>
4:19 am - Friday July 1, 2022

የባለአደራው ምክር ቤት መግለጫ ተልእኮ በተሰጣቸው ወጣቶች  ተረበሸ!!! (ብርሀኑ ተክለአረጋይ)

የባለአደራው ምክር ቤት መግለጫ ተልእኮ በተሰጣቸው ወጣቶች  ተረበሸ!!!
ብርሀኑ ተክለአረጋይ
በመግለጫው ላይ አባይ ሚዲያን ወክዬ ታድሜ ነበር እናም መግለጫው በፅሁፍ ተነቦ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ መስጠቱ እስኪጋመስ ድረስ ፍፁም ሰላማዊ ነበር።
ድንገት እስክንድር ማብራሪያ ላይ በነበረበት ወቅት ሌባ! ዝም በል!! የሚሉ ጩኸቶች ተሰሙ ረባሾቹ ይዘውት ከነበሩት ፌስታል ውስጥ ባንዲራ አውጥተው ለበሱ።ወጣቶች መንገድ ዘግተው ወደ እስክንድር እንዳያልፉ ቢያደርጓቸውም በተደጋጋሚ እየተጋፉ ወደ እስክንድር ለመጠጋት ይሞክሩ ነበር።
ሁላችንም በቦታው የነበርን ሰዎች ቁጭ ብለውና ተረጋግተው ጥያቄ እንዲጠይቁ ብንነግራቸውም የተረፈን ስድብና ለመማታት ማስፈራራት ነበር።
ነገሩ እየጠነከረ ሲሄድ እስክንድር በሌላ በር ከክፍሉ እንዲወጣ ተደረገ የእርሱን ከክፍሉ መውጣት ተከትሎ ረብሸኞቹ ይዘውት የመጡትን ባንዲራ በየወንበሩ ወርውረው እየጮኹ ከህንፃው ወረዱ ።
አስገራሚው ነገር፦
እየተሳደቡና እየጮኹ ከህንፃው የወረዱት ወጣቶች በህንፃው በር ላይ የሰውና የመኪና መንገድ ዘግተው መግለጫ እየሰጡ ፖሊሶች ጥበቃ ያደርጉላቸው ነበር።
እስክንድር መግለጫ በሰጠባቸው ጊዜያት ሁሉ መጥተው የማያውቁ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ይህ ሊከሰት እንደሚችል ያወቁ ይመስል ግርር ብለው ከመገኘታቸው በላይ ረብሸኞቹ እየሰጡት የነበረውን መግለጫ ያስተባብሩ ነበር።
ይህ ሁሉ የሆነው በኛይቱ አዲስ አበባ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን 100 ሜትር በማይርቅ ቦታ ነው።
የአዲስ አበባ ጉዳይ የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ ይወስናል!
ተስፋ መቁረጥ አልፈጠረበትምና ዛሬም የኦነጋውያኑን ጫና ተቋቁሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የሚዲያ አካላትን ጠርቶ የነበረው እስክንድር ዴሞክራሲን በማያውቁ ግለሰቦች ጩኸት ተበትኗል፡፡
ይህ ሲሆን በስልጣን ወንበራቸው ላይ ሆነው እያዩ ብቻም ሳይሆን እያስፈፀሙ ስለዴሞክራሲ የሚያላዝኑ ኦነጋውያን የታሪክም ተወቃሾች ናቸውና ሊያፍሩ ይገባል፡፡
የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጋዜጣዊ መግለጫ እንደዚህ የሚፈሩት በሀሳብ ትግል ስለማይችሉት ጉልበትን እንደመጨረሻ አማራጭ መጠቀማቸው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህ ግን ይዋል ይደር እንጅ በአገር እና በህዝብ ላይ እየተለኮሰ ያለ ፈንጅ በመሆኑ ማንም አይጠቀምም፡፡
ሁሉም በአድርባይነት ተሸብቦ አገር እየፈረሰች ዝምታውን መርጧል፡፡ የሚናገሩትም ለአገር አፍራሾች ዶማ እያቀበሉ መሆኑን የምንታዘበው ነው፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ለአዲስ አበቤዎች ተትቶ የከተማዋ ነዋሪዎች በከተማቸው ጉዳይ አድራጊ ፈጣሪ ካልሆኑና ሞግዚትነቱ ከቀጠለ የኢትዮጵያን ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚያደርገው አትጠራጠሩ!
Filed in: Amharic