በማየቴና በመስማቴ ነው፡፡ ማን አስገደዳቸው? ምን ዓይነት በሽታ ነው የተጣባን? እስከ መቼ የማስመሰልና የቅጥፈት ሕይወት እየመራን እንዘልቃለን? እውነት በጠብመንጃ አፈሙዝ ተገደው ነው? ነገ የለውጥ ነፋስ ቢነፍስ እነዚህ አድርባዮች ለመራገምና ለመዝለፍ የሚቀድማቸው የለም፡፡ ምን ዓይነትእሥሥታዊ ጠባይ ነው?
የውስጥና የውጭ ጠላት ባሰፈሰፉበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ይህን ውዳቂ አገዛዝ ማንቆላጰስ ምን ይሉታል? ይሄ ለግል ጥቅምና ሆድ ማሽቃበጥ÷ ይሄ የክህደት/የባንዳነት መንፈስ የት ያደርሰን ይሆን? እንዲህ ዓይነቱ ተልካሻ ለባርነት የሚያመቻች ጠባይ ፊደልን ቆጥረናል ከሚለው ክፍል በስፋት ከታየ እንደ ሕዝብ ዕጣ ፈንታችን ዕድል ተርታችን ምን ይሆን?
















