>
9:19 am - Saturday December 10, 2022

ፑሽክን ያዝንብሃል! (ደረጄ ደስታ)

ፑሽክን ያዝንብሃል!
ደረጄ ደስታ
*  የፑሽክን አያት አብርሃም ሃኒባል በራሽያ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነበር። አባት እናቱን ያልተቀበልክ አያቱን እንዴት አሰብክ? አንተማ አማራ ነህ፣ አንተማ ጋሞ ነህ እያልክ ከወዲህ ወዲያ እምታላጋኝ ወገኔ ሆይ፣ እኔን እያሳደድክ የሩቁ ፑሽክን ምን ያደርግልሃል!!!
ወዳጄ ሆይ ወንድምና እህት አይገዳደልብህ፣ ደምህ የደምህ መላሽ ሆኖ ለበቀል አይነሳሳብህ፣ እንደኔ ደምህ ከደምህ ያልጠራ እንደ ሀበሻ ድብልቅ አድርጎ አይፍጠርህ። ባለ ንጽሁ ደም ነኝ! የጠራሁ የዚህ የዚያ ወገን ነኝ ብለህ፣ ለይተህና ተለይተህ በተጀነንክ ዘመኑን በዘፈንክ ወዲህኛውን በወዲያኛው ባራገብክ ነበር። የዚህ ብሔር የዚያ ብሔር ተወላጅ ነኝ ከማለት ሀበሻ መሆን ወይም እንደ ኢትዮጵያዊ ዥጉርጉር መሆን ከባድ ፍርጃ ነው። ኢትዮጵያዊ ቅይጥነትና ዲቃላነት መጥፎ ነገር ከሆነ፣ እንዲህ ሊገዳደሉ ከሚዛዛቱ፣ ከሚናናቁና ከሚጠላሉ “ደመ ንጹህ” ወገኖች መወለድ እንዴት እንደሚያኮራ ማሰቡም ያሳስባል። ግን ስጋ ናቸውና ሞትና እንግልታቸው ያማል፣ አጥንትነታቸው ካጥንት ዘልቆ ይሰማል። አባቱና እናቱ ሲገዳደሉበት ማን ደስ ይለዋል?
ጎበዝ ከትግሬና አማራ ወይም ከኦሮሞና አማራ ወይም ከጉራጌና ዶርዜ የመወለድ ኢትዮጵያዊነት ሎጂክና ፖለቲካ አይደለም- ለበርካቶች ነፍስና ሥጋ ያለበት እውነት ነው። እናንት ጎሰኞች፣ እናንት ግራና ቀኞች፣ ከናንተ መወለድ ምርጫችን ባልሆነ ነበር። ግን ተወልደናል። ግማሽ ግማሽነታችሁን ይዘናል። እኛ በሥጋ ግማሽ ነን እናንተ ደግሞ በመንፈስና በነፍስ እንዲሁ ግማሽ ሆናችኋልና ሙሉ ሰው ሁኑ። አገር ሙሉ ትሁን! ፑሽክን በአያቱ እያልክ ጠብታ ደም እየቆጠርክ እምታሰላ ግብዝ ሆይ! ምኒልክ ደስ ሲልህ በናቱ እየተዛመድክ፣ ሲከፋህ ደግሞ በአባቱ እያወገዝክ፣ አይሁድ ነኝ ብለህ ከሰሎሞን የተዛመድክ፣ መልሰህ አፈር ልሰህ ደግሞ ምንትሱ ኢትዮጵያዊ ምንትሱ የመናዊ ማለቱን የተያያዝክ አገር ሆይ፣ “የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው?” ማለቱ ይብቃህ። ካመጣኸውማ ለዛሬው የአክሱምስ ሰው ቢሆን የአክሱም ሐውልት ምኑ ነው? ባህር ተሻግሮ የገዛው ቀበሌ ከልሎ ከሚገዛው ምኑ ይዛመዳል? የጥበቡ ላሊበላ ህንጻስ ፈንጠር ብሎ ላለው የዛሬው ጎጆ ቤት ምኑ ነው? ጠላት አስገብሮ አገር ባስገበረው ቴዎድሮስ እየኮራ ሱዳን ስለቆረሰችው መሬት እሚያለቃቅሰውስ ምን ይባላል? የዛሬው ገጀራና ቆንጨራ የገዳው ሲስተም አርማና ባንዲራ የሆነውስ ከመቸ ጊዜ ጀምሮ ነው?
ደግሞ በታዋቂው የሩሲያ ጸሐፊ ስም ሐውልት አቁመሃል፣ የአሌክዛንደር ፑሽክን ጎዳና የሚል መንገድ ሰይመሃል። ምክንያቱም የፑሽክን አያት አብርሃም ሃኒባል በራሽያ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነበር። አባት እናቱን ያልተቀበልክ አያቱን እንዴት አሰብክ? አንተማ አማራ ነህ፣ አንተማ ጋሞ ነህ እያልክ ከወዲህ ወዲያ እምታላጋኝ ወገኔ ሆይ፣ እኔን እያሳደድክ የሩቁ ፑሽክን ምን ያደርግልሃል? ቅይጡ ፑሽክንም እንደኔው ያዝንብሃል።
Filed in: Amharic