>
5:26 pm - Friday September 15, 0084

‹‹ይቅር ለእግዚአብሔር›› እና ‹‹ዕርቅ ደም ያደርቅ›› (ከይኄይስ እውነቱ)

‹‹ይቅር ለእግዚአብሔር›› እና ‹‹ዕርቅ ደም ያደርቅ››

ከይኄይስ እውነቱ

እነዚህ ሁለት አገራዊ ይትበሀሎች በሃይማኖትም ሆነ በባህል ከፍተኛ የሆነ ግብረ ገባዊ ልዕልናን የሚያሳዩ ውድ ዕሤቶች ናቸው፡፡ ይቅርታና ዕርቅን የአንድ ኩታ ሁለት ፈርጆች አድርጎ ማየት ይቻላል፡፡ ለዕርቅ መሠረቱ ይቅርታ ነው፡፡ ይቅርታም ሆነ ዕርቅ የሚፈጸሙት በበዳይና በተበዳይ መካከል ነው፡፡ በተለይም በግጭቶች ውስጥ ለቆየ ኅብረተሰብ ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት፣ ማኅበረሰባዊ ፈውስን ለማግኘት፣ በፈርጀ-ብዙ መከራዎች ያለፈ ሕዝብ ቁስል እንዲያጠግ ብሎም እንዲሽር ለማድረግ፣ ባለፈ ክስተት ላይ መቆዘምን አቁሞ ወደፊት በአዲስ ውጥን በብሩህ ተስፋ ለመቀጠል የሚረዱ የበጎ ምግባር ቁንጮዎች እንደሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ይህ ወንጀለኞችን ከወንጀል ተጠቂዎች እና ከማኅበረሰቡ ጋር በማስታረቅ በእርማት/በተሐድሶ (Rehabilitation) እንዲያልፉና ጠቃሚ የኅብረተሰቡ አካል እንዲሆኑ የሚያደርገው የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ሊቃውንቱ ‹‹ዕርቅ-ተኮር ፍትሕ›› /ትርጓሜው በጊዜያዊነት ይያዝልኝ/ (Restorative Justice) ይሉታል፡፡ በዚህ ፅንሰ ሃሳብ ዙሪያ ያሉ አካዳሚያዊም ሆኑ ተግባራዊ ክርክሮችን ለጊዜው ወደ ጎን አድርገን በኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት 27 የወያኔ ትግሬ አገዛዝ ዓውድ የይቅርታና ዕርቅ ጉዳይ በለበጣም ሆነ ከልብ በአገር ውስጥና በውጭ በሚገኙ ግለሰብ ዜጎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ማኅበራት፣ የማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ‹‹የአገር ሽማግሎች››፣ ‹‹የሃይማኖት አባቶች›› ሲነሳ ቆይቷል፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ በዐቢይ ‹አስተዳደር› እየተቀነቀነ ይገኛል፡፡

ለመሆኑ ይቅርታም ሆነ ዕርቅ ምንድን ናቸው? የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኙ መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ይቅርታና ዕርቅን በምናነሳበት አገራዊ ዓውድ በዳይና ተበዳይ እነማን ናቸው? በሕይወተ ሥጋ በሌሉ ተበዳዮች ተገብቶ ይቅርታ አድራጊው ማነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ አድርጓል እየተባለ የሚነገረው ለማነው ይቅርታ ያደረገው? እነዚህንና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ባጭሩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

በተሰማ ሀብተሚካኤል በተዘጋጀው ‹‹ከሣቴ ብርሃን ተሰማ፤ አማርኛ መዝገበ ቃላት››

ይቅርታ፤ በደልን÷ ኀጢአትን ይቅር ማለት፤ ቂምን መተውና ይቅር ለእግዚአብሔር ማለት ሲሆን፤

ዕርቅ፤ የተጣላ ሰውን ሽማግሎች ማስታረቅ÷ ማስማማት፤ ዕርቀ ሰላምን ማውረድ÷ ፍቅርን መስበክ፤

በማለት ፍቺ ሰጥቷቸዋል፡፡

ይቅርታ በብላሽ የሚገኝ ወይስ ለዚህ በጎ ፈቃድ/የቸርነት ድርጊት የሚገባ/ብቁ ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል?  

