>

ዶ/ር አብይ አገሪቱን እየመሩ ነው ወይስ እያስታመሟት? (ያሬድ ሀይለማርያም) 

ዶ/ር አብይ አገሪቱን እየመሩ ነው ወይስ እያስታመሟት?
ያሬድ ሀይለማርያም 
 
ይህ አመት ለኢትዮጵያ ወሳኝ የፖለቲካ ምዕራፍ ይመስላል። በርካታ ችግሮች ከፊታችን አስቀድመን የጀመርነው አዲስ አመት አዳዲስ የሚመስሉ ነባር ፈተናዎችን መልሶ ከፊታችን ደቅኗቸዋል። እያንዳንዱን ችግር ዘርዝሮ መወያየት ቢያስፈልግም በእንዲህ አይነት አጭር የዳሰሳ ጽሁፍ ለመሸፈን ስለማይቻል ዋና እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የትኩረት ነጥቦች ላይ አንዳንድ አሳቦችን ለመለዋወጥ ያመች ዘንድ ከፊታችን የሚጠብቀን ምርጫ፣ ያገረሸው የፖለቲካ ውጥረት እና በአደባባይ መወያያ እየሆነ በመጣው የተረኝነት እና የተገፊነት ስሜት ላይ ለማተኮር ወደድኩ። 
 
በዚህ ጽሑፍ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ እና የእኔን አስተያየት ለጊዜው ላቆየው እና ለውይይት የሚሆኑ ጥያቄዎችን ብቻ ላቅርብ። በተከታታይ በማቀርባቸው ጽሁፎች ደግሞ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የራሴን ትዝብት እና የመፍትሔ ሃሳብ የምላቸውን ለውይይት አቀርባለሁ።
 
፩/ ምርጫ
 
ይህ አመት የሽግግሩን ዘመን በምርጫ ለመቋጨት ወይም የምርጫውን ጊዜ በማራዘም የሽግግሩን እድሜ ገፋ ለማድረግ ወሳኝ ወቅት ላይ ደርሰናል። ምርጫውን በተመለከተ በርካታ አወዛጋቢ እና የተራራቁ ሃሳቦች ከወዲሁ እየተደመጡ ነው። ከነዚህም ውስጥ፤
 
 የምርጫው ጊዜን በተመለከተ በታቀደለት ወቅት ይካሄድ ወይም ይራዘም የሚሉ እሰጣገባዎች በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ጎራ አካፍሎ እያወዛገበ ሲሆን በገዢው ፓርቲ አባላ ድርጅቶችም ውስጥ አንድ አይነት መግባባት ያለ አይመስልም። የምርጫው በጊዜው ለመካሄድም ሆነ ላለመካሄድ ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች መካከል ዋናዎቹ እና መልስ የሚሹት ጥያቄዎች መካከል፤
 
+ የምርጫ ቦርድ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የጀመረውን አዲስ አደረጃጀት እና አውቃቀር አጠናቆ ምርጫ ለማካሄድ በሚያስችል ቁመና ውስጥ ይገኛል ወይ? አዳዲስ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ገና በመመልመል እና ቅርንጫፎችን በማደራጀት ላይ ያለው ቦርዱ ዝግጅቱን በቀጣዮቹ ወርቶች ማጠናቀቅ ይችላል ወይ? 
 
+አዲስ በወጣው ሕግ መሰረት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማሰባሰብ የሚገባቸውን ያህል ድጋፍ ፊርማ አሰባስበው ለምርጫ መዘጋጀት ይችላሉ ወይ? ድጋፉንስ ለማሰባሰብ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ይፈቅዳል ወይ? ለምሳሌ መኖሪያ ቤት መከራየት የተከለከሉት የአረና አባላት ትግራይ ውስጥ እንደልባቸው ተዘዋውረው ድጋፍ ማሰባሰብ ይችላሉ ወይ? 
 
+ በበርካታ የአገሪቱ ክፍል እየታየ ያለው የሰላም መታጣት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት በቀሩን ወራት ውስጥ ተሻሽሎ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታን ይፈጥራል ወይ? 
 
+ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመላ አገሪቱ ወይም በሚወዳደሩባቸው አካባቢዎች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ቅስቀሳ የማድረግ፣ አባላት እና ደጋፊ የመመልመል፣ ጽሕፈት ቤት የመክፈት እና ሕዝባዊ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ አለ ወይ? 
 
+ መንግስት በመላ አገሪቱ ሕግ እና ሥርዓት ለማስፈን ቁርጠኝነቱ እና ዝግጅቱስ አለው ወይ? 
 
