>
8:40 am - Saturday November 26, 2022

አስቂኞቹ የዘውጌ ፖለቲከኞቻችን!!! (መስከረም አበራ)

አስቂኞቹ የዘውጌ ፖለቲከኞቻችን!!!
መስከረም አበራ
የዘውግ ፖለቲከኞች ኮሜዲያን እየመሰሉኝ የመጡት እኔን ብቻ ነው?ምኒልክ እንትን ቆርጦ እንትን አንጠልጥሎ፣ የእንቶተኔን  ብሄር ባህል ደምስሶ የእንቶኔን ተክቶ እያሉ ሲያወሩ ማቋረጥ በአሃዳዊነት ያስከስሳል እና ዝም ብሎ መስማት ነው፡፡ ደግነቱ መሃል ላይ “ሃይሉ” ወይ “ብሩ” የተባሉበትን በደል የጀርባ ታሪክ እንደማውራት ያለ ዘና የሚያደርግ  ነገር ያመጣሉ እንጅ አልቆልን ነበር!  (እንደሚያዝኑልን የማውቀው እንዲህ ያለ ቀልድ ጣል በማድረጋቸው ነው-ምንስ ቢሆን ያገርልጅ አይደለን!) በመሃል በመሃል “ምኒልክን አላውቀውም”፣”ከእናት እና አባትህ አንዱን ምረጥ” አይነት ነገሮችን ጣል ጣል ባያደርጉ ኖሮ ይሄን ነገር እንዴት እንዘልቀው ነበር ግን?
ከሁሉ የሚያስቀኝ አማራን ለመርገም ሲሆን የሰዎችን ዘር ቆጥረው(ጉራጌውም፣በግማሽ ኦሮሞውም አማራ እየተባለ ማለት ነው) የጭቆና ስርዓቱ  የተገነባው በአማራ ገዥ መደብ ነው ብለው ሲያለቃቅሱ “በዚህ ስርዓት ውስጥ ኦሮሞዎችስ፣ጉራጌዎችስ፣ሌሎችስ  አልነበሩም ወይ?” ሲባሉ “ሰው አትጥሩ እኛ ስለ ስርዓት ነው የምናወራው” ብለው ቁጭ የሚሉት ነገር ነው፡፡ ስርዓት ግን የሚገነባው  ከሰው ካልሆነ ከምንድን  ነው? “የአማራ ገዥ መደብ ጨቋኝ ስርዓት” በሚለው ሃሳብ ውስጥ ሰው አልተጠራም አይደል? ስርዓት የሚባል ነገር የሚገነባው የአማራ ተወላጅ ሰዎች ብቻ ሲሸምኑት ነው?ወይስ “ስለ ስርዓት ሲወራ ሰው አይጠራም ከአማራ በቀር” በሚል ቀመር እንከተላቸው?
ሌላው አስቂኝ ነገር አማራ ባደረሰባቸው የባህል ከበባ ምክንያት አማርኛ ተገደው እንደሚናገሩ ህይወታቸውን ሁሉ እያማረሩ የሚያወሩ ሰዎች እንግሊዝኛ ቋንቋን ተሟሙተው ተምረው፣ ደስ እያላቸው አሳምረው ማውራታቸው ነው (እንደ ፕሮፍ እዝቅኤል እንግሊዝኛ የሚያምርለት ሰው ሰምታችሁ ታውቃላችሁ ግን ?) ይህ ለምን ሆነ ካላችሁ እንግሊዝ የአማራን ያህል ቅኝ ገዥ ስላልሆነች መሆኑ ነው(ከት ..ከት..!)
ሶስተኛ ገራሚ ነገር አማርኛ ቋንቋ ተጫነብኝ የሚለው ሁሉ አማርኛ ከማን በምን በልጦ የኢትዮጵያ ቋንቋ ሆነ ለማለት ፕሮፌሰርነቱ እንኳን ያልረዳው መሆኑ ነው፡፡
አማርኛ ከጥንት ጀምሮ የፅሁፍ ፊደል ያለው ቋንቋ መሆኑ ለነገስታት ብራናቸውን ዘርግተው የፖለቲካ ስራቸውን በፅሁፍ እንዲያሳልጡ መርዳት መቻሉ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ትንሽ የረዳው የማይመስላቸው ግን ለምን ይሆን?አማርኛ  የፀሁፍ ፊደል ያለው ቋንቋ መሆኑ በሚጠሉት አማራ መበለጥ ስለሚመስላቸው ይሆን? ወይስ ፊደሉን የቀረፀውም ያ “እርጉም” ሚኒሊክ ይመስላቸው  ይሆን? ወይ ፊደሉን የቀረፁው አካላት ዘር በታወቀና (በተቻለ መጠን ኩሽ በሆኑ ) በተገላገልን ባይ ነኝ ……
Filed in: Amharic