እውነተኛ ይቅርታ ተፈጽሞ ዕርቀ ሰላም ወርዷል ለማለት ሦስት ዐበይት ቅድመ ሁኔታዎች ባንድነት ተሟልተው መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡

1ኛ/ ምን ቀረኝ እያሉ ንቅስ አድርገው በግላጭና በስውር የፈጸሙትን በደል ባደባባይ እውነቱን መናገር÷ማመን፤ (ማመን እንደ ሁኔታው ለማኅበረሰቡ/ለሕዝብ)

2ኛ/ ከልብ በመጸጸት ለተበዳይ የምሕረት ተማፅኖ/ልመና ማቅረብ፤ በፈጸሙት በደል መቆጨት፣ ከክፋት መመለስ፣ በደሉን ዳግም ላለመፈጸም ቃል መግባት፣ መታመን፤ (መታመን ለራስ)

3ኛ/ የበደሉትን መካሥ፤ የቀሙትን/የሠረቁትን መመለስ፤

ጠቅለል ባለ አነጋገር ይቅርታና ዕርቅ በደልን አምኖና ታምኖ፣ እውነትን በጸጸት ስሜት አውጥቶ በይፋ በመናገር ተበዳዩን ለመካሥ በቊርጠኝነት መወሰን ነው፡፡ በመሆኑም ይቅርታ በበዳዩ ጠባይ የሚገኝ (earned/deserved) እንጂ በዳዩ በጥፋቱ እስመጨረሻው ገፍቶበት ዝሎ ሲወድቅ አሁን ምንም ማድረግ አይችልም ተብሎ የሚታደል ሥጦታ አይደለም፡፡ ታዲያ ስለ ይቅርታና ዕርቅ የሚያነሱ ወገኖች በተለይ መንግሥት እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ብሔራዊ መግባባትን ሊያመጣ ይችላል ተብሎ የሚታሰበውን ይቅርታና ዕርቅ በዚህ መንፈስ ይሆን የሚያዩት? ራሳችሁን መርምሩ፡፡ ከዚህ መለስ ያለው ንግግር ማሳመር ኹሉ የለበጣ፣ እነዚህ የፍቅር ትሩፋት የሆኑ ሥነ ምግባራት አቀንቃኝ ሆኖ ለመታየት የሚደረግ ማስመሰል ሲሆን፣ ሲከፋም ለተቀደሰ አገራዊ ዓላማ ሰማዕትነት የከፈሉ ወገኖች ላይ መሣለቅ ይሆናል፡፡ በእኔ እምነት የእስካሁኑ የይቅርታና ዕርቅ ጩኸት ከዚህ ከኋለኛው መንገድ ፈቀቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ የተድበሰበሰ ወይም የተውሸለሸለ ይቅርታና ዕርቅ እንኳን ደም ሊያደርቅ የቂም በቀል ስሜትን የበለጠ ያገዝፈዋል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ ባንፃሩም ይቅርታና ዕርቅ ባንድ ዐቢይ በጎ ፈቃድ ብቻ የሚመጣ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የይቅርታና የዕርቅ ሂደቱ ተሳታፊ የሚሆኑ በዳይና ተበዳይ እነማን ናቸው?

በዚህ አስተያየት አግባብ በዳይ የምንለው ባለፉት 27 የግፍና ሰቈቃ ዓመታት አሁንም ጭምር የኢትዮጵያ መንግሥትን ሥልጣን በጉልበት ይዞ የመንግሥትን መዋቅርና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብት በመጠቀም በዜጎች ላይ መንግሥታዊ ሽብርን ሲፈጽም የቆየውና እየፈጸመ ያለው የዘረኛው ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) አገዛዝ (ድርጅቱና ከደደቢት ጀምሮ በአመራር ላይ የነበሩና ያሉ ግለሰቦች) እና ከዚህ ጽሑፍ በኋላ ‹‹ተረፈ-ወያኔ›› ብዬ የምጠራቸው በትግራይ ሕዝብ ስም የተደራጁ አስመሳይ ተቃዋሚዎች እና ከወያኔ ትግሬ ሽርፍራፊ ሥልጣንና የዝርፊያ ፍርፋሪ ለመለቃቀም ሲሉ ከወያኔ ትግሬ ያልተናነሱ ግፎችን/በደሎችን በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸሙ፣ ሕወሓት ለዓላማው ማስመፈጸሚያ ብሎ በፈጠራቸው 3ቱም ድርጅቶች (ኦሕዴድ፣ ብአዴንና ደሕዴን) ውስጥ የሚገኙ ኅሊና ቢስ ሆድ አደሮችን ነው፡፡ በተጨማሪም ቅድመ-ዘመነ ዐቢይ እነዚህ 3 ድርጅቶች እንደ ድርጅት ከሕወሓት ጋር በጋራ ባሳለፏቸው ውሳኔዎች ባገርና በሕዝብ ላይ የፈጸሟቸው በደሎች ተጠያቂ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡

