>
2:46 am - Tuesday May 24, 2022

እውነት ከእርሱ ዘንድ ነችና አካሄዴን ከእስክንድር ጋ አደረግኹ!!! (ሄኖክ የሺጥላ)

እውነት ከእርሱ ዘንድ ነችና አካሄዴን ከእስክንድር ጋ አደረግኹ!!!

ሄኖክ የሺጥላ
አዲሱን ወይን ባሮጌ አቁማዳ ማስቀመጥን ስለማልሻ፣ የወይኔንም ክብር ላለመንካት ስል፣ በደከመ አቁማዳም ስለማልታመን ፣ አካሄዴን ከእስክንድር ጋ አደረግኹ። ጠላቶች ይፈሩታል፣ ተመርጧልና አያሸንፉትም። ተሰጥቶታል እና አይቀሙትም። እውነት የሱ ነችና በትሩም የጭቆና ባህርን ትከፍላለች። ብዙዎችን ያድን ዘንድ የተመረጠ ነውና አመጣጡም እስከ ዘመናት ይዘልቃል። በስባሪ እውነት ተራራ የሚገፉትን እንደ አመዳይ ያጠፋቸዋል። በተንኮል የቆሙት ከፊቱ አቅምን ይነጥፋሉ። የክህደት አምላኪዎች እንደ ጠዋት ጤዛ ይተናሉ።
እርሱ የሚታመንበት አምላኩ እና የሚወደው ህዝብ ጠሎት የትግሉ አናት ያደርገዋል። ከገጀራ እና ከቄሮ ሊታደጋቸው የቆመላቸው ህጻናት መንፈስ እንደ ጥላ ይከልለዋል። ልበ ብርሃን ነውና ፣ ሃይሉ በግፈኞች አይቆምም። መንፈሱ ለግፍ አይንበረከክም። ደቂቆቹ ሰላምን ፈላጊዎች ፣ ከመብታቸው በላይ መብት የማይጠይቁ ኢትዮጵያዊያኖች ናቸው። በዘር እና በምንጅላት የተቀነበበ ልበ ስውር አይዶለም። ደሙን አንጥሮ፣
የመጣበትን ሃረግ ቆጥሮ ፣ ለዚህ ዘር ይህ ይገባዋል ፣ ለዚህኛው ደሞ ይህ አይገባውም አላለም። አይልምም። እርሱ ዘርን ለዕህል ብቻ ነው የሚያውቀው። እትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ዘሩ ነው። እርሱ የአለም ሰው እንጂ አለማዊ አይዶለም። እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። ( ወፈርሀ ሳኦል እምቅድመ ገጹ ለዳዊት ።)
Filed in: Amharic