>
3:43 am - Tuesday May 24, 2022

ዞምቢዎቹ!!! (ቴዎድሮስ መብራቱ)

ዞምቢዎቹ!!!

 

ቴዎድሮስ መብራቱ
ስለ ዞምቢዎች ተጽፎ ያነበብኩት የ፭ኛ ዓመት የሕግ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነው። 2005 ዓ.ም። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ በ “ልዕልና” ጋዜጣ ላይ። እነሆ ከ፯ ዓመታት በኋላ ዛሬም የዞምቢዎቹ ብዛት፣ ተለዋዋጭነትና ሁሉም ስፍራ ሁሉንም መስለው የመከሰታቸው  ሁኔታ በህሊናዬ ግዘፍ ነሥቶ ሳየው ከቃላትነቱም በላይ ምስል ከሳች ሆኖ ስላገኘሁት እናንተም ትናንትን ና ዛሬን ታዩበት ዘንድ እነሆ ብያለሁ፦
“ዞምቢዎች መጀመሪያውንም የሚገለጡት በሞተ ልብ፣ በበሰበሰ ህሊና፣ በቆሸሸ ስብዕና በመሆኑ መልካም ነገር አይታያቸውም፤ እውነት የሚባል ነገር  ቦታ የለውም። የሕይወት  መርሀቸውም በሀሰት ወንጅል፣  በሀሰት ስም አጥፋ፣ አቆሽሽ፣ ከእውነት ራቅ፣ የአማልክትን ስም እየጠራህ አታልል፣ አጭበርብር፣ ነው።
 ዞምቢዎቹ ጥቅማቸውን ሲያሳድዱ ክፋትን ለመፈፀም የማይፈሩት በሰማይ ያለውን አምላካቸውን ብቻ አይደለም፤ ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ ጐረቤትንም ነው። ይታዘቡኝ ይሆን? ይጠየፉኝ ይሆን? ብለው አይሳቀቁም። አካላቸው ባማረና በንፁህ ልብስ መሸፈኑ ዞምቢነታቸውን የሚጋርድ ስለሚመስላቸው በአደባባይ ሲውሉ አይሸማቀቁም።
ዞምቢዎች እውነትን እንዲረዱም ሆነ ወደ ህሊናቸው እንዲመለሱ ማድረግ አይቻልም፤ ህሊናቸው በስብሷል- ሊለመልም በማይችልበት የድርቀት ደረጃ።
 ለዞምቢዎቹ ሥነ ምግባር ፋይዳ የለውም፤ የማይለጥፉባችሁ የሀሰት ውንጀላ፣ የማያወሩባችሁ አሉባልታ የለም፤ ስብዕናችሁን ለማዋረድ፣ ዕውነቶቻችሁን ለማልኮስኮስ ሲሉ የፈጠሩባችሁን ወሬ ያወሩባችኋል፤ ያስወሩባችኋል፣ ሁላችሁም ወደዞምቢነት እስክትቀየሩ ድረስ።
ዞምቢዎች ይመስላቸዋል እንጅ ሃይማኖት የላቸውም። ስለሚያስመስሉ ብቻ ሰውን ያታልላሉ፣ያሳስታሉ።
 ዞምቢዎቹ ሲያጠቁ ተደራጅተው ነው። የበሰበሰ ህሊናን እና ሥጋን ባማረ ልብስ ሸፍነው አደባባይ የሚውሉ ዞምቢዎች ምን ያህል ርቀት ሄደው እንደሚዋሹ ላስተዋል ዞምቢነት ምን ያህል ሰይጣናዊነት እንደሆነ ይረዳበታል።
 በማይክል ጃክሰን “ትሪለር” ዘፈን ውስጥ መቃብር ፈንቅለው የሚወጡት ዞምቢዎች የአካላቸው መጎሳቆልና የልብሳቸው በጭቃ መለወስ ከየት እንደመጡ ቢናገርም የእኛዎቹ ዞምቢዎች ግን እንደዚያ አይደሉም። ንጹህ ይለብሳሉ፣ በቤተ መንግስቱ ይገማሸራሉ ወሬ ሌላ ተግባር ሌላ ሆነው ይገኛሉ፣ በቤተ ክህነቱ ቀዳሽ ፣ በመስጊዱ ሰጋጅ፣  በአደባባዩ ከእናንተ ያስቀድመኝ፣ ሞታችሁን ልሙት ባዮች ፤  በጓሮ ጉድጓዳችንን ቆፋሪዎች –  ስለዴሞክራሲ፣ ስለ ፍትህ ከዛም አልፈው ስለፈጣሪ አዳኝነት፣ …  ሲያወሩ ትሰሟቸዋላችሁ። ዞምቢ መሆናቸውን አያምኑምና”

ፈጣሪ ከዞምቢዎች ይጠብቀን!!

Filed in: Amharic