ተበዳይ የምንላቸው የዚህ ሽብርተኛ አገዛዝ (በዳይ ያልናቸው ቡድኖች) ሰለባ የሆኑ በሕይወተ ሥጋ የሌሉና በሕይተ ሥጋ ያሉ ነገር ግን ቃላት ሊገልጸው የማይችል የአካልና የሥነ ልቦና ቁስል ተሸክመው የሚኖሩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በዋነኛነት ሲሆኑ፤ ከሰው በታች ወርዶና ተዋርዶ፣ ከቤት ንብረቱ ተነቅሎና ተፈናቅሎ፣ የሚወዳት አገሩም በዕኩዮች መሠሪ ድርጊት ትበታተናለች በሚል ሥጋትና በከፋ የኑሮ ማጥ ውስጥ ተዘፍቆ ከሕይወት ይልቅ ሞቱን ሲናፍቅ የኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብም የወያኔ ትግሬ አገዛዝ ቀጥተኛ ሰላባ ነው፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ አድርጓል እየተባለ የሚነገረው ለማነው? በእኔ እምነት ዶ/ር ዐቢይን አብነት አድርገው ቅንነትን፣ በጎነትን፣ ፍቅርና ይቅር ባይነትን ገንዘብ አድርገው በሱ መንፈስ እየተጓዙ ላሉት አጋሮቹ እንጂ በጅምላ የተደረገ ይቅርታ ዕርቅ አለ ብዬ አላስብም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዐቢይና ጓደኞቹ ላደረጉት በጎ ጅምር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምቀቱ በሆነው ልዩነት ውስጥ አንድነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ላሳዩት ቊርጠኝነት፣ ከአድሎና ንቅዘት በፀዳ ምግባር መላ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን አገርንና ሕዝብን ለመካሥ በገቡት ቃል ኪዳን እና ለፈነጠቁት ብሩህ ተስፋ፣ የወያኔ አገዛዝ አሸባሪነትን ባደባባይ አምነው ሕዝብን ስለጠየቁት ይቅርታ በሰላማዊ ሰልፍ ድጋፉን ሲሰጥ ባንድምታ ይቅርታውን ያደረገው ለእነዚሁ ለተጠቀሱት ወገኖች እንደሆነ ነው የምረዳው፡፡

ከዚህ ውጪ የተጀመረውን መልካም የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ እነ ዐቢይ በሚገኙበት ግምባር ውስጥ ተወሽቀው በሕዝባችንና ባገራችን ላይ የሽብር ድርጊት እየፈጸሙ ያሉትን፣ አገር ለመበተን የሚንቀሳቀሱትን ወያኔ ትግሬ እና ተረፈ-ወያኔዎችን ለበርካታ ዓመታት የይቅርታና ዕርቅ ዕድል ቢሰጣቸውም የተጠጋቸው አጋንንት ይዟቸው የሚጠፋ በመሆኑ ወደ ልማደኛ ነፍሰ ገዳይነትና ዘራፊነት (አውሬነት) ለውጧቸዋል፡፡ በመሆኑም ለነዚህ ዕቡያንና ዕኩያን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምሕረት ለማድረግ ፈቃደኛ አይመስለኝም፡፡ በሕግ አግባብም ጥፋታቸው ለምሕረት የሚያበቃቸው አይደለም፡፡ በእኔ እምነትና አስተያየት ወያኔዎች ከፍ ብለን የጠቀስናቸውን የይቅርታ/ዕርቅ መሥፈርቶች አሟልተው ዕርቀ ሰላም ይወርዳል ማለት ፀሐይ በምዕራብ ትወጣለች እንደማለት ነው፡፡ ይህ አመለካከቴ ወያኔዎች ኤርትራን አስገንጥለው፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር ዘግተው፣ የጠላት ወረዳ የሚሏትን ኢትዮጵያ በወረራ ከያዙበትና የኢትዮጵያውያንን ደም ማፍሰስ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የዘለቀ ነው፡፡ እነዚህ በዘር ልክፍት የተንሸዋረሩ ሽፍቶች እንደ ገል ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው፤ በእጃቸው ጭብጥ በእግራቸው ርግጥ አድርገው የማይገዟትና የማይዘርፏት ኢትዮጵያ መበታተን አለባት ብለው በጽኑዕ ዲያቢሎሳዊ እምነት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