+ ገዢው ፓርቲ ከወዲሁ ያሉትን የመንግስት ሚዲያዎች ተጠቅሞ ምርጫ ተኮር የሚመስሉ የቅስቀሳ ሥራዎችን እያከናወነ ይመስላ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሞኑ የቪዲዮ ዶክመንተሪ እና በርካታ እንቅስቃሴዎቻቸው ምርጫን ታሳቢ ያደረጉ ይመስላሉ። ተቃዋሚዎች ምን እየሰሩ ነው? 
 
+ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለገዢው ፓርቲ ክፍት የሆኑትን ያህል ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ያህል ክፍት ናቸው? የሚዲያ ድጋፍ ያላቸው እና ሚዲያ የሌላቸው ፓርቲዎች ባሉበት አገር ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ይቻላል ወይ? ሁሉም ፓርቲዎች እኩል የተደራሽነት እድል እንዲያገኙ የሚያስችል የሚዲያ አጠቃቀም መፍጠር ይቻላል ወይ?  
 
+ በመንግስት ተቋማት እና በገዢው ፓርቲ መካከል ያለው መቀላቀል ዶ/ር አብይ ለሚመሩት ፓርቲ የፈጠረውን ምቹ እድል ያህል የሩቡን እሩብ እንኳ አቅም እና መንግስታዊ ተቋማትን የመጠቀም እድል የሌላቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች አቻ ተፎካካሪ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ ወይ? 
 
+ አብዛኛው የመንግስት ተቋማት የገዢውን ፓርቲ የምርጫ ተኮር እንቅስቃሴ ለማስፈጸሚያ እንደ መሳሪያነት እያገለገሉ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ገዢውን ፓርቲ ሊገዳደር የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ ሊፈጠር ይችላል ወይ? የመንግስትን በጀት ተጠቅመው የግል ገጽታቸውን የሚገነቡ ሹማምንት እና መሪ ድርጅቶች ባሉበት ሁኔታ በመራጩ ሕዝብ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ልዩ እድል አልሰጣቸውም ወይ? 
 
+ በአማራ እና በትግራይ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተለይም በወልቃይት እና በራያ የባለቤትነ እና የማንነት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ በእነዚህ አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ? መዘዙስ?
 
የሚሉ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስተን ልንወያይ እና መልስ ልናገኝላቸው የሚገባ ይመስለኛል።     
 
፪/ የፖለቲካ ውጥረት
 
ያዲያቆነ ሴጣን እንዲሉ የአገራችንን ፓለቲካ የተጠናወተው መጠላለፍ፣ ንቁሪያ እና ሸር አሁንም እንደ አዲስ አገርሽቶበታል። በብሔር በተሰባሰቡትም ሆነ በሌላ መልኩ በተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ዛሬም ጤናማ ግንኙነት እንደሌለ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ይህ ወረርሽኝ ወደ ገዢው ፓርቲም መንደር ዘልቆ አባል ድርጅቶቹን እያመሰና አእርስ በርስ ከማናቆር አልፎ በእያንዳንዱ ድርጅትም ውስጥ የመከፋፈል ወረርሽኝ እየተዛመተ ይመስላል። 
 
የተጀመረው ለውጥ ገሸሽ ያደረጋቸው እና መልስ ሳይሰጥ ያለፋቸው አንዳንድ ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮችም አሁን አፈጠው እና አግጠው መምጣት ጀምረዋል። ለውጡን በበላይነት እየመራ ያለው ኦዴፓም ከተለያዩ አቅጣጫዎች’ ሲደግፉት ከነበሩ የኦሮሞ ልሂቃን ሳይቀር ጠንከር ያሉ ነቀፌታዎችን ማስተናገድ ጀምሯል። ኢትዮጵያ ከዛሬ ሁለት አመት በፊት ተሰንቅራበት የነበረውን መስቀለኛ መንገድ በመደመር ፍልስፍና የተሻገረች ቢመስልም ዛሬ ደግሞ ሌላ የገደል አፋፍ ላይ የቆመች መስላለችም። ከጭንቀት አትውጣ ያለው ሕዝብም ዛሬም ይች አገር እንዴት ልትሆን ነው? ምን አደጋ ሊመጣባት ነው? የሚል ስጋት ተጭኖታል። በዚህም ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎች ሊነሱ ቢችሉም ዋና ዋና ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማካሄድ የግድ ይላል። እነዚህም፤
 
+ የዶ/ር አብይ የመደመር ፍልስፍና ለምን መሬት ሊረግጥ እና በሁሉም ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት አልቻለም? ሰርጾስ ከሆነ ለምን ውጤት አላፈራም? ውጤት አፍርቶስ ከሆነ ለምን ዛሬ መልሰን ወደ ሌላ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገባን?
 
