>

ከ100 አመት በፊት "አምጣ" ብለው ሳይሆን "እንካ" የተባሉትን የ50ሺ ብር ጉቦ የተጠየፉ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተ/ማርያም (ሲሳይ ተፈራ)

ከ100 አመት በፊት “አምጣ” ብለው ሳይሆን “እንካ” የተባሉትን የ50ሺ ብር ጉቦ የተጠየፉት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተ/ማርያም

ሲሳይ ተፈራ መኮንን
.
ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ አስጠርተውኝ፣ ሙሴ ሳቡሬ የሸጠልን የመስኮብ ጠመንጃና 40 ሚሊዮን ጥይት ድሬደዋ ስለደረሰ ወደ ድሬደዋ ወርጄ ርክክብ እንድፈጽም ጠየቁኝ፡፡ ልጅ ኢያሱ ግን ለዚህ ጉዳይ እኔ እንደማላስፈልግ በመግለጽ ሌላ ሰው እንዲሄድ ቢያዙም ከተማርኩባት ሩሲያ የመጡትን መሳሪያዎቹ ለመመርመር የኔ መሄድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጬ በማሳመን ወደ ድሬደዋ እንድሄድ ፈቀዱልኝ፡፡
.
ወደ ድሬደዋ ደርሼ ሆቴል እንዳረፍኩ ማካልዲስ የሚባል የግሪክ ሰው የሙሴ ሳቡሬ ወኪል ነኝ በማለት ወዳረፍኩበት ሆቴል መጣ፡፡ ነገ ጠዋት መሳሪያዎቹን እያወረድን መመርመር እንጀምራለን፣ ጧት ጉምሩክ እንድትመጣ ብዬው ተለያየን፡፡ ይኸው ሰው በድጋሚ ማታ ወዳረፍኩበት ሆቴል በመምጣት ልክ ብዙ ዘመን እንደሚያውቀኝ በወዳጅነት አይነት ያነጋግረኝ ጀመር፡፡ በመጨረሻም ወጪ ይበዛብዎታል በማለት ሙሴ ሳቡሬ 50ሺ ብር እርዳታ ስጥ ብለውኛል በማለት ገንዘቡን ሊሰጠኝ ሞከረ፡፡ በከንቱ አትድከም፣ ምንም አያስፈልግም፣ ይልቅስ ነገ ጥዋት እንድትመጣና ስራችንን እንድንሰራ ብዬ አሰናበትኩት፡፡
.
በነጋታው በቀጠሯችን መሰረት ለናሙና 1 ሳጥን ጠመንጃና 10 ሳጥን ያህል ጥይቶችን አስከፍቼ መመርመር ጀመርኩ፡፡ ጠመንጆቹ ዝገዋል፣ በብርጭቆ ወረቀት እየተፈገፈጉም ተቀብተዋል፡፡ ጥይቶቹም ተበላሽዋል፣ ቀለሆቹ ተቦርቡረው ና ተጎድተው አረሮቹና ቀለሆቹ ተለያይተዋል፣ ባሩዱም ከቀለሆቹ ውስጥ እየተዘረገፈ በስብሶ ነጥቶ ጨው መስሏል፡፡ ይህንኑ ባሩድ በእሳት እያቃጠልኩ ስመረምረው መቃጠል አይችልም፡፡ እንደዚሁ ከየረድፉ አምስት አምስት ሳጥኖች እያስከፈትኩ በየቀኑ ከመረመርኩ በኋላ የምርመራዬን ውጤት ለሳቡሬ ወኪል አሳየሁት፡፡
.
 ለፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስም ጠመንጆቹ ዝገው የተጠረጉ አሮጌ ጠመንጆች እንጂ አዲስ አለመሆናቸውን፣ ጥይቶቹም ሁሉም የጠበላሹና ጥቅም የማይሰጡ መሆናቸውን በመዘርዘር መሳሪያዎቹን እንደማልረከብ በሪኮማንዴ ሪፖርት ጽፌ ላኩላቸው፡፡ ከ100 አመት በፊት 50ሺ ብር የነበረው የመግዛት አቅም ዛሬ ምን ያህል ይሆን? 5ሚሊዮን? 50 ሚሊዮን? እስኪ የስነ ምጣኔ ባለሙያዎች አስረዱን
.
የሕይወቴ ታሪክ፣ ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት
Filed in: Amharic