በመሆኑም የተቀደሱ የፍቅር ፍሬዎች የሆኑትን ይቅርታና ዕርቅን ከሰውነት ከወጡ ወያኔ ትግሬዎች ጋር አያይዞ ማንሳት ጉም እንደመዝገን ነፋስን እንደመጐሰም ይመስለኛል፡፡

ብዙዎቻችን ሰለ ይቅርታና ዕርቅ ሲነሳ አፍኣዊ ድርጊታችንና ውሳጣዊ ልቦናችን ሥምረት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ከልብ አምነውበት የአገራችንና የሕዝቧ ዕጣ ፈንታ አሳስቧቸው ስለ ይቅርታና ዕርቅ የሚዘምሩ መኖራቸው አይካድም (ከላይ የተጠቀሱትን መሥፈርቶች በማሟላት ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ አይደለሁም)፡፡ አንዳንዱ ዘገሩን እየነቀነቀና ሰይፉን እየሳለ ለታይታ ወይም ከበጎ አሳቢዎች ተነጥሎ ላለመታየት፤ አንዳንዱ ከጊዜው ነፋስ ጋር በወረት ለመንፈስ፤ አንዳንዱ እነዚህን በጎ ዕሤቶች ማቀንቀን የሥልጣኔ ምልክት በመሆኑ ሥልጡን ኾኖ ለመታየት፤ አሁንም አንዳንዱ ከነዚህ ከኋለኞቹ ወገን የሚሰለፍ ሆኖ በጥራዝ ነጠቅ ንባብ የቃረመውን ጫጭሮ ‹አዋቂነቱን› ለማሳየት ወዘተርፈ ነው፡፡ ታዲያ አድርባዩም፣ ሆድ አምላኩም፣ ግብዙም በሰማዕታቱ ነፍሳት ተገብቶ በደም የተለከፉ ልማደኛና የማይታረሙ ወንጀለኞችን በነፃ ለማሰናበት ውክልናውን ከየት ነው ያገኘው? እያልኹ ያለኹት ዓይን ላጠፋ ዓይን፤ ጥርስ ላወለቀ ጥርስ የሚለው የሐሙራቢ ሕግ ይፈጸም አይደለም፡፡ ይቅርታና ዕርቁ በሥርዓት (መሥፈርቶቹ ተሟልተው) ያለምንም ማድበስበስ በግልጽነት፣ ባደባባይ መፈጸም ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በጎ ቀን እንዲመጣ ለተቀደሰ ዓላማ የማይተካ ሕይወታቸውን በአውሬዎቹ ወያኔዎችና ተረፈ-ወያኔዎች የተነጠቁት አእላፋት ወትልፍኢት ዜጎች ፍትሕ ርትዕ ማግኘት እንደሚገባቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ በርእሰ መጻሕፍቱ እንደተመዘገበው እግዚአብሔር አምላክ መሐሪ ወመስተሣሕል (ምሕረትና ይቅርታ አድራጊ) እንደሆነ ኹሉ ኰናኒ በጽድቅ ፈታሔ በርትዕ ም (እውነተኛ ፈራጅ፤ ፍርድ አስተካካይም) ነው፡፡ ከፈጣሪ በላይ ለምሕረትና ይቅርታ አሳቢ መምሰሉም ግብዝነት እንዳይሆንብን ማሳሰብ እፈልጋለኹ፡፡ ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው ነው፡፡ ወንድምህ ቢበድል ለብቻው ምከረው፤ እምቢ ካለ ምስክር ጨምረህ ምከረው፤ አሁንም እምቢ ካለ ለቤተክርስቲያን ንገራት (ለምእመናን አሳውቃቸው)፤ ይህም ሆኖ አሻፈረኝ ካለ መለየትን መርጧልና እንደ አረማዊ ይሁንልህ (ከሱ ጋር ኅብረት አይኑርህ)፤ አውግዘህ ከሕዝብ አንድነት ለየው ይላል ታላቁ መጽሐፍ፡፡

