የብልጽግና ማኒፌስቶ እና ኦርቶዶክስ ቤ/ክ

ከንዋይ ካሳሁን 

አዲሱ የብልጽግና አገዛዝ ካቢኔውን ሲያዋቅር 54 % የብልጽግና ወንጌል ፕሮቴስታንት፣ 38 % ሙስሊም እና 8 % ስመ ኦርቶዶክስ ሆኖ ተዋቅሯል። ይሄንን ተከትሎ እንደአዲስ አንዳንድ ተቃውሞዎች ይነሳሉ፡፡ ነገሩን ከመሰረቱ መመርመር ተገቢ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥርስ ውስጥ ገብታ የምትላመጠው በግለሰቦች አልያ በቡድኖች ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መነሻው የመንግሥታዊ መዋቅር አስተሳሰብ ነው። ላለፉት ሃያ አመታት “ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ማእከል በመሆኗ አስተዳደሩን ይዞ በመቆጣጠር ማዳከም” መሆኑን ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ጽፈውታል። በፊት ለፊትም “ኦርቶዶክስን አከርካሪዋን ሰብረናታል” ብለውን ሊሰብሯት ሲታገሉ ቀድመው እነሱ ተሰበሩ እንጅ።

ዛሬ ደግሞ ሌላኛው ትርክት በአዲስ ብልጽግና ስም ብቅ ብሎ ቀስቱን ወደ ቤተ ክርስቲያን አዙሯል። ፀረ ብልጽግና፣ የነገሥታት መፈንጫ፣ ጸረ ዲሞክራሲ እያለ ካድሬው መከራ ሊያበላት ሥልጠና ወስዷል።

አንደኛ ነጥብ:-

የብልጽግና የፖለቲካ ሰነድ ስለ ሀብት ክምችት ከጅምሩ እንዲህ ይላል “ በአንድ ሀገር ውስጥ ሕዝቦች ስለ ሀብት ማካበት ያላቸው አመለካከት እምነትና እና ለሀብት የሚሰጡት ግምት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲሻሻልም እንዲወድም ሊያደርግ ይችላል። በአንዳንድ ቤተ አምልኮ አስተምህሮቻቸው ለሀብት ክምችት ከሚሰጡት ግምት እጅግ ዝቅተኛ ነው። በነዚህ ቤቶች ገንዘብ የኃጢአት ምንጭ ተደርጎ ሲታሰብ ራስን ከሀብት በማራቅ ሙሉ ጊዜንና ለፈጣሪ መስጠት እንደ ጽድቅ ይቆጠራል። በአማኙ ዘንድ ሀብታም መሆን ገሃነም ሲያስወረውር ድሃ መሆን ደግሞ መንግሥተ ሰማያትን ያደርሳል ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ ከሀብት ርቀው በመጎሳቆል ከሞት በኋላ በሚኖረው ሕይወት ዘላለማዊ ምቾት ማግኘትን ይመርጣሉ። በመሆኑም ይህንን እንደ እሴት በሚቆጥር ማኅበረሰብ ውስጥ ለብልጽግና የሚደረግ ጉዞ ፈታኝ መሆኑ እሙን ነው” ይላል። ይህንን እንደ መግቢያ ብናየውው ትርጉሙ ግልጽ ይመስለኛል።

በመሠረቱ “ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። ” የሚለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ሲቀጥል ቤተ ክርስቲያን “ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው ” ብላ ታስተምራለች እንጂ ሀብታም አትሁኑ፡ ሀብታም መሆን ኃጢአት ነው። ድሃ መሆን ያጸድቃል የሚል ትምህርት የላትም። አማንያን ገንዘብን ተከትሎ ከሚመጣ ክፋት እንዲጠበቁ ስታስተምር ገንዘብን ለሌላው አካፍለው ጽድቅን እንዲሰሩ ታስተምራለች። አብርሃም ድሆችን ይመግብ የነበረው ሀብታም ስለሆነ ነው። ሰሎሞን ብር እንደ ቅጠል ወርቅ እንደ ጠጠር የተረገጠ ባለጠጋ ነበር።

