>
6:34 pm - Thursday September 16, 2021

የአዲስ አበባው በአል ተጠናቋል.. ከታዘብናቸው ነገሮች በጥቂቱ ... (ኢያስፔድ ተስፋዬ)

የአዲስ አበባው በአል ተጠናቋል.. ከታዘብናቸው ነገሮች በጥቂቱ …
ኢያስፔድ ተስፋዬ
1- ለአደባባዩ እጅግ በጣም ሩቅ የሆኑ ሰፈሮች እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መዘጋት አላስፈላጊ ነበር- ለምሳሌ እኔ ከገርጂ አንበሳ ጋራዥ አካባቢ ጀምሮ መኪና ማለፍ ተከልክሎ ስለነበር በእግሬ ወደ በአሉ ለመሄድ ተገድጃለሁ….አብዮት አደባባይ ለሚከበር በአል ገርጂ ጋር መንገድ መዝጋት ያውም ከጥዋቱ 12 ሰአት ጀምሮ በምንም መመዘኛ አግባብ አይደለም…ቢሾፍቱ ለሚከበር በአል ሳሪስ ላይ መንገድ እንደ መዝጋት ያህል ነው ርቀቱ….ለበአሉ የተቀላጠፈ አከባበርም የሚሰጠው ጥቅም አይታየኝም።
2- በየ 100 ሜትሩ ከአብዮት አደባባይ እጅግ በሚርቁ ሰፈሮች የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሳይቀር ፍተሻ ሲያካሂዱ የነበሩ ፎሌዎችም ስራ አስፈላጊነቱ አልታየኝም። አንደኛ ወደ ስራ ቦታ የሚሄዱ ሰዎችን (ለምሳሌ ከመገናኛ ወደ ቦሌ) ሄድፎን ነሽ፣ ቻርጀር ነሽ… ቀምተው ይዛችሁ መሄድ አትችሉም በሚል በየቦታው የፈጠሩት እሰጥአገባ ልክ አይደለም። በዚያ ላይ በቋንቋም ተግባብተው ማስረዳት አልቻሉም…ሁለተኛ ቢያንስ ለአንድ ቀን እንኳን የሚያገለግል ጊዜያዊ መታወቂያ ቢሰጣቸው ጥሩ ነበር…. አብዛኛው ፈታሽ ምንም የሚያሳየው መታወቂያ ያልያዘ እና ቴረራይዝ የሚያደርግ ነበር። ለምሳሌ ዝለሉ ብሎ ፍተሻ ምንድነው? አሮጊት የለ ሽማግሌ ወደ ላይ ዝለሉ እያሉ ማዘለል እና ሌላም ሌላም በፍፁም ተገቢ አልነበረም።  ይሄ ሰዎች በአሉን በመጥፎ እንዲያዩት የሚያደርግ ስለሆነ በሚቀጥለው መስተካከል አለበት።
3- ከተለያዩ የኦሮምያ አካባቢ የመጡ አዛውንቶች፣ ሴቶች እና ወጣቶች የሚያድሩበት አጥተው ጎዳና ላይ ተኝተው ሲያድሩ ማየት በጣም የሚያሳዝን ነበር….በሚቀጥለው ቢያንስ የከተማ አስተዳደሩ ጊዜያዊ ዳስ መጣል ቢችል ጥሩ ነው።
4– የከተማ መስተዳድሩ ህዝባዊ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ያለባቸውን ሱቆች ምግብ ቤቶች ወዘተ በስራ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት- አንደኛ ከተማዋ እና ነጋዴዎቿ ትልቅ ገቢ የሚያገኙበት ቀን ነው። ሁለተኛ የበአሉ ታዳሚ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ መንከራተት የለበትም።….በእርግጥ ለአብዛኞቹ ሱቆች እና ምግብ ቤቶች መዘጋት የመንገድ መዘጋት በራሱ ያለው ተፅእኖ ሳይዘነጋ።
5- በእንዲህ ያለ ዝግጅት ላይ ከመድረክ በተለይም ከባለስልጣኖች የሚነገሩ ንግግሮች ፀብ አጫሪ መሆን ቀርቶ በፍፁም ለፖለቲከኞች እንኳን አጀንዳ ሰጥቶ የሚያልፍ መሆን የለበትም…ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሻዋል።
6- መንግስት መከልከል የማይችለውን ነገር በፍፁም መከልከል እንደሌለበት ከዚህ በአል ልምድ ይውሰድ። የኦነግን አርማ ለመቀማት ባደረገው ጥረት ከበአሉ ታዳሚ ጋር ሲጋጭ – ጨርሶውኑ መከልከል ባለመቻሉ ደግሞ ለእኛ ጊዜ ሲሆን ከልክሎ ለእነሱ ፈቀደ ከሚለው ማህበረሰብ ቂምን አትርፏል። በሁለቱም በኩል ኪሳራ ነበር። ይኸው ነው።
Filed in: Amharic