‹‹ለምርጫ ከመጣደፍ በፊት ቆም ብለን እናስብ››
ኦባንግ ሜቶ- ከአዲስ አድማስ ጋር
አለማየሁ አንበሴ
– ትኩረት የተሰጠው ለአገር ሉአላዊነት ሳይሆን ለብሄር ሉአላዊነት ነው
– የነሐሴ ምርጫ ከተስፋው ይልቅ ስጋቱ ያመዝንብኛል
– ሀሳብ ሳይሆን ብሔር የሚመረጥበት ምርጫ ነው የሚጠበቀው
– ስለ ጋራ ቤታችን መነጋገር ገና አልተጀመረም
– ሕዝቡ ከምርጫው ይልቅ ሰላም ነው የሚፈልገው
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በመጪው ምርጫ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ እንደሚከተለው ተወያይተዋል፡፡
—
በቀጣይ ምርጫ ያለዎት ስጋትና ተስፋ ምንድነው?
እኔ ቀጣዩን ምርጫ ሳስብ ከተስፋው ይልቅ አስፈሪነቱ ነው ጐልቶ የሚታየኝ:: ዛሬ በዩኒቨርስቲ የህግ የበላይነትና ሠላም ማረጋገጥ ተስኖን ት/ቤቶች እየተዘጉ ባሉበት፣ አገሪቱ ምርጫን የሚያህል ጉዳይ ለማከናወን እየተዘጋጀች ነው ለኔ ይከብደኛል፡፡ የጎላ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ባልተፈጠረበት ሁኔታ እንኳን ተማሪዎች እየታገቱ፣ እየታፈኑ፣ ትምህርታቸውን ትተው ወደቤተሠባቸው እየተመለሱ… ዩኒቨርሲቲዎችም እየተዘጉ ነው ያለው፡፡ በፖለቲካ ስልጣን ላይ ያሉ መሪዎችም እየተገደሉ መሆኑን በስፋት እያየን ነው፡፡ ለዚህ ወንጀል ደግሞ እስካሁን የተሰጠውን ቅጣት አናውቅም፡፡ እነዚህ ሁሉ ባሉበት የሚደረግ ምርጫ፣ ለኔ ከተስፋው ይልቅ ስጋቱ ያመዝንብኛል፡፡
ከምርጫ በፊት በመጀመሪያ ሠላም መረጋገጥ አለበት፡፡ ለሠላም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ የጠራ ነገር አለመኖሩ በራሱ አስጨናቂ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዘዋውረው ህዝብ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ አይደለም፡፡
‹‹እገሌ የተባልክ የፖለቲካ ፓርቲ እዚህ ክልል መምጣት አትችልም፤ ስብሰባ አታደርግም የሚል ተቃውሞ እየሰማን ባለበት ሁኔታ ለምርጫ ዝግጁ ነን ማለት ይቻላል?
ስለ ምርጫ ማሰብ የሚቻለው ሀገሩ ቁስሉ ተፈውሶ፣ ጤንነቱ ተሻሽሎ ሠላም ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡
ግን እንዴት ነው ቁስሉ የሚፈወሰው? እንዴት ነው ሠላም ሊመጣ አይቻልም?
በመነጋገር፣ ችግሮችን ለይቶ በመወያየት በመደራደር… ነው፡፡ እስካሁን ችግሮች በሚገባ ተለይተው፣ ድርድርና ውይይት አልተካሄደም፤ በሚገባ የተደራጀ ውይይትና ድርድር ቢካሄድ ኖሮ፣ ብዙ ቁስሎችን መፈወስ ይቻል ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን እኮ ሁሉም በብሔር ሆኗል:: ብሔር ሃይል ሆኗል፣ ብሔር መነገጃ ሆኗል፣ ብሔር ስልጣን ማግኛ ሆኗል፡፡ ከዚህ አንፃር ምርጫውም በእውቀት ሳይሆን በብሔር ሚዛን የሚከናወን ነው የሚሆነው፤ ሃሳብ ሳይሆን ብሔር የሚወዳደርበት፣ ብሔር የሚመረጥበት:: ምርጫ ነው የሚጠበቀው፡፡
ስለዚህ ምርጫውን ለጊዜው አዘግይተን፣ ሌሎች መቅደም ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ብናተኩር የተሻለ ይሆናል፡፡ የምርጫው አለመካሄድ ህግ ይጥሳል የሚለው ሃሳብ፣ የሀገር ህልውና የሚያፈርስ በመሆኑ መተው አለብን፡፡
ከምርጫው በፊት መደረግ ያለባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ምንድን ናቸው ይላሉ?
