>
11:16 pm - Wednesday November 30, 2022

የኦሮሞ ድርጅቶች ስምምነት ከልብ ወይስ በየወንዙ መማማል? (ያሬድ ሀይለማርያም)

የኦሮሞ ድርጅቶች ስምምነት ከልብ ወይስ በየወንዙ መማማል?
ያሬድ ሀይለማርያም
የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ አላውቅም ዛሬም አብሮ ለመስራት የተፈራረሙ መሆኑን በዜና ተገልጿል። እሰየው ነው። ኦሮሚያ ክልል በሰላም እጦት እና በሕግ የበላይነት መታጣት ከሚታመሱት የአገሪቱ ክፍሎች መካከል አንዱ ነው። በመሆኑም በዚህ ክልል ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ለመፍታት ከቻሉ የሚደገፍ ነገር ነው።
እንኳን የፖለቲካ ድርጅቶች ይቅርና የግለሰቦችም መስማማት ለአንድ አገር ሰላም እና ጤናማ ፖለቲካ ወሳኝ ነው። ትልቁ ጥያቄ የተስማሙበት ፍሬ ጉዳይ፣ በስምምነቱ መጽናት መቻል እና በተስማሙበት ልክ አብሮ መስራትና ለፊርማቸው ተገዢ መሆን ነው። በዚህ አጭር የለውጥ ጊዜ ውስጥ የኦሮሞ ድርጅቶች ስምምነት ተፈራረሙ እየተባላ ባለሥልጣናቱ እጅ ለእጅ እየተያያዙና ፎቶ እየተነሱ የዜና እወጃ ፍጆታን ሲያሟሉ አይተናል። ሰበር የስምምነት ዜና ባወጁ ማግስት በአደባባይ ሲወነጃጀሉ እና ገመድ ሲጓተቱ ማየትም የተለመደ ሆኗል። የአሁኑን ስምምነት የሚለየው የጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል መገኘት ይመስለኛል። ስምምነቱ እንደማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ የመማማል ነገር? ወይስ ከልብ የመነጨ?
በስምምነታቸው ውስጥ እነዚህን ነገሮች አካተዋል ብለን ተስፋ እናድርግ?
+ በክልሉ ውስጥ የሚታየውን አስከፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆም፤
+ በክልሉ ውስጥ ኢ መደበኛ በሆኑ ቡድኖች እየተፈጸሙ ያሉ የደቦ እና ሕገ ወጥ እርምጃዎችን ለማስቆም፣
+ በክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጅ ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎች እና መፈናቀሎችን ለማስቆምም
+ ሁሉም ከሕግ በታች ሆነው የተጀመረው ለውጥ ከሌሎች የአገሪቱ ባለድርሻ አካላት ጋር ሆነው እንዲሳካ ማድረግ እና
+ በክልሉ ውስጥ ሌሎች የተቃዋሚ ድርጅቶች ከእነሱ እኩል ተንቀሳቅሰው ለምርጫ እዝቡን የማንቃት፣ የማደራጀት እና ጽ/ቤቶቻቸውን ከፍተው የመንገሳቀስ መብታችውን ማክበር እና እንዲከበር ማድረግን ይጨምራል ብለን እናስባለን።
እንዲህ ከሆነ ከዚህ በጎ ሂደት ሌሎችም ክልሎች ልምድ ቀስመው ተመሳሳይ ስምምነት በየክልሎቻቸው ካሉ ኃይሎች ጋር ቢያደርጉ ምርጫው መቼ ይካሄድ መንገዱን ግን ከወዲህ ቀና እንዲሆን ያደርገዋል።
የኦሮሞ ፓርቲዎች አብረው ለመስራት ተስማምተዋል። ይህ በራሱ ክፋቱ አይታየኝም።አስተሳሰብ ካልተቀየረ በየወንዙ መፈራረሙ ብቻውንም የሚፈይደው ነገር ያለ አይመስለኝም።
በነገራችን ላይ   ከእነዚህ ፈራሚ የኦሮሞ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ኦዴፓ ከኢህአዴግ አባል እና አጋር ፓርቲዎች ጋር ሊዋሃድ እየተደገሰ ነው።ውህደት ሲደረግ ደግሞ ክስመት ይኖራል።
 ክስመቱ እና ውህደቱ ደግሞ በጣም በቅርቡ እንደሚደረግ ጠ/ሚ አብይ ከወ/ሮ መዓዛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል። የዛሬው ፍረማ ታዲያ ከውህደቱ በሃላ ምን ፋይዳ እና ህልውና ሊኖረው ነው? –
በተመሳሳይ በሰላም እጦት የሚታመሰው እና ከፍተኛ የመብት ጥሰት እየተፈጸመበት ያለው የአማራ ክልልም ይህን አይነት ስምምነት ከአብን እና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ቢያደርግ ውጥረቱን ለማብረድ ይቻላል።
የኦሮሞ ፓርቲዎች ቃላችውን የምታከብሩ እና ስምምነታችውም ለአገር የሚበጅ እንዲሆን መልካም ምኞቴ ነው።
Filed in: Amharic