+ የመደመሩን ወይም የለውጡን መቀመሪያ ማሽን እኛ ነን የሰራነው እያሉ ሲፎክሩ እና ለውጡ መቼም ሊቀለበስ አይችልም ሲሉ የነበሩ የኦሮሞ ልሂቃን ዛሬ በአደባባይ ለውጡ ተቀልብሷል፣ አብይ አታሎናል፣ ከስልጣን ይልቀቅ የሚሉ ነቀፌታዎችን ለመሰንዘር ምን አፈጠናቸው?
 
+ ዶ/ር አብይ አገሪቱን እየመሩ ነው ወይስ እያስታመሟት? እርግጥ ነው እጅግ የታወከች እና ፖለቲካዋም እጅግ የታመመ አገር ነው ያለችን። የእሳቸው ድርሻ የሃኪም፣ የአስታማሚ፣ የጠያቂ ወይስ አብሮ የመታመም? ክልሎችን በሙሉ አቅም እያስተዳደሩ ነው ወይ? ትግራይ ላይ ሥልጣን አላቸው ወይ? ለሥልጣን ባበቃቸው የኦሮሚያ ክልል ውስጥ ምን ያህል ተሰሚነት አላቸው? ነገ ጠዋት ኦዴፓ ከሊቀመንበርነት፣ ከኦሮሚያ ክልልም ከፕሬዝደንትነት እና ከተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ቢያነሳቸው ጠቅላይ ሚንስትርነታቸው አደጋ ላይ አይወድቅም ወይ? ይህ ልጓም በእጁ የገባው ኦዴፓ እና የኦሮሚያ ክልል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እና ውሳኔ ላይ ጫና የመፍጠር እድል የለውም ወይ? ለዚያስ ይሆን ወይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል ባሉ አክራሪ ብሔረተኞች ላይ ክርናቸው ውኃ የሆነው?
 
+ በደቡብ ክልል የተነሳውን የክልል ጥያቄ በሲዳማ ላይ ብቻ እንዲያበቃ ማድረግ ይቻላል ወይ? የሲዳማን መልሶ የሌሎቹን በይደር ለማቆየት የሚቻልበት እድል አለ ወይ? የሲዳማ ክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ በአዋሳ ከተማ ባለቤትነት ላይ የተነሳውን ጥያቄ ምን መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ተጠንቷል ወይ? በሲዳማ ሪፈረንደም የሲዳማ ተወላጅ ያልሆኑ ነገር ግን የዞኑ ነዋሪዎች የሆኑ በምርጫው የመሳተፍ መብት በምን መልኩ ይስተናገዳል?
 
+ የኢህአዴግ ወደ ውህድ ሕብረ ብሔረ ድርጅት የመለወጥ ሂደት በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ይሳካለታል ወይስ ፓርቲው ሁለት ይሰነጠቃል? 
 
   
፫/ በተረኝነት እና በተገፊነት ዙሪያ
 
ኦዴፓ መራሽ የሆነው የለውጥ ኃይል ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጥቂት ወራት ጀምሮ በተለያዩ ወገኖች የተረኝነት ነገር ጎልቶ ይታያል እየተባለ በአደባባይ ጭምር ሲነገር እና ቅሬታ ሲቀርብ እየሰማን ነው። እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ የተረኝነት መገለጫዎቹ ምንድን ናቸው የሚል ነው። ተረኛ ማለት ከፊተኛው እና ካለፈው የተከተለ ወይም በሄደው ሥርዓት እግር የተተካ ማለት ነው። ሕውሃት መራሽ የነበረው የአገዛዝ ዘመን አግላይነት የነገሰብት፣ በጥቅም መሳሳብ ጎልቶ የታየበት፣ የመንግስትን እና የፓርቲን መዋቅር ተጠቅሞ ሥልጣን፣ ሃብት፣ መሬት እና ገንዘብ በአንድ አካባቢ ተወላጅ ልሂቃን እጅ እንዲገባ የማድረግ ሥራዎች በአደባባይ እና አይን ባወጣ ሁኔታ የተካሄዱበት ወቅት ነው። የትግራይ ልሂቃን (ሕዝብ አላልኩም) ከሕግ እና ሥርዓት አፈንግጠው መረን የለቀቁበት አስከፊ ዘመን ነበር። ዜጎች በየማጎሪያው ተጥለው ግፍ ሲፈጸምባቸው እና በየመንግስዱ ሲገደሉ የቆዩበት ጨለማ ዘመን። እንግዲህ ዛሬ ተረኝነት አለ ከተባለ፤ ኦዴፓ ስለሆነ የዛሬው ተረኛው ከዚህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ የግድ ይላል፤
 
+  ለኦሮሞ ተወላጆች ብቻ የሚደረግ እና ሌላውን ሕዝብ የሚያገል ተግባር በመንግስት ደረጃ ተፈጽሟል ወይ?  ከተፈጸመስ ምን ምን? 
 