አንዱና ዋነኛው የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ አጠንክረው መስራት ነበረባቸው፡፡ አሁን ግን ባለው ችግርም ጥሩ መፍትሔ ይሆን የነበረው ሁሉም በጋራ ተሰባስቦ መነጋገር ቢችል ነበር፡፡ አሁን አማራ ለብቻው፣ ኦሮሞ ለብቻው፣ ትግራዩ ለብቻው… ሌላውም ለብቻው ነው… ስለ ራሱ እየተነጋገረ ያለው፡፡ ስለ ጋራ ቤታችን ኢትዮጵያ መነጋገር ገና አልተጀመረም፡፡ ወደ ብሔራዊ መግባባት የሚወስደን መንገድ ላይ አይደለንም:: በየራሣችን መንገድ ነው እየተጓዝን ያለነው፡፡
ሁለተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ስለ ሀገሪቱ የጠራ የጋራ አቋም አልያዙም፡፡ ትልቁ አንኳር ጉዳይ ሀገር ነው፡፡ በሀገሪቱ ጉዳይ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ አልተስማሙም፡፡ ስለሚመሩት ህዝብ የጋራ ነገር አላስቀመጡም:: ሀገሪቱ እንዴት ትቀጥል? ወዴት ትጓዝ?… ግብና መዳረሻዋን በተመለከተ ሁሉን አሳታፊ ውይይት ተደርጐ፣ የጋራ አቋም አልተያዘም፡፡ ስለ ሀገር ሉአላዊነት ስምምነት የለንም፡፡ አሁን ጐልቶ ያለው የሀገር ሉአላዊነት ሳይሆን የብሔር ሉአላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ የሀይማኖት አባቶችም የሚጠበቅባቸውን አልሠሩም፡፡ በደሎች በይፋ ወጥተው ቁስሎች መፈወስ ነበረባቸው:: በመሸፋፈን ማለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ እነ ደቡብ አፍሪካ ወደተሻለ ነገር የተሸጋገሩት… በዚህ መንገድ ነው፡፡ እነሱ ምርጫን አይደለም ያስቀደሙት፡፡ ለውይይትና ብሔራዊ መግባባት ነው ቅድምያ መሰጠት ያለበት ከምርጫው በፊት እኛ ጋ ግን ሹፌሩ ተለውጦ፣ መኪናው ያልተለወጠበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ተሳፋሪዎች እርስ በእርሳቸው የሚጣሉት ሹፌሩ ብቻ መቀየሩ ብዙም ለውጥ አያመጣም፡፡ ሹፌሩ ሲለወጥ የመኪናው አካልና ሞተር መለወጥ ነበረበት፡፡ ይሄም ማለት ህገመንግስቱ መስተካከል መለወጥ ነበረበት፡፡
ህዝቡስ ለምርጫው የተዘጋጀ ይመስልዎታል?
ምርጫ የስነልቦና ዝግጅትን ይፈልጋል፡፡ እኔ በምረዳው ልክ እንደ ህዝብ አካልም ሆኜ በማየው፤ ህዝቡ ለምርጫው አልተዘጋጀም:: ህዝቡ ከምርጫው ይልቅ ሠላም ነው የሚፈልገው፡፡ ህዝብ ትኩረቱ ሠላም እንዴት ይስፈን? የኢኮኖሚ ችግሬ እንዴት ይቃለልኝ በሚለው ላይ ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስንመለከት የትኛውም በብቃትና በሙሉ ልቡ ተዘጋጅቻለሁ አይልም:: ብዙዎቹ ዝግጁነት የላቸውም፡፡ ፓርቲዎች ወደ ህዝብ ቀርበው ፕሮግራማቸውን ባላስተዋወቁበት ሁኔታ ሊደረግ የሚችለው ምርጫ፤ ምናልባትም በህዝብ ፍላጐት ያልተደገፈ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ የሚቀርብበት ነው የሚሆነው፡፡
ከዚህ ምርጫ በኋላ ምን አይነት ሁኔታ ይከሰታል ብለው ይገምታሉ?
አሁን ምርጫ በሌለበት ግጭት እየተፈጠረ ነው፡፡ ምርጫ ደግሞ በባህሪውም ሠላምን የሚፈታተን ነው፡፡ ታዲያ ሠላም በሌለበት የሚደረግ ምርጫ፣ ምን ሊሆን ይችላል? ግልጽ ነው፡፡ አሁን ካለውም የባሰ ችግር ነው የሚመጣው፡፡ ቢያንስ አሁንም ምርጫው በነሐሴ የሚካሄድ ከሆነ፣ ፖለቲከኞች አስቀድመው ተነጋግረው፣ ከምርጫው በኋላ በሚኖረው ሁኔታ ላይ የማይጣስ አስገዳጅ ስምምነት ውል መግባት አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ነገሩ ከባድ መዘዝ ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ እኔም እንደ ማንኛውም ሰው ከምርጫው በኋላ ያለው ነገር በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡
ስለዚህ ሁላችንም ለሀገሪቱ ሠላምና ህልውና መቀጠል ብዙ መስራት ይገባናል፡፡ ፖለቲከኞች ይሄን ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡ ምርጫ የሚደረገውም ሆነ ሥልጣን የሚያዘው የአገር ህልውና ሲረጋገጥ ነው፡፡ ሁላችንም ለምርጫ ከመጣደፍ በፊት ቆም ብለን ማሰብ አለብን፡፡