ወያኔ ትግሬዎች ‹በተፈጥሮ ወንድምነታቸው› የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዴ ሁለቴ ሳይሆን ለበርካታ ዓመታት ቢመከሩ፣ ቢገሠፁ፣ ቢሸመገሉ ‹ጥልም በደልም የለም፤ ዕርቅም የለም› በማለት የቀረበላቸውን የይቅርታና የዕርቅ ማዕድ ኹሉ ገልብጠው በመሠሪነታቸው ቀጥለዋል፡፡ የተሰጣቸውን ዕድል ኹሉ ረግጠዋል፡፡ ስለሆነም በእኔ እምነት በቂ ማስታመም ተደርጓል፡፡ ቀሪው ፍትሕ ርትዕ ማስፈን ነው፡፡ በሁለት ልብ ሳያነክሱ እነዚህን ጋጠ ወጦች በሕግ ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ ያለብን ሥልጣንን መከታ በማድረግ ባገርና ሕዝብ ላይ ጥፋት የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች ያለተጠያቂነት እንዲታለፉ የሚያበረታታው ባህል አንድ ቦታ መቆም ስላለበትና ለወደፊቱም የሕዝብ ሥልጣን የሚይዙ ግለሰቦችና ቡድኖች በማንአለብኝነት አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ ተግባራት እንዳይፈጽሙ፤ ፈጽመውም ከተገኙ በሕግ ተጠያቂነት መኖሩን ማስጠንቀቂያና ማስተማሪያ ስለሚሆን ነው፡፡

ነገርን ነገር ያነሣዋልና በማጠቃለያነት ማንሳት የምፈልጋቸው ጉዳዮች (ከርእሰ ጉዳዬ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባይኖራቸውም) የሽብር ወሬን መንዛት እና የትኩረት አቅጣጫን የሚያስቱ አጀንዳዎች ላይ መነታረክን ይመለከታል፡፡

ብዙዎች አገር ለአደጋ ትጋለጣለች የሚል ተገቢ ሥጋት እንዳላቸው አምናለኹ፡፡ ይህንን ሥጋት በጻዕረ ሞት የሚገኙ ወያኔና ተረፈ-ወያኔዎች በአፈ ቀላጤዎቻቸው አማካይነት አለቅጥ ሲያጋንኑት ይስተዋላል፡፡ ለጥፋት ያንሳሉ እያልኹ አይደለም፡፡ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ለጥፋት መዘጋጀታቸውም የሚደንቅ አይደለም፡፡ ሆኖም እባካችሁ ይህንን የሽብር ወሬ በተለይ አገር ወዳድ ወገኖች በማወቅም ይሁን አለእውቀት አታራግቡት፡፡ ከማስጠንቀቁ ይልቅ ጠቀሜታው ለሽብርተኞቹ መሆኑን እንገንዘብ፡፡ የወያኔ ደናቁርት ባናፉ ቁጥር አንረበሽ፡፡ ሰሞኑን የወያኔ ትግሬ ቡድንን ትንሽነት ዓይነተኛ ማሳያ የሆነ ጉድ ታዝበናል፡፡ እንደው ከትምህርቱ ቢቀር ሰው ከአእምሮ ጠባይ (በተፈጥሮ ከሚገኝ እውቀት) እንዲህ ይራቆታል? አገሬ ኢትዮጵያ በእንደዚህ ዓይነት ጉዶች እጅ ወድቋ መቆየቷ አያስደነግጥም ትላላችሁ? የወያኔ ነገር ካልጠገቡ አይዘሉ ካልዘለሉ አይሰበሩ፤ ክፉ ራሱን ስለት ድጉሡን፤ ከወደቁ ወዲያ መገለባበጥ ለመላላጥ እንደሚሉት ከኢትዮጵያችን ጽዋ ተርታ ዕድል ፈንታ እንዳይኖራቸው ተግተው እየሠሩ ይመስላል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ሆይ ‹‹ባለጌን ካሳደገ ….›› እንደሚባለው እነዚህ ‹‹ልጆቻችሁን›› ሀይ በሏቸው፡፡ ካልሰሟችሁ በማሱት ጉድጓድ እንደሚገቡበት ጥርጥር የለውም፡፡

