>

ችሎት ለመታደም የሔዱት የአብን አባላት ና ደጋፊዎች ታሠሩ!!! (ህብር ራድዮ)

ችሎት ለመታደም የሔዱት የአብን አባላት ና ደጋፊዎች ታሠሩ!!!
ህብር ራድዮ
* የአራዳ ፍርድ ቤት የወጣቶች አፈሳ ምን ያስከትል ይሆን!?
 
በዛሬው እለት ሀምሌ 16/2011 ዓ.ም ፥ አራዳ ምድብ የወንጀል ችሎት የቀረቡትን የአብን አባላትና አመራሮች ፤ የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶችን ችሎት ለመታደም የሄዱ የአብን የአዲስአበባ አመራርና አባላት በፖሊስ ታስረዋል፡፡
አራዳ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ በቅርቡ የታሰሩ የአብን አባላትን ለማየት የሔዱ ” እውነት እና አማራነት አይታሰርም” የሚል ካናቴራ የለበሱ ቁጥራቸው አሥራ ስምንት የሚደርሱ ወጣቶች ይህን ወንጀል ሆኖ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
የተሞካሸው ለውጥ አቅጣጫውን እየሳተ ዜጎች ሀሳባቸውን ካናቴራም በመልበስ መግለጽ ወንጀል ሆኖ መቆጠር ከጀመረ በእርግጠኝነት ይህ ጡንቻ ወለድ እርምጃ የስርዓቱን ጉድጉዋድ እንደ መማስ ይቆጠራል።
ትላንት የኮየ ፈጬ ኮንደሚኒየም ዕጣን እንደውም ያሉ አጠና ላይ ምስማር ሰክተው በጃዋር አዝማችነት ሰልፍ ሲወጡ፣በፍርድ ቤት ደጃፍ ጭምር ገጀራ እያውለበለቡ በሰልፍ እየፎከሩ ሲያልፉ በፖሊስ አጀብ ደህንነታቸውን ሲጠብቅ የቆየው መንግስት ያ ትዕግስቱ ዛሬ የት ገብቶ ነው?
በአገሪቱ አሰቃቂ ወንጀል የተቃውሞ ድምጻቸውን ባሰሙ፣ለመቃወም ሞክረዋል በተባሉ ዜጎች ይህ ነው የማይባል ግፍ ሲያስፈጽም እና ሲፈጽም የነበረው ጌታቸው አሰፋን በአደባባይ ከሕግ ተጠያቂነት ለመከላከል ብዙዎችን የሚያም ቢሆንም “እኔም ጌታቸው አሰፋ ነኝ” የሚል ካናቴራ አስለብሶ ሰልፍ ሲያወጣ ትንፍሽ ያላለው መንግስት ዛሬ በሰላማዊ መንገድ አደባባይ የፍርድ ቤት ሒደት ለመከታተል የሔዱትን አስሮ ስለ የትኛው ህግ ሊያወራ ነው?
የአምባገነኖች በሽታ ተመሳሳይ ለመሆኑ የዛሬው ድርጊት በቂ ማሳያ ነው። የፈሩት ላይ ህግ አክባሪ መብት ጠባቂ ይመስላሉ።የፈራቸው የመሰላቸው ላይ የተጻፈውንም ያልተጻፈውንም ህግ ጥሰው ጭካኔ እና ነውራቸውን ለማፈን እና ለማስፈራራት ይህን መሰሉን ግፍ ይፈጽማሉ። ጉዳዩ ተራ አድልዎ ብቻ ሳይሆን ይህ ስርዓት እስካልተወገደ ድረስ የዜጎችን መብት ሊያከብር፣የህግ ተጠያቂነትን ሊያሰፍን የሚችልበት ተፈጥሮ የለውም።
ዛሬ የተፈጸመው የእድልዎ እርምጃ በምንም መንገድ ተቀባይነት የለውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም ሽብር የነበርነው እኛ ነን ማለታቸውን ደግመው እንዲያስታውሱ እና ይህን መሰሉን ዜጎችን የማሸበር ድርጊት እንዲያቆሙ እንጠይቃለን
Filed in: Amharic