>
6:42 pm - Sunday July 3, 2022

በጠ/ሚ ዓብይ በኩል ተሟጣ ያላለቀችው ተስፋችን !!! (ሳምሶም ጌታቸው)

በጠ/ሚ ዓብይ በኩል ተሟጣ ያላለቀችው ተስፋችን !!!
ሳምሶም ጌታቸው
ጠ/ሚ ዓብይ ያ ሁሉ ሕዝብ ሲገደል፣ ሲፈናቀል፣ ሲሳደድ ይኼ ነው የሚባል መግለጫ እንኳ መስጠት ሲያቅታቸው አይተናል። በዚህም የተነሳ ብዙ ሰው የየራሱን ምክንያቶች ሲሰነዝር ይሰማል። ግምቶቹን በሁለት ማስቀመጥ ይቻላል። አንደኛው ሰውዬው የድርጅታቸው መዋቅር በአክራሪዎቹ ሙሉ ለሙሉ ተጠልፎባቸዋል የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጠ/ሚሩ የአጥፊዎቹና የሀገር አፍራሾቹ ተባባሪ በመሆናቸው ነው የሚል ነው። በይበልጥ ሁለተኛው ግምት ጎልቶ ሲነገር ይደመጣል።
መቼም እየሆነ ያለው ነገር ቅስም የሚሰብር ቢሆንም፣ በጣም በብዙ ምክንያቶች ጠ/ሚሩ የአጥፊዎቹ ተባባሪ ይሆናሉ ብሎ ለመደምደም ይከብዳል። ምክንያቱም አንድ ፖለቲከኛ በሕይወት ዘመኑ የመጨረሻው ግቡ ጥቂቶች ብቻ የሚሳካላቸውን የፖለቲካ ስልጣን መያዝ ነው። ጠ/ሚ ዓብይ ደግሞ ያንን ስኬት ያውም የመጨረሻውን የሀገሪቱን ስልጣን በመጨበጥ አሳክተውታል። ስለዚህ እንደ ፖለቲከኛ የያዙትን ማጥበቅ እንጂ ይሄ ቀረኝ ብለው የሚያጓጓቸው ነገር አይኖርም።
ደግሞም የተቆናጠጡት ስልጣንም በሕይወት ዘመናቸው ሊያገኙት የሚችሉትን የመጨረሻውን ስኬት ሁሉ እያጎናፀፋቸው እንደሆነ መመልከት ይቻላል። እጅግ ትልቅ እና ተዝቆ የማያልቅ ስኬቶችንም ገና ማስመዝገብ የሚችሉበት ዕድልም በእጃቸው መግባቱ የሚያጠራጥር አይሆንም። ስለዚህ ዓብይ አህመድ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ቢያብሩ ሊያገኙ የሚችሉት “ጥቅም” ሀገራቸውን በመሪነት በማገልገላቸው ከሚያገኙት ስኬት አንፃር በቁጥር ሊለካም ሆነ ሊመዝን የሚችል አይደለም።
ስለዚህ ጠ/ሚ ዓብይ የአክራሪዎቹ ተባባሪ ናቸው ብሎ ሙሉ ለሙሉ መደምደም ውሃ የሚያነሳ ግምት አይሆንም። በመሆኑም ዋነኛው አቅመቢስ ያስመሰላቸው እና የእነ ጃ-war መፈንጫ ያደረጋቸው የመዋቅር መጠለፍ የመሆን ዕድሉ ያመዝናል ማለት ነው። ስለዚህ የተተበተበውን መዋቅር በጉልበት ከማፅዳት ይልቅ በዘዴ ማላቀቅን መርጠው ነው የሚለው የደጋፊዎቻቸውን ዕምነት መጋራት አያስከፋም።
በዕውነትም ያ ሁሉ መከራና ሰቆቃ ሲከሰት በመጣበት መልስ ይሰጠው ቢባል፤ ወታደር እስከመከፋፈል የደረሰ ውጤት ሊያመጣና የሀገር መፈረካከስን ሊያስከትል ይችልም ይሆናል።  ይሄን ግምት ስህተት ነው ማለት አይቻልም። ስለዚህ የዓብይ አካኼድ ሀገርን ለማፍረስ ሳይሆን ሀገርን ለመታደግ ነው የሚለው ግምት ነፍሱ አለች ማለት ነው። ያድርግልን።
ይህ ከሆነ ደግሞ የሰሞኑ ውህደት #ብዙ ስጋቶችን ያረገዘውን ያህል፣ ሰውዬው ለሀገሬ አለኝ ያሉት ቀናዒነት አሁንም አብሯቸው ከሆነ፣ በጣም ትልቅ ሀገራዊ ስኬትንም ሊያመጣ ይችላል። በሀገር ተስፋ ቆርጦ መቁረጥ አይቻልምና ከተከመረው የውድቀት ገለባ ውስጥ ምናልባት የቀረች የተስፋ ፍሬ እናገኝ እንደሆን ብለን ገለባውን ደጋግመን እናበጥራለን። ታዲያ ሰው ሀገሩን አኩርፎ፣ ተስፋውን ተበልቶ መኖር እንዴት ይቻለዋል?
Filed in: Amharic