ይሁንና እንኳን መንፈሳዊው አለም ፖለቲካው አለም የሚታመስበት አንዱና ዋናው በዳቦ ስም የሚጠሩት “ሙስና” ወይም ሀብት ማጋበስ አይደለም ወይ? ሜቴክ መርከብ ሸጠ፣ ግድቡን ገንዘብ በሉት ሲሉን “የገንዘብን ተገን አድርጎ የተፈጠረ ክፋትን” ማየት በቂ ነው። በጥቅሉ “ቤተ ክርስቲያን ለብልጽግና አሳብ ፈታኝ በመሆኗ ካድሬዎቹ በምን አይነት እይታ እንዲስሏት እንደ ተፈለገ ማሰብ ቀላል ነው። ትህነግ ነፍጠኛ፤ ጎታች ሲላት የኖረችው ቤ/ክ የብልጽግና ፓርቲ ደግሞ አዲስ “ጸረ ብልጽግና” የሚል ተረክ ፈጥሮላታል።

ይቀጥልና ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ሀብትን በማግኘት የሚያበራታቱ ሃይማኖቶችን ሰነዱ ሲጠቅስ “በተቃራኒው ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ማካብት በፈጣሪ ዘንድ ሞገስ እንደ ማግኘት ተደርጎ የሚቆጠርበት ማኅበረሰብ አለ። ለምሳሌ በአይሁዳውያንና በአንዳንድ የፕሮቴስታንት ክርስትና ተከታይ በሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ሕዝቦች ዘንድ ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አወንታዊ የሆነ የሞራል ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ትርጓሜ እንደ ሚሰጠው በዘርፉ ብዙ ጥናት ያደረገው ማክስ ዌበር ይግልጻል” ይላል።

ይንን አባባል በብዙ መልኩ መሞገት እንችላለን። በተለይ የኢኮኖሚክስ እውቀት ላጠና ሰው ጉዳዩ ተራ አሳብ መሆኑ ግልጽ ነው። በመጀመሪያ ማክስ ዌበር ማነው ብሎ መጠየቅ አለም እንደ አንስታይን ፎርሙላ ተስማምቶ ያጸደቀለት አስተሳሰብ ነው ወይ? ማክስ ዌበር ስለተናገረ ትክክል ነው ያለው ማነው? ሌኒንምኮ መጽሐፍ ጽፏል፤ ሰው ከዝግመተ ለውጥ መጣ ያለውኮ ዳርዊን የአለም መነጋግሪያ ብሎም ኅሳቡ በብዙዎች ዘንድ ቦታ የያዘ ቲዎሪ ጽፏል ግን ጠቅሟል ወይ? ትክክል ነው ወይ? ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። ዶ/ር ገመቺስ አለልህ አይደል እንዴ “ኦሮሞ ሲጠመቅ ኢትዮጵያዊ ይሆናል” ያለ። ነገ ይሄም ሊጠቀስ ነው። ፈረንጅ ስለ ተናገረው ሳያላምጡ መዋጥ ሞኝነት ነው። ሕዝቅኤል ጋቢሳ እንዳለው ብለን ከጠቀስንኮ እውቀት የሚባል ነገር የለም። ጃዋርስ የፖለቲካ ሳይንቲስት ነኝ ይል የለም ወይ? ሜንጫ ሎጂGejera logy አጥንቶ።

እዚህ ላይ ማወቅ የሚገባን ፕሮቲስታንት በትልቅ ቲዎሪ ደረጃ የሚቀበሉት “ prosperity Gospel” የብልጽግና ወንጌል ትምህርቱን በአጭሩ “ብልጽግና የእግዚአብሔር በረከት ነው፤ ድህነት የእግዚአብሔር እርግማን ነው” በሚለው ማጠቃለል ይቻላል “ ይላሉ።

