>

«ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት!!!" (አቻምየለህ ታምሩ)

«ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት!!!”
አቻምየለህ ታምሩ
አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ «የጋራ ታሪክ አለን ወይስ የለንም» በሚል ርዕስ  ከሰሞኑ «ፖለቲከኞቻችን»  ያከራከረበትን አንድ  ፕሮግራም እየተከታተልሁ ነበር። የጋራ ታሪክ አለን የሚል አንጓ ይዞ የሚከራከረው ፖለቲከኛ  ጭብጡን ለማስረዳት ኦሮሞ በኢትዮጵያ ታሪክና  ስነ ጥበብ ጭምር አስተዋጽዖ  ያለውን አስተዋጽዖ በመጥቀስ በምሳሌነት  የኢትዮጵያ ዘፋኞችን ንጉሥ የሆነው  ጥላሁን ገሠሠ ኦሮሞ በመሆኑ ታሪክ የሆነው ጥላሁን ና ሥራዎቹ የጋራ ታሪካችን አካል  እንደሆነ ለማብራራት ሞክሮ ነበር።
በዚህ ማብራሪያ ያልተደሰተው አንዱ ኦነጋውያን ጭንቅላቱን  ያበላሹት የኦሮሞ ብሔርተኛ  ሲባል የሰማውን ሳይመረምር  በመድገም «ጋላ እየተባለን ስንጠራ በኖርንበት አገር የጋራ ታሪክ የለንም፤ የዘፋኞችን ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠን ጋላ እያለች ትጠራ በነበረ አገር ውስጥም  የጋራ  ታሪክ የለንም» ሲል አለማወቁን አሳውቆናል።
«የዘፋኞችን ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠን  ጋላ እያለች ትጠራ በነበረ አገር ውስጥ የጋራ  ታሪክ የለንም» የሚለው የኦሮሞ ብሔርተኛ ጋላ የሚለው ቃል ኦሮምኛ እንደሆነ፣ ጥላሁን ገሠሠም በ1950ዎቹ  «አትክልትና ፍሬ» በሚል  የኢትዮጵያን የምግብ አይነቶች ለማስተዋወቅ ባወጣው ዘፈኑ ውስጥ የኦሮሞን ምግብ ሲያስተዋውቅ  «የጋላ ላም ወተት» እያለ እንደዘፈነ ሲባል የሰማውን ተቀብሎ መድገምን እንጂ  መመርመርን  ባሕሪው ስላላደረገ አያውቅም።
ዛሬ በኦነጋውያን ዘንድ  ስድብ የተደረገው «ጋላ»  የሚለው ስም በጥላሁን ዘመን ስድብ አልነበረም። «ጋላ እያላችሁ ትሰድቡን ነበር» የሚለው የኦሮሞ ብሔርተኛ ኦሮሞ ያደረገው ጥላሁን ገሠሠም «አትክልትና ፍሬ» በሚለው ዘፈኑ  «የጋላ ላም ወተት» እያለ የዘፈነው «ጋላ» ስም እንጂ የስድብ ቃል እንዳልነበረ አያውቅም። ለኦሮሞው ጥላሁን ጋላ የሚለው ስም ስድብ ቢሆን ኖሮ ራሱን በዘፈን ሊሰድብ «አትክልትና ፍሬ» በሚለው የኢትዮጵያን የምግብ አይነቶች ባስተዋወቀበት ዘፈኑ «የጋላ ላም ወተት» እያለ አይዘፍንም ነበር። ገራሚው ነገር የዚህ ዘፈን ዜማና ግጥም ደራሲውም ኦሮሞው በኃይሉ እሸቴ መሆኑ ነው።
ስለዚህ ሳትመረምር ሀሳብ የሌለበትን የኦነግ የፈጠራ ወሬ ይዘህ «ጋላ እየተባለን ስንጠራ በኖርንበት አገር የጋራ ታሪክ የለንም፤ የዘፋኞችን ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠን  ጋላ እያለች ትጠራ በነበረ አገር ውስጥ የጋራ  ታሪክ የለንም» እያልህ አማራን ስትወነጅል የምትውለው የኦሮሞ ብሔርተኛ  «ከመጠምጠም መማር ይቅደም» ፤ «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር ልንለግስህ እንደወዳለን!
Filed in: Amharic