ቀደምት ሊቃውንት፡፡ ‹‹ኢይኀድጋ ለብሔር (ኢትዮጵያ) ዘእንበለ አሐዱ ኄር›› (አገርን ያለ በጎ/ቸር ሰው አይተዋትም) ይላሉ፡፡ ደግነቱ ኢትዮጵያችን ሰው አላት ባገር ውስጥም በውጭውም ዓለም የሚገኙ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ከምርጦቹ አንዱ ነው፡፡

ለነሱ ይብላኝ እንጂ ኢትዮጵያ በጭራሽ በጭራሽ በጭራሽ አትበታተንም፡፡ ፈጣሪ ዕድሜውን ያበድረን እንጂ በተራራ ላይ እንዳለ መብራት ብርሃኗን ከራሷ አልፋ ለመላው አፍሪቃ ታበራለች፡፡ ከኛ የሚጠበቀው ሳንለያይ÷ ሳንከፋፈል÷ ሳንዘናጋ÷ በንቃትና በትጋት በየአካባቢያችን ያሉ አፍራሽ ኃይሎችን (የለውጥ ሂደቱን ቀልባሾችን) አጥብቀን መከታተል፣ ለሕግ አሳልፎ መስጠትና ሕዝብን ማረጋጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የትግላችን መዳረሻ በሕግ የበላይነት ላይ የተዋቀረ፣ እኩልነትን የሚያረጋግጥ መንግሥተ ሕዝብ (ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) መመሥረት መሆኑን ከልብ ተገንዝባችሁ በየአካባቢያችሁ ያለውን ማኅበረሰብ አላስፈላጊ ከሆነ ግጭት (በተለይም ጎሣን መሠረት ካደረገ) እንዲጠበቅ ተግታችሁ ሥሩ፡፡ ይህን ካደረግን የወጣቱን መሪ ዶ/ር ዐቢይንና ባልደረቦቹን ጥረት መደገፍ እንችላለን፡፡

ጉንዳንን ባጥንት እንደሚሰበስቡት፣ ከዋናው ጉዳያችን ለማናጠብ ሆን ብለው የነገር አጥንት  በሚጥሉልን ዙሪያ በመሰባሰብ ጊዜያችንንና ኃይላችንን በከንቱ አናባክን፡፡ ከሰሞኑ እንደምናየው የሰንደቅ ዓላማ አጀንዳ፡፡ ለወያኔና ተረፈ-ወያኔዎች የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ እንደ ሟች አለቃቸው ከተራ ጨርቅነት የዘለለ አይደለም፡፡ እነዚህ የቁም ምውታን ባለቀላቸው ሰዓት በተካኑበት የመከፋፈል ወጥመድ እንዳንያዝ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡ ከመንጋ አስተሳሰብ እንውጣ፤ ምንጊዜም ትልቁን አገራዊ ሥዕል አንርሳ፤ ዋል አድርገን እናስብ፤ በጥቂቶች ፍለጎትና ድብቅ ዓላማ አንነዳ፤ አገር በሆያ ሆዬ እንደማትገነባ ጠንቅቀን እንረዳ፤ ዋኖቻችንን/ታላላቆቻችንን እናክብር/እናዳምጥ፤ ቋሚ እና ተለዋዋጭ/ሊሻሻሉ የሚችሉ አገራዊ ጉዳዮችን እንለይ (ለዚህም በእውቀት በልምድ የበለጸጉትን እንጠይቅ፤ እኛም ተግተን እናንብብ) ድጋፋችንም ሆነ ተቃውሞአችን ልክ ይኑረው፤ ማስተዋልንና ምክንያታዊነትን ገንዘብ እናድርግ፡፡ ልቦናውን ይስጠን፡፡

Filed in: Amharic