ሁለተኛው ነጥብ

ማኅበራዊ ወረት ለዲሞክራሲ (social values for democracy)
የብልጽግና ሰነድ ሲቀጥል፦ “ለዲሞክራሲ ግንባታ አንዳንድ ባህሎች ምቹ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ ምቹ አይደሉም.…የተለያዩ ባህሎች ለሁሉም አይነት የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት አማራጮች ተስማሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል። እንዲህ ያለ ክርክር ወደ ሃይማኖት ተሻግሮ አንዳንድ ሃይማኖቶች ለምሳሌ “ፕሮቴስታንት ” ከሌሎች ማለትም ከካቶሊክ፣ እስልምናና ኦርቶዶክስ፣ ኮንፊሲየስ የመሳሰሉት ጋር ሲነጻጸር የዲሞክራሲን ሥርዓት ለመገንባትና ለማጽናት የተሻለ እንደሆነ በመከራከሪያነት ይቀርብ ነበር። ዛሬም ድረስ ሁሉም ባህሎችና ሃይማኖቶች ለዲሞክራሲ ተስማሚ ላይሆኑ እንደሚችሉ መከራከሪያዎችን የሚያቀርቡ ምሁራን አልጠፉም” ይላል።

እዚህ ላይ ለማስተላለፍ የተሞከረውም መልእክትም ግልጽ ነው። የብልጽግና ፓርቲ በአዋጅ አመጣዋለሁ የሚለው ብልጽግና ይሁን ብልግና ባይታወቅም ፕሮቴስታንትን መርጧል። ብልጽግና ሊረጋገጥ የሚችለው ኢትዮጵያ በፕሮቴስታንት ሃይማኖት አስተሳሰብ ብትመራ ነው የሚል ነው። ሀገር መሥርታለች ሕዝቡን በባህልም በሥነ ምግባርም አንጻለች የምትባለው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለብልጽግና ኃሳብ የምትመች አይደለችምና ይህንን ለመቀየር በፕሮቴስታንት መመራት አለበት የሚል ነው።

ፓርቲው እያለ እንዳለው ሕዝቡን ለማበልጸግ መጀመሪያ የሚበለጽገው የፓርቲው አባላት ናቸው። በመሆኑም የብልጽግና አስተሳሰብ እንዲያመጡ ፕሮቴስታንት መሆን እንደ አንድ መመዘኛ መሆኑ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም (ባልተጻፈ ሕግ ማለት ነው)። ሃይማኖትህን ካልቀየርክና ካልተማርክ፣ ካልተሳተፍክበት የብልጽግና አስተሳሰብ ሊመጣ አይችልም ብለህ በሰነድ ተምረሃል።

አቶ አባ ዱላ ገመዳ የፓርላማ ጊዜ ቆይታቸውን በአርትስ ቲቪ በነገራችን ላይ ፕሮግራም ለጋዜጠኛ ደረጃ ሲያስረዱት “ፓርላማ መደበቂያ ሆነኝ… ብዙ ነገር የሰራሁት እዚያ ሆኜ ነው” የሚለውን ልብ በሉ። በለውጡ ውስጥ ወሳኝ ሰው እንደ ነበሩ ከንግግራቸው መስማት ይቻላል። በፓርላማ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ነው እጅ ተጭኖላቸው ሃይማኖት የተቀበሉት።

ካድሬ ደግሞ አለቃው ያለውን ከመቀበል ውጭ መጠየቅም፣ መሞገትም ስለሚያስገመግም ይቀበላል። በዚህ መልኩ የሃገሪቱን የሃይማኖት ዲሞግራፊ ለመቀየር ይጠቅማል። የነገ ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ እንዴት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

በጥቅሉ “የብልጽግና” ፓርቲ ለኢትዮጵያ አኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የደቀነባትን አዲስ ትርክት በማወቅ ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ ይጠቅም ዘንድ እንደ መነሻ ኃሳብ ተጻፈ። በጾመ ማርያም ምንም እንዳልጽፍ አስቤ ነበር ግን ግድ የሚል አጀንዳ መጣ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.