+ የኦሮሞ ተወላጆች በሌሎች ሰዎች እየተተኩ እና ሌላው እየተገለለ ሥልጣን እንዲይዝ ተደርጎ ከሆነ የት?  መቼ እና ማን በማን እንዲተካ ተደረገ?  የኦሮሞ ሕዝብ ካላው የሕዝብ ቁጥር ስፋት በላይ የማይገባውን የመንግስት ስልጣን ድርሻ ከቀበሌ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለው የሥልጣን እርከን ተቆጣጥሮ ከሆነ በቁጥር እና መዝርዝርም ማስረዳት ይቻላል ወይ? 
 
+ ኦዴፓ ለውጡን በያዘበት ጊዜ ውስጥ ምን ያህል የመንግስት ሹም ሽር ተካሄዱ?  እነማን ተገልለው እነማን ተተኩ?  በምን መስፈርት?  የአገሪቱን ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች ከያዙት ሰዎች ውስጥ የብሔር ስብጥሩ ምን ያህል ፍትሃዊ ነው?  በሚንስትር መስሪያ ቤቶች ውስጥ በተደረገ የሥልጣን ድልድልስ ውስጥ ፍትሃዊነቱ ምን ያህል ተንጸባርቋል? 
 
+ ሌሎች የተረኝነት መገለጫ የሆኑ የመሬት ክፍፍል፣ የቤቶች ክፍፍል፣ የአገልግሎt አቅርቦት እና የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ላይ የታዩ አድልዎች አሉ ወይ? 
 
+ በግለሰቦች ውስጥ ጊዜው የኛ ነው የሚል ስሜት ሊፈጠር ይችላል። ዋናው አደጋ ተቋማዊ ድጋፊ ሲያገኝ ነው። የተረኝነቱ ስሜት ሌሎችን በሚያገል እና በሚጎዳ መልኩ እየተተገበረ ለመሆኑ በማስረጃ የተደገፈ ነገር ማቅረብ ይቻላል ወይ? 
 
መገፋትን በተመለከተ በማንነቱ ምክንያት ብዙ ሰው ለጥቃት ሲጋለጥ ማየት ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ ሆኗል። ይህ ችግር በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ታይቷል ማለት ይቻላል። የትግራይ ተወላጆች በአማራና በደቡብ ክልሎች ውስጥ ተገፍተዋል። የአማራ ተወላጆች በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል፣ በትግራይ እና በደቡብ አንዳንድ ቦታዎች ተገፍተዋል። የኦሮሞ ተወላጆች በአማራ፣ በቤኒሻንጉል እና በሶማሌ ክልል ተገፍተዋል። በደቡብ ክልልም አንዱ ሌላውን ገፍቷል፤ ተገፍቷል። ተከፊው አስከፊ፤ አስከፊውም ተከፊ የሆነባቸው ብዙ ምስቅልቅሎች አስተናግደናል። 
 
+ ከዚህ የመገፋፋት እና አንዱ ሌላውን ሆድ የሚያስብስበት የግጭት አዙሪት እንዴት ልንወጣ እንችላለን? እንዲህ ያሉ የብሶት ትርክቶች የቀጣዩን ምርጫ ሂደት ሊያዛቡ ወይም ሊያደናቅፉ አይችሉም ወይ? 
 
እስቲ በእነዚህ እና እናንነም በምታነሱዋቸው ጥያቄዎች ዙሪያ እንወያይ። ውይይቱ አንዳችን ሌላችንን ጥላሸት ለመቀባት ወይም ለመዝለፍ ሳይሆን እንደ አገር ከገባንበት ቅርቃር ለመውጣት መንገድ ያመላክቱን እንደሆን ለመፈተሽ ነው። ከሃሳብ ውጪ ዝልፊያና ስድቦች በዚህ ውይይት አይስተናገዱም።
 
ማንኛውንም በአመክንዮ የተደገፈ ሃሳብ፣ ጥያቄ፣ መልስ እና አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።
 
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic